በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለው ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየት – ክፍል 7

ለተከበራቹህ ወገኖች                                                                           

የኮሮና ልምድ ከጀርመን  10.09.2020

ይዘት- [ኢኮኖሚዊ እይታ | ትልቁ ሎክዳውን |  መሰረታዊ ፍጆታ |   ምግብ ቤቶች |  ቴያትር እና ፊልም |  ቸልተኝነት |  ሰላማዊ ሰልፎች |  ማጠቃልያ ነጥቦች ]

ከአለፈው በመቀጠል ለኢትዮጵያ ቴክኒካዊ ይዘቱ እና ለአጠቃላይ ግንዛቤ በአጣቃሽነት እንዲረዳ በማሰብ ከተጓዳኝ ነጥቦች ጋር የዓመቱ መደምደሚያ የሆነውን ክፍል ሰባትን አቀርባልሁ።

በጀርመን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተረጋጋ ቁጥር ላይ ሲገኝ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ቀን ከቀን በብዜታዊ እድገት በመጓዝ በአለም የደርጃ መስፈርት ከመቶ ባሻገር የነበርው ዛሬ ሌሎች አገሮችን በአስገራሚ ፍጥነት በመቅደም ከጥቂት ቀናት ወዲህ ከ50 በታች (Top 50) ገብቷል። ለዚህም ቀዳሚውን የሚይዘው በተለያዩ የኑሮ ዘይቤዎች አብሮ የሚጓዝው ቸልተኝነት  በሚያስደነግጥ መልኩ ሁኔታውን በመቆጣጠሩ ነው።  ጀርመን አገር አሁንም ቢሆን የዜናውን አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍነው ኮሮና ቢሆንም፣ እስከሚታወቀው ኢትዮጵያ ግን ከተደርገው ምርመራ አኳያ የተያዦቹ ቁጥር በቀን ከአንድ ሺህ በላይ በገባበት ዕለት ከሚዴያም ሆነ የማህበራዊ ትስስር ገፆች „ሰበር ዜና“ ተብሎ እንኳን አልተመዘገበም።

ጀርመን ባልፉት ሳምንታት በበሽታው የተያዙትን ቁጥር በመጠኑም ቢሆን ያስጨመሩት ከእረፍት ተመላሾች ሲሆን በየቀኑ የሚሞተውም ከኢትዮጵያ ሲነፃፀ በእጅጉ የቀነስ ነው (ለምሳሌ ሟች በ10.09.20 ጀርመን 2 – ኢትዮጵያ 8)።

ጀርመን እዚህ ላይ የደረሰው በአለፉት 6 ተከታታይ ፅሁፎች እንደገለጽኩት በከፍትኛ ትዕግስት፣ ዲስፕሊን እና ማዕቀቦችን በማለፍ፣  በቅርብ ታሪካችው አይተውት የማያውቁትን የኢኮኖም እና የነፃነት ግድበት ተቀብለው፣ አልፈው ነው። ይህም የሳይንስ ፊክሽን ፊልም የሚመስል ጊዜ ነበር።

 1. ኢኮኖሚዊ እይታ – ትልቁ ሎክዳውን

ትልቁ ሎክዳውን (The Great Lockdown) በመባል መታወቅ የጀመረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቋቋም በወጣው እርምጃ የተነሳ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ በዚህ አመት የአለምን ኢኮኖሚ በ3-6% እንደሚቀንስ ሲተነበይ ይህም በ1930ውቹ እጅግ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ካደረስው ታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት (The Great Depression) ቀጥሎ የሚታይ ነው። የዓለም ባንክ ትንበያ እንደሚያሳየው የኢኮኖሚ ጉዳቱ ቁጥጥሩ በላላ መልኩ ከተካሄደ እስከ 2022 እንደሚያገግም፣ ቁጥጥሩ በጠበቀ መልኩ ከሆነ ደግሞ እስከ 2024 ሊያገግም እንደሚችል ነው። በተጨማሪም ኢንቨስትመንትን እና ግብይትን የሚያዳክመውም ከፍራቻ በመነሳት ገንዘብን አንቆ በመያዝ ሲሆን የማይንቀሳቀስ እና አላስፈላጊ የሆነ የሃብት ማከማቸት ኢንቨስትመንቱን ጎድቶታል።  ትልልቅ ኩባንያዎችም ከ 15% እስከ 30% ኢንቨስት የማድረግ መጠናቸው በመቀነስ ብዙ አምራች እና ሸማች ሃይል ያላቸውን ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ እንዲዘጋጁ እያደርጋቸው ነው።

