እንኳን ደስ አለን።በፈጣሪያችን ፈቃድ ፣ በመጨረሻ መቀሌ የመሸገውን ፀረ ኢትዮጵያ የሆነውን ፋሺስታዊ ቡድን ፣ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጀች ፣በታላቅ ተጋድሎ አሸንፈው ድሉን ህዳር 19/2013 ዓ/ም አብሥረውናል።
ይህ ድል ለዘላለም የሚታወስ ነው። የድሉን ቀን፣ በየዓመቱ ልንዘክረው ይገባናል።በዚህ ቀን በውድ ልጆቻችን መሥዋትነት ፣በኢትዮጵያ ጠላቶች ላይ አንፀባራቂ ድል ተጎናፅፈናልና !!
ይህን በከባድ መሥዋዕትነት የተጎናፀፍነውን አንፀባራቂ ድል ፣ በተመሳሳይ አንፀባራቂ የሠላም፣የልማት ና የብልፅግና ድሎች በመላው ኢትዮጵያ ማሥቀጠል አለብን ብዬም አምናለሁ።ይህንን በማድረግም “ ዳውን ! ዳውን ! ኢትዮጵያ “ ባዮችን በማሳፈር “ ምነው መሬት ተከፍታ በዋጠችን ? “ እንዲሉ ማድረግ ቀጣዩ ሥራችን ቢሆን ደስ ይለኛል።…
እነዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ውጪ አገር እየኖሩ፣” ኢትዮጵያ ትውደም ! ” የሚሉት ፣ የገዛ ወገናቸው የሆነውን የአገር መከላከያ ሠራዊትን ግብዣ ብለው ጠርተው የኢትዮጵያን ኩራት ያዋረዱትን ፣ጥቂት ነፍሰ ገዳዮች እና ፋሽሥቶችን በመደገፍ መሆኑ ይታወቃልና በዚህ ቅሌታቸው መሬት ተከፍታ እንድትውጣቸው ቢመኙ አይገርምም።ይሁን እንጂ ከእነዚህ ውሥጥ ሀፍረተ ቢሶች እንዳሉም እገነዘባለሁ።
ዛሬ ከድሉ በኋላ ፣የንዴታቸውን ልክ፣የበሥጭታቸውን መጠን ሳስበው ደግሞ ምን ያህል አእምሯቸው እንደታመመ እረዳለሁ።…ያም ሆነ ይህ አብቅቷል።
ለመሆኑ፣እነዚህ ራሳቸውን በአግባቡ መምራት የማይችሉ ምግባረ ቢሶች ፣ እሥከ ዛሬ በቀቢፀ ተሥፋ የተፍጨረጨሩት ፣ገንዘብ ና ሥልጣን አሥክሯቸው ናላቸው ማሰብ አቁሞ አይደለምን? ነገሮች ሁሉ ባለአሥፈላጊ መስዋትነት ከሚጠናቀቁ በሠላማዊ መንገድ እንዲቋጩ ለዓመት አልተለመኑምን?
እነዚህ በውጪ አገር እየኖሩ “ ዳዎን !ዳዎን !” ባዮች የእናት ጡት ነካሾችሥ፣ጁንታዎቹ በውጪ ጠላቶቻችን አይዞችሁ የተባሉ መሆናቸውን እያወቁ፣ለእነዚህ ሆዳም እብዶች ወግነው ዳዎን ! ዳዎን ! ” ሲሉ እነሱም በፍርፋሪ እንደተገዙ አያሳብቅባቸውምን ?
