የሁለት ደብዳቤዎች ወግ ከአዲስ አበባ እና ከመቀሌ – መሳይ መኮነን

አንደኛው ከአዲስ አበባ የተጻፈ ነው። ሁለተኛው ከመቀሌ የተከተበ ነው። ሁለቱ ደብዳቤዎች በይዘት የሰማይና የምድርን ያህል ይራራቃሉ። የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር የተጻፉበት ቋንቋ እንግሊዘኛ መሆኑና መዳረሻቸውን ከአንድ ቦታ ከነጩ ቤተመንግስት ማድረጋቸው ነው። ሁለቱም ለአንድ መግለጫ መልስ ለመስጠት የተጻፉ ናቸው። የይዘት ልዩነታቸው የሰሜንና ደቡብ ዋልታዎች ዓይነት መራራቅ እንኳን የማይገልጸው፣ አንደኛው ድፍረትና ሀገራዊ ቁርጠኝነት የነገሰበት፣ ሌላኛው ልምምጥና ልፍስፍስነት ያጠቃው፣ አንደኛው ደጄን አትርገጡ ሲል ሌላኛው ጓዳችን ድረስ ዘልቃችሁ ፈትፍቱ ብሎ የሚጋብዝ ነው። አንደኛው በሀቅና እውነት የተንቆጠቆጠ፣ ሌላኛው በውሸትና ቅጥፈት የተሽሞነሞነ ነው። አንደኛው አትድረሱብን ብሎ ሲያስጠነቅቅ፣ ሁለተኛው ደግሞ ድረሱልን እያለ የሚማጸን ነው። ሁለቱም የተላኩት ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ነው።

ከአዲስ አበባ የተላከው ደብዳቤ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የተጻፈ ነው። የመቀሌው ከህወሀት ጽ/ቤት በደብረጺዮን ፊርማና ማህተም የተተዘጋጀ ነው። ባለፈው ዓርብ ጆ ባይደን ጦርነቱን አቁሙ፣ አለበለዚያ ሁላችሁንም እቀጣለሁ ብለው ላስተላለፉት ማስፈራሪያ የተሰጡ ምላሾች ናቸው። ጆ ባይደን በአንዲት ልዑዋላዊት ሀገር ጉዳይ ምን ኮነሰራቸውና ነው እንዲህ የሚውረገረጉት የሚለውን ለጊዜው ተወት አድርገን ስለሁለቱ ደብዳቤዎች ትንሽ ወግ እንጠርቅ።

/ሚ አብይ ታሪካዊ ደብዳቤ ስለመጻፋቸው የሚስማሙት ጥቂቶች አይደሉም። አጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ የጻፉትን ቆፍጠን ያለ ደብዳቤ የሚያስታውስ እንደሆነ ይነገርለታል። የጠ/ሚሩ ዋንኛ ጭብጥ እኛ ለራሳችን አናንስም፣ እዚያው በቅጥራችሁ ተሰብሰቡ የሚል ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ በማጣቀስ ለውጭ ሃይሎች ሳትንበረከክ ዛሬን የደረሰች መሆኗን ለባይደን ግልጽ በሆነ ቋንቋ አስቀምጠውላቸዋል። የእሳቸው የፍርድ ሚዛን በአሉባልታዎችና በአንዳንድ ሸቃይ ጎትጓች ተቋማት የተሳሳቱ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመግለጽ አሜሪካንን ከምታህል ትልቅና ሀብታም ሀገር የማይጠብቅ አቋም ማራመዳቸው እንዳሳዘናቸው የገለጹበት ደብዳቤ ነው። ኢትዮጵያ ህወህትን አጥፍታ፣ ከመቃብር አስገብታ፣ ሰላምና ደህንነቷን ለማረጋገጥ የማንንም ቡራኬና ይሁንታ እንደማትፈልግ በመግለጽ እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሚያሳስብ መልዕክት ያዘለ ነው። በአጭሩ ኢትዮጵያ የተገለጸችበት፣ የህዝቧ ጀግንነትና አይበገሬነት የተንጸባረቀበት፣ ለየትኛውም ጫና የሚሰበር አንገት የሌለን መሆኑ ጎልቶ የተነገረበት ደብዳቤ ነው ማለት ይቻላል። በትክክልም በታሪክ ቅብብሎሽ ለትውልድ የሚተላለፍ ድንቅ ደብዳቤ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነገረ ኢትዮጵያ ቁጥር - 5 ቁልፍ አገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን ይዛ እነሆ በPDF ያንብቧት