 1. ኢኮኖሚዊ እይታ – መሰርታዊ ፍጆታ

ጀርመን ያለው ሰው ከስራ ቢወጣ፣ ገቢ ቢያንሰው የሴፍቲ መረቡ መሰርታዊ መጠለያ፣ የምግብ ፍላጎቶችን ማሟላት ይስችለዋል። ባለው ማህበራዊ የጤና ኢንሹራንስ ስረዓትም የተንሳ ለህክምና አይከፈልም። የማይነፃፀሩትን ሀገሮች ለማነፃፀር ባይሆንም በኢትዮጵያ ያሉ ጥናቶች እንደሚይሳዩት ገቢያቸው በወርሃዊ ደሞዝ በመቋረጥ፣ በቀጥታ ገቢ በመቋረጥ ወይም ሪመተንስ የማያገኙትን በከፈተኛ ሁኔታ እንደመታቸው ነው። በዚህ የተነሳም መሰረታዊ የሆነን የምግብ ፈጆታን አለማግኘት እና የመገብየት አቅም መቋረጥን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ንረት፣ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ፣ ወዘተ እንዳባባሱት ይሰማል። ጀርመን የመፀዳጃ ወረቀት ለመግዛት ሰው ሰራሽ እጥረት ተፈጥሮበት በነበረት ጊዜ ሱፐር ማርኬቶች በሸቀጦች ላይ በሳንቲም ደርጃ እንኳን የዋጋ ጭማሪ አላደርጉም ነበር። በቅርቡም የቫት 3% ቅናሽ የተደረገ ሲሆን ይህም ዝም ብሎ የሚቀንስ ሳይሆን መንግስት ለዚህ ክስረት የሚሆን ድጎማ 130 ቢሊዮን ዩሮ አስቀምጦ ነው። ይህን ልምድ ወስዶ ኢትዮጵያ ላይ አድርጉ ለማለት መንግስት በዚህ ቅነሳ የሚያጣውን ገቢ የሚያካክስበትን አስቀድሞ የማዘጋጀት አቅም እንዳለው ማስላትም ተገቢ ነው።

 1. ኢኮኖሚዊ እይታ – የጨምሩ ፍጆታዎች
ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: በእርግዝና ወቅት የሚፈጠር የሰውነት መለጠጥ ከወሊድ በኋላ ቋሚ ሆኖ እንዳይቀር 3 ዘዴዎች

ጀርመን ውስጥ በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንድሚያሳዩት የመኖርያ ቤቶች ዋጋዎች እየጨምሩ የመጡ ሲሆን (ጀርመን ቤት ሲገዛ መሬቱንም ጭምር ነው፣ እንደ ኢትዮጵያ ለረዥም አመት ሊዚንግ ተብሎ በዲፋክቶ ደርጃ የሚውሰድ አይደለም)። በኮሮና ወረርሽኝ ጊዜ አብዛኛው ሰው እቤት በመቀመጡ ወደ ውስጥ ትኩረት በመሰጠት የቤት ውስጥ እቃዎችን፣ መገልገያዎችን፣ የቤት ማሳዋብያዎችን በመገበየት የእነዚህ ዕቃዎች ፍጆታ በ30% ጨምሯል። የኤሊክትሮኒክስ እቃዎች ግብይትም በ5.5% ጨምሯል። የዲጂታል ግብይት፣ የመብራት ሃይል እና ቴሌኮሙኒኬሽን የወረርሽኙ ተጠቃሚዎች መሆናቸው እንደቀጠለ ሲሆን፣ የከባቢ አየር ጥበቃም ልዩ ትኩረት አግኝቷል።