የእነዚህ አይነቶቹ ከንቱ ሰዎች አሳፋሪ ሠላማዊ ሰልፍ ወደፊትም በውጪ አገራት እንደሚከሰት አትጠራጠሩ።ምክንያቱም ይህ የፍርፋሪ ፣የሆድ ጉዳይ ነውና! … በተጨባጭ ተግባር አገራችንን እሥካላበለፀግን ግዜ ድረሥም አደንቋሪ ፕሮፖጋንዳቸው እንደማያባራ መገንዘብ ይኖርብናል።
መገንዘብ ያለብን ሌላው እውነት ደግሞ ፣ ትህነግ ነገም ከታራካዊ ሥግብግብ ጠላቶቻችን ጋር በመመሣጠር ፣ የሽፍትነት ተግባር ከመፈፀም ወደኋላ እንደማይል ነው።
ይህንንም እውነት ሥዩም መሥፍን ከጦርነቱ አሥቀድሞ ተናግሮ ነበር። የኢትዮጵያ ጠላቶች ጦርነቱን ከከሃዲ ና አልጠግብ ባይ ከሆኑ ከሥልጣን ጥመኞች ጋር ተመሳጥረው እንደጀመሩትም የሥዩም መሥፍን ቃለ መጠይቅ ይመሰክራል ። እናም ነገ ተነገወዲያ ጥቂት ህሊና ቢሶች በገንዘብ ተገዝተው የሽምቅ ውጊያ ለማድረግ በጎረቤት አገራት እንዲመሽጉ እነዚህ ጠላቶቻችን እንደሚያደርጉ መታወቅ አለበት።የማይካድራ ጭፍጨፋም ቀጣይ ቁርሾ በህዝቧች መካከል ለመተው የተደረገ መሆኑንን አሥተውሉ።
በማይካድራ ዜጎቻችንን በሂትለራዊ እና ሞሶሎናዊ የጭካኔ መንገድ በዘግናኝ ጭካኔ በሥለት ያረዱ ከየጎረቤት አገሩ ተለቃቅመው ለፍርድ መቅረብ እሥካልቻሉ ድረሥ ነገ ሌላ ማይካድራ ይፈጥሩልናል ። እናም የጎረቤት አገሮች ዛሬና አሁን ፣እነዚህን ፋሺሥቶች ለቃቅማችሁ አሥረክቡን ሊባሉ ይገባል ።
ፋሺሥቶቹን እጃቸውን ይዘህ አሥረክበኝ እ እየተባለ እነዚህን ፣ አረመኔዎች ሸሽጎ የሚያሥቀምጥ የጎረቤት አገር መንግሥት ይኖራል ብዬ አላስብም ።ድንገት ከተፈጠረ ግን ያ መንግሥት ለሚመራው አገር ህዝብ ደንታ ቢስ እንደሆነ መሥክሯልና በወንበሩ እንደማይሰነብት ከወዲሁ ቢገነዘብ መልካም ነው።…
እርግጥ ነው ፣ታሪካዊ ጠላቶቻችን ለእነዚህ ፋሺሥቶች፣ከለላ ና መጠጊያ ሊሰጧቸው ይችላሉ። ኢትዮጵያና ጎረቤት አገሮቿ ዘላቂ ሰላም እንዳይኖራቸው የተለያየ ሤራ የሚያሴሩና እዛና እዚህ ግጭት፣ ውንብድና፣ዘረፋ፣እንዲሁም መሰል የሽፍትነት ተግባራት በየጊዜው እንዲፈፀም የሚያደርጉ የማይተኙልን ሥግብግብ ጠላቶች እንዳሉን እናውቃለን። እነዚህ ጠላቶቻችን ከዘመኑ ጋር ያልተለወጡ ፣ በትብብር እና በመተጋገዝ የሚመሩትን ህዝብ በአጭር ጊዜ ኑሮውን ማሻሻል እንደሚቻል ያልተገነዘቡ፣ለህዝብ ሰላምና ብልፅግና ሳይሆን ለራሳቸው ምቾትና ድሎት የሚጨነቁ ናቸው።
ትላንት በኢትዮጵያ ያልነበረውን ፣የቋንቋ ፖለቲካ የፈጠሩብን እነዚሁ ታሪካዊ ስግብግብ ጠላቶቻችን ናቸው።እንደምታውቁት እሥከ 1983 የቋንቋ ፖለቲካ በኢትዮጵያ አልነበረም።ኢትዮጵያም በአፍሪካ ውሥጥ የሚሥተዋለውን የጎሳ ግጭት የምታወግዝ እና በጎሣ አሥተሳሰብ የተበረዘ ዜጋ የሌለባት አገር ነበረች።ዛሬ ግን በእያንዳንዶ ቀበሌ ና በእያንዳንዱ የመንግሥትም ሆነ የግል የሥራ ተቋም፣በፋብሪካዎች ጭምር ሰው መሆናቸውን ዘንግተው እኔ ቋንቋ ነኝ የሚሉ ዜጎች እንደአሸን ፈልተዋል።
