(ሰርካለም ፋሲል የእስክንድር ነጋ ባለቤት ናት፡፡ እርሷም እንደ እስክንድር ጋዜጠኛ ነበረች፡፡ በ97 ሰባት ከቅንጅት መሪዎች ጋር አብረው ለሁለት አመት ከታሰሩ ጋዜጠኞች መካከል እርሷና ባለቤቷ እስክንደር ነጋ ይገኙበት ነበር፡፡ እስር ቤት እያለች ነፍሰ ጡር ስለነበረች እዚያ እያለች ነበር አንድና ብቸኛ ልጃቸውን ናፍቆት እስክንድርን የወለደችው)
በእኔ አስተሳሰብ እስክንድር አልተካደም። ክህደት ካለም ከሃጂው ህሊናውን ፣ዓላማውን፣ ትግሉን ራሱን ነው የከዳው።
ትላንት ህገ-መንግሥቱ አይወክለንም ስትል ከርመህ፣ ዛሬ ምንም ማሻሻያ ያልተደረገበት ህገ- መንግሥት ይወክለኛል ካልክ እስክንድር ሳይሆን፣ ዓላማህን፣ ትግልህን ራስህን ክደህዋል።
ትላንት ኤምባሲዎች በሙሉ የወያኔ ናቸው ማንም ሰው እንዳይገባ ብለህ ስትቀሰቅስ ፣ ዛሬ ስብሰባ እና ጭፈራ ስታካሄድበት-እስክንድርን ሳይኾን፣ ዓላማህን፣ ትግልህን ራስህን ነው የካድከው።
ትላንት የአንድን ዘር የበላይነት ስትቃወም፣ ዛሬ የአንድ ዘር የበላይነት ከተቀበልክ እስክንድርን ሳይሆን ትግሉን ፣ ዓላማህን፣ ራስህን ክደኸዋል።
ትላንት የፍትህ ተቁሙን ፣ የፀረ-ሽብር አንቀፁ ፣ህገ-ወጥ እስር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን፣ በመቃወም ድምፅህን ስታሰማ ኖረህ፣ ዛሬ የሰው ልጅ በአደባባይ አካሉ ሲቆራረጥ፣ ንፁሃን ትላንት በተቃወምከው የህግ አንቀፅ ተከሰው ወህኒ ሲወረወሩ ዝምታን ከመረጥህ የከዳኸው እስክንድርን ሳይኾን ራስህን ነው። የከዳኸው ሰምቶ እንዳልሰማ ዓይቶ እንዳላየ ዝምታን የመረጠው ህሊናህን እንጅ እስክንድርን አይደለም።
ትላንት ሕወኃትን ስትቃወም ፅድቅ፣ የሕወኃት የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ኦህዴድን ስትቃወም ወንጀል ከሆነ የከዳኸው እስክንድርን ሳይኾን ትግሉንና ራስህን ነው።
አዎ …ግን ደግሞ እስክንድር ተክድዋል። ክህደት የምለው፣
ትላንት እስክንድርን፣ እንደመታገያ ስልት ተጠቅመው ስሙን ሲያነሱ የነበሩ፣ ዛሬ እስክንድር ያልተናገረው የተናገረ በማስመሰል ‘ካልታሰረ’ ብለው ማመልከቻ እስከ ማስገባት(ማመልከቻው ግነት ነች) የደረሱ፣ አለፍ ብለውም፣’ህብዕ’ ሲሉ ለዐቃቤ ህግ የክስ ማጠናከሪያ እስከመኾን የተጉዋዙ ነበሩ። ለእኔ ክህደት ይህ ብቻ ነው። ሰውን በሃሰት መወንጀል። ለዚያውም ጥንቅቅ አድርገህ የምታውቀውን። ከእጁ የበላህ የጠጣኸው። (ጌታው ዐቃቤ ህግ በምስክር ድርቅ ተመትዋል እኮ ያቺ ፌስቡክ ላይ የለጠፍካትን በአካል ቀርበህ ብትመሰክር ስል…ሃሳብ አቀረብኩኝ።)
:
ትላንት…….. ብዙ ማለት ይቻላል ወ.ዘ.ተ ብለን ካላለፍነው።
እስክንድርማ ትላንት በጋዜጠኝነቱ ፣ ዛሬም በፖለቲከኝነቱ ፣ ፍትህ ተጎደለ ደሃ ተበደለ ብሎ ድምፁን ከማሰማት አልተቆጠበም። እስክንድርማ ላመነበት መስዋዕት መክፈሉን ዛሬም አላቆመም። እናም… እስክንድር ተክድትዋል አትበሉኝ። የተካዳካዳችኹ ካላችኹ ተጠያየቁ። ለእኔ፣ እስክንድር ዓላማ አለው። መነሻና መድረሻውን ያውቃል። ዳገት ላይ ሸብረክ አላለም። አቁራጭ መንገድ ፈልጎ ርምጃውን አልገታም። ጉዞ ላይ ነው።
በመጨረሻም እንደኔ ፍላጎት ምርጫው ቢሆን(እመኛለሁ) አሜሪካ ቢኖር። በተለይ፣ ለእስክንድር ይመቸዋል። አይደክምም፣ አይጎሳቆልም፣ አይከሳም አይጠቁርም። በቀላሉ፣ እጅግ በቀላሉ ዘና ብሎ፣ መኖር የሚያስችለው ብቃት አለው። ፈጣሪ ፀሎቴን ይስማ!!!
የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ!!!
ሰርካለም ፋሲል ( የእስክንድር ነጋ ባለቤት