እንዳንድ ጥቆማዎች እንደሚያሳዩት የጀርመን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ቢወድቅም እንደተጠበቀው ሳይሆን ቶሎ ሊያገግም ይችላል የሚሉ ስሌቶች ይታያሉ። ይህም የጀርመን መንግስት በወሰዳቸው አፋጣኝ እና ውጤታም እርምጃዎች የተንሳ እንደሆን ይታመናል። ቀውስን የመቋቋም ይዘት ያለው የጀርመን ኢኮኖሚ ስረዓትም አንዱን ሚና ይጫወታል (ኤክስፖርት ተኮር፣ ቤተስባዊ ይዘት ያለው፣ ከብድር ይልቅ የማጠራቀም ባህል፣ ጥራት ተኮር የሆኑ የኢንቨስትመንት መሳርያዎች ምርት፣ የመደጋገፍ ባህል)።

 1. ቸልተኝነት

ኮንፊሲየስ የተባለ ፈላስፋ ከሺ ዓመታት በፊት „መልካሙን ዘር የሚያጠፉው የገበሬው ቸልተኝነት እንጂ እንክርዳዱ አይደለም፡፡“ እንዳለው ለኮሮና መስፋፋት ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው የሰው ቸልተኝነት ነው። በጀርመን የወንጀል ህግ በማውቅም ሆን ባለማወቅ ቸልተኝነት የሚፈጠሩ መተላለፎች የሚያስቀጡ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፣  ይህም ኢትዮጵያም ሆነ ሌላም ሀገር ከዚህ የተለየ አይደለም።

ከመቶሺ ሰው በላይ የሞተባት ብራዚል መንሳኤው ከፍተኛ ቸልተኝነት እንደሆነ ይነግራል። በተለይም የፕሬዚዳንቱ ወረርሽኙ መካድ።

በጀርመንኛ ገዳዩ ቸልተኝነት የሚባለው (tödliche Arroganz / Fahrlässigkeit)  ኮሮና አስቀድሞ መቆጣጠር ይቻል የነበረው ባለመፈፀሙ እንዲበዛ የማድረጉ መግለጫ ነው። በተለይም ቁጥሩ መቀነስ ካሳየ በኋላም ወጣት ጀርመኖች ወደ ስፓኝ ለእረፍት በመሄድ በጭፈራ ቤቶች ወዘተ በብዛት በመገኘት እና በሽታውን ይዘው በመመለሳቸው ባለፉት ወራት መብዛት ጀምሮ ነበር። በዚህም የእስያውያን የዲስፕሊን ባህል እንደ ብረት የጠነከረውን የጀርመንን የዲስፕሊን ባህልን እያስናቀም መጥቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም የጤና ኢንስቲትዩት ከመጀመሪያ ጀምሮ በከፍተኛ ጥረት ወረርሽኙ እንዳይገባ፣ ከገባም እንዳይስፋፋ፣ ከተስፋፋም ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ሲሰሩ ታይቷል። ቢሆንም ቸልተኝነትን ለማጥፋት በሚደርገው ጥረት ላይ ብዙ ድጋፍ እና ብዙ መሰራት ይኖርበታል። የቸልተኝነቱ፣ የመሰላቸቱ እና ምንም እንዳልሆነ የመውሰዱ ሁኔታ ዛሬ ከቀዳሚ 50ዎቹ ውስጥ የገባችውን ኢትዮጵያ ወደ ቀዳሚ 20 ሃገራት እንዳትመጣ ያሰጋል። እንደሚሰማውም ከከተማ ውጭ ስለኮሮና ያለው ግንዛቤም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው። በእርግጥ ገደብ ለማድረግ፣ አትውጡ ለማለት፣ ስራን ለመዝጋት የሚያስችል እና ለሚደርሰው ክስራት የሚክስ ሁኔታ እና አቅምም ያስፈልጋል።

 1. ምግብ ቤቶች
ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: ‹‹በእንቅልፍ ማጣት የዕለት ተዕለት ሕይወቴ ደስታ ርቆታል›› ጥያቄና የሕክምናው ምላሾች

ኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች ወይም መሰል ቦታዎች ያለገደብ ሰው ገብቶ እንደሚስተናገድ እና እንደሚዝናና ይሰማል። ጀርመን ግን ተጠቃሚው ወደ ሪስቶራንቱ ሲገባ ስሙን፣ አድራሻውን እና ስልክ ቁጥሩ ይመዘገባል። እስኪቀምጥ ድረስ ማስክ ያደርጋል። ከወንበሩ ተንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ለምሳሌ ወደ መፀዳጃ ቤት ሲኬድ ማስክ ተደርጎ ነው። ጠረጴዛዎች ተራርቀው ነው የሚቀምጡት፣ በየቦታው ሳኒታይዘር ይቀምጣል። ይህንንም በገበያ ማዕከላት፣ በተለያዩ ሰዎች በሚመገቡባቸው እና በሚወጡባቸው ቦታዎች የሚታይ ነው። የተወሰነ ቁጥር ያለው ሰው ከገባ፣ ቀሪው በትዕግስት ውጭ ሆኖ ርቀቱን ጠብቆ የሚቆይበት ነው። በር ላይ ሆኖ የሚቆጥር ወይም የሚቆጣጠርም አለ።

 1. ቴያትር እና ፊልም

ሲኒማ ቤቶች ተከፍተዋል። ይህም ጥብቅ በሆነ የኮሮና ገደቦችን በመከተል ነው። ለምሳሌ ከፊት፣ ከኋላ፣ በግራ እና  ቀኝ ተመልካች አይቀመጥም። ሲኒማ አዳራሹ ቢበዛ አንድ አራተኛ ቦታ ብቻ መያዝ ነው የሚፈቀድለት። የሚታየው ፊልም ድግግሞሽ እና ሌላኛው እስከሚቀጥልም በመሀከሉ ለማጽዳት፣ አየር ለማናፍስ ለሰዓታት ዝግ ይሆናል። በተጨማሪም የፊልም ቀርፃም ተጀምሯል። ለምሳሌ አሜሪካ በተፈጠረው ሁኔታ መቀረፅ ያልተቻሉ ፌልሞች እንደ „ማትሪክስ ቀጥር 4“ የመሳሰሉት በጀርመን የባብልስበርግ ፊልም ኢንዱስትሪ ፓርክ እየተሰሩ፣ በበርሊን ያሉ ቦታዎችም የኒውዮርክ ጎራንጎሮችን እያስመሰሉ እየቀርፁ ይገኛሉ። ለዚህም ዋናው ከእያንዳንዱ የቀርፃም ሆነ ፊቲንግ በፊት አንድ ቀን አስቅድሞ የኮሮና ምርምራ የሚደረግ እና ኔጋቲቭ ውጤቱን  ይዞ የመቅረብ ቅድመ ሁኔታ ነው።