እነዚህ እንደ አሸን የፈሉ ማመዛዘን የማይችሉ ዜጎችን የፈጠረቻቸው ወያኔ ናት። በዓለም ላይ በየትም አገር ሂዱ በመንግሥት ደረጃ በጎሳ የተከፋፋለ የሀገር መሬት የለም።ሲጀመር መሬቱ የተፈጥሮ ወይም የፈጣሪ ንብረት ነው።ማንም ሰው ፈጥሮ መሬትን አልሰራትምና ይህ የእኔ መሬት ነው ለማለት ከቶም አይችልም። በለሊት ቀና ብለህ ስታያቸው እንደሚያበሩት ኮኮቦች ሁሉ መሬትም በተፈጥሮ ወይም ከአእምሮአችን በላይ በሆነው እግዚአብሔር የተፈጠረች ናት።በዚህች መሬት ላይ በምትገኝ ንዑሥ ወርቅ ምድር ላይ ኢትዮጵያዊያን ተብለን እንድንኖር ያደረጉን ደግሞ የትላንትናዎቹ ጀግኖች አባቶቻችን በመስዋእትነት እንደሆነ አንዘንጋ።
የምንኖርበት መሬት የኢትዮጵያ መሬት የመሰዋትነት መሬት ነው።የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጎሳዎች መሰዋትነት ያኖረልን ወይም ያቆየልን ዳር ና ድንብር ነው። የአማራ፣የኦሮሞ፣የትግሬ፣የሲዳማ፣የቤንሻንጉል ፣የጋምቤላ ፣የአፋር፣የሐረሪ ፣የሱማሌ፣የደቡብ የአዲስ አበባ፣የድሬድዋ ወዘተ ብሎ መሬትም ሆነ ዳር ድበር በተናጥል የለም።ሁሉም የአሥተዳደር ሥያሜዎች ናቸው።
አለ ብለን ካመንን ፣ ለ85 የኢትዮጵያ ጎሳዎች ሸንሽነን መሬት በመሥጠት የራሳቸውን መንግሥት እንዲመሠርቱ ማድረግ አለብን።ይህ ደግሞ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ብርቱ ፍላጎት በቀላሉ ለማሳካት በተግባር መሥራት ነው።
ይህንን ሥል እያንዳንዱ ጎሣ ዴሞክራሲያዊ መብቱ አይከበር እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። 85 ቋንቋዎች እንደ ቋንቋ የሚገባቸውን ክብር ሊያገኙና ተናጋሪዎቻቸውም ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያሥተማሩ ሊያሳድጓቸው ይገባል።ምክንያቱም ቋንቋ መግባብያ በመሆኑ እና አንድ ትልቅ ባህልም ሥለሆነ ተጠብቆ መቆየት ሥላለበት ቋንቋዎቻችንን ሁሉ በእኩል ደረጃ ማክበር አለብን።
በነገራችን ላይ አንዱ ቋንቋ ከሌላው አይበልጥም፣አያንሥም።አንተ አማርኛ ሥለተናገርክ ትልቅ እርሱ ሀመርኛ ሥለ ተናገር ትንሽ አይሆንም።ይሁን እንጂ ትህነግ (ነፃ የሆነውን የትግራይ ክልል ነዋሪ እንደ ቅኝ ተገዢ የሚቆጥረው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር) ለብዝበዛ እንዲያመቸው ጥቂቱን የኢትዮጵያ ቋንቋ በማግዘፍ ሌሎቹን በማኳሰስ ፣በቋንቋ ተቧድነን እንድንጫወት አድርጎናል።
እናም በዚህ አሥቀያሚ ጫወታ የሚሰማው ትርክት አሥቂኝና አሳዛኝ ነው።ትርክቱም ፣ “ተግራይ እያታለለ ነው ! እያታለለነው ! ወደጎሉ እየቀረበ ነው…ኦ!ሊያገባ ሲል ኦሮሞ ቀማው።ኦሮሞ አሰያታለለ ነው ! እያታለለ ነው ! እያታለለ ነው!!…ኦ! …” የሚል ነው።በአጭሩ።
ከድሉ በኋላ ምን ይፈጠር ይሆን? ይህ ጫወታ ያከትም ይሆንን?? እውን፣ ባለፈው ሣምንት ” ኦሮማይ ! ” በሚል ርእስ በፃፍኩት ፅሑፊ የጠቆምኳቸው ሃሳቦች ተግባራዊ ይሆናሉ።ወይስ የትህነግ ሥግብግቦች፣ዘራፊዎች፣ሌቦች፣አረመኔዎች ብቻ ተለቃቅመው ዘብጥያ ሲወርዱ ሌሎች በፖርቲ ና በነፃ አውጪ ሥም ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀሙ ” ሰዎች ” በዝምታ ይታለፋሉ ???
