በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለው ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየት – ክፍል 11

/

ለተከበራቹህ ወገኖች                                                                           

ሁለተኛው ዙር የከረርው ጥብቅ ሎክዳውን – 07.01.2021

ካለፈው በመቀጠል ስለ ኮቪድ-19  ወረርሽኝ 2ኛ ማዕበል የተወሰነውን ጥብቅ ሎክዳውን የያዘውን ክፍል አስራ አንድን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

የጀርመን መንግስት ቻንስለር ክብርት አንጌላ ሜርክል ከፌዴራል መንግስታት ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር በመመካከር ከዚህ በፊት በ10ኛው ገለፃ አቅርቤ የነበርውን ሙሉ በሙሉ ሎክ ዳውን በማጥበቅ ከጥር 11 ቀን 2021 እስከ የካቲት 1 ቀን 2021  በጀርመን የሚቆይ ከበፊቱ እጅግ የጠበቀ ሎክዳውን ጥለዋል።

የኮሮናው ቫይረስም በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨቱን የቀጠለ ሲሆን የሮበርት ኮህ ኢንስቲትዩት እንደዘገበው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በተመሳሳይ የናሙና ምርመራ መጠን ካለፉት ጊዜያቶች ሲነጻጸር የታሰበውን ያህል መሻሻል አላሳየም። በአልፉት ቀናት የሚሞቱትም ቁጥር ከ1ሺ በላይ አልወረደም። ጀርመን ላይ እስካሁን ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ሲያዙ፣ ከዛ ውስጥ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አገግመዋል። ከ38ሺ በላይ ሰዎች በወረርሽኙ በተገናኘ ህይወታቸው አልፏል። ከዚህ በመነሳት ከላይ የተጠቀሰው ጥብቅ እርምጃ በአስቀድሞ መከላከል እቅድ መሰረት ሲወሰን፣  የሌሎቹ እርምጃዎች ትግበራ ቀጥሏል፤ ጥር 25 ቀን እንደገና የእርምጃዎቹ ውጤት ይፈተሻልም ተብሏል።

  1. የማህበራዊ ግንኙነት ገደቦች።

ለወደፊቱ ከቤተሰብ ውጭ የሚፈቀደው ማህበራዊ ግንኙነት ከሌላ አንድ ሰው ጋር ብቻ የሚደርግ ነው ።

  1. ተንቀሳቃሽነት

ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል ከ 200 በላይ አዳዲስ ኢንፌክሽኖች ለሰባት ቀናት በተገኙባቸው ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪዎች ያለ በቂ ምክንያት ከሚኖሩበት ቦታ ከ 15 ኪሎ ሜትር በላይ እንዲዘዋወሩ አይፈቀድላቸውም።  ለምሳሌ በዚህ ሳምንት ከተጠቀሱት 55 ቦታዎች መሀከል- Eisenach (429,5)፣ Cottbus (348,2) Zwickau (336)፣ Nürnberg (310,6)፣ Dresden (309,9)፣ Gießen (253,6)፣ Potsdam (241,5)፣ Fürth (223,1)

ከሌላ አገር ወደ ጀርመን የሚገባ ማንኛውም ሰው በጉዞው ዕለት ወይም ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት 48 ሰዓት ያልሞላው ኔግቴቭ የኮሮና ናሙና ውጤት ማቅረብ አለበት። አስር ቀናት የሚዘልቀውን የኳራንታይን ግዴታ በአምስተኛው ቀን በሚቀርብ ኔጋቲቭ ናሙና ማቋረጥ ይቻላል።

  1. የሰዓት እላፊ

በሁሉም ባይሆን በተለያዩ ሪጅናል ስቴቶች የሰዓት እላፊ ይቀጥላል። ለምሳሌ በትልቁ የጀርመን ግዛት ባቫሪያ ከምሽቱ 3  ሰዓት (9 p.m.) እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት (5. a.m) የሰዓት እላፊ ሲቀጥል በዚህ ጊዜ ውስጥ መኖሪያ ቤት ለቅቆ መውጣት አይቻልም።  በልዩ ሁኔታ የሚፈቀዱባቸው – ድንገተኛ ሕክምና ፣ አስቸኳይ የስራ ሁኔታ፣ ሟችን ለማጀብ፣ የእንስሳት እንክብካቤ ናቸው። በቱሪንጊያ ሪጅናል ስቴትም በተመሳሳይ የሰዓት እላፊው ከምሽቱ 4  ሰዓት (10 p.m.) ይጀምራል። በአብዛኞዎቹ ከተሞች ፖሊሶችም ቁጥጥር ሲያደርጉ፣ እስከ መኖሪያ ቤት ተከታትለው ማጥራት እና ገብተው መፈተሽም ይችላሉ፣ የትራፊክ መብራቶችም ቀይ ላይ እንደሆኑ ይረጋሉ። በተቃራኒው ደግሞ በሌሎች ሪጅናል ስቴቶች እና ከተሞች እንደ በርሊን፣ ፍራንክፈርት፣ ሃምቡርግ፣ ኮልኝ፣ ሽቱትጋርት የመሳሰሉትን ጨምሮ የሰዓት እላፊ አላወጁም።

  1. የዕለታዊ ፍጆታ ጅምላ ሻጮች እና ቸርቻሪዎች፣
ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሰላም መቶ በመቶ ያሸልማል” ፕሮግራም ላይ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ያደረጉት ንግግር

የዕለታዊ ፍጆታ ከሚሸፍኑ በስተቀር ሁሉም ሱቆችና  የገበያ ቦታዎች እስከ ጃኑዋሪ 31 ቀን 2021 /ጥር 23 ድረስ ዝግ ሆነው ይቆያሉ። ይህ እገዳ የማይመለክታቸው የምግብ ቸርቻሪዎች፣ ሳምንታዊ ገበያ እና አካፋፍዮች፣ የሸቀጣሸቀጠ ሱቆች፣ የፖስታ እና የእቃ የመሰብሰብ እና የማደል አገልግሎቶች፣ የመጠጥ ገበያዎች፣ የጤና ምግብ መደብሮች እና ፋርማሲዎች፣  ነዳጅ ማደያዎች ፣ የመኪና እና የብስክሌት ጋራዦች፣ ባንኮች፣ የልብስ ማጠቢያዎች ፣ የጋዜጣ ሽያጭ ፣ የቤት እንስሳት አቅርቦቶች፣ የእንስሳት መኖ ገበያዎች  ሲሆን፣ የሆቴሎች እና ሪስቶራንቶች ዝግ ሆኖ መቆየት ይቀጥላል። በመስሪያ ቤቶች የሚገኙ ምግብ ቤቶች/ ካንቲንስ ዝግ ናቸው። ቢሆንም ምግብ እና መጠጥ ይዞ ለሚሄድ ሊያቀርቡ ይችላሉ።

  1. ትምህርት ቤቶች እና መዋለ ሕጻናት፣

ትምህርት ቤቶች እና መዋዕለ ሕጻናት ዝግ እንደሆኑ ይቀጥላሉ፤ የመቀራረብ ገደቦችም ተፈጻሚ ይሆናሉ። ልጆች በተቻለ ሁሉ በቤት ውስጥ ትምህርት መከታተል አለባቸው። ጀርመን አገር አንድ ሰው በአካል ተገኝቶ ትምህርትን የመከታተል ግዴታው በድጋሚ ለጊዜው የተነሳ ሲሆን አስቸኳይ የርቀት ትምህርት ይበረታታል። ወላጆች በተጠቀሰው ጊዜ ልጆቻቸውን ከቤት ሆነው ለመንከባከብ ፈቃድ ከደሞዝ ጋር መውሰድ እንዲችሉ ተጨማሪ ዕድሎች ይፈጠራሉ። ለተመራቂ ተማሪዎች ትምህርት የተለዩ ደንቦች ሊተገበሩ ይችላሉ። ሕፃናት የታመሙበት ወላጅ በዓመት እስከ አስር የሥራ ቀናት ደሞዙ ሳይቀነስ ከስራ ቀርቶ  ልጁን መንከባከብ የሚችለው መመሪያ ተሻሽሎ፣ ወላጆችን እስከ 20 ቀናት ድረስ ሕፃናትን ለማስታመም እንዲችሉ፣ ለብቻ የሚያሳዳጉ ደግሞ እስከ 40 ቀን ከስራ መቅረት የሚችሉ ሲሆን ይደጎማል። ይህ ድጎማም ልጁ በኮሮና ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት ወይም ወደ መዋዕለ ሕፃናት መሄድ ካልቻለም ተግባራዊ ይሆናል።

በአንዳንድ የፌዴራል ግዛቶች ውስጥ የተለ ደንቦች ሊኖሩ ይችላል።

  1. የአልኮል መጠጥ

እስከ የካቲት 1 ቀን 2021 ድርስ  በአደባባይ አልኮል መጠጣት ክልክል ነው። ይህንን ደንብ የሚጥስ ይቀጣል።

  1. የእምነት ቦታዎች

በአብያተ-ክርስቲያናት፣ በምኩራቦች እና በመስጊዶች፣ እንዲሁም በሌሎች የሃይማኖት ማህበራት አገልግሎቶች የሚፈቀዱት የ1.5 ሜትር ርቀት መተግበር ከቻሉ ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳል። የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ሲሆን፣ በእነዚህ ስነስርዓቶች ወቅት የጋራ መዘሙሮች የተከለከሉ ናቸው። ተሳታፊዎችም አስቀድመው መመዝገብ አለባቸው።

  1. ቤተ አረጋውያን / የአረጋዊያን መጦሪያ

ለቤተ አረጋውያን የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚሰሩ እና ተመላላሽ የህክምና ሰራተኞች በሳምንት ውስጥ በተደጋጋሚ የግዴታ የኮሮና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የበሽታው መጠን እየጨመረ በሄደባቸው ቦታዎችም ጎብኝዎች አዲስ ኔገቲቭ የኮሮና ናሙና ማቅረብ አለባቸው።

  1. የመዋቢያ ስቱዲዮዎች እና የመታሻ ቤቶች

የግል እንክብካቤ የሚሰጡ ተቋማት እንደ የፀጉር አስተካካዮች ፣ የመዋቢያ ስቱዲዮዎች ፣ የጤና መታሻ ቤቶች እና የንቅሳት ስቱዲዮዎች የመሳሰሉት እንደተዘጉ ይቀጥላሉ። ሆኖም እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሕክምናዎች፣  ማለትም የፊዚዮቴራፒ፣ የኤርጎ እና ሎግቴራፒ እንዲሁም የእግር እንክብካቤ ሊፈቀድላቸው ይችላል።

  1. የሥራ ቦታ Home Office (HO)
ተጨማሪ ያንብቡ:  ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ዋንጫ ውጭ ሆነ

አሠሪዎች በኩባንያዎች ወይም በተቋማት ለሰራተኞቻቸው የቤት የስራ ቦታዎችን Home Office በአስቸኳይ እንዲያመቻቹ እና እንዲያጠናክሩ ይጠበቃል።

  1. ስፖርት እና የመዝናኛ ተቋማት

የጤና ተኮር ስፖርት እና የአማተር ስፖርት ዝግ እንደሆኑ ሲቀጥል፣ የተናጠል ስፖርት ለምሳሌ ሩጫን ወይም ከቤተሰብ ጋር ወይም ከአንድ ከቤተሰብ  ውጭ ከሆነ ሰው ጋር የሚሰራ ስፖርት እገዳው አይመለከተውም። ለመዝናኛ የሚያገለግሉ ተቋማት ዝግ እንደሆኑ ሲቀጥሉ፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ቲያትር ቤቶች፣ ኦፔራዎች እና የኮንሰርት አዳራሾች ዝግ ሆነው ይቀጥላሉ።

  1.  ኢኮኖሚ እና ቱሪዝም

የኮሮና ቀውስ ኢኮኖሚውን ክፉኛ ቢመታውም፣ ጥብቁ ሁለተኛው ሎክዳውን ቢጣልም የጀርመን ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት ከአራት በመቶ ደረጃ እንደሚያድግ አና ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ውጤት በተሻለ እየተቋቋመ እንደሚመጣ የማይክሮ ኢኮኖሚክስ እና ቢዝነስ ሳይክል ምርምሮች ያሳያሉ። በሎክዳውን ለተጎዱ ኩባንያዎች፣ ተቋማት የኢኮኖሚ ድጋፍ እፎይታ መደርጉ አሁንም ቀጥሏል።  የቱሪስቱ ሲክተር በከፍተኛ ሁኔታ በመመታቱ  የኢኮኖሚው እንቀስቃሴ በተጓዳኝ መስኮች ላይ በመሸጋገር ለቱሪስት ይወጣ የነበርው በርቀት ኢኮኖሚው (Distance Economy) ላይ፣ በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ በቤት ውስጥ እቃዎች፣ የጤና ግልጋሎት እቃዎች፣ በብስክሌት፣ በቅርቡም በመኪና ላይ ከፍተኛ ጭማሪን አሳይቷል። በ2019 ከ70 ሚሊዮን በላይ ጀርመኖች ወደ ውጭ እና በአገር ውስጥ ውስጥ ለቱሪስት ጉዞ 73 ቢልዮን ዮሮ ሲያወጡ ከ55 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶችም በ2019 ጀርመንን ጎብኝተው ነበር። ስፔን፣ ጣሊያን፣ ቱርክ፣ ኦስትራያ፣ ግሪክ፣ ፈረንሳይ በይበልጥ በጀርመኖች ሲጎበኙ ወደ አፍሪካ ስንመጣ 1.7 ሚሊዮን ጀርመኖች በአመት ውስጥ ግብጽን በመጎብኘት ቀዳሚ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት እርግጠኛ ባልሆንም በአማካይ በአመት ወደ 20ሺ የሚጠጋ እንደሆን ይሰማል።

  1. ክትባት

ጀርመን ውስጥ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኮቪድ 19 መከላክያ  ክትባት መሰጠት ተጀምሯል። ሁሉም በእንክብካቤ ተቋማት የሚገኙ ነዋሪዎች እስከ የካቲት 2021 አጋማሽ ድረስ መከተብ ያለባቸው ሲሆን እስከ የካቲት 1 ድረስ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ክትባቶችን ለመስጠት ዕቅድ ተይዟል።

እስከ ጃኑዋሪ 5 ቀን 2021 ድረስ ከ300ሺ በላይ ክትባቶች ሲሰጡ ከነዚህም 130ሺ የሆኑት ለአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከሎች የተሰጠ ነው። አንከተብም ያሉ ሰዎች አንዳሉም ተገልጿል። ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጻር በተለይም እስከ አሁን 1 ሚሊዮን ዜጎቿን ከከተበችው እስራኤል አንጻር ሲታይ የጀርመን የተጓተተ ነው ተብሎም ተተችቷል። በሙያቸው ሃኪም የሆኑት የጀርመን ቻንስለር ጽ/ቤት ሃላፊ እና የልዩ ጉዳዩች ሚኒስትር የሆኑት ፕሮፌሰር ሂልገ ብራውን ራሳቸው ሲከትቡም ታይተዋል። የጀርመን ክትባት ቅደም ተከተል በሶስት ቡድን ላይ የተከፋፈሉ ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰበር መረጃ: ዛሬም የዩኒቨርስቲ ተማሪወች በወለጋ አማራወች ላይ የተፈፀመውን ዘር የማጥፋት ጭፍጨፋ ተቃውመው ሰልፍ በተለያዩ ከተሞች ቀጥላል

■            ቡድን አንድ – እጅግ በጣም ከፍተኛ ትኩረት

ከፍተኛውን ቅድሚያ የሚሰጠው ዕድሜያቸው 80 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ አረጋውያን እንዲሁም እንክብካቤ ለሚሹ ፣ እንክብካቤ በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ሁሉ ነው። የመጀመሪያው ቡድን በተጨማሪ በከፍተኛ እንክብካቤ ክፍሎች ውስጥ፣ በድንገተኛ የህሙማን ክፍሎች ውስጥ፣ በድንገተኛ አገልግሎት ወይም በክትባት ማዕከላት ውስጥ የሚሰሩትን ያጠቃልላል ።

■            ቡድን ሁለት – በጣም ከፍተኛ ትኩረት

ሁለተኛው ምድብ ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጠው ዕድሜያቸው 70 እና ከዚያ በላይ የሆኑ እና እንዲሁም ከባድ ወይም ከፍተኛ በሽታ ያለባቸው፣ በወረርሽኙ ቢያዙ ህይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል ተብሎ የሚታሰቡትን ያጠቃልላል። ይህ ቡድን የመርሳት በሽታ ያለባቸውን ሰዎች እንዲሁም ትራይሶሚ 21 እና የአካል ንቅለ ተከላ ያደርጉ በሽተኞችን ያጠቃልላል። ለነዚያ ሰዎች እንክብካቤ የሚያደርጉ ሰዎች እና እርጉዞችም መከተብ ይችላሉ፤  የህክምና ሰዎችንና በጥገኝነት ወይም ቤት አልባ መጠለያ ውስጥ ያሉ ወይም የሚሰሩ ሰዎችንም ይጨምራል።

■            ቡድን ሦስት – ከፍተኛ ትኩረት

ሦስተኛው ቡድን ከ 60 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ከ 30 Body-Mass-Index በላይ የሰውነት ክብደት ያላቸውን ፣ ሥር የሰደደ የኩላሊት ወይም የጉበት በሽታ ያለባቸውን፣ በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ እና በኤች አይ ቪ የተጠቁ፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም ወይም ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸውን ሰዎች ሁሉ  ያጠቃልላል። የካንሰር እና የአስም በሽታ ተጠቂዎች፣ እንዲሁም የሩማኒክ በሽታ እና የመሳሰሉት ያለባቸው ሰዎችም እዚህ ቡድን ተካትተዋል። በተጨማሪም በሦስተኛው ቡድን ውስጥ የተጠቃለሉት የሕገ መንግሥት አካላት፣ የመንግሥትና አስተዳደር ሠራተኞች ፣ የመከላከያ ኃይሎች ፣ ፖሊሶች ፣ እንዲሁም የጉምሩክ ፣ የእሳት አደጋ አገልግሎት ፣ የሲቪል ጥበቃ እና የፍትህ አካላት ሰራተኞች፣ ፋርማሲስቶች፣ እንዲሁም የምግብ ቸርቻሪዎችን እና መምህራንን ይጨምራል። እንደ በአስጊ የሥራ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችም አሉበት ።

የተቀረው ህዝብ በትዕግስት እንዲጠብቅ ይፈለጋል። እኛም መቼ እንድሚደርሰን የምናውቀው እነዚህ ከተከትቡ በኋላ ይሆናል።

  1. 2021

ቀደም ሲል በወረርሽኙ የተነሳ ገዢዎችን ለማበረታታት ከ19% ወደ 16% ወርዶ የነበረው ቫት በ2021 ተመልሶ ወደነበረበት 19% ሲያድግ፣ የመኪና ግብርም ጨምሯል። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ብክለትን ማካካሻ ግብርም ስራ ላይ ውሏል። በ2021 ለልጆች የሚሰጠው ድጎማ በ15 ዮሮ ሲጨምር፣ ከውህደቱ ጀምሮ ከ30 ዓምታት በላይ ለምስራቅ ጀርመን ግንባታ ተብሎ ከደሞዝ ላይ 5.5% የሚቆረጠው የሶሊዳሪቲ ግብር ይቀራል። በትልልቅ ኩባንያዎች ቦርድ ውስጥ ከሶስቱ አንዷ ሴት እንድትሆን የሚያስገደድ መመሪያም መተገበር የሚጀመርበት ወቅት ነው። በጀርመን የስነምህዳር እንክብካቤን በማስመልከት በወጡት ደንቦች መሰረት ከሐምሌ 2021 ጀምሮ  የአንድ ጊዜ የፕላስቲክ መጠቀሚያዎች ለምሳሌ ሳህን፣ ቢላዋ፣ ሹካ፣ ማንኪያ፣ ኩባያ፣ የፕላስቲክ ምግብ ማሸጊያዎች፣ ወዘተ ይቀራሉ። ይህንን ደንብ የተላለፈም ይቀጣል።


ማጠቃለል ባልፈው የገለጽኩትን በመድገም ኢትዮጵያ ውስጥ ስርጭቱ ቢቀንስም፣ የሚታዩ መዘናጋቶች የቫይረሱን ስርጭት በማፋጠን ሁለተኛው ዙር ተመልሶ እንዳይመጣ ወይም ተዘጋጅቶ ለመጠብቅ  እንዲያስችል ጀርመንና እና የቀሪውን አለም ሁኔታን በማየት ኢትዮጵያ  እንዳትዘንጋ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

መልካም የኢትዮጵያ ገና እንዲሁም ተስፋ በ2021!

„ተስፋ ማለት ጨለማ ቢኖርም ብርሃን እንዳለ ማየት መቻል ነው።“
–  ዲዝመንድ ቱቱ

ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share