ሲናገር ዉሎ ሳይሰማ ገባ – ማላጂ

በኢትዮጵያ ያለዉን ፣የነበረዉን እና ሊሆን የሚችለዉን አገራዊ እና ህዝባዊ ጉዳይ ዞትር ማሳነስ እና ማድበስበስ ብሎም በየጊዜዉ የስብስብ /ኮሚቴ እና ስብሰባ ዘላቂ ብሄራዊ አንድነትም ሆነ መግባባት የሚያስችል ዕርቅ ማምጣት እንደማያስችል በተግባር ላለፉት ሁለት አሰርተ ዓመታት የታየ ዕዉነት ነዉ ፡፡

ከዚህ ይልቅ ምድር ላይ ከነበረዉ እና ካለዉ ዕዉነት እና የዘመናት ታሪክ እኛም ሆነ መንግስት እንዴት መማር እንዳቃተን ለሚያስተዉል ከማለባበስ እና ከማደባበስ ዉጭ ዘላቂ ዕምርታ ለማምጣት አለመፈለግ እና ቁርጠኝነት የማጣት ችግር ይስተዋላል፡፡

ዜጎች ለዓመታት እንደ ዱር አዉሬ እየታደኑ በሚገደሉባት እና በሚሳደዱባት አገር  የነገሮችን ስረ መሰረት ከምንጩ ለማድረቅ እና ዕዉነተኛ ብሄራዊ ዕርቅ ለማንበር ከመጣር ይልቅ በየዘመኑ ተደጋጋሚ እና አክሳሚ ሰሞንተኛነት አገሪቷን እና ህዝቧን አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል  ፡፡

ለዚህ በአብነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት የአገራችን ጥቂት አካባቢዎች መካከል በቀድሞዉ ጎጃም ክፍለ ሀገር የመተከል አዉራጃ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የየኪ ወረዳን መጥቀስ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዉያን ህብረት እና አንድነት መጠናከር ለሚደረገዉ የህልዉና ትግል ወሳኝ እና በአብነት ሊወሰድ የሚገባ ነዉ ፡፡

መተከል ፡

በቀድሞዉ የኢትዮጵያ የግዛት አስተዳደር በጎጃም ክፍለ ሀገር መተከል አዉራጃ ስር የነበሩት ስድስት ወረዳዎች በቤንሻንጉል ክልል ከመጠቃለላቸዉ አስቀድሞ እና ከተጠቃለሉ በኋላ የሆነዉን የዜጎች የሞት ፣ የስደት ፣ መፈናቀል እና ዘርፈ ብዙ የዜጎች ምስቅልቅል ሰቆቃ መንስኤ እና ጅምር የሁለት ዓመት ዕድሜ ማድረግ በራሱ ለጉዳዩ የሚሰጠዉን ትኩረት እና ከረጅም ዓመታት አስቀድሞ የነበረዉን አካባቢዉን እና አገሪቷን በታሪክ እና በትዉፊት ለማደብዘዝ የተኬደበትን የሴራ ደቦ ማረሳሳት ይሆናል፡፡

በመተከል ፓዌ በነበረ የመንግስት እና አካባቢ ኗሪ ህዝብ ዉይይት በአሁነ ስዓት ስላለዉ አጠቃላይ ሁኔታ ግጭት ብሎ ጉዳዩን ዝቅ ማድረግ እና መንስዔዉም የዓባይ ኃይል እና መብራት የልማት ጅምር እና ሂደት ለማደናቀፍ ነዉ ማለት በአገራዊ አንድነት እና የህዝቦች ደህንነት ላይ የደረሰዉን እና ሊደርስ የሚችለዉን ጉዳት ለማስቆም ሊወሰድ የሚገባዉን አገራዊ እርምጃ የሚያዘገይ ብሎም ሌላ ዋጋ የሚያስከፍል እንዳይሆን ስጋት አለ ፡፡

