September 17, 2021
7 mins read

አራት የቤተሰብ አባላቶቼ በአሸባሪው ቡድን በግፍ ተገድለዋል

242201506 3027814300794362 7415102565538590134 n

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ደባርቅን ለመያዝ በፈጸመው ወረራ ” ቦዛ ” በተባለው ቀበሌ አራት የቤተሰብ አባላቶቼን በግፍ ገድሎ፤ በአንድ ጉድጓድ ቀብሯል ሲሉ አሜሪካ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጅ ተናገሩ።

ትዕግስት አንጋው ይባላሉ፤ ከአሜሪካን መጥተው የአንድ ዓመት ዕድሜ ያለው ህጻን ልጃቸውን ጎንደር ከተማ ትተው ለ12 ቀናት በደባርቅ ግንባር ከሽብር ቡድኑ ጋር ከሚዋደቀው ሰራዊት ጋር (ቁመዋል) ፤ በማበረታታት ድጋፍ አድርገዋል።

የሽብር ቡድኑ በሰሜን ጎንደር ዞን ወቅን ጭና ቀበሌ የፈጸመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በአካል ተገኝተው ተመልክተዋል።

የሽብር ቡድኑ በፍጹም ጥላቻ ተነሳስቶ የፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ከኢትዮጵያዊነት እሴቶች ያፈነገጠ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መሆኑን ይገልጻሉ።

ህወሃት በስልጣን ዘመኑ ወንድሞቼን በእስር ከማንገላታቱም በላይ አንድ አጎቴንም በግፍ መግደሉ የጭካኔ ጥግ ማሳያ ነው ይላሉ።

ይሄ አልበቃ ብሎት ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ደባርቅ ለመያዝ በፈጸመው ወረራ “ቦዛ” በተባለው ቀበሌ አራት የቤተሰብ አባላቶቼን በግፍ ገድሎ በአንድ ጉድጓድ ቀብሯል ሲሉ በቁጭት ገልጸዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው ግፍና በደል ተዘርዝሮ እንደማያልቅ የተናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት፤ የአካባቢው ህዝብ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ያደረገው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የሴት ተዋጊዎች የውጊያ ሞራልና ብቃት ጉልህ ስፍራ እንዳለው ነው ወይዘሮ ትዕግስት የተናገሩት።

ለተዋጊ ሰራዊቱ ከ200 ሺህ ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ብስኩት፣የዝናብ ልብስ፣ ውሃና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እንደቻሉ አመልክተዋል።

ለሴት ተዋጊዎችም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ የዜግነት ድርሻቸው ለመወጣት ጥረት አድርገዋል፡፡

በአውደ ውጊያዎች በጀግንነት ሲዋጉ የሚቆስሉትን የሰራዊት አባላት በመንከባከብ እንዲሁም ወደ ሆስፒታል በፍጥነት በማድረስ በኩል ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበር ድጋፍ ሰጥተዋል።

”የአማራና የትግራይ ህዝቦች ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ የአብሮነት እሴቶች ቢኖረንም የሽብር ቡድኑ ይህን ዘመናት የተሻገረ አብሮነት በማጥፋት በህዝቦች መካከል እልቂት እንዲፈጠር እየሰራ ነው ”ብለዋል፡፡

ጦርነቱ ኢትዮጵያውያን አንድ እንድንሆን ያደረገ፤ በሁሉም አውደ ውጊያዎች የታዘብኩት ነገር ቢኖር ህዝቡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የሽብር ቡድኑን ሲፋለም ለማየት ችያለሁ ነው ያሉት፡፡

በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ዜጎችም ሆነ በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሃይል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሚችለው አቅም ሊያግዝ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት ያወገዙት ወይዘሮ ትግስት፤ ሴት ዲያስፖራዎች በአለም አቀፍ መድረኮች ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ የሽብር ቡድኑን ወንጀል ለማጋለጥ እንደሚሰሩ ነው ያስታወቁት።

በተለይም ውጭ ሀገር ሆነው የህወሃት የሽብር ቡድንን የሀሰት ወሬዎች በማናፈስ አለም አቀፉን ማህበረሰብ እያደናገሩ ያሉ ቅጥረኛ አክቲቪስቶችን ሴራ ለማክሸፍ ሀገር ወዳድ ዲያስፖራዎችን በማስተባበር ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል።

የጎንደር ከተማ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኜ ፤ ወይዘሮ ትዕግስት አንጋው ከአሜሪካን መጥተው ሰራዊቱን በግንባር ተገኝተው በማበረታታትና በመደገፍ በኩል የሴት ዲያስፖራዎች ግንባር ቀደም አርአያ ናቸው ነው ያሉት።

ዲያስፖራው ለህልውና ዘመቻው በገንዘብና በቁሳቁስ ጭምር እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን አውስተው፤ ወደፊትም ይሄው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈፈዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድንን የሴራ ፖለቲካ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድ የዳያስፖራው አስተዋጽኦ የላቀ በመሆኑ በዚህም የድርሻቸውን እንዲወጣ አመልክተዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችና በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለህልውና ዘመቻው በጥሬ ገንዘብና ዓይነት ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

መስከረም 07/2014(ኢዜአ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop