የአዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የምርጫ ቀን ፖለቲካዊ አንድምታ አለው በሚል የሚነሱ ሀሳቦች የተሳሳቱ ናቸው – ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ

የአዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የምርጫ ቀን  ፖለቲካዊ አንድምታ አለው በሚል የሚነሱ ሀሳቦች የተሳሳቱ መሆናቸውን  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን  ሚደቅሳ  አስታወቁ።

ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ባለበት አካባቢ ምርጫ እንደማይደረግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ  ቦርድ“በምርጫ ብቻ”  በሚል  ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት  ተከታታይ       ቀናት “ምርጫ ቦርድን ይጠይቁ” በሚል ርእስ የማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ መድረክ  አዘጋጅቷል።

ቦርዱ በማህበራዊ ሚዲያ የተነሱለትን ጥያቄዎች በመሰብሰብ በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

የአዲስ አበባንና ድሬደዋን የምርጫ ቀን በተመለከተ የፖለቲካ ምልከታ ሊኖረው ይችላል በሚል የሚነሳ ሃሰብ መኖሩን የጠቆሙት ዋና ሰብሳቢዋ÷ የሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የምርጫ ቀናት ከሌሎች አካባቢዎች የተለየበት ምክንያት የምርጫውን ተአማኒነት ለማረጋገጥና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳይከሰቱ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ከ1997  ዓ.ም በኋላ አስተዳደራዊ ለውጦች መደረጋቸውን ተከትሎ የቀበሌ አስተዳደር በመቅረቱ ድሮ በምርጫ አከላለል የነበረው የቀበሌ ሁኔታ አሁን አለመኖሩን አንስተው÷ አዳዲስ ክፍለ ከተሞች መኖራቸው  እንዲሁም  የወረዳ ወንበሮች በክፍለከተማ ደረጃ በሚገኝ ምክር ቤት እንዲሆን በከተማ ደረጃ መወሰኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ ምርጫ ከክልሎች ምርጫ ጋር እኩል ቢካሄድ አከላለቻቸው አስቸጋሪ በሆኑ በነዚህ ቦታዎች ላይ የሚካሄደውን ምርጫ  ለመቆጣጠርና በተአማኒነት ለመቀበል ምቹ  አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

ይህም ለፓርቲዎችም ታዛቢና ወኪሎቻቸውን ለመላክ አስቸጋሪና አጠራጣሪ እንደሚያደርግባቸው  ተናግረዋል።

የሁለቱ ከተማ መስተዳደሮች ምርጫ ግልጽና ቁጥጥር የተደረገበት እንዲሆን ከሌሎች አካባቢዎች ምርጫ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ መወሰኑን አመልክተዋል።

በዚህም የከተሞቹ ምርጫ ቀን መራዘም ፖለቲካዊ አንድምታ አለው የሚለው መታሰብ የሌለበትና ከተሳሳተ አተያይ የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህ በኩል የሚሱ ጉዳዮች ተቀባይነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዘግይቶ ባገኘነው ዜና: ለቸኮለ! ማክሰኞ ኅዳር 28/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ የሚነሱትን ጉዳዮች ለመፍታት ተቋሙ የራሱን አሰራር እንደዘረጋና ቁጥጥር እንደሚደረግ ነው የገለጹት።

ህብረተሰቡም ከእነሱ ቀበሌ ውጪ ነዋሪ የሆነ አካል ወደ ምርጫው በሚመጣበት ጊዜ መቆጣጠርና ማጋለጥ እንዳለበት አስገንዝበው ÷በዚህ ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲቪክ ማህበራትም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ምርጫና የጸጥታና ደህንነትን በተመከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ቦርዱ ከፌደራል መንግስትና ከክልሎች ጋር ስልጠናዎችን በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ ስራው ግን ከዚህ በተሻለ ፍጥነት መሰራት አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

ችግሮች ሲከሰቱ የሚፈቱበትን መንገድ በመፈለግና በማሳሰብ ከመንግስት ጋረ አብሮ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ዋና ሰብሳቢዋ÷ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ በመስጠት ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ባለበት አካባቢ ምርጫ እንደማይደረግም  ገልጸው÷ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ባለበት ቦታ ዜጎች በታማኝነት ምርጫ ያደርጋሉ ተብሎ እንደማይታሰብም ነው ያስታወቁት።

በትግራይ ክልልም በጸጥታው ዘርፍና በአስተዳደሩ ክፍል ከፍተኛ መሻሻል ሲመጣ ምርጫው እንደሚደረግ ገልጸው÷በክልሉ ለሚካሄደው ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

የክልልነት ጥያቄዎች ሳይመለሱ ምርጫው ሊካሄድ ይችላል? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄም የክልል ጥያቄዎች እስከሚመለሱ  ተብሎ ምርጫው እንደማይዘገይና ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ ጥያቄው መቅረብ እንደሚችል ምላሽ ሰጥተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎችን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሰራ እንደሚገኝና የስልጣን ወሰንነት እስከሚገድበው ድረስ ቦርዱ ሃላፊነቱን በገለልተኝነት በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆነው ግጭት በመቀስቀስ በአመጽ በመሳተፍና በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ አካለትን ጉዳይ በተመለከተ ምርጫ ቦርድ በቀጥታ ገብቶ መፍትሔ መስጠት እንደማይችልና የስራ ሃላፊነቱም  እንደማይፈቅድለት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔ ሲያስር አሜን….ሲገድልም አሜን

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው “በምርጫ ብቻ” የማህበራዊ ሚዲያ የጥያቄ ተሳትፎ 1200 ገደማ ጥያቄዎች የተነሱበት ሲሆን ጥያቀዎቹን በመጭመቅ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምላሽ ሰጥተውበታል።

ኤፍ ቢ ሲ

3 Comments

  1. ለቡርቴ
    የምርጫዋ እመቤት ብርቱካን ሚደቅሳ
    ይቅርብሽ ይህ ወንጀል ስምሽ አይነሳ
    በሕግም ያለ ሕግ ሲመታ ወሪሳ
    በቃኝ ብለሽ ውጪ ለታሪክ ጠባሳ
    አንቺንም እኛንም አይዳርገን ግሪሳ።

  2. ማህበራዊ ሚድያ ላይ በተደጋጋሚ ተጠይቆ መልስ ሳይገኝለት በክፍል ውስጥ ያለ ዝሆን (Elephant in the room) የሆነብንን የሚከተለውን ጥያቄ ምነው ምርጫ ከመምጣቱ በፊት መልስ ጠፋለት? ፡ “እስክንድር ነጋ ፣ ስንታየሁ ቸኮል ፣ አስቴር ስዩም እና አጋሮቻቸው በአሸባሪነት ተከሰው እና በህግ ቁጥጥር ስር ሳሉ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ለምርጫ እንዲወዳደር እና ቅስቀሳ እንዲያካሂድ መፍቀድ ህገ ወጥ አይሆንም ወይ?”

    ይህንን ጥያቄ ወቅታዊ አፋጣኝ መልስ ባለመስጠታችን በአለም ዙርያ ያሉ ዴያስፖራዎችን ለጥፋት እንዲሰለፉ ምክንያት እየሆነ ስለመጣ ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት የሰማነው ” የባልደራሰ  መኢአድ ቅንጅት ድጋፍ ኮሚቴ በሰሜን አሜሪካና ካናዳ ተመሰረተ ” የተባለው ዜና ስለሚያመላክት አሁንም ከላይ የተጠቀሰው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ተሰጥቶት እልባት እንዲያገኝ በድጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አቤቱታችን ይድረስልን።

  3. ምርጫ ቦርድ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ህገ-ወጥ የሆኑ ነገሮችን እና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ የፓርቲ አባሎችን ለፍርድ ቤት እንዲጠየቁ ስልጣን ካልተሰጠው ምንም ዋጋ የለውም/Functional/ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ እንደውም ከአሁኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልፅግና ጭምር በውስጣቸው ያሉት ሁሉም አባለቶች የምርጫው ውጤት ምንም ሆነ ምንም ህዝብን ወደ አመፅና ግጭት የሚያመሩ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ዘብጥያ መወረድ ያለባቸው እነሱ እንደሆነ በህግ አካለት በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ከአሁኑ መፈረም አለባቸው፡፡ እንዲህ እንደቀላል መታየት የለበትም፡፡ የፓርላማ አባላት ተብዬዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ በመምከር አስቸኳይ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ማድረግ አለባቸው፡፡ እንደራሲ የምክር ቤት መባል ህዝብን ካልወከለ እና ለህዝብ የህግ ከለላ ማድረግ ካልቻለ ዋጋ የለውም፡፡ ብርቱካን መዴቅሳም ያ በፊት የነበረ የህግ ባለሙያ አቅም እንዳይሰለብ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ያኔ በቅንጅት ጊዜ ተፈጥሮ የነበረ ግፍ እና እልቂት አሁንም ደግሞ እንዳይፈጠር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ነገ የምርጫ ቦርድ ስልጣን እና ኃላፊነት አይደለም በማለት ነገሮችን መግፋት ሊታሰብበት ይገባል፡፡

    የአዲስ አባባ እና ድሬዳዋ ምርጫን ማዘግየት እራሱ የተለየ ችግር ያመጠል፡፡ አጠቃላይ ምርጫ ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ የአሜሪካ ምርጫ እንኳን ተንዛዝቶ ስንት ነገር የተፈጠረው ለዛውም ሰለጠነች በተባለች አገር፡፡ ስለዚህ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህ የተጎዳ ህዝብ ጥንቃቄ ባልተደረገበት ምርጫ ሌላ ስቃይና መከራ ማየት አይፈልግም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share