የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ የዘመን መሸጋገሪያ ድልድይ ነው

ጠላት ይጥፋ ብሎ ወገን ቢጠራቸው፣
ተነሱ ከእስራኤል ከሞቀ ቤታቸው

241507148 1626343224207332 8178090627574858817 n

ታሪክን ጠብቆ ማለፍ ክብር ነው፣ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ደግሞ እንደመታደል ይቆጠራል። እንደ ታጋይ ሠረበ በየነ ተዓምር የሠራ ሲገኝ ግን አጃኢብ ከማለት ውጪ ከትቦ ለማስነበብም ሆነ ተናግሮ ለማሳመን ይቸግራል። ታጋይ ሠረበ በየነ ኢትዮጵያዊነትን ከደምና ከአጥንቱ ካዋሃደው የአማራ ሕዝብ አብራክ የወጡ ጀግና ናቸው።

የተወለዱት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አዲጋባ ጊዮርጊስ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው። ወያኔ ማንነትን ሊያጠፋ፣ ሀገር ሊበድል፣ አማራን ከርስቱ በማፈናቀል ወደ ባርነት ለማስገባት አቅዶ ሲንቀሳቀስ የመጀመሪያ ዒላማ ያደረገው የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ ነው። ይህ የአማራ ሕዝብ የምንጊዜም ጠላት የሆነው ስብስብ ቀያቸው ድረስ ዘልቆ ደርግን እንዲዋጉ ካልሆነ ደግሞ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፈ። አቶ ሠረበ እና ጓደኞቻቸው ግን ትእዛዙን አልተቀበሉም፣ አካባቢያቸውንም ለተገንጣይ አስረክቦ መሄድ አልፈለጉም። በማናምንበት ዓላማ ከምንሰለፍ ለህልውናችን ታግለን ብንሞት ይሻለናል በማለት ከአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ኀይል ጋር ፍልሚያ ጀመሩ።
ሚያዝያ 30/1980 ዓ.ም ስንቅ ከራሳችን ትጥቅ ከጠላታችን በማለት 8 መሣሪያ ብቻ በመያዝ 105 ሰዎችን አስከትለው ወደ ጫካ ገቡ። በቃብትያ ወረዳ እስከ ነሐሴ 15/1980 ዓ.ም ከፍተኛ ውጊያ በማድረግ ለወረራ የገባውን አልሞ ተኳሽ ኮማንዶ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው አባረሩት። ከዚያም ጳጉሜን 3/1980 ዓ.ም ወደ አዲ ጎሹ በማቅናት ጠላትን ደምስሰው ከ45 በላይ መሳሪያ ማርከዋል። ሚያዝያ 23/1982 ዓ.ም ዳንሻ አካባቢ ባደረጉት ከባድ ውጊያም ከአሸባሪው ቡድን መትረየስ፣ መገናኛ እና ከ50 በላይ የነፍሰ ወከፍ መሳሪያ ማርከዋል።

241562319 1626343174207337 7481047544588669701 n

እስከ 1984 ዓ.ም ጫካ ገብተው ባደረጉት ትግል ሀገሪቱን ለመከራ ሕዝቡንም ለባርነት አስቦ በተንቀሳቀሰው ተገንጣይ ኀይል ላይ ከፍተኛ ቁሳዊና ሰብዓዊ ኪሳራ አድርሰዋል። የነበረውን የመሳሪያ እጥረትም ጠላትን በመማረክ ማሟላት ችለዋል። ከዚያም ወደ ኤርትራ በርሃ አቅንተው ትግላቸውን ሲቀጥሉ ነሐሴ 25/1986 ዓ.ም በአሸባሪው የትህነግ ታጣቂዎች ታፈኑ።

