July 10, 2010
17 mins read

ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው – ዳንኤል ክብረት

ሁለት እራት አግባ ብልሃተኞች ወደ አንድ ንጉሥ ግቢ ያመሩና ደጅ ይመታሉ፡፡ የግቢው ጠባቂም አቤት ይላል፡፡ እነዚያ ብልሃተኞችም «ለንጉሡ ኃጢአተኛ ሰው የማያየው አዲስ ልብስ ልንሠራ መጥተናል» ይላሉ፡፡ ግቢ ጠባቂውም ሲሮጥ ሄዶ ለንጉሡ ጉዳዩን ያቀርባል፡፡ ንጉሡ ይፈቅዱና ሰዎቹ ገብተው እጅ ነሡ፡፡ «ምን ዓይነት ልብስ ነው የምትሠሩት» አሉ ንጉሡ፡፡ ብልሃተኞቹም «ኃጢአት የሠራ ቀርቶ ያሰበም ሰው ሊያየው የማይችል አዲስ ዓይነት ልብስ ነው» ሲሉ ማብራርያ ሰጡ፡፡ ንጉሡም በነገሩ ተደስተው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ መድበው ልብሱን እንዲሠሩላቸው አዘዙ፡፡

 

በወርቅ እና በብር የተንቆጠቆጡት፣ ልዩ ድርጎ እና ቤት የተሰጣቸው እነዚያ ብልሃተኞች ቤቱን ዘግተው ሥራ ጀመሩ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ንጉሡ አንዱን ባለሟላቸውን ሥራው የት እንደ ደረሰ እንዲያይላቸውት ላኩት፡፡ ብልሃተኞቹም ተቀብለው አስተናገዱት፡፡ ባለሟሉ ወደ ቤታቸው ሲገባ የሚያየው ነገር አልነበረም፡፡ ባዶ የልብስ መሥሪያ ማሽን፣ ባዶ ጠረጲዛ እና ባዶ አዳራሽ፡፡ ግራ ተጋባ፡፡ ከብልሃተኞቹ አንዱ ወደ ጠረጴዛው አመራና «አዩ ጌታው፤ እጀ ጠባቡ እያለቀ ነው» አለው ባዶውን ጠረጴዛ እያሳየ፡፡ ባለሟሉ ግን እንኳን እጀ ጠባብ ብጫቂም ጨርቅ በጠረጴዛው ላይ ለማየት አልቻለም፡፡ ነገር ግን «ኃጢአት የሠራ ሰው ልብሱን ማየት አይችልም» ተብሏልና «አላየሁም» ቢል ኃጢአት ስለ ሠራህ ነው የሚለው እንጂ የሚያምነው ስለሌለ «በጣም የሚገርም እጀ ጠባብ ነው፡፡ መቼም ንጉሣችን ሲያዩት ይደሰታሉ» ብሎ ራሱን እየነቀነቀ አደነቀ፡፡ በልቡ ግን ግራ እንደተጋባ ነበር፡፡

 

«ንጉሥ የሚያምረውን እንጂ የሚያምርበትን፣ ንጉሥ የሚፈልገውን እንጂ የሚያስፈልገውን አይነግሩትም» ይባላልና ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመልሶ ለንጉሡ «እጅግ የሚገርም፣ ዓይን ያላየው ጆሮም ያልሰማው ልዩ የሆነ እጀ ጠባብ ተሠርቷል፡፡» ሲል ሪፖርቱን አቀረበ፡፡ አሁንም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ንጉሡ ሌላ ባለሟላቸውን ላኩት፡፡ ያም ባለሟል ወደ ብልሃተኞቹ ቤት ገብቶ አካባቢውን ሲያይ ደነገጠ፡፡ እንኳን የተሰፋ ልብስ የተዘረጋ ክር የለም፡፡ ነገር ግን የቀድሞው ባለሟል አየሁ ብሎ ይሄኛው አላየሁም ቢል ከጓደኛው ማነሱ ነው፡፡ ብልሃተኞቹም ወደ ጠረጴዛው ወስደው «እጀ ጠባቡ ይህንን ይመስላል፤ ሱሪው ደግሞ በመሰፋት ላይ ነው፡፡ የሚቀረን ጫማው ነው» እያሉ ማስጎብኘት ቀጠሉ፡፡

 

ባለሟሉ እንኳንስ አዲስ የተሠራ እጀ ጠባብና የተሰፋ ሱሪ ቀርቶ አሮጌ ልብስ እንኳን እንኳን ለማየት አልታደለም፡፡ ነገር ግን ኃጢአተኛ ከሚባል «እንደ ዘመኑ ይኖሩ እንደ ንጉሡ ይናገሩ» ነውና «ይህንን ነገር ለማየት በመታደሌ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ፡፡ ይህንን ነገር ለማየት ፈልገው ያላዩ ስንት አሉ፡፡ በሥራችሁ ንጉሡ እንደሚደሰቱ ርግጠኛ ነኝ» ብሎ አመስግኗቸው ወጣ፡፡ በልቡ ግን «እነዚህ ሰዎች ያሾፋሉ እንዴ፤ ምን ዓይነት ነገር ነው እየሠሩ ያሉት» እያለ ያጉተመትም ነበር፡፡ ለንጉሡም ድንቅ ነገር ማየቱን ከዚያኛው አስበልጦ አንቆለጳጵሶ አቀረበ፡፡

 

በመጨረሻ ራሳቸው ንጉሡ የሥራውን ማለቅ ለማየት ከባለሟሎቻቸው ጋር መጡ፡፡ እነዚያም ብልሃተኞች እንደተለመደው ወገባቸውን አሥረው ማስጎብኘት ጀመሩ፡፡ «ይሄ እጀ ጠባቡ፣ ይሄ ሱሪው፣ ይሄ ካባው፣ ይሄ ጫማው ነው» እያሉ ያሳያሉ፡፡ ንጉሡ ምንም ነገር ለማየት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን የእርሳቸው ባለሟሎች አየን ብለው እያወሩ እርሳቸው አላየሁም ቢሉ ራሳቸውን ማስገመት ነው፡፡ ሕዝቡስ ምን ይላል? ደግሞም ዋናው ነገር እርሳቸው አየሁ ማለታቸው እንጂ ማየታቸው አይደለም፡፡ ይህንን ሁሉ አስበው «በሕይወቴ ላየው የምፈልገውን ነገር ነው ያየሁት፡፡ በነገሥታት ታሪክ እንደዚህ ያለ ልብስ መልበሱ የተነገረለት ንጉሥ የለም፡፡ ልዩ የሆነ ሽልማት ይዘጋጅላችኋል» ብለው አድናቆታቸውን ገለጡ፡፡ አጅበዋቸው የመጡትም ምንም ነገር ለማየት ባይችሉም ኃጢአተኛ እንዳይባሉ ሲሉ አደነቁ፤ አመሰገኑ፡፡

 

«ንጉሥ ሆይ» አለ አንደኛው ብልሃተኛ «ሕዝቡ ሁሉ በዐዋጅ ተጠርቶ ይህንን ልብስ ለብሰው ማየት አለበት»፡፡ የንጉሡም ባለሟሎች «እውነት ነው፤ ይህንን መሰሉ ልብስማ የቤት ልብስ አይሆንም» ብለው እያዳነቁ ሃሳቡን ደገፉት፡፡ ንጉሡም ተስማሙ፡፡

 

ዐዋጅ ታወጀ፡፡ «ንጉሡ ኃጢአት የሠራ ሰው ሊያየው የማይችል ልብስ ስላሠሩ እንዲህ ባለ ቀን፣ እንዲህ ባለ ቦታ፣ በዚህ ሰዓት ወጥታችሁ እንድታዩ» ተባለ፡፡ በተባለውም ቀን ሕዝቡ ጉድ ለማየት ግልብጥ ብሎ ወጣ፡፡ ንጉሡም ወደ ብልሃተኞቹ ዘንድ መጡ፡፡ ሁለቱ ጓደኞች እየተረዳዱ ንጉሡን ማልበስ ቀጠሉ፡፡ እነዚያ ብልሃተኞች ንጉሡ የለበሱትን ልብስ ሙልጭ አድርገው አውልቀው «አሁን ሱሪውን፣ አሁን እጀ ጠባቡን፣ አሁን ካባውን» እያሉ አለበሷቸው፡፡ ንጉሡም እየሳቁ፣ፈገግ እያሉ፤ በዙርያቸው የተሰለፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ልብሱን ለበሱ ተባለ፡፡ ንጉሡም በልባቸው «ራቁቴን ሊያስኬዱኝ ነው እንዴ?» ይላሉ፡፡ ግን አይናገሩትም፡፡ ተከታዮቻቸውም «እኒህ ሰውዬ ሊያብዱ ነው እንዴ፤ ራቁታቸውን ናቸውኮ» ይላሉ ግን አይናገሩትም፡፡ አፍ እና ልብ እንደ ተለያዩ ንጉሡ ለብሰው ጨረሱ ተባለ፡፡

 

ከዚያም ሠረገላው ቀረበና ንጉሡ በትረ መንግሥት ጨብጠው ቆሙ፡፡ ባለሟሎቻቸውም ሰግደው አጨበጨቡ፡፡ ከዚያም ሠረገላ ነጅው እንደ ዛሬ ንጉሡን ራቁታቸውን አይቷቸው ስለማያውቅ ሳቅ እያፈነው ሠረገላውን መንዳት ጀመረ፡፡ ወደ አደባባዩም ወጡ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ አጨበጨበ፡፡ አንዱ ለጓደኛው «ግሩምኮ ነው፤ ከየት አገኙት ባክህ» ይላል፡፡ ኃጢአተኛ እንዳይባል፡፡ በልቡ ግን «በቃ ስምንተኛው ሺ ማለት ይሄ አይደለም እንዴ፡፡ ንጉሥ ራቁቱን ሲሄድ ከማየት በላይ ምን ምልክት አለ» ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ «ተመልከት፣ ተመልከት እጀ ጠባቡ ሲያብረቀርቅ፣ ንጹሕ ሐር እኮ ነው» ይልና በውስጡ ግን «አብደዋል፣ አብደዋል እንጂ፤ ደኅና ዘመድ አጥተዋል» ብሎ ያማል፡፡ ሁሉም ራሱን ላለማዋረድ እና ኃጢአተኛ ላለመባል ሲል ያላየውን እንዳየ እያደረገ ይጨዋወታል፡፡ በልቡ ግን ግማሹ ይስቃል፣ግማሹ ያፍራል፣ ግማሹ ይራገማል፣ ቀሪውም ያማል፡፡

 

ንጉሡም ከሕዝቡ የሚቀርብላቸውን ልክ የሌለው ሙገሳ እየሰሙ፤ የባለሟሎቻቸውን ውዳሴ እያዳመጡ ሰውነታቸው በሙሉ ጥርስ በጥርስ ሆነ፡፡ በውስጣቸው ግን ብርዱ አላስቆም አላቸው፡፡ ነፋሱ ይቀጠቅጣቸው ጀመር፡፡ «ምን ዓይነት ሞኝ ብሆን ነው የነዚያን አጭበርባሪዎች ምክር የሰማሁት፤ አሁን የውስጤን ብናገር ማን ያምነኛል» ይሉ ነበር፡፡

 

በዚህ መካከል እናቱን ተከትሎ የመጣ አንድ ሕፃን ልጅ «እማዬ፣ እማዬ እይ፣ ንጉሡኮ ራቁታቸውን ናቸው» አለና ጮኸ፡፡ በዙርያው የነበሩ ሁሉ «ዝም በል፤ ይሄ ገና ከልጅነቱ ኃጢአት የወረሰው፡፡ ምን የዛሬ ዘመን ልጆች እንዲህ ያለው ግሩም ነገር አይታያችሁ፡፡ ዝም በል፤ የተረገመ» እያሉ ተረባረቡበት፡፡ እናቱም አፈሩ፡፡ በዚህ ሰዓት ካፊያ እየጣለ ነበር፡፡ ንጉሡ ግን ፈገግታቸው እየጨመረ፣ ስቃያቸውም እያየለ ሄደ፡፡ ያ ሕፃን ልጅ ከእናቱ እጅ አፈትልኮ ወጣና ሠረገላውን እየተከተለ «ኧረ ንጉሡ ራቁታ ቸውን፤ ኧረ ንጉሡ ራቁታቸውን» እያለ መጮኽ ቀጠለ፡፡ ሕዝቡም በኃጢአተኛነቱ እያዘነበት፣ ርግማኑንም እያዥጎ ደጎደበት፣ ዝናሙም እያየለ፣ ንጉሡም እንደቆሙ ትእይንቱ ቀጠለ፡፡

 