 1. ኮቪድ 19 እና ሰላማዊ ሰልፍ

በ28.08.2020 ጀርመንን እጅግ ያስቆጣው እና ያሳፈረው የሰላምዊ ሰልፍ በበርሊን ተደርጎ ነበር። ይህም በኮሮና የተያዥ ቁጥር መቀንስን ምክንያት በማድርግ የላላውን ሰላምዊ ሰልፍ የመውጣት እገዳን በመጠቀም ተጠረቶ በነበረው እራሱን የኮሮናን እገዳን በመቃወም „የኮሮና ዲክታትርነት ይቁም“፣ „መንግስት ከስልጣን ይውረድ“ ወዘተ የሚል መልዕክት ይዘው የውጡ ሰልፈኞች የታደሙበት ነበር። ከነዚህም ማህከል የከንስፐረሲ አይዲዮሎጂስቶች ሃሳብን የያዙ፣ „ኪው አነን“ (Qanon) እየተባለ በህቡዕ የሚጠራውን የሚደግፉ፣ የወቅቱን የአሜርካ ፕሬዝዳንትን የሚደግፉም ነበሩበት። በዚህ ሰልፍ ላይም የተከለከለውን የናዚ ዘመን ባንዲራ በማውለብለብ ሰልፉን የተደባለቁ እና ጀርመንን ያሳፈሩ ዘርኞች የተሳተፉበትም ነበር። ዋናው ተቃውሟቸውም „በኮሮና የተነሳ የተፈጠረው እገዳ ሆን ተብሎ፣ ታስቦ እና ታቀዶ የሰውን ልጅን ባሪያ ለማድረግ፣ አዲስ የኢኮኖሚ ስራዓት ለመመስርት ነው“፣ „ሚስጢርዊ ቡድን የሚመራው ነው“ ወዘተ የሚሉ ነበር። „ማስክ አለማድረግም መብቴ ነው“ በማለት ማስክ ያላደርጉም ይገኙ ነበር። አብዛኛው ሰልፈኛ በተፈቀደው መሰረት በሰላማዊ መልክ ሃስቡን በመግለፅ ማስክም አድርጎ የተገኘ ቢሆንም፣ ከፖሊስ ጋር በተደረገው ግጭት ከ500 በላይ ክስ ሲመሰረትባቸው በ59 ፖሊሶች ላይ ቀላል አደጋ አድርሰዋል። ይህም ከሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት እና ከቻንስለሯ ጨምሮ ብዙን ያስቆጣ እና ትልቅ የመነጋገሪያ መድርክ ወስዶ የነበር ነው። የህገ መንግስት ጠባቂ (Verfassungsschutz) ለሚባለው የጀርመን የአገር ውስጥ ደህንነት ተቋምም ፈተና ፈጥሮ ነው ያለፈው። በአሁን ሰዓት ከዚህ ተመክሮ በመውሰድ ይህ ቸልተኛነት እንደገና እንዳይደገም እየተሰራበት ነው።

