በአጣዬና ዙሪያዋ የሆነው ይህ ነው

በአጣዬና ዙሪያዋ የሆነው ይህ ነው


ለቸኮለ! ቅዳሜ ሚያዚያ 9/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች
—————————–
1፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ካራቆሬ ከተማ “የኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች ዛሬ ካባድ ጥቃት ሲፈጽሙ መዋላቸውን የክልሉ ጸጥታ ሃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ለክልሉ ሜዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል። ማጀቴ፣ አንጾቂያ፣ ሸዋ ሮቢት እና ካራቆሬን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች ታጣቂ ሃይሉ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን እየገደለ እና መኖሪያ ቤቶችን እያቃጠለ መሆኑን እና በይፋ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል። በአጣዬ ከተማ ታጣቂዎች ማረሚያ ቤቱን ሰብረው እስረኞች እንዲወጡ ማድረጋቸውንም ገልጠዋል።
——————–
2፤ ኤርትራ ወታደሮቿን ከትግራይ ክልል ለማስወጣት መስማማቷን ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ አስታውቃለች። ኤርትራ ጦሯን እንድታስወጣ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች በዐለማቀፉ ድንበር ላይ እንዲሰፍሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ እንደተደረሰ በተመድ የኤርትራ መልዕክተኛ ሶፊያ ተስፋ ማርያም በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል። ወታደሮቿ የሚወጡበትን ጊዜ ግን ኤርትራ አልጠቀሰችም።
——————————–
3፤ ኤርትራ በአሥመራ የተመድ ቋሚ ተወካይን እና የተመድ ሰብዓዊ ዕርዳታ ሃላፊን ጠርታ ቅሬታዋን እንደገለጸች የሀገሪቱ ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው ገልጠዋል። የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተመድ ተወካዮቹን በአካል ጠርቶ ያነጋገረው፣ በትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ በተመድ ዋና መስሪያ ቤት ያሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ እና ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊዎች በኤርትራ ላይ የሚያወጧቸውን የሴራ ውጤት የሆኑ ሐሰተኛ ሪፖርቶች ላይ ተቃውሞዋን ለመግለጽ ነው።
——————————————
4፤ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት በወረራ እንደያዘች እና ኢትዮጵያዊያንን ከአልፋሽጋ እንዳፈናቀለች አድርጋ ኢትዮጵያ የምትሰጣቸው መግለጫዎች “አሳዛኝ እና አሳሳቢ ናችው” ሲሉ የሱዳን ሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀኔራል ቡርሃን ለአል ዐረቢያ ቴሌቪዥን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መግለጫዎች ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ናቸው፤ ሆኖም ሱዳን በአልፋሽጋ የተነሳ ጦርነት ውስጥ የመግባት ዕቅድ የላትም- ብለዋል ጄኔራሉ። ኢትዮጵያ በሱዳን መሬት ያሠፈረቻቸውን ወታደሮቿን እንድታስወጣ የጠየቁት ጄኔራሉ፣ ድንበር ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ግን ለመነጋገር ዝግጁነታቸውን ገልጠዋል። የኢትዮጵያን የጦርነት ጉሰማ ለማስቆም፣ ሦስተኛ አሸማጋይ ወገኖች በጉዳዩ ቢገቡም ተቃውሞ የለንም- ብለዋል ቡርሃን።
————————————-
5፤ በሱማሊያ አዲስ የፓርላማ ምርጫ መርሃ ግብር ለማውጣት፣ አፍሪካ ኅብረት እና ዐለማቀፍ አጋሮች በፖለቲካ ሃይሎች መካከል በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አዲስ ውይይት እንዲጀመር ግፊት እንዲያደርጉ ዐለማቀፉ የግጭት አጥኝ ቡድን (አይሲጄ) ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ጠይቋል። ተቃዋሚዎች የፕሬዝዳንት ፎርማጆ ሥልጣን ዘመን መራዘሙን በመቃወም፣ ትይዩ መንግሥት ለማቋቋም እያሰቡ መሆኑን እና በሀገሪቱ ጸጥታ መዋቅር ውስጥ ስንጠቃ መፈጠሩ አደገኛ ምልክቶች መሆናቸውን ቡድኑ ጠቅሷል። ለአካታች ውይይት እና ምርጫ እንቅፋት በሚሆኑ ወገኖች ላይ የሱማሊያ አጋሮች ማዕቀብ ለመጣል ቁርጠኝነት እንዲያሳዩም ቡድኑ ጠይቋል።
—————-
[ዋዜማ ራዲዮ]

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግራ የሚያጋባ ሁኔታ፣ ግራ የተጋባ መሪ፣ ግራ የገባው ህዝብና ምሁር፣ እንዲሁም የለውጥ ጉዳይ ! - ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share