የካቲት 9፣ 2012
እቴጌ ጠሐይቱ አዲስ አበባ የሚለውን ስያሜ እንደሰጧት የሚነገርላት ከተማ ሁልጊዜ እንዳበበች፤ መዓዛዋም እንዳወደን ይገኛል። ሊአጠፏት ሴራ ሲሸረቡ፤ ሰላሟንና ፍቅሯን ሊነሷት ቢዶልቱባትም ታሪክ እየሰራች ከመጓዝ ግን አልቦዘነችም።
አዲስ አበባ የሁላችን ከተማ፤ የአፍሪካና የዓለም መዲና በመሆኗ በቀላሉ አትጠፋም። ከተማዋ የተቆረቆረችውና የተመሰረተችው በጠንካራ ኢትዮጵያዊ አርበኞች፤ ምሁራን፤ መሐንዲሶች፤ ሐኪሞች፤ አርቲስቶች፤ የሕግ ባለሙያዎች፤ የእምነት አባቶች፤ ነጋዴዎችና ፖለቲከኞች ነው። መስራቾቿን ወልዳ፤ በየፈርጁ አስተምራና አሳድጋ አቋቁማለች፤ ለወግ ለመአረግ አብቅታለች። ልጆቿ ከአስራ አራቱም ክፍለ ሃገራት ወይም ጠቅላይ ግዛትና ከሌሎች ዓለማት ጭምር መጥተው የተማሩባት፤ የነገዱባት፤ የሰሩባት፤ የበለጸጉባት፤ ትዳር የመሰረቱባት የሁሉም ከተማ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል።
መሐሙድ አሕመድ አዲስ አበባ ቤቴ ብሎ ያንጎራጎረላት፤ ቲወድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) የመሰለ አዲስ ትውልድ ከያኒ ያፈራች የግብረገብ ከተማ ነች። በዚህና መሰል በሐሪዋ አዲስ አበባ እንደ ኒዮርክ፤ ሎንዶን፤ ናይሮቢ፤ ቶሮንቶ፤ ዋሽንግቶን ወዘተ ሁለገብ ከተማነቷን (Cosmopolitan City) መካድ ከቶ አይቻልም።
አዲስ አበባ ፍቅር እንጂ ዘር፤ ጎሳ፤ ቀለምና ጎጥ አታውቅም። ከአብሮነት ውጪ የመነጣጠል ትርክት አይገባትም። ይህንም ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2012 በቴዲ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ነዋሪዎች በአንድ ድምፅ መስክረዋል። ነዋሪዎቿ የሚአውቁት ሶስት ቀለማትን ማለት አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሲሆን ዘሯም ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
በከተማዋ ተወልዶ ያደገው የኪነት ባለሙያ ቴዲ አፍሮ ታሪክ የተመራመረ፤ ለሕዝብና ለሃገር አንድነት የቆመ፤ የተሟገተ፤ የዘመረ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጅና ከያኔ ነው። ኢትዮጵያንና ታሪኳን ፤ፍቅርንና ሰላምን ሲአዜም ኖሯል። በመረዋ ድምጹ ኢትዮጵያን በፍቅር ይዞ ሊጓዛ የተነሳ የልጅ አዋቂ፤ አስተማሪና ሰባኪም ነው። የመልካም ስነምግባሩና የኪነት ውጤቱ የሆነውን ‘ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ’ የተሰኘውን የሙዚቃ ውጤቶች ለህዝብ ለማቅረብ ለአያሌ ዓመታት ሲባዝን ኖሯል። ብዙ ጊዜ ሞክሮ ሳይሳካለት ቆይቷል።
የፍቅር ጉዞ መልዕክቱን ለሕዝብ እንዳያቀርብ ሲከለክሉ የቆዩ የኢሕአዴግና ሕወሃት ባለስልጣናት አንገላተውታል። ሕዝቡም ፍቀዱለት እያለ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሲጠይቅና ጫና ሲአደርግ ሃያ ዓመት በምጥ ኖሯል። ዛሬ ቴዲ ተከልክሎ የነበረው ተፈቅዶ የፍቅር ጉዞ ኮንሰርቱንና የሙዚቃ ቅኝቱን ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2012 ለሕዝብ አሳይቷል። የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል እንዲሉ ትእግስትም ፍቅርን ወለደች። አዲስ አበባና ኢትዮጵያም እንኳን ደስያላችሁ። በኮንሰርቱ ኢትዮጵያዊነትና ሰባዊ ፍቅር ነግሰው አምሽተዋል።
የኢትዮጵያና የዓለም ማህበረሰብ ለዓመታት ሲአምጥ የኖረውን ከባድ ምጥ በኮንሰርቱ ተገላግሏል። ምጡ በቀዶ ጥገና ሳይሆን በተፈትሮ ሕግ ፆታ የሌለው፤ በልብ ቅርጽና በቀይ አበባ የሚመሰለው ሁሉን የሚአስማማ ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት የተባሉ መንታ ልጆችን ወልደው ተገላግለዋል። መልካም ልደት።
በመጨረሻም 150, 000 ሕዝብ በመስቀል አደባባይ በፍቅር ሲታደም ያለኮሽታ፤ ሕይውት ሳይጠፋ፤ ንብረት ሳይወድም የቴዲ መርሃ ግብር በሰላም እንዲጠናቀቅ በማድረጋችሁ ለአዲስ አበባ ሕዝብና ወጣቶች አክብሮታችን የላቀ ነው። የፍቅርና የሰላም ከተማ መሆኗን ስላስመሰከራችሁ በድጋሜ እንኳን ደስያላችሁ፤ ደስያለን። ቴዲም በሕዝብ መወደድና በፍቅር መጓዝ ያለውን ጥቅም ስላሳየኸን እግዚአብሔር እደሜና ጤና ይስጥህ-ኑርልን።
የሁሉም ሙዚቃዎችህ ሱሰኛና የባህር ማዶ አድናቂህ፤
ሰማነህ ጀመረ፤ ካናዳ