ልማት የማደናቀፍ ተልዕኮ አነዱ ወንጀል ቢሆንም የጥፋት መልዕተኞች አገር እና ህዝብን ለዓመታት ሲያመሰቃቅሉ መኖራቸዉ አንሶ ዛሬም በቀጥታ ተጠያቂ አለመሆናቸዉ በህዝብ ለፍትህ ተስፋ ማጣት ለወንጀለኞች ማን አለብኝነትን አጎልብቷል፡፡

ከዓባይ (ከህዳሴ ) ግድብ መጀመር በፊት በነበሩ መሠረታዊ እና ጥልቅ አገራዊ ችግሮች መነሻቸዉ ዓባይ ነዉ ብሎ የሁለት ዓመት ችግር ማድረግ በራሱ የዚህችን አገር እና ህዝብ የዘመናት ሰቆቃ እና መከራ ለመቅረፍ ከሚፈይደዉ ይልቅ የሚያስከትለዉ መዘዝ እንዳይንዘዛዘም ማስተዋል ይገባል ፡፡

በመላ አግሪቷ ከህዝብ ተሳትፎ እና ዕዉነተኛ ማንነት እና ታሪክ ተቃራኒ በሆነ በጥቂት ፍርደ ገምድል እና ጭፍን አገራዊ ጥላቻ በነበራቸዉ ግለሰቦች እና ቡድኖች በማን አለብንነት በተደረገ ያልተማከለ /ፌደራል የአስተዳደር አወቃቀር ምክነያት በሠፊዉ ህዝብ እና በአገሪቷ ሊደርስ የቻለዉን የሁለት አሰርተ ዓመታት መከራ ለሚሰማዉ ለዚህ ሁሉ ምንጭ ምን እንደሆነ ለመረዳትም ሆነ የማያዳግም እርምጃ ለመዉሰድ አይቸገርም ፡፡

የማንኛዉም አገር ህዝብ እና ሉዓላዊነት አስተማማኝ በሆነ ቀጣይነት የሚረጋገጠዉ በንግር እና በመሰባሰብ ቢሆን ኖሮ እንደ ኢትዮጵያ ያለ በኮሚቴ ብዛት ፣ዓይነት እና ስብሰባ በጨረቃ የሚካሄድባት ብቸኛዋ ሳያደርጋት አይቀርም ፡፡

ነገር ግን የስልጣን ማስከበሪያ እና የህዝብን የመከራ ጊዜ ማራዘሚያ ከመሆን ዉጭ የፈየደዉ ቁም ነገር አለመኖሩ በግላጭ በድግግሞሽ ከመታየቱ በላይ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የሚታየዉ የዜጎች ላይ የሚደርሰ የዉስጥ ስደት ፣መፈናቀል እና ልዩ ልዩ በደል የዚህ አመላካች ነዉ ፡፡

ከዚህ አኳያ ከታሪክ እና ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ የመተከል አዉራጃ የዜጎች እንግልት እና ሞት መንስዔ የዓባይ የኃይል ስራ ነዉ ማለት በአገሪቷ ያለዉን ነባራዊ ችግር ለዘለቄታ ለመፍታት ማዘናጊያ እንዳይሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በቀድሞዉ አሀዳዊ የአገር አስተዳደር መንግስት በአካባቢ መራቆት እና በህዝብ ብዛት የተነሳ ይደርስ የነበረን ድህነት ለመከላከል እና የሠዉ ኃይል እና ተፈጥሯዊ ሀብትን በመጠቀም ምርታማነትን (በምግብ ራስን መቻል መርህ) ከወሎ፣ ከሸዋ እና ከሌሎችም የአገሪቷ ክፍላተ ሀገራት ወደ ቀድሞዉ ጎጃም ክፍለ ሀገር ያአሁኑ መተከል ማስፈሩም ለኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ የሚታወቅ ቢሆንም መልካም ብሄራዊ አንድነት እና የህዝቦች ትስስር ለማጠናከር እንደምሳሌ አለመወሰዱ ግን በአሁኑ ጊዜ ላለዉ የአካባቢዉ ችግር ከድጥ  ወደ ማጥ  አድርጎታል፡፡

