ለቸኮለ! ቅዳሜ ነሐሴ 29/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የትግራዩን ግጭት ለማሸማገል ሃሳብ ማቅረባቸውን ዥንዋ ዘግቧል፡፡ ኪር ከሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ በተጓዙ ጊዜ የአሸማጋይነት ሃሳባቸውን ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እንዳቀረቡላቸው የጠቀሰው ዘገባው፣ ኪር አሸማጋይ እንዲሆኑ የጠየቋቸው ደሞ የኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ናቸው። የኪርን አሸማጋይነት ጥያቄ ዐቢይም እንደተቀበሉት አንድ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች የተናገሩ ሲሆን፣ ኪር የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ውዝግብንም እንዲያሸማግሉ ዐቢይ እንደጠየቋቸው ባለሥልጣኑ ገልጠዋል፡፡

2፤ መንግሥት ሕወሃትን ከአሸባሪነት ፍረጃ እንዲሰርዝ አፍሪካ ኅብረት ሃሳብ ማቅረቡን ከምንጮች ሰምቻለሁ በማለት የኬንያው ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የሰላም ሃሳቡ ሕወሃት ጦር መሳሪያ እንዲያስቀምጥ እና መንግሥት በክልሉ ምርጫ እንዲያካሂድ እንዲፈቅድ የሚጠይቅ ነው፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ በቀደም ከኬንያ አቻቸው ጋር በተወያዩ ጊዜ የትግራይ ግጭት ዋነኛ መወያያ እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ለድርድር እንዲያመች መንግሥት ሕወሃትን ከአሸባሪነት ይሰረዝ የሚል አቋሟን ኬንያ በተመድ ጸጥታው ምክር ቤትም ከሳምንት በፊት አንጸባርቃዋለች። በአፍሪካ ቀንድ አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት መልዕክተኛ ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ቀጠናው እንደሚጓዙ ያመለከተው ዘገባው፣ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች በ6 ወራት ውስጥ ብሄራዊ ዕርቅ እንዲያደርጉ የኅብረቱ ፍላጎት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

3፤ የሕወሃት ተዋጊዎች በአማራ ክልል በደረሱባቸው አካባቢዎች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ሌሎች ወንጀሎችን እንደፈጸሙ አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ተዋጊዎቹ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በበቀል ስሜት ተነሳስተው እንደገደሉ፣ ንብረት እንደዘረፉ፣ የጤና ተቋማትን እንዳወደሙ እና የእምነት ተቋማትን በከባድ መሳሪያ እንደደበደቡ ዓይን ምስክሮች ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል፡፡ ተዋጊዎቹ በደቡብ ጎንደር ዞን የንፋስ መውጫ ከተማ ሆስፒታልን የሕክምና መሳሪያዎችና መድሃኒቶችን በማውደማቸው እና በመዝረፋቸው በአስራዎች የሚቆጠሩ ታማሚዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከፌደራል ፖሊስ ማስጠንቀቂያ በኋላ ሙስሊሞች በመላው ሃገሪቱ የጠሩትን ተቃውሞ ሰረዙ

4፤ አማጺው ሕወሃት በሦስት አቅጣጫዎች ያሠማራው ታጣቂ ኃይል እንደተመታ የመከላከያ ሠራዊት አቅም ግንባታ ሃላፊ ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል በዳባት እና ደባርቅ በኩል ጎንደር ከተማን ለመያዝ የተንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል ከተመቱት መካከል አንደኛው ነው፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት በከዱት ሜ/ጀኔራል ምግበይ ኃይሌ የተመራው ተዋጊ ኃይል ደሞ ወደ ሱዳን ለመቁረጥ ያደረገውን ሙከራ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች አክሽፈውታል ያሉት ጀኔራሉ፣ በብርጋዴር ጀኔራል ፍስሃ ኪዳኑ የተመራው ታጣቂ ኃይል ደሞ በሱዳን በኩል ሕዳሴ ግድብን ለማጥቃት ሞክሮ እንደተመታ ገልጠዋል፡፡

5፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት ለሕወሃት አማጺያን ድጋፍ አድርጓል ተብሎ የቀረበበትን ውንጀላ በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫ እንዳስተባበለ የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ፈጽሞ እጁን አላስገባም- ብሏል የቃል አቀባዩ መግለጫ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሱዳን ተነስተው ጥቃት የሰነዘሩ ከ50 በላይ የሕወሃት ታጣቂዎችን ገድያለሁ ያለው ትናንት ነበር፡፡ የሕወሃት ጥቃት ዓላማ ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የሕዳሴ ግድብን ማጥቃት እንደነበር ሠራዊቱ ገልጧል፡፡

6፤ ባለፉት ሁለት ቀናት 152 ዕርዳታ ጫኝ ካሚዮኖች ወደ ትግራይ ክልል እንደገቡ ሰላም ሚንስቴር ዛሬ በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ወደ ትግራይ ለመግባት መንግሥት ያቋቋማቸው የፍተሻ ጣቢያዎች ብዛት ከ7 ወደ 2 ተቀንሷል ተብሏል፡፡ በክልሉ 400 ሺህ ያህል ነዋሪዎች በከባድ ርሃብ ቋፍ ላይ ናቸው ሲል ተመድ በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

7፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ 19 ሴቶች ከሕጻናት ልጆቻቸው ጋር መታሰራቸው እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ታሳሪዎቹ በአካባቢው የተቋቋመው የፌደራል ጸጥታ ዕዝ እየወሰደ ባለው ወታደራዊ ርምጃ በወንጀል በሚፈለጉ ባሎቻቸው ሳቢያ የታሰሩ ናቸው፡፡ የወንጀል ተጠርጣሪ ሚስቶችን ማሰር ሕገወጥ እንደሆነ የጠቆመው ኮሚሽኑ እስረኞቹ ባስቸኳይ እንዲፈቱ አሳስቧል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቴዲ አፍሮ መልዕክት አስተላለፈ (ቪድዮውን ይዘናል)

8፤ የኬንያው ሳፋሪኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ ለሚጀምረው የቴሌኮም አገልግሎት የሠራተኛ ቅጥር ማስታወቂያ እንዳወጣ አስታውቋል፡፡ ለቀጣዮቹ 3 ዓመታት በየዓመቱ 159 በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞችን እንደሚቀጥር መናገሩን የዘገበው የኬንያው ስታር ጋዜጣ ነው፡፡ ኩባንያው በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ለኢትዮጵያዊያን 1.5 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና 8.5 ቢሊዮን ዶላር ሙዓለ ንዋይ ለማፍሰስ አቅዷል፡፡

9፤ በሰላም ሚንስቴር የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑካን ቡድን በኢትዮ-ጅቡቲ የጋራ ድንበር አስተዳደር ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ጅቡቲ እንደገባ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ የድንበር አስተዳደር ኮሚሽኑ ስብሰባ የሚካሄደው ነገ እና ከነገ ወዲያ ነው፡፡ ስብሰባው በጋራ የድንበር ጸጥታ፣ በድንበር ዘለል ንግድ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ይወያያል፡፡

[ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share