አባይ…አባይ፤ የታላቁ የአባይ ግድብ እና የድርድር ውጣ ውረድ

የካቲት 15 2012

መግቢያ:

የአባይ ወንዝ ግድብን ብሎም የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ኢትዮጵያ በተለያየ ወቅትና መድረክ አቋሟን ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ብትሞክርም አሁንም ቢሆን ብሄራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንድትሰጥና የሌሎች ወገኖች መጠቀሚያ እንድትሆን ግፊት ሲደርስባት እናስተውላለን። በመሆኑም ለረጅም አመታት በጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤቶች የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በተወካዮቻቸው መንግስታት መካከል የሶስትዮች ድርድሮችና ስምምነቶችን ለማከናወን ጥረት አድርገዋል። በመሰረቱ ሶስቱም ሃገራትና መንግስቶቻቸው የሃገራቸውን ጥቅም የሚያራምድላቸው አቋም ማራመዳቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ሁሉንም ሃገራት በሚጠቅምና የጋራ ጥቅማቸውን የሚያዳብር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለዘላቂ ግንኙነታቸውም ሆነ ሰላማቸው ወሳኝ መሆኑን መገንዘባቸው የግድ ነው። ይህ መሰረታዊ አቋም ግን በቅርቡ በሚካሄዱ ድርድሮች ላይ ከመታየት ይልቅ በየሰበቡ የስራ መጓተትና መተማመን እንዲሸረሸር የሚያድርጉ ክስተቶችን መገንዘብ ችለናል። በመሆኑም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በወቅቱ በስልጣን ላይ ለአለው መንግስት የሚከተለውን ሃሳባችንን በግልፅ ማሳወቅ እንፈልጋለን።

የአባይ ወንዝ ግድብ አጀማመርና ትግበራ

        የአባይ ግድብ እንዲገደብና ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም እንዲውል ያለው ፍላጎት ዘመን ያስቆጠረና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የሚነካና ድጋፍ የሚቸረው ሃገራዊ ጉዳይ ቢሆንም ሃሳቡ ከፍላጎት ተሻግሮ የዕቅድ ጥናት የተሰራለት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ነበር። የአባይን ወንዝ ውሃ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠርና የመጠቀም ፍላጎት የተነሳ ግብፅ በከፊልም ሱዳን ለዘመናት የኢትዮጵያን ሃሳብ በመቃወማቸውና በተቻላቸው መድረኮች ሁሉ ተፅዕኖና አንዳንዴም የሃይል ማስፈራራት ውስጥ እስከ መግባት ደርሰው ነበር። ከዚህም ባሻገር የአባይ ወንዝን መገደብና ለጥቅም ለማብቃት ብዙ ገንዘብና ዕውቀት የሚጠይቅ ግዙፍ ፕሮጀክት በመሆኑ የተነሳና በወቅቱ ግድብ ለመገደብ የሚያበቃ ኢኮኖሚያዊ አቅም ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ጥቅሟን ማስጠበቅ ፍላጎቱ ቢኖራትም እንኳን በተግባር ለመተርጎም የሚያስችላት የኢኮኖሚና የምህንድስና አቅም አልነበራትም። ስራውን በውጪ ብድርና የቴክኒክ ድጋፍ ለማከናወን ቢሞከርም ብድር የሚያበድሩ ድርጅቶችም ሆኑ ሃገራት አሻፈረኝ በማለታቸው አባይ የሃገሬውን ልጆች ርሃብና ድህነት ሳይፈታ የግብፆች ሲሳይ ሆኖ ቀርቷል።

የአፄው ስርዓት ከወደቀና በደርግ ስርዓት ከተተካም በኋላ በመንግስቱ ኃይለማሪያም መንግሥት ዘመንም የአባይ ወንዝ ሰፊ ጥናት ተደርጎበት እንደ ነበር እና በተመሳሳይ በገንዘብ እጥረትና የውስጥ ብጥብጥ ምክንያት ሳይገነባ በእቅድ ላይ መቅረቱን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ በመጨረሻም የደርግን ስርዓት በመጣል ስልጣኑን የተረከበው የኢህአዴግ መንግሥት የውጪውንም የውስጡንም ጫና በመቋቋም፤ የገንዘብ ዕጥረት የሚፈጥረውን ችግርንም ለመቋቋም በራስ በጀት ለመሸፈን በማሰብ፤ የአባይ ወንዝ ግድብ ለማስጀመር አጋጣሚ ግዜና ሁኔታን በመጠቀም አስጀምሮታል። ኢህአዴግ አባይን ሊገድብ ስራውን ሲያስጀምር ምስጢራዊ አሰራሩ የማንንም ፍቃድም ሆነ ዕርዳታ አልጠየቀም፣ በራሱና በህዝቡ ተሳትፎ እገነባዋለሁ ብሎ ነበር ወደ ግድብ ትግበራው የገባው። ይህንን በማድረጉ ስርዓቱን ከሚቃወሙት ኢትዮጵያውያን ሳይቀር ድጋፍ አግኝቷል። ኢህአዴግ አባይን መገደብ አለብን ብሎ ሲወስን የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ግድቡን የጀመረውም የሚጨርሰውም የግድቡ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነው በሚል እሳቤ ነበር፡፡ በመሆኑንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደአቅሙ ለግድቡ ማስፈፅሚያ የሚሆን መጠነ ሰፊ የገንዘብ ዕርዳታና የቦንድ ግዥ አድርጓል።