ይባስ ብሎ የነባር ነዋሪዉን ህልዉና የሚፈታተን  ተደጋጋሚ ወንጀል ሲፈፀም ለዓመታት የህግ የበላይነት በሚል ስም ብቻ በየጊዜዉ በንግግር እና በመሀላ የአገር ሉዓላዊነትን እና የህዝቦች /ዜጎች በአገራቸዉ በህይወት የመኖር ተፈጥሯዊ  እና ሠባዊ መብት አለመከበር መንስዔዉ ጥፋተኛ ተጠያቂ አለመሆኑን ህዝብ እና መንግስት በአንድነት  ያለመተማመን እና ያለማረጋገጥ  ችግር መሆኑ ሊረሳ አይገባም ፡፡

በከፍተኛ የመንግስት አካላት አካባቢዉ መገኘት እና ህዝብ ማወያየት ፡

ብዙ ጊዜ በዕኛ አገር አንድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ወይም ሹም በአንድ አካባቢ መገኘት በዚሁ አካባባቢ  ለሚኖር ችግር እንደ መፍትሄ  አድርጎ የማየት ችግር በራሱ አንድ ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የአንድ ነገር መንስኤ እና ዉጤት የሚለካዉ በችግሩ መነሻ እና መድረሻ ልክ በዕዉነት እና በዕዉቀት ለመፍታት የሚያስችል  ስርዓት መዘርጋት እንጅ በግል እና በቡድን በሚደረግ ንግግር ወይም ጉብኝት አይደለም ፡፡

በአስረጅነት ፡ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በተለያዩ የማንነት እና የአካባቢ ወሰን ፣ የስልጣን መጋራት……ወዘተ በቀድሞዉ (ሟች) እና በበተኪዉ ያልተደረገ ድርድር፣ ሽምግልና……..የለም ዳሩ ጊዜ መግዣ እንጅ ለህዝብ እና አገር ዘላቂ ሠላም፣ ልማት እና በአንድነት ላይ የተመሰረተች ህብረ ብሄራዊ ኢትዮጵያ ለማስቀጠል አለመሆኑን  እንረዳለን፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የኪ ወረዳ ከ 1988 ዓ.ም አካባቢ አስካሁን ስላለዉ የአካባቢ መንስዔ እና ያስከተለዉ ዳፋ በግልፅ እየታወቀ በወቅተ በተለይም በ2007 ዓ.ም. በነበረዉ ከፍተኛ የአካባቢዉ ፀጥታ መናጋት ጠ/ሚ የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ  ለሳምንት ከሚመለከታቸዉ አካላት(የክልል፣ ኗሪ፣ ሽማግሌ…….) ጋር ተወያዩ ተባለ ምን ዉጤት ተገኘ ከተባለ አሁንም በተደጋጋሚ የሠላም ሚ/ር ሂደዉ ምንም ተጨባጭ እና ጠብ ያለ ይህ ነዉ የሚባል አለመኖሩን መመልከት ይቻላል፡፡

ይህ የሚያሳየዉ ችግሩን ለመፍታት የምንሄድበት መንገድ እና የችግሩን ምንጭ ትተን የተቸገረዉን እና የድረሱልኝ ጥሪ ድምጽ  ለመስማት እና ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት የቁርጠኝነት ማነስ ነዉ ፡፡

በቀድሞዋ የኢትዮጵያ የግዛት አስተዳደር የግል የድንበር ግጭት ካልሆነ በቀር በቋንቋ እና በኃይማኖት ጉልበተኛ ነባሩን ባይተዋር የማድረግ እና የማባረር ከዚህም ሲያልፍ የመግደል ፣ሠባዊ ክብሩን የማዋረድ ያየነዉ በእኛ ዘመን ነዉ ፡፡

