አነጋጋሪው የኮሮና በሽታ መድሀኒትና እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች ግድፈት – ሰርፀ ደስታ

/

ተስፋ የተጣለባቸው የኮረና መድሀኒቶች፡፡  በአሁኑ ሰዓት ወደ 24 የሚሆኑ ከዚህ በፊት ለሌላ በሽታ ማከሚያነት የዋሉ መድሀኒቶች የኮረናን ቫይረስ ለማከም እንደሚረዱ እየተነገረ ነው፡፡ በተለይ ግን በተከታታይ በላቦራቶሪና በበሽተኞች ላይ የተደረጉ ሙከራዎች እንደሚያሳዩት ለወባ መድሀኒትነት ለዘመናት ሲያገለግል የቆየው ክሎሮኪዊኒን ከሌሎች ነባር መድሀኒቶች ጋር ከፍተኛ የማዳን ሀይል እንዳለው ይጠቁማል፡፡ በዚህም የተነሳ ይመስላል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጨዋታውን የሚቀይር (ጌም ቼንጀር) ሲሉት ለበሽተኞችም ይሄው መድሀኒት ቢሰጣቸው እንደሚፈልጉ በይፋ የተናገሩት፡፡ ሆኖም ከባለሙያዎች ድጋፍ ያገኙ አይመስልም፡፡ የሳይንሳዊ ጥናቶች በግልጽ ከሚያሳዩት የዚሁ የወባ መድሀኒት በኮሮና በሽታ ላይ ያለውን ውጤታማነት በተቃራኒ ብዙ ሚዲያዎች ስለዚህ መድሀኒት አደገኝነትና በአንዳንድ ቦታዎች እንደውም ሰዎች ተጠቅመው እንደሞቱ ሳይቀር እየዘገቡ ነው፡፡ እኔ የሳይንሳዊ ጥናት ውጤቶቹ አሳማኝ እንደሆኑ ብዙም ጥርጥር የለኝም፡፡ ችግሩ ምን አልባት በአንዳንድ ሰዎች ላይ መድሀኒቱ ሌላ የጎንዮሽ ጉዳት ካለው አላውቅም፡፡ ሆኖም ይሄ መድሀኒት ለሰዎች ለብዙ ዓመታት ሲሰጥ የነበረ ስለሆነ ምን የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ በሚዲያዎች እየተዘገበ ያለው ጉዳት ግን ምንጩ ምን እንደሆነ ግልጽ አደለም፡፡ ሞቱ የተባሉ ሰዎች በመድሀኒቱ የአጠቃቀም ስህተት ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ማንኛውንም ነገር ያለልክ ከተጠቀሙት መርዝ ሊሆን ይችላልና እንኳንስ መድሀኒት፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ይሄን የወባ መድሀኒት ከሌሎች ጋር በማድረግ ቻይናዎች እንደተጠቀሙበትና ብዙ ውጤት እንደዩበት ከሌሎች መረጃዎች እየሰማን ነው፡፡ ምን አልባትም ከተያዘው ሰው እንጻር በቻያና ትንሽ ሰው ለመሞቱ ምክነያት እንዲህ ያሉ አማራጮችን መጠቀማቸው ነው፡፡ የሳይናዊ ጥናቶቹ ይሄን ተከትለው የተሰሩና በትክክልም ይህ የወባ መዳሕኒት የኮሮናን በሽታ ለማከም ትልቅ አቅም እንዳለው አሳይተዋል፡፡ በመሆኑም የአገሬ የሕክምና ባለሙያዎች በኮረና ምክነያት ለአደጋ የደረሰን በሽተኛ ለማከም እንደ አንድ አማራጭ ቢያስቡት እላለሁ፡፡ በየሚዲያው የሚወሩ ወሬዎች ከሳይንሳዊ ጥናቶቹና በትክክልም ብዙ እንደረዳቸው ከሚናገሩት የቻይና የሕክምና ባለሙያዎች የተግባር ውጤት ጋር የማይሄድ ነው፡፡ ስለዚህ በመረጃ ባልተደገፉ የሚዲያ ወሬዎች መዘናጋቱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ሆኖም አጠቃቀሙን በጥንቃቄ ማድረግና በጥናቶቹ የተመለከቱትን አግባቦች መከተል ያስፈልጋል ከዚህ በታች ገና በመታተም ላይ ያለውን የፈረንሳይ ተመራማሪዎች ያሳዩትን ውጤት ተመልከቱ፡፡ በድጋሜ ማሳሰብ የምፈልገው ግን ይሄ ውጤት የሚያሳየው በተመረጡ በሽተኞች በመሆኑ ለሁሉም ተመሳሳይ ላይሆን ስለሚችል በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ መፍትሄ በሌለበት እንደ አማራጭ ግን ባለሙያዎች ቢመለከቱት መልካም ነው፡፡ ምስሉን እንደምታዩት ጥቁሩ ምንም መድሀኒት ያልተሰጣቸው ሲሆነ ሰማያዊው የወባ መድሀኒት ብቻ አረንጓዴው ደግሞ የወባ መድሀኒቱ ከሌላ መድሀኒት ጋር በመደባለቅ የተሰጠ ነው፡፡ በግልጽ 㙀ንደሚታየው በተለይ የሁለቱ መድሀኒቶች ድብልቅ በፍጥነት በሽታውን ከሰውነት ሲያጠፋው ነው፡፡ እዚህ ላይ እንደሚታየው በአምስተኛው ቀን ጠፍቶ ነው፡፡ ሌሎቹ በተለይ ምንም መድሀኒት ያልወሰዱት ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅባቸው አመላካች ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  መከላከያ መኮንኖች አሻጥር ሰርተውብኛል ግደሉልኝ | 2 ፓትሮል፣ 1 ኦራል ወደመ"| አብይ ያልተጠበቀ ሹም ሽር ሰጠ