በዝምታ ከታለፉ ያው ” የቴድ በ17 መርፌ …” የተባለውን ቅኔ መልሰን መዝረፋችን አይቀርም።ማን ከማን ያንሳል?ሰው ወርቅ ና አልማዝ ሲዘርፍ እኛ ቅኔ እንዝረፍ እንጂ።
ማጠቃለያ
ይህ ድል፣የጎሣን ፖለቲካ ካልቀበረ ከጎረቤት አገራት ጋር እንኳን ሰላምን በአሥተማማኝ መልኩ ልንፈጥር አንችልም።የጎሳና የቋንቋ ፖለቲካን በዚህ ድል ማግሥት በመቅበር የተረጋጋች ኢትዮጵያን፣ሁሉም ዜጋ በዜግነቱ መምረጥ ፣መመረጥ የየቀበሌው፣የየከተማው፣የየወረዳው፣የየዞኑ፣እና የየክልሉ ምክር ቤት አባል መሆን ይኖርበታል።በሁሉም ክልሎች የተየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ በዜግነቱ፣በኗሪነቱ ሙሉ መብቱ ሊከበርለት ይገባል።ሃሳቡን በአሥተርጓሚ ሊያቀርብ ይችላል።እናም ትህነግ ከቸከላችው “የጅብ ፖለቲካ “ በዚህ ዓይነት “ሥልጡን የፖለቲካ “ መንገድ ልንወጣ ይገባናል ብዬ አሥባለሁ።
የብልፅግና ፓርቲ ራእይ ይህ ይመሥለኛል።ዜጎች እንደዜጋ ና ሰው እርስ በእርሱ እንደሰው እንዲተያይ ማድረግ የብልፅግና ተቀዳሚ ዓለማ መሆኑ በዚህ ወቅት ግልፅ መሆን ይኖርበታል።
የተማራው ዜጋ ኢትዮጵያ አገሩ መሆኖንን የሚገነዘበው በሁሉም ክልል ያለ አንዳች ቋንቋ መሥፈርት በሙያው ለማገልገል በግልም ሆነ በቅጥር ሠርቶ እንዲኖር ሲመቻችለት ብቻ ነው።
የአንዱ ክልል ነዋሪ በሌሎች ክልሎች ሁሉ፣ሌሎችም በዚህ ክልል ያለአንዳች መድሎ ና ዘረኝነት ተቀጥረውም ሆነ በግላቸው እንደዜጋ እንዲሰሩ ሲፈቅድላቸው ነው።
የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሁሉም ክልል በሙያቸው ተቀጥረው ሊሰሩ ይገባል።ትህነግ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋራ ተመሣጥራ የተከለችው የቋንቋ አጥር የሚፈርሰው ይህንን በየእያንዳንዱ የአፍሪካመ፣የአውሮፖ፣የአሜሪካ፣የኢሲያ፣የላቲን አሜሪካ አገራት የሚተገበረውን የሥራ ቅጥር ህግ በእኛ ተግባራዋ ሥናደርግ ና አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ሲኖረን ብቻ ነው። ይህንን እሥካላደረግን ጊዜ ድረሥ የኢትዮጵያን ጠላቶች ሴራ እሥከወዲያኛው ማክሸፍ አንችልም።
የውጪ ኃይሎች በህቡ የሚሸርቧቸውን ሴራ ለማክሸፍ በጠ/ሚ አብይ አህመድ ( ዶ/ር ) የሚመራው መንግሥት ዝግጁነት ብቻ ሳይሆን ቁርጠኛ አቋም እንዳለው በበኩሌ አምናለሁ።
ጠ/ሚ አብይ አህመድ ዶ/ር ኢትዮጵያን ለማበልፀግ በእጅጉ እንደሚሹ ና ይህንን መሻታቸውንም በተግባር ለማሳየት ከልብ እየሰሩ እንደሆነ ግልፅ ነው። የትበብብር ፣የመተሳሰብ ፣የህብረት ፣የአንድነት ፣የፍቅር ፣በአጠቃላይ የቅንነት ጋሬጣዎችን ከመንገዳችን ለማሶገድና የመከላከያ ሠራዊታችንን ሞራል የበለጠ ከፍ ለማድረግ አያሌ ተጨባጭ ተግባራዊ ሥራዎችን እንደሰሩና ወደፊትም እንደሚሰሩ አምናለሁ።
ትህነግ በ21ኛው ክ/ዘ ቆርጦ ቀጥሎች፣ ውሸታሞች፣ሂትለሮችና ሞሶሎኒዎች እየተመራ ግብአተ መሬቱን እንዳፋጠነ ይታወቃል። ይህ እውነት ደግሞ ከተራው ሰው የበለጠ ለእርሳቸው ትልቅ ትምህርት እንደሚሆናቸው አምናለሁ።
ከዚህ ያልተጠበቀ ክሥተት በመማር ጠ/ሚ አብይ አህመድ (ዶ/ር) እያንዳንዱን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ ና ፖለቲካዊ ጉዳይ አጥብቀው በእርጋታና በማሥተዋል ከአዓለም ተጨባጭ መሠል ሁኔታዎች ጋር እንደሚመለከቱም አምናለሁ።በእርግጠኝነት አጥብቀው ነገሮችን ሁሉ በጥበብ ካሰሩ ዘቅዝቀው እንኳ ቢሸከሙ በሀገር ላይ የሚፈጠር ክፉ ነገር አይኖርም።