በዚህ መልኩ የተጀመረው ግድብ በተቀመጠለት የግዜና የወጪ ገደብ ፐሮጄክቱን ለማስኬድ ካለመቻሉና ከፍተኛ ብክነትና ምዝበራ በመፈፀሙ የተነሳ ስራው በወቅቱ ለመጠናቀቅ አልቻለም። ይልቁንም ኢህአድግ በደረሰንት ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ምክንያት የለውጥ እርምጃዎችን ለመውሰድ በመገደዱ ግድቡንም እንደታለመለት ሳይተገብር ዕዳውን ለለውጡ አመራሮች ለማሸጋገር ተገዷል።

የአባይን ግድብ ጉዳይ በአዲስ ሁኔታ መገምገም

በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት ወቅት ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ይህንን ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ያለውን የአባይ ወንዝ ግድብ በተመለከተ መጀመሪያ የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ሁኔታ መገምገም ይጠበቅበት ነበር። በዚህ ግምገማ ፍንትው ብሎ የታየው በታሪካችን ተፈፅሞ የማያውቅ ምዝበራና ድሃው ህዝብ ያዋጣውን ገንዘብ ብክነት አስከትሏል። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ከታለመለት አፈፃፀም አንፃር ሲታይ በጣም የዘገየ ከመሆኑም ባሻገር በሚስጥር በተከናወኑ የውል ክፍፍል ምክንያት ብዙ ተጨማሪ መጓተቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ግሃድ ወጥቷል። በመሆኑም መንግስት አፋጣኝና ወሳኝ እርምጃዎችን መውሰድ ነበረበት። ምን ያህል ከምዝበራ የተረፈ ንብረት እንዳለ በግልፅና አስተማማኝ የሂሳብ ምርመራ ውጤት ለህዝብ ይፋ ባይሆንም ከሞላ ጎደል የግድብ ስራው እንዲቀጥልና ዘግይቶም ቢሆን እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ሁኔታዎች ለመፍጠር እየተሞከረ ይገኛል። ይህንን ምዝበራና ብክነት በተመለከተ ሙሉ ምርመራና ተጠያቂነት የማይታለፍ ስራ ሲሆን በዋንኛነት ግን ግድቡንም ሆነ የሃይል ማመንጨት ስራውም በአፋጣኝ ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቡ ከተጨማሪ ወጨም ሆነ ከሚታጣው የገቢ ፍሰት ይታደጋልና የሁላችንንም ትኩረትና ድጋፍ አግኝቶ ሊፈፀም ይገባል እንላለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስሜቱ ይቁምና እስቲ አማራጮችን በእርጋታ እንመልከት - ግርማ ካሳ

የአባይ ግድብ ግንባታና ወደ መጠናቀቅ የሚያደርገው ዝግመታዊ ጉዞ ለግብፅ መንግስትና ደጋፊዎቹ የራስ ምታት ሆኖባቸዋል። አንዴ ለግድቡ ድጋፉን ሲሰጥ ሲቻለው ደግሞ ሲያስፈራራ ሁሉም አልሆንለት ሲለው ደግሞ በሌሎች መንግስታትና ተቋማት በኩል እጃችንን ለመጠምዘዝ ሲሞክር ይታያል። ለዚህ ማርከሻው ደግሞ ሳያወላዱና ሳይዘናጉ ግድቡን ማጠናቀቅና የሃይል ማመንጨት ስራውን ማስጀመር ነው። እርሙን ካወጣ በኋላ ምናልባትም ማሰናከሉት ትቶ ከጥቅሙ ለመቋደስ አይኑን በጨው ውሃ ታጥቦ ይመጣል። እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን ኢትዮጵያና ወክለዋት ለድርድር የሚቀመጡት ባለሙያዎቿ ከግንዛቤ ሊያስገቡት የሚገባ ጉዳዮች አሉ።

1ኛ.  የኢትዮጵያ መንግስት የህዝቡን አቅም አሰባስቦ ግድቡን ማጠናቀቅ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ተገንዝቦ ግድቡን ለማጠናቀቅ  እንደ የዓለም ባንክ ከመሳሰሉት የፋይናንስ ተቋማት ብድር ከመፈለግ ይልቅ አዲስ የዩሮ ቦንድ ለኢትዮጵያውን ለማቅረብ መሞከር ተመራጭ ይመስለናል። በመሰረቱ እነዚህ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮዽያን እጅ በመጠምዘዝ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር ፍላጎታቸውን በሐገራችን ላይ ለመጣል ፍላጎትም ግፊትም ያለባቸው ተቋማት ናቸው፡፡

2ኛ. ኢህአዴግ ጀምሮት የነበረው በቦንድ ግዥ፣ የመንግስት ሠራተኛው የወር ደሞዙን በዓመት ክፍያ በቦንድ ግዥ እንዲደግፍ የማድረግና ነጋዴው ገበሬው ባለሃብቱ የሚችለውን እንዲደግፍ ማድረግ የሚያስችለውን አሠራር ለመጀመሪያው አምስት አመታት ለመተግበር ቢሞከርም አሁን በአለበት መልኩ ማስቀጠል አይቻልም። በመሆኑም በቦንድ ሽያጭና በተሰበሰበው ገንዘብ የደረሰውን ምዝበራና ብክነት በአፋጣኝ የሂሳብ ምርመራ ተደርጎበት ውጤቱ ለህዝብ እንዲገለፅ እየጠየቅን በመቀጠልም በአዲስ መልክ የቦንድ ሽያጭን የሚያስተባብርና የሚመራ ገለልተኛ በባለሙያዎች የተደገፈ ተቋም በማደራጀት ተገቢውን ስራ እንዲያከናውን ማስቻል ያስፈልጋል።

3ኛ. የኢህዴግ መንግስት በአባይ ግድብ ላይ ይዞት የበረውን የሶስተኛ ወገን አደራዳሪ አለመቀበል ውሳኔ በመሻር ታዛቢ በሚል ያስገባቸው የአሜሪካ መንግሥት፣የዓለም ባንክና የመሳሰሉትን የገንዘብ ተቋማት ማካተቱ ታሪካዊ ስህተት በመሆኑ ተገቢውና ወቅታዊ ውሳኔ በመውሰድ ከሶስቱ ሃገራት መንግስታት ውጪ የሚኖሩ አደራዳሪዎችም ሆኑ ታዛቢዎች ጉዳይ እንደገና እንዲታይ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በታዛቢነት መሳተፍን አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ እንኳን መሳተፍ ያለባቸውን ተቋማት በብልሃት መገምገምና መጋበዝ አስፈላጊ ይመስለናል።

የአባ ግድብ እውነት ግብፅን ይጎዳል?

ታላቁ የአባይ ግድብ ጥናት እንደሚያሳየው ከገዳቢው ሐገር ባልተናነሰ ግድቡ በመሠራቱ ተጠቃሚው ግብፅና በተፋሰሱ ስር ያሉ ሃገራት መሆናቸውን ተደጋግሞ ተገልጿል። የግብፅ መንግስትም በተመሳሳይ በምሁራኖቹና  በሚዲያዎቻቸው የአባይ መገደብ ለታችኛው የተፋሰሱ ሃገሮች ያለው ፋይዳ የማያቋርጥ የውሃ ምንጭ ነው፣የአካባቢውን የአየር ፀባይ በቀጣይነት እንዲጠበቅ የሚያደርግና ለከፍተኛ የቱሪዝም እንዲሁም የኢኮኖሚ ምንጭነቱን ከኤሌክትሪክ ማመንጫነቱ በዘለለ ከፍተኛ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ታላቅ ግድብ መሆኑን ራሳቸውም ያረጋገጡትና እማኝነታቸውን የሰጡት ጉዳይ ነው።

የግብፆችን ጥቅም የማይጎዳና ጠቀሜታው ለእነሱም ከሆነ ለምን ተቃውሟቸውን በአንድ መልኩ ወይ በሌላው መቀጠል ፈለጉ የሚለውን ጉዳይ መመልከት ተገቢ ነው።

1ኛ. ግብፆች በእንግሊዞች የቅኝ ግዛት ዘመን የአባይን ውሃ በብቸንነት ለመጠቀም እንደ አምላክ ስጦታ በማየት የግሏ ማድረግ ፍላጎት አሁን በደረስንበት ዘመንም እንዲቀጥል መፈለግ ታላቅ ህልሟ ነው። በእርግጥም ግድቡ ባይገነባ እናም እንደ አለፈው ሁሉ የአባይን ውሃም ሆነ ወንዙን በተመለከተ ብቸኛ ውሳኔ ሰጭ መሆን ያምራቸዋል። ይህ መሰል አቋም በማራመዳቸው ሊገርመን አይገባም። የራሱን ሃብትና መብት አሳልፎ የሚሰጣቸው ሃገር እስካገኙ ድረስ በዚህ አቋማቸው ሊቀጥሉበት እንደሚችሉ መገንዘብ ብልህነት ነው።