ታፍነው ወደ ኢትዮጵያ በሚወሰዱበት ጊዜ አሰቃቂ ግድያ ሊፈጽሙባቸው እንደሆነ የተገነዘቡት አርበኛ ሠረበ ነሐሴ 28/1986 ዓ.ም ከተሳፈሩበት ተሽከርካሪ ላይ አምልጠው በመዝለል ወደ ተከዜ ወንዝ ገቡ። ወቅቱ ክረምት ስለነበር ተከዜ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቷል። አቶ ሠረበ ወደ ወንዙ ሲገቡ ታጣቂዎቹ ጥይት ተኮሱባቸው። በሂደቱ ከፍተኛ ስቃይ ቢደርስባቸውም ከጠላት ጥይትም ሆነ ከጎርፍ አደጋው በሚያስደንቅ ተዓምር ተርፈው ሰባት ኪሎሜትር ያህል ጎርፉን ተከትለው ሄደዋል። ምቹ ቦታ እና መውጣት የሚያስችላቸውን ሁኔታ ባገኙ ጊዜ ወደ ወንዙ ዳር በመውጣት ሕይወታቸውን ማትረፍ ችለዋል። በሚደንቅ ተዓምር ከዚያ ሰቃይ የወጡት ታጋይ ሠረበ ከወንዙ ከወጡ በኋላም መቋቋም ከሚችሉት በላይ ፈተና ገጠማቸው። እዚያው ቦታ ሳር ውስጥ ተኝተው ያለ ምግብ እና ውኃ ሁለት ቀናት ውለው አደሩ። መጓዝ ሲጀምሩም አቃቅማ የሚባል እሾህ አገኙ፣ ሲራመዱ፣ ሲደገፉና ሲያርፉ እየወጋ ስቃያቸውን አበዛው። እግሩን በብልሃት ለማለፍም ሁለት ጠፍጣፋ ድንጋይ ፈልገው አንዱን እየረገጡ ሌላኛውን ወደ ፊት እያስቀደሙ ተጓዙና የተሻለ ቦታ ደረሱ። በደከመ ሰውነታቸው በራበው አንጀታቸው ከእረኛ ጫማ ለምነው ጉዟቸውን ቀጠሉ። ድካምና ርሃብ ሲበረታባቸው ወደ ካምፕ ተጠግተው በመሥራት ለቀናት በኋላ ገዳሪፍ ወደምትባለው የሱዳን ግዛት ደረሱ።
ገዳሪፍም ሌላ ፈተና ጠበቃቸው። ያግዘኛል ብለው የተጠጉት የኢዲዩ መሥሪያ ቤት መጥፊያቸው ሆኖ አገኙት። ሁኔታውን በዝርዝር ያጫወቱት የመሥሪያ ቤቱ ኀላፊ ሊያስገደላቸው መሆኑን በተገነዘቡ ጊዜ በፍጥነት አካባቢውን ጥለው ሸሹ። ከብዙ ድካምና በኋላም ወደ ካርቱም አቀኑ። ከካርቱም ራሳቸውን ጨምሮ 12 ሆነው በግብጽ በርሃ በኩል ወደ እስራኤል ጉዞ ጀመሩ። በዚያ ጉዞም መራራ መስዋእትነት ተከፍሏል፣ ወደ እስራኤል ከሚጓዙት መካከል ሦስቱ በግብጽ ወታደሮች ተገደሉ፤ አምስቱ እጃቸውን ሲሰጡ ታጋይ ሠረበን ጨምሮ አራት ሰዎች ብቻ እስራኤል ገቡ። አቶ ሠረበ በዚህ ሁሉ ትግል መሀል የወልቃይት ጠገዴን ትግል ሲደግፉ እንደነበር ተናግረዋል።
በእስራኤል መኖር ከጀመሩም በኋላ ለአጋሮቻቸው ገንዘብ በመላክ እና የሐሳብ ድጋፍ በማድረግ ትግሉን ፍሬ ለማየት ጥረት አድርገዋል። አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ተወልደው ባደጉበት ቀየ ከገባ አንስቶ ከባድ ትግል ያደረጉት አርበኛ ሠረበ መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተቀብለው ሀገራቸውን በለቀቁ በ28 ዓመታቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በሁመራ በኩል ተከዜ ድልድይ በመገኘትም ተዓምረኛውን ቦታ ጎብኝተዋል። በቀሪ ዘመኔ ለሀገሬ እታገላለሁ በማለትም ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል። የእሳቸው እልህ አስጨራሽ የትግል ጉዞ በችግር ውስጥም ሆኖ አሸናፊነት እንዳለ ማሳያ መሆኑን የትግል አጋሮቻቸውና የከፋኝ ቡድን አባላት ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ኀይል የአማራን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት እና ኢትዮጵያን ለመበታተን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን ወራሪ ኀይል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት በአንድነት እየተፋለመው ነው።
አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለመበታተን እኩይ ድርጊት እየፈጸመ ያለውን አሸባሪው የትህነግ ቡድን መላው ሕዝብ ማስወገድ እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል። ለዚህም በጽናትና በቁርጠኝነት መታገል ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ሁመራ፡ ነሐሴ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ)
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ/አሜኮ

1 Comment

  1. አቶ ታዲዮስ ታንቱ በ80 አመታቸው እንክብካቤ እንጅ እስር አይገባቸውም መታሰር ያለባቸው ብዙ ባንዳዎች እያሉ የሳቸው መታሰር ኢፍትሀዊ ነው

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.