https://www.sciencedirect.com/science/article/pii/S0924857920300996?via%3Dihub

ወሳኝ ምክር ለኢትዮጵያውያን የተሳሳተ መረጃ በብዛት እየተላለፈ ይመስላልና

  1. በየኔታ ሚዲያ የቀረቡት የምግብ ተመራማሪ፡ የምግብ ተመራማሪ የተባሉት በሥም አለሙ መኮንን ተብለው የተጠቀሱት ሰው ኮረናን አስመልክቶ መድሀኒት የሚሆን ፎርሙላ አለኝ ያሉት ትክክለኛ መረጃ አይመስለኝም፡፡ እኔ በባሕል ሕክምናዎች አምናለሁ፡፡ ከለይ ለኮሮና ቫይረስ መድሀኒትነት በሳይንስ ጥናት እየተደረገባቸው ካሉ 24 ተስፋ ሰጭ መድሀኒቶች ውስጥ አንዱ የቻይና የባሕል መድሀኒት ነው፡፡ ከዛም በላይ ዛሬ ለኮረና መድሀኒትነት እጩ ሆኖ የቀረበው የወባ መድሀኒቱ ክሎሮኪዊን ራሱ መነሻዋው የባሕል መድሀኒት የሆነውና በደቡብ አሜሪካ የሚበቅሉ ሲንኮና (Cinchona) የተባሉ የዛፎች ዝርያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዛፎች በቅርፊታቸው ስር ኩዊኒን የተባለ ንጥረነገር ያመነጫሉ፡፡ ይሄ ንጥረ ነገር ነው በቀጥታ ለወባ መዳህኒትነት የሚውለው፡፡ በአገራችን የመድሀኒት እንክብል ሁሉ ኪኒን በመባል ይታወቃል፡፡ የዚህ ሥም አጠራር መነሻው ይሄው ኩዊኒን የተባለው መድሀኒት እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ እጠቁማለሁ፡፡ በየኔታ ቀርበው የሚናገሩት ተመራማሪ ነኝ ያሉት ሰው የተናገሯቸው መረጃዎች ብዙ ግድፈቶች አይቼባቸዋለሁ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ስለቫይረስ ያላቸው አረዳድ ስህተት እንደሆነ ነው፡፡ ቫይረስ አይመገብም፡፡ እጃችንን የምንታጠበው ባይረሱ የሚመገበው ነገር እንዲያጣ ሳይሆን ቫይረሱን ከላያችን ላይ ለማጠብ ወይም በሳሙና ኬሚካሎች ለመደምሰስ ነው፡፡ በመሠረቱ ቫይረስ ከሕይወት ካለው ነገርም አይመደብም፡፡ ባይረስ በራሱ አይባዛም፡፡ ወደ ሰውነት በመግባት የሰውን መለዘር በመጠቀም የሚባዛ ነው፡፡ ሆኖም የራሱን መለዘር መሸፈኛ ይሰራል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አይመገብም በራሱም አይራባም፡፡ ለዛም ነው ሕይወት ካለው ነገር የማይቆጠረው፡፡ ሌላው የኮረናን ቫይረስ ለመከላለከል ፎርሙላው አለኝ ያሉትም ስህተት ነው፡፡ ኮሮና የተያዘ ሰው ላይ ሞክረውት ያላረጋገጡትን ነገር በዚህ ደረጃ መናገር ትክክል አደለም፡፡ እርግጥ ነው ፌጦ በሉት ለላ ድብልቅ ጉንፋንን ጨምሮ ለሌሎች መድሀኒትነት ይውላሉ፡፡ የኮሮና 19 ቫይረስ ሌላ ጉንፋን ከሚያመጡ የኮሮና ቫይረሶች ጋር ተመሳሳይነት ስላላቸው ተመሳሳይ መድሀኒት ሊሰራ ይችላል፡፡ ችግሩ በአልተሞከረ ነገር አላስፈላጊ የሆነ መረጃ መስጠቱ ላይና በሚዲያ ሳይቀር መተላለፉ ነው፡፡ ሰውዬው የሚያቁትን ያህል ብቻ ከመናገር በቀር ሌላውን ጉዳይ ባይናገሩ ጥሩ ነው፡፡ መዘናጋትን ይፈጥራልና