ሕዝቡ ያጨበጭባል፣ ባለሟሎችም እንጀራቸው ነውና ሕዝቡ እንዲያጨበጭብ ያስተባብራሉ፡፡ ቀራቢዎቻቸው እጅ ያውለበልባሉ፤ ንጉሡም የሚቀርብላቸውን ሁሉ በደስታ ይቀበላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡም ያማል፡፡ በዚህ ዘመን መፈጠሩን ይረግማል፡፡ በንጉሡ እብደት ይናደዳል፣ ይዝታል፡፡ ባለሟሎቻቸውም በውስጣቸው አፍረዋል፡፡ በነዚያ ሁለት ብልሃተኞች ድርጊት ተበሳጭተዋል፡፡ እንዲህ ባለው ዘመን ባለሟል በመሆናቸው ራሳቸውን ይረግማሉ፤ ዘመኑንም ይረግማሉ፣ በውስጣቸውም ያማሉ፡፡ ግን ምኑንም አይናገሩትም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ሥራቸው ነውና ሳያጨበጭብ ቆሞ የሚያዩትን ሰው «አጨብጭብ፣ ኃጢአተኛ!´ እያሉ ይቆጣሉ፡፡

 

ብርዱ እየከፋ፣ ዝናሙ እየጨመረ መጣ፡፡ ንጉሡም ጥርሳቸውን እያፋጩ፣ ሰውነታቸው በብርድ እየተርገፈገፈ፣ ብርዱ አጥንታቸው ድረስ እየሠረሠራቸውም ቢሆን ከመሳቅና፣ ፈገግ ከማለት፣በደስታ እጃቸውን ለሕዝቡ ከማንሣትና ራሳቸውን ከመነቅነቅ አልተቆጠቡም፡፡ ያ ሕፃን ልጅ ብቻ ከኋላ ከኋላ እየተከተለ «ኧረ ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው፣ ኧረ ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው» እያለ ይጮኻል፡፡ በርሱ ላይ የሚደርሰው ርግማኑና ቁጣውም አሁንም እንደ ቀጠለ ነው፡፡

 

በመጨረሻ ግን ንጉሡ አልቻሉም፡፡ ብርዱ እና ዝናቡ ከዐቅማቸው በላይ ሆነ፡፡ ሰውነታቸው መርገፍገፍ፣ ጥርሳቸውም እንደ ገጠር ወፍጮ መፋጨት ጀመረ፡፡ ውጫዊ ማስመሰያ ውስጥን ሸፍኖ መቆየት የሚችለው ጥቂት ጊዜ ነውና ንጉሡም የውስጣቸው ሕመም እንደልብ ፈገግ ለማለት እና ደስተኛ ለመምሰል አላስቻላቸውም፡፡ የሆነውን ሳይሆን እንዲሆን የሚፈልጉትን ተቀብሎ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ሽል ከሆነ ይገፋል፣ ቂጣ ከሆነ ይጠፋል፡፡

 

በድንገት ንጉሡ ሠረገላ ነጅውን «አቁም!» ብለው በቁጣ ተናገሩት፡፡ እርሱም ሳቁ ወደ ድንጋጤ ተለወጠበትና አቆመ፡፡ «ያ ሕፃን ልጅ ብቻ ነው እውነተኛ፡፡ አዎን እውነት ነው እኔ ራቁቴን ነኝ፡፡ ሁላችሁም ውሸታችሁን ነው፡፡ እኔም ውሸቴን ነው» አሉና ተቀመጡ፡፡ ባለሟሎቻቸውም የቀድሞ ካባቸውን ሰጧቸው፡፡

 

አንዳንዶቹ ባለሟሎች «እኛ ምን እናድርግ ራሳቸው ናቸው ለዚህ የበቁት» አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ «ጥፋተኞቹ እኛ ሳንሆን ያኔ ተልከው ያላዩትን እንዳዩ አድርገው የተናገሩት ናቸው» ብለው ወቀሱ፡፡ የቀሩትም «ሰሚ አጥተን ነው እንጂ ኧረ እኛስ ተናግረን ነበር» ብለዋል፡፡ ከሕዝቡም አንዳንዶቹ «አላልኳችሁም፣ እኔ ቀድሞም ተናግሬ ነበር» ያሉ አሉ፡፡ «ድሮም ነገሩ አላማረኝም ነበር» ያሉም ነበሩ፡፡

 

አንደኛው ሰውዬ ደግሞ ሁሉንም ያስደነቀ ነገር ተናገረ፡፡

 

«ለዚያ ሕፃን ልጅ ንጉሡ ራቁታቸውን መሆናቸውን የነገርኩትኮ እኔ ነኝ» ሲል፡፡

 

እነዚያ ሁለት ብልሃተኞች ግን ብራቸውን ይዘው የት እንደ ደረሱ እስካሁን አልታወቀም፡፡

 

ዳንኤል ክብረት

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

እማማ አብስኒያ

Next Story

ESAT interview Abune Mekarios part 1 of 4 April 2011

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop