“እቤት ድረስ መጥተው እንጀራ አምጣ አሉት፤ እንጀራ ከቤቱ ይዞ ቢወጣም ገደሉት”

በደብረ ዘቢጥ ከተማ በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ባለቤታቸውን የተነጠቁት እማወራ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉ ግድያ፣ ዘረፋና ውድመት መገለጫው አድርጎታል። ጋሳይ፣ ክምር ድንጋይ፣ ነፋስ መውጫና ሌሎች የደቡብ ጎንደር ዞን ከተሞችና አካባቢዎችን በወረረበት ወቅትም በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ግፎችን መፈጸሙን መዘገባችን ይታወሳል።

ቡድኑ እንደለመደው በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የምትገኘውን ደብረ ዘቢጥና አካባቢዋን ለቅቆ እንዲወጣ ቢገደድም በቆይታው በከተማዋ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሏል።

241303261 1625667980941523 5268680744011258845 n

አቶ ሞላ ልባይ የደብረ ዘቢጥ ከተማ ነዋሪ ነበሩ። በከተማዋ የተጣላን በማስታረቅ፣ የተራበን በመመገብ፣ በትህትናቸውም እንደሚታወቁ አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሆኖም አቶ ሞላ በግፈኛው የሽብር ቡድኑ ጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። “እቤት ድረስ መጥተው እንጀራ አምጣ አሉት፤ እንጀራ ከቤቱ ይዞ ቢወጣም ገደሉት” ሲሉ ባለቤታቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ጉበና ተናግረዋል።

በአሸባሪው ቡድን በግፍ የተገደሉት አባውራ የሰባት ልጆች አባት ነበሩ።

ወይዘሮ ዘውዲቱ ባለቤታቸውን ብቻ ሳይሆን የቤት ጥሪታቸውንም ጨምሮ እንደዘረፉባቸው ተናግረዋል።

የሽብርተኛው ቡድን አባላት አቶ ሞላን ከገደሉ በኋላም አስክሬኑ እንዲነሳ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ገልጸዋል። ቡድኑ በደረሰበት ሁሉ ሕዝብን እየገደለና እየዘረፈ ሕዝባዊ ነኝ ማለቱ እንደገረማቸው ባለቤታቸው አስረድተዋል።

ባለቤታቸውን ያጡት ወይዘሮ ዘውዲቱ የልብ ሕመምተኛ በመሆናቸው ልጆቻቸውን ማስተዳደር እንደሚከብዳቸው ጠቁመዋል።

“አንተ አስተኳሽ ነህ በማለት ድብደባና እንግልት አድርሰውብኛል” ያለው ደግሞ የሟች ልጅ ደረጄ ሞላ ነው። የቡድኑ አባላት “ዓላማችን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥትና አማራን ማጥፋት ነው” ሲሉ እንደነበርም ወጣቱ ተናግሯል።

አሸባሪው ቡድን በደብረ ዘቢጥ ከተማ ቆይታው የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ሲያጠፋ፣ የሕዝብን ሀብትና ንብረት ሲያወድም እንደነበረም ወጣቱ ተናግሯል። ወጣት ደረጄ የአማራ ጠላት የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ከሠራዊቱ ጎን ለመሰለፍ ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግሯል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከደብረ ዘቢጥ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.