  2. በአሜሪካን አገር በነርስነት ስታገለግል በቫይረሱ የተያዘች እህት ቪዲዮ፡- በእኔ እይታ ይሄ በብዛት ሰዎች እየተቀባበሉ እያስተላለሰፉት ያለው ቪዲዮ ሀሰት ነው፡፡ ሲጀምር ልጅቱ ምንም አይነት ሳል ኖሮባት ሳይሆን እያስመሰለች እንደሆነ ማስተዋል ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ሲቀጥል የኮረና ቫይረስ እሷ እንደምታሳይን አይነት እንዲህ የቀልድ የሚመስል ሳይሆን ብዙዎች ከአደገኝነቱ የተነሳ እየተጎዱበት ያለ ደረቅ ሳል የሚያመጣ ከዚህ በፊት ከነበሩት ጉንፋኖች ሁሉ የከፋ የተባለ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ልጅቱ እንኳንስ በጤና ባለሙያነት በአሜሪካን አገር የምትሰራ አሜሪካን አገርን ከእነጭርሱ የምታውቀው አይመስልም፡፡ ይሄን ያልኩት አሁንም የለበጣ የሚመስለውን አሳሳል በመመልከት ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ በተለይ ከ2008/9 የስዋይን ፍሉ በኋላ ሁሉም ሰው ሲስል ወይም ሲያስነጥስ አፉን በክንዱ መሸፈን እንደ ባሕል ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ደግሞ አይሳሳቱም፡፡ ስለዚህ ይሄ የተሳሳተ መረጃ ሊሆን ስለሚችልና ተመሳሳይ ቪዲዮዎችም ተመልካች ለማግኘት ሲባል ብቻ ሊሰሩ እንደሚችሉ ተመለክቾች አውቀው ከአላስፈላጊ መረጃ እንዲቆጠቡ፡፡ መልዕክቱ ትክክለኛ አለመሆኑ ከማዘናጋትም በላይ ለሌሎች መሰል የተሳሳቱ መረጃዎች በር የሚከፍት ነው፡፡ የዚችንው ልጅ ቪዲዮ ዛሬ ደግሞ ጸልዩልኝ ብላለች በሚል በሰፊው እየተሰራጨ ነው፡፡ ሰዎች በእንደነዚህ ያሉ ስህተት መረጃዎች ተጠምደው ትክክለኛ መረጃ ባለማግኘት መደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ላያደርጉም ይችላሉና
  3. አካብዳለሁ፡ ይሄ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ነገሮችን ለማናናቅ የሚሞክሩ በበዙበት ጥሩ ኃይለቃል (ሞቶ) ነው፡፡ ወድጄዋለሁ፡፡ ሆኖም ከመጠን በላይ እንዳይከር አሰጋለሁ፡፡ ሌሎችም አላስፈላጊ ፍራቻን ሊያመጡ የሚችሉ መልዕክቶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ አካብዳለሁ የሚለው ሞቶ ከመጠንቀቅ አኳያ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም አላስፈላጊ ፍራቻን እንዳያሳድር መጠንቀቅም ያሻል፡፡ ችግሩ ጥንቃቄያችንን ሁሉ አልፎ ከመጣ ለመጋፈጥም መዘጋጀት መልካም ነውና፡፡ እንደዛ ሲሆን መረዳዳቱና ብዙ አደጋዎችን ማስቀረት ይቻላልና ነው፡፡ በጣሊያን ከሚጠቀሱ ስህተቶች አንዱ ኮረና በአካባቢያችሁ ገባ ሲባሉ ብዙ ሰዎች ከመፍራታቸው የተነሳ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው ወደሌላ መሸሻቸው ሆኖም ሳያቁት ራሳቸው ቫይረሱን ይዘው ለጤናማው አካባቢ በማዛመታቸው ነው ይባላል፡፡ በጥንቃቄና በተረጋጋ ሁኔታ መንቀሳቀሱ ከምንም በላይ የዚህን በሽታ ለመከላከል ይረዳል፡፡ በተቻለ መጠን ርቀትን መጠበቅ ዋናው ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ተደርጎም አደጋው ቢመጣ የመሠራጨት ፍጥነቱን መግታት ዋና ሥልት ነው፡፡ አለበለዚያ ሁሉም በአንዴ ከተያዘ ከተያዙት ብዙ ሕክምና ወይም ሌላ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው በአንዴ መርዳት ስለማይቻል ብቻ ብዙ ሰው ሊጎዳ ይችላል፡፡ ይሄ ነው በጣሊያን የሆነው፡፡ ብዙ በሕክምና ወይም በሌሎች ሰዎች እርዳታ ሊድኑ የሚችሉ ሰዎችን ነው ጣሊያን አሁን ደግሞ ስፔን ሌሎችም እያጡ ያሉት፡፡ ስለዚህ ርቀትን መጠበቅ አስፈላጊየሆኑ ጥንቃቄዎችን ማድረግ የበሽታውን የስርጭት ፍጥነት ለመግታት ወሳኝ ናቸው፡፡ ቀስ እያለ ከሆነ ግን የአገሪቱ ሰው በሙሉ ቢያዝ እንኳን የሚያመጣው አደጋ ቀላል ነው፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  ህዝባዊ ዉይይት በሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነት እና በህዝቦቿ ላይ ያንዧበቡ አደጋዎችና፤ መንስኤዎቻቸው፤ እንዲሁም መፍትሄዎች ላይ ዋሽንግተን ዲሲ

በአጠቃላይ በለሙያዎች ለከፋ አደጋ የተጋለጡ በሽተኞችን ይረዳሉ የተባሉ መድሀኒቶችን በተቻላቸው ጥንቃቄ እንዲሰጡ፣ ሕዝብ በትክክል የሚሰጡ መረጃዎችን በመከተል አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርግ፣ አላስፈላጊ ፍራቻን እንዲያስወግድ (ማቃለል ግን አደለም)፣ ትክልለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን ከመከተል እንዲቆጠብ እላለሁ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ምህረቱን ለዓለም ሁሉ ያውርድ! አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! አሜን

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share