የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ሦስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል

146376270 3992426360838115 8989100973877419179 nየህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ሦስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን፤ የምርጫ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ደንብ ደግሞ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በቀዳሚነት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት የሚውል የብድር ስምምነት ሲሆን፤ ስምምነቱ በሀገራቱ በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል የተደረገ ነው፡፡

የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ስምምነቱ ሀገራችን የጀመረችውን የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ማገዝን ዓላማ ያደረገ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ የአዋጁ አተገባበር ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ከምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ታክሎበት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

ለሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተገኘውን የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በስድስት ተቃውሞ እና በዘጠኝ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡ በመጨረሻ የጸደቀው ረቂቅ አዋጅ የሜቲዎሮሎጂ ምልከታ መሰረተ ልማት እና ትንበያ አቅም ግንባታን የሚመለከት ነው፤ ፕሮጀክቱ ሀገራችንን ከአደገኛ የአየር ሁኔታ ለመከላከል የሚያስችል ስለመሆኑ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ረቂቅ አዋጁን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

በምክር ቤቱ የጸደቁት ሦስቱም አዋጆች ከወለድ ነጻና በመካከለኛ ጊዜ ተከፍለው የሚጠናቀቁ በመሆኑ ከሀገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የተጣጠሙ ስለመሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል አከራካሪ የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ስለሚስተናገዱበት አግባብ የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ዋና አፈ-ጉባኤው ታገሰ ጫፎ ከቀረበ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

ረቂቁም ደምብ ቁጥር 1/2013 በመሆን ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ እንዲመራ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ተስማምቷል፡፡ ምንጭ፡-የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

አብመድ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.