ከመቀሌ ህወሀት ጽ/ቤት ደብረጺዮን የጻፈው ደብዳቤ በተቃራኒው ፍርሃት፣ ቅጥፈት፣ ልመናና ድረሱልን በሚሉ ስሜቶች ሊገለጹ በሚችሉ መልዕክቶች የተሞላ ነው። ህወሓት እንደልማዱ ቆርጦ ቀጥል መረጃዎችን በአሰልቺ አቀራረብ ያዘጋጀው ተመሳሳይ ዲስኩር ነው። የእምዬን ለአብዬ እንዲሉ የህወሀትን ሀጢያትና ኩነኔ እንዳለ መንግስት ላይ ለጥፎ የሚያለቃቅስበት ደብዳቤ ነው። ከህሊናና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የቀረው አማራጭ የአሜሪካን አማላጅነት ነው ብሎ ተስፋ የቆረጠ ቡድን የጻፈው ደብዳቤ እንደሆነ ከጅማሬው እስከፍጻሜው በተሰገሰጉት መልዕክቶች መረዳት ይቻላል። ህወሓት በደብዳቤው የባይደንን የማዕቀብ ውሳኔ ከፈጣሪ የተላከ የህይወት መዳኛ በረከት አድርጎ ከልቡ እንደተቀበለው ሳያቅማማ አስታውቋል። መንገድም ብርሃንም አሜሪካ አንቺው ነሽ ሲል ያሞካሻል። ማዕቀቡ የህወሀትን መሪዎች የሚነካ መሆኑ አላስጨነቀውም። ይልቅስ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ገብታ መንግስት እንድትሾም፣ መንግስት እንድትሽር ተንበርክኮ የሚለምን የሚመስልበት ደብዳቤ ነው። ተስፋ መቁረጡን፣ አሜሪካ አንዳች ነገር ካላደረገች መጥፊያው እየተቃረበ መሆኑን በመግለጽ ድረሺልንየሚል የተማጽኖ ደብዳቤ ነው የሚመስለው። በአጭሩ ተለማማጭነት የሚታይበት፣ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተሞላ፣ ተንበርካኪና ሰጋጅ ደብዳቤ ነው ማለት ይቻላል።

ዋናው ነገር አሜሪካን መሄድ የምትችለውን፣ በአቅምና ጉልበቷ ማድረግ የምፈልገውን ሁሉ ብታደርግ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የግዛት ልዑላዊነት ጋር በእኩል ሚዛን የምናስቀመጠው አይደለም። ህወሀትን ለማዳን ብላ ኢትዮጵያን በሚያፈርስ እንቅስቃሴ ውስጥ የምትገባ ከሆነ እንግዲህ የሚመጣውንም አብረን የምናየው ነው። በእርግጥ አሜሪካኖቹ ሁኔታውን አይተው መንገዳቸውን ማስተካከላቸው አይቀርም። ልክ እንደሻርክ ፍርሃትን ያነባሉ። ሻርክ ከሌላው እንስሳ የሚለየው የባላንጣው ፍርሃት የሚለይበት የስሜት ህዋስ አለው። ከፈራህ ይሰለቅጥሃል፣ አለበለዚያ አይነካህም። አሜሪካም እንደዚያው ናት። የሚፈራ መንግስት ካገኘች በነፍሰ ስጋው ትጫወትበታለች። ቆፍጠን፣ ኮራ ጀነን ካልክባት ደግሞ እጥፍ ትልና ሸሪክህ ሆና ትመጣለች። ከዚያ ያለፈ ነገር የለውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተረግመሻል ይሆን????!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share