ታሪክ አቅጣጫውን እንዳይስት

Yatwld(ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በህወሓት ላይ የተገኘውን ወታደራዊ ድል አስመልክቶ ከያ ትውልድ ተቋም ጋዜጣዊ መግለጫ)

ኢትዮጵያ ሀገራችንን ለአለፉት 28 ዓመታት ቀፍድዶ የያዘው ዘረኛ የወያኔ/ህወሓት ቡድን በመደምሰስ ሂደት ላይ በመሆኑ የተሰማንን ደስታ “ያ ትውልድ ተቋም” እንገልጻለን። ይህ የወንበዴ አገዛዝ ኢትዮጵያችንን በዘርና ቋንቋ ከፋፍሎ ሲያባላና ሲያናቁረን ኖሮ ሀገራችንን ሊበታትን የቀበረው ፈንጂ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በአማራ አገርወዳድ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ እየመከነ ነው።

“ያ ትውልድ” ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ይዞ የተነሳውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አጀንዳ ሰርስሮ በመግባትና አቅጣጫ በማሳት የኢትዮጵያ የአንድነት ኃይል እንዲኮላሽ የተወጠነው ሤራ ውጤት የሆነው ወያኔ/ህወሓት የመጨረሻው መጀመሪያ እየታየ ነው። የኤርትራን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ለማስባል በሻቢያ ተጠፍጥፎ የተሠራው ወያኔ/ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ይመራ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ኃይል በተቀነባበረ ተንኮልና ሤራ በማኮላሸት ኢትዮጵያ አንድነቷን አጥታ መጨረሻዋ መበታተን ይሆን ዘንድ ለአለፉት 28 ዓመት የመንግሥት ሥልጣን ይዞ ሀገር ያራቆተው፣ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜትን የቀበረው ወያኔ ወደ ከርሰ መቃብሩ እየተወረወረ ይገኛል።

“ያ ትውልድ ተቋም” የቀይ ሽብር ሰማዕታትን መታሰቢያው አድርጎ ከ8 ዓመት ተኩል በፊት ይፋ ባደረገው ድረ ገጹ (http://yatewlid.com/, http://yatewlid.org/) የደርግ ገዳዮችን ለታሪክ ማኅደርነት እንዳስቀመጠው ሁሉ “አገዛዞች” በሚለው አምዱ የህወሓትን ወንጀለኞችና ግፈኞች ተዳፍነው እንዳይቀሩ ከታሪክ ማኅደር ይከታቸዋል። በማያያዝም ህወሓት ከምሥረታው ጀምሮ በሥልጣን ዘመኑም ያፈናቸውን፣ የፈጃቸውን የኢሕአፓ አባላትና ውድ ሀገር ወዳዶችንም ቦታ ሰጥተናቸዋል። በተጨማሪም በዘር ማጥፋት ወንጀል የጅምላ ፍጅት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን በተለይ የአማራውን ሕዝብ ፍጅት በድረ ገጻችን በአጭር ጊዜ እንደምናካትት እናሳውቃለን።

የደርግ 17 ዓመት ፋሽስታዊ አገዛዝ ዳግም እንዳይደገም በድረ ገጻችን ለትውልድ መታሰቢያ ያስቀመጥነው የቀይ ሽብር ሰማዕታትና የሌሎች ወገኖች እልቂት አሁንም የፍትህ ያለህ ይላል። ዛሬ ሀገር ለወያኔና ሻቢያ አስረክቦ የፈረጠጠው ፋሽስታዊ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም ለፍርድ መቅረብ ሲገባው ይህንን በህወሓት/ኢሕአዴግ 28 ዓመት አገዛዝ ላይ እየተገኘ ያለውን ድል ምክንያት በማድረግ እንደ ጀግና ለመሳል የሚደረገው ሩጫ በሚልዮን የሚቆጠር ተከላካይ ቤተሰብ እንዳለው ልናስገነዝብ እንወዳለን። ወንጀላቸውና ያፈሰሱት ደም የሚያባንናቸው የደርግ ኢሠፓ ርዝራዦችና አጫፋሪዎቻቸው ዛሬም በየፖለቲካ ድርጅቶቹ ውስጥ ተሰግስገው በሀገር አንድነት ስም የደም ወንጀላቸውን ለማደስ የሚያደርጉትን ሩጫ “ያ ትውልድ ተቋም” አጥብቀን እናወግዛለን።

“ያ ትውልድ ተቋም” የደርግ ኢሠፓ እና አጃቢ ድርጅቶቻቸው የወንጀል ታሪክ በአግባቡ ይነገር፣ ይጻፍ፣ ይተረክ ዘንድ የምናደርገው ጥረት ከህወሓት/ሻቢያ ተግባራት ጋራ ተዛማጅነትና ተያያዥነት አለውና አሁንም ታሪኩ አቅጣጫውን እንዳይስት እንሞግታለን። በ1983 ዓ.ም. በወያኔ ታፍነው ለተወሰዱት የእነ ጸጋዬ ደብተራው ጉዳይ፣ የእነ አሰፋ ማሩ መሰል ኢትዮጵያውያን የግፍ አገዳደል እና በግፍ እሥር ማቀው የተሰዉት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ነፍስ ፍትህን ይጠይቃልና ዛሬም በዚህ አጋጣሚ የፍትህ ያለ እንላለን።

የያ ትውልድ ታሪክ ህያው ነው!!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቧን ይጠብቅልን!!!

ያ ትውልድ ተቋም

ኅዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም. (November 29, 2020)

Email : [email protected]

website : http://www.yatewlid.com, http://www.yatewlid.org

Facebook:- Yatewlid

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.