ሕውሃትን በተመለከተ ለመንግስት የማቀርበው ጥያቄ፤ የወንጀል ተጠርጣሪ ወይስ የፖለቲካ ባላንጣ? – ያሬድ ኃይለማርያም

የመንግስት ባለሥልጣናት ሰሞኑን ስለተፈጸመው ግድያ እና እልቂት አስመልክቶ በየቀኑ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ሁሉ ተጠያቂዎች አድርገው ከሚገልጿቸው አካላት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ወያኔ እና ባለሥልጣናቶቹ ናቸው። በአጫሉ ግድያም ሆነ ከዛ በኋላ በተከሰቱት ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች ወያኔ እጇ እንዳለበት ተገልጿል። ለመንግስት የማቀርበው ጥያቄ ታዲያ ህውሃት እና ባለሥልጣናቶቹ እንዲህ አይነት አገርን የማተራመስ እና የሽብር ተግባር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው በመረጃዎች ከተረጋገጠ እነዚህ ግለሰቦች በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ምን እየተሰራ እንደሆነ አብራችው ብትገልጹልን ጥሩ ነው?
እንደ ድርጅት ህውሃት በዚህ አይነት የሽብር ተግባር ላይ እስከተሰማራ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ድርጅቱን ሕጋዊ እውቅና መንፈግ እና እቀባ መጣል አይገባም ወይ?
አመራሮቹ እና አባላቱ በተጠቀሱት ወንጀሎች ላይ ባላቸው የወንጀል ተሳትፎ ልክ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ በስም ተዘርዝረው ተጠቅሰው፤ ልክ የቀድሞው የደህንነት ሹም ላይ እንደተደረገው የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣት አይገባም ወይ? አንድ ጌታቸውን መያዝ ከባድ ለሆነበት መንግስት ደባቂዎቹንም አብሮ መክሰስ የት ያደርሰዋል ቢባልም ሁሉንም በሌሉበትም ቢሆን ክስ መስርቶ በፍርድ ቤት ጥፋተኝነታቸውን ማረጋገጡ መንግስት ክልሉን ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ጥረት (ካለ) አያግዝም ወይ?
በመላ አገሪቱ ያሉ እና ህውሃት በባለቤትነት በሚያንቀሳቅሳቸው ንብረቶች፤ እንዲሁም የድርጅቱ ባለሥልጣናት እና አመራሮች የሚያንቀሳቅሷቸው ንብረቶች እና የባንክ ሂሳቦቸቸውም ላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እገዳ መጣል አይቻልም ወይ?
ከህውሃት ጋር ቀጥተኛ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው እና ድርጅቱ አገርን ለማፈራረስ፣ የንጹሃን ዜጎችን ደም ለማፍሰስ እና ሕዝቡን ለማሸበር በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ የተግባር ተሳትፎ እና ድጋፍ በሚሰጡ ተቋማትን እና ግለሰቦችንስ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
እነዚህን ጥያቄ ለማንሳት ያስገደደኝ እስካሁን መንግስት በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ደጋግሞ ሲናገር ሕውሃትን እና አመራሮችን ግን በመግለጫ ከማውገዝ እና ከመዝለፍ ባለፈ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ማሰቡንም ሆነ ምን እየሰራ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ነገር ስላልሰማው ነው። ህውሃትን ልክ እንደ ግብጽ ወይም አልሻባብ የመሰሉ የውጭ መንግስታት እና ቡድኖች እንዲሁ በመግለጫ እያወገዙ መቀጠል የት ያደርሳል? ህውሃትን በሕግ የማንበርከኩ ሥራ እንዲህ ቀላል ባይሆንም ትግራይን ያቀፈች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከተፈለገ ሂደቱን ከላይ በተጠቀሱት እርምጃዎች ከወዲሁ መጀመር ይገባል።
መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ግዛት የሕግ የበላይነትን የማስፈን ፍላጎት እና አቅም ያለው መሆኑንም ማሳየት ይኖርበታል። ስለ ህውሃት ሲወራ ልክ እንደ አንድ በክፉ የሚነሳና እራሱን የቻለ ሉዓላዊ ጎረቤት አገር አስመስሎ ማቅረቡ ትግራይን ለሕውሃት ሙሉ በሙሉ የመተው አዝማሚያ ይመስላል። በአንድ ወንጀል ተሳትፎ ያላቸውን አካላት ሁሉ አብሮ ማቅረቡ ከፍትሕ እና ሕግን ከማስከበርም ባለፈም ትልቅ የፖለቲካ ፋይዳ አለው።
ያሬድ ኃይለማርያም

4 Comments

  1. አቶ ያሬድ
    በትክክል አስቀምጠሀል ብራቮ:: ባዶ የተቃውሞ መግለጫዎች ዛሬ ምንም እርባና አይኖራቸውም:: መጀመሪያ በወንጀለኛነት የተረጋገጠበት የቀድሞው የደህንነት ሹም ለምን ለፍርድ አይቀርብም? መንግስት ይህን ለማድረግ ጉልበት ከሌለው ይህን ግልፅ ያድርግ:: አንተ እንደገለጥከው እነዚህን ሰዎች ሄዶ በአካል ማሰር እጅግ የሚቀለው አዲስ አበባ ንብረታቸውን ለማገድ ለመንግስት እጅግ ቀላል ነው:: የኢትዮጵያ ብር ኖቶች መንግስት ቢለውጥ ካዝናቸው ባዶ ይቀራል:: ወንጀለኞችን ለማድከም ከጦርነት ውጪ ብዙ አማራጮች አሉ:: የትግራይ ህዝብ ሳይጎዳ ዘራፊና ሀገር አፍራሾችን ለፍርድ ማቅረብ ይቻላል

  2. አይሄሄ! ቀላል አይመስለኝም። እንደ ዶር አቢይ አያያዝ ቢሆንማ ስልጣን በያዘ ማግስት ነበር የሚለቅማቸው። ችግሩ ማንን ይዞ ነው? በፊትም ይሁን አሁን የምለው የውስጥ ባለሟሎቹ መች በቅጡ ተደመሩና ነው ህውሀትን የሚያክል አስፈሪ አውሬ ብቻውን አደን የሚሄደው ዶር አቢይ? አሁን ገና በዚህ ምስኪን ልጅ ሞት አይደለም እንዴ እነ ሺመልስስ አይናቸው ረጥቦ መጥረግና ማየት የቻሉት? ኢትዮጵያውያን አለመታደል ሆኖ ሌማታችን ላይ የቀረበልንን ማኛ ጤፍ ትተን የጎረቤት ገብስ እንጀራ ላይ ነው አይናችን የሚያርፈው። የዚህን አቢይ ድንቅነት ለሁሉ እድሜ ሰጥቶ ለማየት ያብቃን። ከእውነተኛው ድል በሁዋላ ሰውዬው ለንባብ የሚያበቃልንን ታሪክ ወገን ሲያነበው “ለካንስ ወዶን አልነበረም ውስጡ እየተቃጠለ ትእግስት” ይለን የነበረው ባንል። እንዲህ ነው ልቤ የሚነግረኝ። ይህው ነው። ከጠቅላይ አቃቤ ህግ እንኳ ያ ያለፈው ሰውዬ ምን ሰራ? ይቺኛዋ ግስላ አዳነች አቤቤ ግን ለየት ያለች ናት። ለማየት ያብቃችሁ። የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ እንዲሉ።

  3. “ትግራይን ያቀፈች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከተፈለገ ”
    ምን….? ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታምያለሽ እንዲሉት፣ ያቅምህን ያህል ማሰቡን ብታስብበት እንዴት ባማረብህ…..!

  4. እኔ በጣም የሚገርመኝ አሁንም በአብይ ሴራ ፖለቲካ ተስፋ አለመቁረጣችሁ ነው ስንት ግዜ የወያኔ እጅ አለበት ተባላችሁ ሁለት አመት ሙሉ ነገር ግን መረጃ የለም እንዴት አድርጎ ነው ወደ ህግ ሊያቀርበው የሚችለው ወዶት ይመስለሀል ለምን ጌታቸው አልያዘውም ሴራ መሆኑ ሲታወቅ የትግራይ ወጣት አሳልፈን አንሰጥም አለ አንድ መንግስት በጠራራ ፀሀይ የተገደለው እ/ር ስመኝ ራሱ አጠፋ የሚል ከሆነ እንዲሁም ጀነራሎች እና የክልል ባለስልጣናት በተለያየ ሴራ ሲገደሉ ለጊዜው በፉከራ እና ሽለላ የምታልፈው ከሆነ መንግስት ራሱ አሰገዳይ ነው ወይም ተባባሪ ነው የሚል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡ አሁን አብይ ኢ/ያ ኢ/ያ ሲል እውነት ይመስላሀል ሺመልስ አብዲሳ ኢ/ያ ኢ/ያ ሲል እውነት ይመስላሀል አትሸወድ ከዚህ በፊት ያደረግዋቸው ንግግሮች ደግመህ ደጋግመህ አድምጣቸው ያኔ ይገባሀል ነገር ግን አንተ ራስህ ሳታውቅ ቀርተህ አይደለም ግማሽ መንገድ አብረሀው መሄድ ስለ ፈለክ ነው፡፡ ያሬዶ መፍትሄ ብለህ ያስቀመጥቃቸው ነጥቦች በፍፁም መፍቲሄ ሊሆኑ አይችሉም ህዘቡ እንደ ሀገር አብሮ እንዳይቀጥል ያደርገዋል እንጂ አንተ እንደምትለው ህዝቡ በቀላሉ ደፍጥጠህ ለመግዛት እጅ ሚሰጥ ህዝብ አይደለም ከፌደራል መንግሰት ከሚደረጉ ጫናዎች ምክንያት የትግራይ ህዝበ በአሁኑ ሰአት ከህወሀት በላይ ከኢትጵያ ጋር መቀጠለል አይፈልግም፡፡ ስለዚህ አብረን ለመቀጠለል መግባባት ፤ መከባበር ፤ መቻቻል አለብን፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.