እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ! – ወለላዬ ከስዊድን

አዎን ኢትዮጵያዊ ነኝ በለኝ
መቼም አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም
ካልሆንክም ግድ የለም
እቅጩን ሀቁን ንገረኝ
ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ።
የኔነቴን የአገሬን ትዝታ
የቀየው የአድባሩን ሽታ
የፍቅሬን የአንድነት ጥላ
ለዘመናት ያኖረኝን ከለላ
ወዲያ ጥለኸው ሰባብረህ
ከናት አባትህን ቃል ኪዳን ርቀህ
እንዲህ ሆነህ ያገኘሁህ
ማነህ
እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ?!

በመልክማ፣ ትመስለኛለህ አንድ ነን
በቀለምስ በቁመትስ ምን ለየን
ግን አንተ፣ ምድረ አገርህን ክደሃት
በአደባባይ አዋርደሃት
እውን ኢትዮጵያዊ ነህ?
ኢትዮጵያስ ያንተ ናት
ማነህ?
እውነት አንተ ምንድነህ?
አገር እናቴን ፍቅሬን
የደስታ የሃዘን ገበናዬን
የኔነቴን ቅርስ መጠሪያዬን
የነፃነት ብርሃን ኩታዬን
የጣልክብኝ ያገር ክብሬን
ማን ነው ልበልህ ማነህ ንገረኝ ማነህ!
እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ?
መቼም፣ አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም
ካልሆንክም ግድ የለም
እቅጩን ሀቁን ንገረኝ
ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ
እናት ከልጅ አስገድደህ ደፍረህ
ወገንህን ዘቅዝቀህ ገድለህ
ሀይማኖት እምነትህን የሻርክ
አገርን ለማፍረስ የደፈርክ
ማነህ
እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ?
ያንን መተዛዘን ደግነት
የፍቅረ ሰላም አንድነት
የአብሮ መኖርን እሴት
ለዘመናት የኖረን ተውፊት
የት አደረስከው
እንዴት አድርገህ ደፈጠጥከው
ምን ያህል አውጥቶልህ ሸጥከው
በል ንገረኝ እውነት እውነቱን እናውራ
አንተም በኢትዮጵያዊነት ትጠራ
መቼም አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም
ካልሆንክም ግድ የለም
እቅጩን ሀቁን ንገረኝ
ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ

ለመልኩማ፣ መልክህ መልኬን ወርሷል
እትብትህ በኔው ቀዬ ተቀብሯል
ዜግነትህ በዜግነቴ ተጠርቷል
ወዝህ ከወዜ ተነካክቷል
ዘርህ ከዘሬ ተጋምዷል
ግብርህ ግን ይሄን ሁሉ ሽሮ
አመለካከትህ ተጠናብሮ
እያየሁህ እያየኸኝ
ማነኝ ነው የምትለኝ
መቼም አፍህ ከተግባርህ አይከብደኝም
ግድ የለም
እቅጩን ሀቁን ንገረኝ
ያንተ ነገር ቁርጡ ይግባኝ
ማነህ
እውነት አንተም ኢትዮጵያዊ ነህ!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነፍሴ ቃተተች - በላቸው ገላሁን

፳፻፲፪ ዓ.ም ስዊድን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share