እኮ እንዴት ነዉ ባለቤት ቤት አልባ  አገር እና ሠዉ ጠል የሆነዉ እና ለአገር አንድነት እና የህዝብ አብሮነት ጠንቅ በንግግር እና ድርድር ከክፉ ድርጊቱ ሊታቀብ የሚችለዉ ፡፡

የህግ የበላይነት ማረጋገጥም ዕዉን መሆን ያለበት በዜጎች መሰዋዕትነት ሳይሆን በወንጀለኞች እና በራሳቸዉ ቸገር እና ህዝብ ክህደት በሚፈፅሙት ላይ የማያዳግም ርምጃ በመዉሰድ ተጠያቂ ማድረግ እንጅ ከአገር እና ህዝብ በላይ ለሚሆኑት ጅብ ከሄደ ዉሻ ጮኸ ዓይነት አካሄድ መቸ እንደሚቆም ባይታወቅም ከምንም በላይ አገር እና ህዝብ   መሆኑን መተማመን እና ማረጋገጥ በይደር የማይታለፍ የህዝብ እና መንግስት የጋራ ጉዳይ መሆን አለበት ፡፡

የሁሉ ነገር መሰረት እና ምንነት የሚገለፀዉ ፣የሚኖረዉ እና ሁሉም የሚሆነዉ በአገር ነዉ አገርም ሠዉ ነዉ፤ ሠዉም አገር እና ዜጋ ነዉ ፡፡

የቀደሙት እና ዛሬ ጨካኝ እና ወንጀለኞች የምንላቸዉ ህዝብ የሚጨቁኑበትን ፣አገር የሚከፋፍሉበትን፣ ዳር ድንበር የሚያስደፍሩበትን……….. ህግ ለእነርሱ መከበሪያ ለብዙሃን ኢትዮጵያዉያን አንገት ማስደፊያ፣ ማስፈራሪያ እና ማሳደጃነት የሚገለገሉበት መሳሪያቸዉ የህግ የበላይነት የሚል ነበር ፡፡

ሁሉም ሠዉ በጋራ በሚስማማበት ህግ በዕኩል አስካልታየ ድረስ ህግ የወንጀለኞች መደበቂያ፣ መመኪያ እና በትር ሲሆን ለጨዋዉ የመከራ ቀንበር እንደመጫን ይሆናል ፡፡

በእኛ አገር ስላለዉ የህግ አፈጻፀም ምድር ላይ ካለዉ ሀቅ ጋር ትተን በአንድ ወቅት የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ እና አይነኬ ጣዖቶች ( ሳዳም ሁሴን-ኢራቅ፣ ሁስሜን ሙባረክ -ግብፅ፣ ሙዓመር ጋዳፊ-ሊቢያ፣ ቤን አሊ-ቱኒዚያ፣ ዚ ድባሪ-ሶማሊያ፣ አልበሽር-ጎረቤት ሱዳን ……..) የእነርሱን የግል መሳሪያ እና ማስፈራሪያ የነበረዉን ህግ የሚሉት ህገ መንግስት የስልጣን ዘመናቸዉን አራዘሙበት እንጅ ለአገር እና ህዝብ ጥቶት ያለፈዉ የማይሽር ቁስል ነበር ፡፡

ይህም በአገራቱ የየአገራቸዉን ሉዓላዊነት እና የህዝቦች ዘላቂ አንድነት እና ዕድገት ከመስራት ለአላፊ እና ጠፊ ጣዖትነት እነርሱ የማይሩትን እና የማይገዙለትን ህግ በህዝብ ጫንቃ ለመጨና ሲባዝኑ የጥፋት ዕሳት አቀጣጥለዉ አልፈዋል፡፡

