June 26, 2020
6 mins read

ድሮ (ዘ-ጌርሣም)

ገና ልጆች እያለን
ከየሠፈሩ ተጠራርተን
ስነገናኝ ተነፋፍቀን
ስንለያይ ተሸኛኝተን
ጭቃ አቡክተን
ውሃ ተራጭተን
ስንጠራ አቤት( እመት) ብለን
ለታላቆች ተላልከን
ጉልበት ስመን
ተመርቀን አደግን
በወግና በሥርዓት ታንፀን
ድሮ
በታዳጊው አዕምሮአችን
የሁሉ ቤት ቤታችን
የሁሉ እናት እናታችን
የሁሉ አባት አባታችን
ሳንሳቀቅ ተዝናንተን
ባይወልዱንም ልጆች ሁነን
እንግድነት ሳይሰማን
ያገኘነውን ተካፍለን
ሳንጣላ ተስማምተን
ያስቀና ነበር ዕድገታችን
ድሮ
የሠፈር ልጆች ተጠራርተን
ሜዳ ወይም ወንዝ ወርደን
የልባችን አውርተን
ዘለንና ፈንጥዘን
ጊዜውን በደስታ አሳልፈን
ስንሄድ ወደየቤታችን
ዛሬን ብቻ ሳይሆን
ነበር ነገንም እያሰብን
እንደምንገናኝ ተስፋ አርገን
የምንጠብቅ መጭውን
ድሮ
ትምህርት በደንብ ሳይለመድ
ፍላጎት ሳይታገድና ሳይገደድ
መርጌታ ተቀጥሮ ለሠፈሩ
ሁ ሁ ብለው ሲያስቆጥሩ
ከትልቅ ዛፍ ሥር ተሰብስበን
የኔታን ከመሐል አስቀምጠን
እኛም ዙሪያውን ከበን
ሁላችንም የየራሳችን
ከፍ አድርገን ድምፃችን
መቁጠር ነበር ውሏችን
ድሮ
አቤት ትዝ ሲለኝ
ያ ጊዜ ሲናፍቀኝ
ልንሄድ ስንል ቤታችን
የየኔታን ጉልበት ስመን
እሳቸውም መርቀው
ዳበስ ዳበስ አድርገው
ያሳድግህ ይግለጥልህ
ጧሪና ቀባሪ ያርግህ
ሁሩ በሰላም ሲሉን
ወሰን የለሽ ነበር ደስታችን
ድሮ
የቄስ ትምህርቱን አቋርጠን
ብዙወቻችን አስኳላ ገባን
ጥቂቶቹ ሲቀጥሉ
ቀሪወቹም ተሰናከሉ
የወደፊት ዕጣ ፈንታ
ተጀመረች በተርታ
የአርባ ቀን ዕድል ወሰነች
እንደሰበዝ ተመዛ ወጣች
መንገዱን እያሳየች
ትዕግሥት ያለው ገፋበት
የቸኮለው ወጣ ጥሎት
ያኔ ተጀመረ መለያየት
ዳገት መውጣት ወድቆ መቅረት
ድሮ አልፎ
ህይወት ጉዞዋን ቀጠለች
ከዕውቀት ጋር ተጎዳኘች
ያልነበረ አዲስ ክስተት
እኛ ቀርቶ ለኔ ማለት
ተጀመረ መደባበቅ
ተቀመመ የተንኮል ስንቅ
የግል ምኞትና ፍላጎት
ቃልን በምላስ አስበላት
ጊዜውም ከፋ መነጠ
የውስጥ ስሜትን ገለጠ
ገንዘብና ሥልጣን ገዘፉ
ሰብዕናን በቁም ዘረፉ
ድሮ አልፎ
ተተካ ሌላ ዘመን
የሚያስተክዝ የሚያሳዝን
የያኔው አብሮ መኖር
በጋብቻ መተሰሰር
በደም በስጋ መዋሃዱ
አብሮ መቆም መዋደዱ
ደስታንም ሆነ መከራ
መካፈሉ በጋራ
ሁሉም ነገር ተረስቶ
እውነት በውሸት ተደርቶ
ፖለቲካ የሚሉት ዕዳ
በየቦታው ፈነዳ
ህይወትን መቅጠፍ ጀመረ
ሥልጣን ፈላጊን አሰከረ
በጎጥ በሠፈር ተጠራርቶ
ሥልጣን ለመያዝ ተስማምቶ
ያምሰው ጀመር ህዝቡን
ያናውጥበት ሰላሙን
ትናንት
ያ ሁሉ ዘመን አልፎ
የሥልጣን ጥሙ ነጥፎ
ወኔና ትዕቢት ዝለው
አብረው የቆሙ ተማምለው
በጀሌው ገቡ ትጥቅ ፈተው
በሰላም ጥሪ ተረተው
ለውጡም በአሸናፊነት ጎመራ
ግቡ ገብተናል ብሎ አጠራራ
የተለጎመ አፍን አስፈትቶ
ነፃ መድረክን አመቻችቶ
እንዲናገር ዕድል ሰጠው
አስደምሞ በእንባ አራጨው
በእስር ሰቆቃ የማቀቁ
ወገኖችም ተለቀቁ
ዕድሜ ለዚያች ቀን ለትናንት
በዓይናችን በብሌኗ ስላየናት
ዛሬ
ገና በእንጭጩ በለጋው
አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው
ያልጠራ እንደ ጉሽ ጠላ
የሚንተከተክ እየፈላ
የእስከዛሬው ላይበቃ
ትውልድን ፈጅቶ ያስጠቃ
ህይወት ተከፍሎ የመጣን ለውጥ
መነወጥና መድፈቅ
በፈጣሪም ዘንድ ያስጠይቃል
ህጉ ከሠራም ያስቀጣል
ምነው ምነው
የጤና ወይስ ዕብደት ነው
እስኪ ዛሬያችን ላይ ቁመን
እናስታውስ ሰቆቃውን በምናቫችን
ምን ነበር ስንል የነበረው
የተማማልነውና ቃል የገባነው
ዳግም ላይደገም ተማምለን
ታዲያ ምን ሾተላይ ገባብን
ሁልጊዜ የሚያባላን
መሳቂያና መሳለቂያ የሚያደርገን
ከሀገራት በፊት ተፈጥረን
የሰው ልጅ መገኛ ተብለን
ታሪክ ጽፈን
አስነግረን አዘክረን
ዓለምም መስክሮልን
ታዲያ እኮ ምን ቢጎለን
እንደ አውሬዎች የሚያባላን
ዛሬም ያልፋል

የነገው ግን ከብዶኛል
መላ ምቱ ጠፍቶኛል
ግን አምናለሁ በአንድ ተስፋ
በማይነጥፍ በማይጠፋ
አለ አንድ ቃል ኪዳን
የሚታደግ ኢትዮጵያን
ከፍ ከፍ የሚያደርጋት
ወደቀች ሲሏት የሚያነሣት
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር
(2019-07-14)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop