ውሸታም ሲጋብዝ (ዘ-ጌርሣም)

ውሸት በኪሶቹ ጢም አድርጎ ሞልቶ
የሚሄድበትን ከወዲሁ አስልቶ
ይሄዳል መጠጥ ቤት ደመቅ ካለው ሰፈር
አድማጭ ከሞላበት ስለሱ እሚናገር

ገና ከመድረሱ ሲጀምር መዋሸት
ልክ ነህ ! አውቃለሁ መባል ነው ያለበት
አውሮፕላን ሲያሾልክ በመርፌ ቀዳዳ
መርከቧን በአየር ላይ በምድር ሲነዳ
መባልን ይወዳል እኔም አይቻለሁ
ከአንተ እሚወዳደር ማነንም አላየሁ

እሱም በመቀጠል እንደዚህ ይልሃል
ተጋበዝ ወዳጀ የቻልከውን ያህል
ምሽቷ ያንተው ነች ተዝናና ከልብህ
አኔ ልኑር እንጅ ይሸፈናል ወጭህ

ምንም ዉሸት ያውራ ካላደናቀፍከው
እንዴት ሊሆን ቻለ ብለህ ካልጠየከው
አድማጭ ከሆንክለት የምትል ልክ ነህ
ሆድህ ይቻል እንጅ የኪሱ እንግዳ ነህ

በአየር ላይ ሲደንስ ዕውነት ነው በማለት
ሲመጣ መቀበል ሲሄድ በመሸኘት
ማውደስ አለብህ ሌሎች እንዲያደንቁት

ነገር ካበላሸ ወለም ብሎት አፍህ
ተጠያቂ አንተው ነህ ለምሽቱ ወጭህ
ሂሣብ እስኪዘጋ መጠንቀቅ አለብህ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የስነግጥም ቅርጽና ይዘት - Bedilu Wakjira Official Channel

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share