ወደ እኛ አገር እና በተለይም መተከል ስንመለስ ለዓመታት መላ ያጣዉ ህዝብ እና የሠዉ ልጆች ስቃይ እንዲሁ በተደጋጋሚ ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ንግግር ዘላቂ አገራዊ እና ህዝባዊ መፍትሄ ይመጣል ማለት ቸር መኘት ከሆነ አይከፋም ነገር ግን ለዓመታት ከከፍተኛ  አስከ ዝቅተኛ አመራር ያልሆነ ፤ያልተባለ የለም ግን እንዴት ችግሩን እያቀለልን ችግሩን ከምንጩ ልናደርቅ እንችላለን፡፡

ወደ ሠላማዊ ህይወት የማይመለስ ሽፋታ በመጣበት ይመለሳል የሚል የመፍትሄ አማራጭ በመንግስት ተገልጧል እኮ ምን ተይዟል ድሮም አገር እያመሰ የሚመለስ እንጅ በመጣበት ላይመለስ የተደረገ ቁርጠኛ እርምጃ አለመኖሩ ነዉ እኮ ችግሩ እናም ስደት ፣ ሞት እና ድህነት በራስ አገር እና ዜጋ የሚታደልበት ሁኔታ ማንም ምንም ከአገር እና ህዝብ በታች መሆኑን በተግባር የሚማርበት እርምጃ ከመዉሰድ ዉጭ ሌላ ከንቱ ጊዜ ማጥፋት ይሆናል፡፡

በአገራችን የህዝብን እና የዜጎችን የዘመናት መከራ እና ዕሮሮ  የበዛበት ዋይታ ድምጽ የሚሰማ እና ኃላፊነት የሚሰማዉ ትዉልድ እየተፈጠረ ባለበት ዋዜማ ላይ መሆናችንን አብሪ ምልክቶች የሚታዩ ቢሆንም መንግስት እና ህዝብ ስለ ዕዉነት እና ዕዉነተኛ የጋራ አንድ አገር ላይ በሚደረግ ርብርብ መንግስት ለኅዝብ ጆሮዉን የሚያዉስበት ወሳኝ ጊዜ ላይ የምንገኝ መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ በተጓዳኝ በኅዝብ እና መንግስት መካከል ያለመናበብ/ያለመሰማማት ብሎም መንግስት እንደ ቀደሙት የሚናገር እና ህዝብን የሚሰማ እንዳይሆን ዕንቅፋት የሚሆኑትን ማጥራት እና መለየት አለበት ፡፡

“በሽታዉን የደበቀ መድኃኒት የለዉም” የሚለዉን ኢትዮጵያዊ ብሂል ወደ ጎን ከተዉንዉ  ይተዋል የዚህች አገር እና ህዝብ ችግርም እንዲቀጥል መስማማት ነዉ  ፡፡

ይህ የዘመናት የአገራችን  ያለመደማመጥ ክፋት ሲናገር ዉሎ ሳይሰማ ገባ የአስመሳይነት እና የአድር ባይነት ባህሪ የሚመነጨዉ በችግር ፈጣሪዎች ከሚመጣ ችግር እነርሱን የችግር መፍትሄ አማጭ የማድረግ አሰራር  ሌባን ሌባ እንዲሰርቅ መጠበቅ ነዉ ፡፡

ይኸ ምን ቸገረኝ የምትሉት ሀረግ እርሱ ነዉ አገሬን ያረዳት እንደ በግ

የተሰኘች ስንኝ ልጽፍ አሰብኩ እና ፣

ምን ቸገረኝ ብየ ቁጭ አልኩ እንደ ገና፡፡ (ነስ ረዲን ሙሳ)

                                                                                              ምንጊዜም እናት አገር !!!

                                                                                                    ማላጂ

 

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቃ!ማኅበራዊ እሴትህን ጠብቅ፤ “ፖለቲከኛን ያመነ ጉም የዘገነ!” - በገ/ክርስቶስ ዓባይ       

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.