ፍኖተ ነፃነት
ለፋሽስቱ ለጦር ወንጀለኛ ለግራዚያኒ የተሰራውን ሀውልትና የመናፈሻ ስፍራ በመቃወም የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ መንግስት በኃይል በተነ፡፡
በኢትዮጵያ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴ፣ በባለራዕይ ወጣቶች ማህበርና በሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪነት የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ህጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ የተዘጋጀ ቢሆንም ፖሊስ ትላንት ቅዳሜ መጋቢት 7 የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ 8 ሰዎችን “ህገወጥ ቅስቀሳ ነው” በማለት አስሯል፡፡
ዛሬ በሰላማዊ ሰልፉ ለመካፈል በስድስት ኪሎ የሰማዓታት ሀውልት አካባቢ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ መሰባሰብ የጀመሩትን ሰልፈኞችም ፖሊስ “የዛሬው ሰልፍ ፍቃድ የሌለው ነው” በሚል እንዲበተኑ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በስፍራው የነበሩት ሰልፈኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድም ፖሊስ ሀይል ተጠቅሞ በመበተን የሰማያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴና የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር አመራሮችን አስሯል፡፡ ፖሊሶች በተለይ በባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ያዘጋጀውን ቲሸርት የለበሱት እየለየ ሲያስር እንደነበር ተስተውሏል፡፡ ትላንት የታሰሩትን ጨምሮ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ግለሰቦች ቁጥር 43 ደርሷል፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፣የኢትዮጵያ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታዲዎስ ታንቱ፣ የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ብርሀኑ ተክለያሬድ፣የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ፀሀፊ ያሬድ አማረ ይገኙባቸዋል፡፡
ሰልፉ በሀይል ከተበተነ በኋላ የሰልፉ አስተባባሪዎች በሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ለጋዜጠኖች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ላይ የመንግስት ተግባር አፓርታይዳዊ መሆኑ የተወሳ ሲሆን በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አመራሮቹ መታሰራቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርቲው ጉዳዩን ወደ 33ቱ ፓርቲዎች በመውሰድ ተከታታይ ትግል እንደሚያደርግም የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሮን ዮሴፍ በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ተናግረዋል፡፡
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ በርካታ ዜጎች ግራዚያኒ ለኢህአዴግ ምኑ ነው በማለት ሲጠይቁ ተስተውሏል፡፡ “መንግስት ይህን ሰልፍ ማስተባበር ሲኖርበት ጭራሽ ተሳታፊዎቹን ማሰሩ ፀረ ኢትዮጵያ አስተሳሰቡን ያጋለጠ መሆኑን ያመላክታል” የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
የሰልፉ አስተባባሪዎች ከአስር ቀናት በፊት ለአዲስ አበባ መስተዳድር የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ ሰጪ ጽ/ቤት ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
Source: http://www.fnotenetsanet.com/?p=3628