የተያዘው የጸሎት ፕሮግራም እመኑኝ አይሠራም! – ፍርዱ ዘገዬ

ቤተሰቤ አዲሱን የቴሌቪዥን የጸሎት መርሐ ግብር እየተከታተለ አብሮም በጸሎቱና ምህላው እየተሳተፈ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የራሴን የግል የዘወትር ጸሎት አድርሼ አልጋየ ላይ ጋደም በማለት በኢንተርኔት የሀገሬን ወቅታዊ ጉዳይ እየተከታተልኩ እንዳስፈላጊነቱም በምችለው እየተሳተፍኩ ነው – ዛሬ ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2013ዓ.ም፡፡

ጸሎቱ ለምን እንደማይሠራ የሚሰማኝን ለመናገር እንዴት ከአልጋየ እንደተስፈነጠርኩ እኔና አንድዬ ነን እምናውቀው፡፡ አሁን ባለቀ ሰዓት ይሉኝታ የለም፡፡ ነገ ልሞት ዛሬ የምደብቀው ነገር አይኖረኝም፡፡ የልቤን እናገራለሁ፡፡

ጓደኛሞች የሆኑ ሙስሊሞች አብረው ሶላት እያደረሱ ነው አሉ፡፡ ሶላትን እያደረሰ ያለ ሙስሊምና በወታደራዊ ሰልፍ ላይ የሚገኝ መለዮ ለባሽን የሚያመሳስላቸው ነገር ለዓላማ ቀጥ ብሎ መቆምን ነውና ጸሎተኛው ሌላ ሃሳብ ወደ አእምሮው ዝር አይልም፤ ወታደሩም እባብ ቢጠመጠምበት እንኳ ከወታደራዊ ሥነ ሥርዓቱ ዝንፍ አይልም – ይባላል፡፡ እናላችሁ እነዚያ ሙስሊም ጓደኛሞች እየሰገዱ ሳለ አንዱ ቁጭ ብሎ የነበረ ተንኮለኛ ጓደኛቸው በርከት ያሉ ዝርዝር ሣንቲሞችን ከበስተኋላቸው በመበተን ያቅጨለጭልባቸዋል፡፡ ያኔ ሁሉም በደመ ነፍስ ወደኋላቸው ይዞራሉ – የሣንቲም ነገር በተለይ በዚህ ዘመን የደም ዝውውር ያህል ሆኗላ፡፡ ተንኮለኛው ጓደኛ “ይህን ዱኣችሁን እንኳን አላህ እኔም አልቀበለውም፡፡” አላቸውና ዱኣቸውን አጣጣለባቸው አሉ፤ ትክክል ነው – ከጸለይክ ከልብ መሆን አለበት፡፡

ሃይማኖታዊ ሚዛናዊነትን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ አጼ ምኒሊክ አንድ ወቅት ለአንዱ መነኩሴ “አንቱ መነኩሴ፣ አቡነ ዘበሰማያትን ያላንዳች ሃሳብ ጣልቃገብነት ቀጥ ብለው ከወጡ የጭን በቅሎየን እሸልመዎታለሁ” ይሏቸዋል አሉ፡፡ መነኩሴው የንጉሠ ነገሥት በቅሎ ሊሸለሙ በደስታ ተውጠው ጸሎታቸውን በለኆሳስ ይጀምራሉ፡፡ እንደጨረሱም ንጉሡ “በቅሎዋን መስጠቱን እሰጥዎታለሁ፤ ግን በኅያው እግዚአብሔር ይሁንብዎና ምንም ዓይነት ሃሳብ አላናጠበዎትም?” በማለት የከረረ የነፍስ ጥያቄ ይጠይቋቸዋል፡፡ መነኩሴውም ለኅሊናቸው ያደሩ ነበሩና “አይ፣ እውነት ነው፣ መቼም …‹እንዲያው ግን ጸሎቴን ቀጥ ብዬ ያላምንም ሌላ ሃሳብ ብጨርስ በቅሎዋን ከምር ይሰጡኝ ይሆን› ብዬ አስቤያለሁ” በማለት መልሱላቸውና በአካባው የነበሩ መሣፍንት መኳንንትን ፈገግ አደረጉ ይባላል፡፡ ጸሎትን ካላንዳች መናጠብ ለመጨረስ ያድላችሁ ወገኖቼ፡፡ በዚህ ዘመንማ አናጣቢው ብዙ ነው፤ ኦነግ/ሸኔስ የት ሄዶ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአባይ ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት ወይንስ የነፃነት ትግላችን! ከግርማ ሞገስ

ሃጂ ሙፍቲ ጨርሰውታል፡፡ እግዚአብሔርም እንበል አላህ እንዲህ እንደዋዛ እንደሰው የሚታለል አይደለም፡፡ አዳሜ የልቡን እየሠራ ይቅር በለኝ ቢል ይመስለዋል እንጂ ይቅርታንና ምሕረትን አያገኝም፡፡ ይቅርታና ምሕረት የሚገኘው ከልባዊ ጸጸትና ንስሃ እንጂ በጧት ታጥቦ ከሰዓት ጭቃ ዓይነት የልጆች ዕቃ ዕቃ ጨዋታ አይደለም፤ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ የዓለማችን ቅርጽ ሌላ በሆነ ነበር፡፡ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው ነገሩ፡፡ ሰውና እግዚአብሔር ሌባና ፖሊስ እየተጫወቱበት ባለ ዘመን ውስጥ የአምላክ ምሕረትና ይቅርታ እንደብርቅ የሚቆጠርና ለጥቂቶች የሚሰጥ እንጂ ማንም ወንጀለኛ እየተነሣ የሚቀልድበትና ለማንም የማይከለከል የቡና ቁርስ አይደለም፡፡

የባል ውሽማ የሚባል ነገር ታውቃላችሁ? የባል ውሽማ ማለት ትዳራቸውን የበተኑ ጥንዶች ያልተቋጨ ፍቅራቸውን ወይም ከሌላ ቦታ ማግኘት የተሳናቸውን በድብቅ እየተገናኙ የሚረክሱበት መንገድ ነው፡፡ አብረው እየኖሩ ያልሆነላቸው በሌላ ሕይወት ገበተው ሳለ በስርቆት ሲማግጡ ነው እንደዚያ የሚባል፡፡ ይህን እዚህ ለምን አመጣሁት?

በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ፣ በየጠቅላይ ግዛቱ፣ በየወረዳና ቀበሌው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን ከዋዜማው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ሌሊቱንና ማርፈጃውን እንዲሁም እኩለ ቀኑንና ተሲያቱን ጭምር ሲዥጎደጎድ የሚያድርና የሚውል ቃለ እግዚአብሔር ከደመና በላይ ዘልቆ የጽርሐ አርያምን ደጅ መርገጥና የመንበረ ፀባዖትን በር ማንኳኳት አቅቶት ሀገር በአጋንንት ደዌ እየታመሰች ባለችበት ሁኔታ ሊያውም በስንት ጉትጎታ በተደራጀ የይምሰል የግማሽ ሰዓት የቴሌቪዥን ጸሎት የአቢይንና የሽመልስን ኦነግ ሸኔ አሸንፋለሁ ማለት ትልቅ ቀልድ ነው፡፡ ቀልዱ በሰው ላይ ቢሆን ምንም አልነበረም፡፡ ግን እየተቀለደ ያለው ልብንና ኩላሊትን በሚመረምረው ኅያው እግዚአብሔር ላይ ነው፡፡

በመጀመሪያ ሰላሳውን ሴት እያገባህ የምትፈታ ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ ነኝ ባይ ራስህ ያቆምከውን ቃላ ዐዋዲ አክብርና ላጠፋኸው ንስሃ ገብተህ በንጽሕና ኑር፡፡ ከሌሎች ኃጢኣቶችም ተቆጠብ፡፡ ሶዶማውያን፣ ሙሰኞች፣ ዘረኞች፣ ሴሰኞችና አመንዝራዎች፣ ዋሾዎች፣ ተብታቢዎች፣ ጠንቋዮች፣ አስማተኞች፣ ሰይጣን ጎታቾች፣ ወዘተ፣ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ ከአጋንንት ዓለም ውጡ፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት እንደማይቻል ክርስቶስ ያስተማረውን ቃለ ወንጌል አስታውሱ፡፡ ለሰው ይምሰል ልብስህንና ጥምጣምህን አሳምረህ እግዚአብሔርን የምታታልል ካህን ሁሉ ከጠፋህበት ዓለም ተመለስና በትክክል ህዝብንና ፈጣሪን አገልግል፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን ማነብነብ እንደሆነ ሰይጣንም አሳምሮ ይችልበታል፡፡ ስለዚህ ይህ ጸሎት በፈጣሪ ዘንድ ቅቡልነት የለውም፡፡ ቢሰማ እኮ አንዲት ቀን በቂ ናት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትንሽ ስለ ‘መለሲ-ዝም’: ከኢህአዴጎች የምስማማበት ነጥብ

በልጅነቴ የሆነውን ልንገርህ፡፡ በአካባቢያችን ድርቅ ገባ፡፡ ጭንቅ ሆነ፡፡ አባቶችና ካህናት የምህላ ፕሮግራም ያዙ፡፡ ጥጆች ከላሞች፣ ሕጻናት ከጡት ታግደው ዋሉ፡፡ ወጣት ጎልማሣውም ፆሙን ዋለ፡፡ ምሽቱን ሕዝቡ ከየቤቱ ወጥቶ በየደጁ እግዞዖታውን አቀለጠው፡፡ እኔም ሕጻን ሆኜ ብዙም ሳይገባኝ ከትልልቆቹ ጋር እወድቅ እነሳ ነበር፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ ወዲያውኑ ሰማይ ጠቋቆረ፤ ታይቶ የማያውቅ ዝናብም እንደጉድ ወረደ፡፡ የዚያን ጊዜው ጸሎት እንዲህ ነበር፡፡ አሁን የት አለ? እግዜርና እኛ እኮ ከተነቃቃን ቆየን፡፡ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል፡፡”

የደብር አለቃዎችን እዩ፤ መዘምራንን እዩ፤ ጳጳሣትን እዩ፤ የሰበካ ጉባኤ ኃላፊዎችን እዩ፤ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አባላትን እዩ፤ … ሁሉንም ተመልከቱ፡፡ ክርስቶስ ነጠላ ጫማ አልነበረውም፡፡ እነዚህ ያነጠነጡና ሊፈርጡ የደረሱ የሃይማኖት ነጋዴዎች ግን የሚጓዙበት መኪና ራቭ4 እና ቪ8 ነው – አነሰ ከተባለም ቪትስና ያሪስ፡፡ ንስሃ አባት ብለህ ብትይዛቸው የልጆችህን አባት ለማወቅ ከመቸገርህ የተነሣ ዲኤንኤህን ማስመርመር ሊኖርብህ ነው፡፡ በጠፋ ሃይማኖት መጽደቅ አለ እንዴ? አሃ! አታናግሩኛ! በዚህ ምክንያት አይደለም እንዴ ህዝቡ ከቤተ ክርስቲያን እየወጣ ለባሱ እዩ ጩፋዎችና እስራኤል ዳንሣዎች የሚጋለጠው? የዚያኛው ጎራማ ከማሳቅም አልፎ እጅጉን ያሳቅቃል፡፡

ጸሎትና ምህላ በእምነት ቦታዎች እንጂ የሚያምረውና መለኮታዊ ተቀባይነትም የሚኖረው እንደኦፕራ ሾው በቲቪ መስኮት እየቀረበ በወፈፌዎች ሊፌዝበትና በኢአማያን ሊላገጥበት አይገባም፡፡ ስለዚህ አትልፉ፡፡ ይልቁንስ ሽማግሌዎችና ሕጻናት፣ አእሩግና አንዳንድ የቶበታችሁ ዜጎች በግላችሁ የጠበቀ ጸሎት ያዙ፡፡ በእናንተ ሀገራችን ልትማር ትችላለች፡፡ ዘንድሮ በደቦ መሞት እንጂ በደቦ መዳን ዱሮ ቀረ ጅሌ፡፡ እንጂ በሀገራችን አማራን በየቀኑ የሚጨፈጭፍ ተንከሲስ ቤተ መንግሥቱን ተቆጣጥሮ ባለበት ሁኔታ አንድም መነኩሴ ሃይ የሚል ሲጠፋ ከዚህ በላይ ሃይማኖታዊ ክስረትና ዝቅጠት ከየት አለ? ዮሐንስ በለው ግርማ፣ ገብረ መስቀል በለው ሄኖክ … ሁሉም አጭበርባሪና በፍቅረ ንዋይ የታወረ ሌባ ነው፡፡ የምለው ውሸት በሆነና ኩነኔውን በወሰድኩ፡፡ ደግነቱ ማመዛዘን የማይችል እንደነዱሽ ምዕመን ስለሞላ ተከታይ ከብት አያጡም፡፡ በቃኝ እባክህን … ባልተፈጠርኩ የሚያሰኝ ዘመን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዉኃን ምን አጮኸዉ ቢሉ ድንጋይ አሉ !

