ሀገር ስታምጥ* (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

ሀገር ስታምጥ*
በሴኮንድ በቅጽበት በእልፍ የሚራባ
የጎሳ አሜባ
ያ ነው የሚያስምጣት
ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ ምናምን አይደለም
የመልካም ተስፋ ጽንስ፤
ተውሳክ እንጂ ተባይ
እየዋለ እያደር ጤና የሚቀንስ።
ከዚህ ካሁኑ ምጥ
አሜባውን ገዳይ መድኀኒት ነው እንጂ፤
የሚወጣው ነገር
ፈውስን አያመጣም ለነገ ሚበጅ።
የምጡ መነሻ
እርግዝና አይደለም የሚወለድ ተስፋ፤
ጥሬው ቅጠል እንጂ
የፈረንጅ ሰላጣ የበላችው ቀጥፋ።
የጎሳ አሜባ በእልፍ የሚራባ
አመንምኖ ገዳይ ከሊቅ እስካንቀልባ
እሱ ነው መንስኤው
ተራው የእለት ግዳጅ የመመገብ ጣጣ
ሰቆቃ ሆኖባት የምትኖር አምጣ።
ሆዷ እንዲህ ተልቆ
በማርገዝ ቢመስልም ከስታ መመንመኗ፤
የምጥ ስቃይዋ ምንጭ
ባንጀቷ ነው ያለው ሳይሆን በማሕፀኗ።

ምጧ
ስታምጥ ብታዩ ሴቲቱ በጠና
የምጧን መንስኤ እዩት በጥሞና
ተውሳክ አሜባ እንጂ የሚያቃውስ ጤና
የጽንስ ጣጣ አይደለም የልጅ እርግዝና
የምጧ ሁኔታ
የምጧ እርዝማኔ
የምጧን መንስኤ ይነግረኛል ለእኔ
ከቶ አለመሆኑን
በማሕፀን ያለ የነገ ቀን ተስፋ
ባንጀቷ ያለ እንጂ
መድኃኒት ካልሰጧት ይዟት የሚጠፋ።

*አስቴር ስዩም (ቀለብ) ለአዲስ አበባ ሕዝብ መብት በመታገሏ ምክንያት ለእስር ከተዳረገችበት ከቃሊቲ እስር ቤት “ሀገር ስታምጥ” የሚል መጽሐፍ ደርሳለች። መጽሐፉ ገና ያልተዳረሰ ቢሆንም በምርቃቱ መርሐግብር ከተነገረው ስለመጽሐፉ ይዘት ጠቅላላ ሃሳብ ለማግኘት ይቻላል። የዚህ ግጥም ርእስ ከአስቴር መጽሐፍ ርእስ የተወሰደ ቢሆንም ይዘቱ የተለየ አመለካከት ያለው ነው። ይህም ሲባል መጽሐፉን ለመቃረን ሳይሆን ስለዚያችው እስቴር ስለተጨነቀችላት ሀገር ምጥ የተለየ ምክንያተ—ሕመም (ፈርጅ/ ዲያግኖሲስ)በማየት በሌላ አንጻር በመፈላሰፍ የተጻፈ ነው።
ምናልባት የስብእና እና የጥንካሬያችንንም ልዩነት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። እነሱ በአፋኞች ጠባብ እስር ቤት ታጉረው ወቅታዊ የሀገሪቱ ምጥ ተስፋን፣ ዲሞክራሲያዊ ወይም ፍትሐዊ ሥርዓትን ለማዋለድ የሚከሠት ጣእር ነው ብለው ያስባሉ። መስዋእትነት የሚከፍሉትም በዚህ እምነትና ተስፋ ነው። ውጪ በ“ነጻው” ዓለም ያለን ሰዎች ደግሞ የተረገዘው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አይታየንምና የምጡና የማማጡ መንስኤ ብለን የምናስበው ጊዜው የተቃረበ ጽንስ ሳይሆን አንጀት በጣጥሶ የሚገድል በፍጥነት የሚራባ አሜባዊ የጎጠኝነት ተውሳክ ነው። ፈውሱም ሊገኝ የሚችለው አሜባውን የጎሳ ፖለቲካ የሚያጠፋውን መድኅኒት በመውሰድ እንጂ ከምጡ በሚገኝ የምጡ ውጤት ወይም በ“መገላገል” አይደለም። እግዚአብሔር በባእዳንና በጎሰኛ ምስለኔዎቻቸው በጭንቅ የተያዘችውን ሀገር ይታደግልን። የአስቴርን የእስክንድርን እና ሌሎችንም የኅሊና እስረኞች ነጻነት ያቅርብልን። ከዚህ ኋላቀር፣ ጨካኝ፣ አቆርቋዥና በታኝ ዘር ቆጣሪ የጎሣ ሥርዓት ነጻ የምንወጣ ትውልድ እንሁን።
አስቴርን እግዚአብሔር ይስጥሽ። ቸሩ አምላክ ቤተሰብሽን ይባርክልሽ። ትግልሽን በድል ይቋጨው። መጽሐፍሽን አግኝቼ እስካነበው ጓጉቺያለሁ። ለማለት እወዳለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የካርታ ጨዋታ (ዘ-ጌርሣም)

በገዢዎቻችን ሴራ በመላ ኢትዮጵያ የሚፈሰውን ደም ያቁምልን። አዲስ አበባንም ከተደገሰላት ጥፋት ይታደጋት።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share