በጠራው ሰማይ ላይ
ፍንትክ ወለል ብሎ ሁሉንም በሚያሳይ
እረጭ ባለ ሌሊት
ድምፅ በሌለበት
የአዕዋፍ ዝማሬ በማይሰማበት
መቀስቀሱ አይቀርም
ድንገት ማስደንገጡ
ኮሽ ያለ ጩኸት ያለየ በቅጡ
አንተ ማነህ ሲሉት እኔ ነኝ ካላለ
ረብሻው ያውካል ልብ እያማለለ
ወይ ጠርቶ ወይ በርቶ መንገዱ ካልታየ
ኮሽታ አደጋ አለው ከኖረ ከቆየ
መፍትሔው አንድ ነው ኮሽታን ለማምከን
መቅደም ያስፈልጋል ማድረግ እፍን ድብን
ፍርሃት አያድንም ጆሮን በጥጥ መድፈን
ሲቆይ ያስከትላል የባሰ ፀፀትን
ችግር በችግር ላይ ከተጨማመረ
መፍትሄ ሳያገኝ ከዋለ ካደረ
መፈንዳቱ አይቀርም ጊዜውን ጠብቆ
የትም አይደርስ ተብሎ ከቆየ ተንቆ
ለሁሉም ጊዜ አለው ሰለሞን አንዳለው
ጊዜን የሚያሸንፍ ያልተቀደመ ነው
ኮሽታ ሲሰማ በፍጥነት ካልነቁ
መሸነፍ ቀላል ነው አደጋን ከናቁ
ነቅቶ ለሚጠብቅ ድምፅ ከቃል ይፈጥናል
ለሚደርስ አደጋ ምልክት ይሰጣል
ስለዚህ ኮሽታን መናቅ አይገባም
ነቅቶ ከጠብቁት ጥቃት አያመጣም