 

4 Comments

  1. የምትለው ውሸት ቢሆንም ባይሆንም ፤ ሀገራችን ምህረቱን ለማግኘት እንድትበቃ እስከ ቀጣዩ ሐሙስ ድረስ በይቅርታ እና በፍቅር መንፈስ ፤ በርትተህ በሁለተኛው ዙር የፀሎት መርሐግብር ላይ ንሰሀ ገብተህ ተሳተፍ።

    • የኔ ምኒልክ እንደኔ አንጀትህ ባያር ባይተክን ነው እንዲህ የምትለኝ፤ ያለንበት ሁለንተናዊ የሞራልና የሃይማኖት መላሸቅ ከአእምሮ በላይ ነው። ቦታውም ጊዜውም ትግሥቱም ስለሌለን የጻፍኩት በጣም ኢምንቱን ነው፥ አባይን በጭልፋ ዓይነት።
      ለማንኛውም ወርቅ ምክርህን ከምሥጋና ጋር እቀበላለሁ። እግዜር ይሥጥልኝ።

  2. https://youtu.be/O4CLY3J4wX0

    * የዋህ አማራ *

    እንዳንግባባ ወይ እንዳይኖረን ሰላም
    ያንዱ ነገር ላንዱ በፍጹም እንዳይጥም
    በግፍ የፈሰሰው የንጹሕ ሰዎች ደም
    አድርጎብን ይሆን አደንዛዥ አዚም?
    መሪዎቹን አስፈጅቶ ሊኖር በጋራ
    በእኩልነት ስም በሶሻሊዝም ጎራ
    ለእልቂት ተመቻቸ ለማያባራ
    አንገቱን ሰጠ ለቂመኞች ካራ
    በደም ለሰከሩ በጫት ሀራራ
    በዛር መንፈስ በሚያጓራ
    ጨፈጨፉት በቀኝም በግራ
    አማራ ሞኙ የዋህ ነው አማራ
    ከማለቁ በፊት ወገኔ በየተራ
    ቀስቅሱት ይነሣ ለጀግንነት ሥራ
    በእናት ሀገራችን እኛም እንድንኮራ።
    ራስን መከላከልን ቆጥሮት እንደ ነውር
    አልደራጅም ካለ በዘውገ ብሔር
    አልሰማም ካለ በቃ ተዉት ይቅር
    ፈቃዱ ይሁን የእግዚአብሔር
    ይክበር ይመስገን ስለሁሉም ነገር
    ኵሎ ዘፈቀደ በሰማይ በምድር።

  3. ይህ ከዚህ በታች ያሥቀመጥኩት አሥተያየት ሌሊቱን በሥሜ ገብቼ fb ስከታተል ላገኘሁት የደጀኔ አሰፋ አንድ ወቅታዊ ጥሪ የሰጠሁት ነው። “በጣም ይቅርታና ይህ ጽሑፍ የብልጽግና ፓርቲ መግለጫ ይመሥላል፤ እውነትም ደጀኔ አሰፋ ጽፎት ከሆነ ማን እንደሚያረጋግጥልኝ አላውቅም። 1. ኢንተርኔት ይዘጋ ይላል። ከተዘጋ የሆነውንና እየሆነ ያለውን እንዴት እናውቃለን? እርግጥ ነው ሀሰትና ግነትን መለየት ይከብዳል፤ ጥቅሙ ግን ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ይዘጋ ማለት ኦህዲድ እንዳሻው በግልጽ ይፈንጭ እንደማለት ነው፣ 2. ደጀኔ የችግሮችን ምንጭ ውጫዊ በማድረግ የአቢይን መንግሥት ከጥፋት ነጻ ያደርጋል። እውነቱ እንደዚህ ነውን? አጣዬ የነደደችው በግብጽ ነው? በዐረቦች ነው? በምዕራባውያን ነው? በሱዳን ነው? በአቢይ አህመድ ነው!!! 3. ደጀኔ የችግሩን ምንጭ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥ ይጠይቃል፤ ይህ እጅግ አሥቂኝ ነው። “መንግሥት ፍጠን!!!” ይላል ደጀኔ። “መንግሥት ሆይ! አማራ ተነሥቶብሃልና ቶሎ ብለህ ካላጠፋኸው ጉድህ ነው!” ለማለት እንደፈለገ ያህል ነው የገባኝ። 4. ትክክለኛውንና ፀሐይ የሞቀውን የችግሩን መንሥኤ አይጠቅሥም። መከላከያና ፌዴራል ከኦነግ ጋር እየተናበቡ በህዝብ ገንዘብ በተገዛ ዘመናዊ ሎጂስቲክስ አማራን እንደሚያርዱ አገር ምድሩ እያወቀ ይህን ሃቅ በተዛዋሪ ለማሥተባበል ያቀደ ይመሥላል። ደጀኔ ማን ነው??? ይህ ደጀኔ በርግጥ ከራያ አካባቢ የማውቀው ደጀኔ ነው ወይንሥ ሌላ ታዬ ልበደንዳና አረዶ ይሆን? ጨንቆኛል በዚህ አድራሻ አጽናኑኝ፤ አንዱ የጥቅሉ፣ ጥቅሉም የአንዱ አካል ናቸውና ጥያቄየን ችላ አትበሉ፦ yinegal3@gmail.com

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share