 1. ማጠቃልያ ነጥቦች
 • ኮሮናን ለመዋጋት ከፍተኛ ግንዛቤ ማስያዝ እና በከፍተኛ ሁኔታ በአእምሮ ውስጥ ተቀርፀው የሚቀሩ ድርጊቶችን ማሳየት ያስፈልጋል፣ ለምሳሌ በፅኑ ማቆያ ያሉ በሽተኞችን (ፕራይቪሲያቸውን በጠበቀ መልኩ) ወይም ከቦታው በተከታታይ በሚዴያ መዘገብ
 • የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የባህሪይ ለውጥ እና የዘመን ዲጂታል እይታዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መስራት
 • ድጎማዎችንም ከቅድመ ሁኔታዎች ጋር በማያያዝ ማህበራዊ ግዴታዎችን ለምሳሌ ከስራ ቦታ መፍጠር፣ (አለመቀንስ)፣ ከዋጋ አለመቀነስ፣  ለከባቢ አየር እንክብካቤ በማድረግ ለሚሰሩ መስጠት
 • ወጣት ተኮር የሆነ የስራ ዕድል መክፈት ላይ እና ፈጠራን ማበረታታት
 • የበጎ አድራጎት ስራን ማበረታታት
 • ብሔራዊ የማህበራዊ ግልጋሎትን ማቀድ (ጀርመን እስከ ቅርብ ዓመታት ጊዜ የነበረው የብሔራዊ ውትድርና ግልጋሎት ግዳጅ ላይ ለማይሳተፉት ወጣቶች እንደመተኪያ ለተወስኑ ወራቶች ማህበራዊ ግልጋሎት የሚሰጡበት ስረዓት ነበር። እንደገና ለመጀመርም ጥናት እየተደረገ ነው።)
 • የምግብ አቅርቦት ሰንሰለትን እንዳይቋረጥ ድጋፍ ማድረግ፣ ለገበሬዎች ወለድ የለሽ ብድር ማቅረብ። ርካሽ እና የተሻሻሉ የማምረቻ መሳሪያዎችን እንዲይገኙ ማስቻል
 • መጨናነቅ እና መጣበብ የሚፈጠረው በትራንስፖርት መስኩ በመጠበቅ፣ በመሰባሰብ ወዘተ ስለሆነ የህዝብ ማመላለሻዎችን ቁጥር ወረርሽኙ እስኪወገድ ድረስ መጨመር፣ የሚመጡበትን የጊዜ ድግግሞሽንም ማሳነስ
 • ስለ ኢትዮጵያ ስንናገር ስለአዲስ አበባ፣ ሌላ ከተሞች ወይም መንግስት የሚያውቀውን ፎርማል ሴክተሩን ብቻ ሳይሆን ከ80% በላይ የሆነውን ገጠሩን፣ ከ70% በላይ ኢኮኖሚያዊ አደርጃጀት የሌለበትን እና የማይመዘገበውን፣ በአብዛኛው ከመንግስት ኢኮኖሚያዊ ቁጥጥር ውጭ የሆነውን ኢንፎርማል ሲክተሩን በተመለከተ ከፍተቶችን ለማጥበብ መስራት
 • የገብያ ማዕከላትን በተለያዩ ቦታዎች መፍጠር
 • ስብሰባዎችን በተቻለ መልኩ መቀንስ፣ አስቀድሞ እንደነበረው የመታጠቢያ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ሳኒታይዘሮችን በየቢሮዎች፣ በየገበያ ቦታዎች፣ ወዘተ ማስቀመጥ ማይክሮፎኖችን በፕላስቲክ መሸፈን ወይም ከተናገሩ በኋል በሳኒታይዘር ማፅዳት፣ ወዘተ
 • አስቀድሞ የማስጠንቀቂያ ስራዓትን ማጠናከር፣ ማለማመድ (ለምሳሌ በዛሬው እለት የአደጋ ጥሪ በማሰማት በመላ ጀርመን ልምምድ ሲካሄድ ውሏል።  ይህም በፌዴራል፣ በሬጅን እና በአካባቢ ደረጃዎች የሚገኙትን ሁሉንም የማስጠንቀቂያ መሣሪያዎችን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የሙከራ ማንቂያ ከቀኑ 5 ሰዓት (11 a.m.) ላይ ተከናውኗል። እነዚህ ለምሳሌ ለሲቪል ጥበቃ ማስጠንቀቂያ የሚመከር ምልክት ካላቸው የማስጠንቀቂያ መተግበሪያዎች፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥኖችን እና እንደ ሲረን ያሉ የአካባቢ ማስጠንቀቂያ መሣሪያዎችን ያካተቱ ነበር።)
ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹ፋይብሮማያልጂያ›› የኢዮብን ትዕግስት የፈተነው ምስጢራዊ በሽታ ከ6000 ዓመታት በኋላ ህክምና ተገኘለት!

በተከታታይ የወጡትን ፅሁፎች በተመለከተ ለደረሱኝ መልካም አስተያየቶች አመሰግናለሁ። ለኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት የተለመደውን ትልቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ኮሮና ወረርሽኝን እና የተፈጠርውን ተጓዳኝ ቀውስ ለመከላከል ራሳቸውን መስዋእት አድርገው ለሚታገሉት ኢትዮጵያውን ትልቅ ምስጋና ሳቀርብ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ወረርሽኙ ከአጥለቀለቃቸው ሀገራት ውስጥ ሁነው ከራሳቸውን ጤና እና ደህንነት ትይዩ ትውልድ አገርቸው ኢትዮጵያን እየረዱ የሚገኙትን የተከብሩ ወገኖችን እንደማይረሱና ምስጋናዬንም አቀርባልሁ።

„አሮጊው ዓመት ጥሩ ከነበር ለአዲሱ አመት መምጣት ሰዉ ደስ ሌለው ይገባል፤ አሮጌው ዓመት ጥሩ ካልነበር ደግሞ ለመጪው አዲሱ ዓመት መምጣት ሰዉ የበለጠ ደስ ሌለው ይገባል።“

                                                                   የጀርመኑ ሳይንቲስት እና ፈላስፋ አልበርት አንስታይን

መልካም የጤና እና የስኬት ዘመን 2013!

ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share