2ኛ. አባይ መገደቡ በራሱ ለኢትዮዽያ ህዝብ ከፍተኛ እድገትን የሚያጎናፅፍ በመሆኑ ለጠቅላላ ለውጥ ወሳኝ ነው ብለው ያምናሉ። በመሆኑም የኢትዮዽያ እድገት እውን በሆነ ቁጥር ግብፆች በአባይ ወንዝ ላይ የነበራቸው ተጠቃሚነትም ሆነ በኋይል ሚዛን በሂደት ሊነጠቅ ስለሚችል የኢትዮዽያ እድገት መገደብ አለበት የሚል ድፍን የኢትዮዽያን በጋራ የመጠቀም መሰረታዊ ፍላጎት ያላገናዘበ ጭፍን አስተሳሰብ አሁንም መቀጠሉ ነው፡፡ ስለሆነም የፍትሃዊነትና የጋራ አብሮ የማደግ አቡጊዳ እንድትማር ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅና መብቷን በመከላከል ማሳየት ይኖርባታል።

3ኛ. በተፋሰሱ አካባቢ ውስጥ ያሉ ሃገሮች አብዛኛዎቹ የአባይ ተፋሰስ ውሃን አጠቃቀም በተመለከተ የጋራ ስምምነት መፈረማቸው ይታወቃል፡፡ በጣም ውስን የሁኑ ሃገሮች ደግሞ ያልፈረሙ አሉ፡፡ እነዚህን ሃገሮች እንዳይፈርሙ ከፍተኛ ጫና በማድረግ የኢትዮዽን የዲፕሎማሲ የሃይል ሚዛንም በከፍተኛ ደረጃ የመፈታተን ሥራዎች አጠናክራ መቀጠሏ ነው፡፡ ስለሆነም ለአሁኑም ይሁን ለወደፊቱ ይበጅ ዘንድ ኢትዮጵያ የሰፊው የአባይ ተፋሰስ ሐገራት ዘንድ ተፈላጊውን ዲፕሎማቲክ ስራዎችን አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለአማራ ህዝብ ታሪካዊ ጉዞ ጥናታዊ ፅሁፍ መነሻና መንደርደሪያ የሚሆን ግንዛቤ፣

4ኛ. ግብፅ ፍላጎቷን ለማሳካት እንደ አሜሪካና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ኃይሎችን በተለያዩ ሰበብ አስባብ እጃቸውን እንዲያስገቡ በማድረግ በኢትዮዽያ ላይ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ እንዲፈጠር ማድረግ ላይ ትኩረቷን ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በመሆኑም ኢትዮጵያም ቢሆን ይህንን ጫና መመከት የሚችልና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ለመስራት የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርባታል።

በሶስትዮሽ ድርድሩ የሱዳኖች ሚና ምን ሊሆን ችላል?

ሱዳን በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሥልታዊ አጋር ሐገር ናት። በሁሉም ዘርፍ ከኢትዮዽያ ጋር የተሳሰረ ለዘመናት የቆየ ግንኙነት እንዳላት ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አራት መሰረታዊ አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባች በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

1ኛ. በቅርቡ በህዝባዊ አመፅ ከስልጣኑ የወረደው መንግስት በዋነኛነት በግብፆች ድጋፍና እርዳታ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

2ኛ. በኢትዮዽያ ውስጥ ተፈጥሮ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ተመልሶ ወደ ሱዳንም እንዳይገባ እና በአልባሸር መንግስት የተፈፀመው ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይደገም ከፍተኛ ስጋት አለባት፡፡

3ኛ. በአሜሪካኖች ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ አለመነሳቱ እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚያቸውና ፖለቲካዊ እንቅስቀሴያቸው ላይ የፈጠረው ድቀት ቀላል ባለመሆኑ ከአሜሪካኖች ጋር ያላቸው የከረረ ሁኔታ እንዲረግብ ይፈልጋሉ፡፡

4ኛ. ሱዳን ከአረብ ሊግ ከሚባለው ስብስብ ከፍተኛ ጫና ይደርስባታል። ይህ ስብስብ ደግሞ የአባይን ግድብ ከመሰረቱ ሲቃወም የነበረና አሁንም በተቻለው አቅም ችግሮችን ለመፍጠር የሚዳክር ድርጅት ነው። በመሆኑም ሱዳን የአባይ ግድብ በጣም እንደሚጠቅማት ብትገነዘብም የድርድሩን ካርድ ተጠቅማ ሌሎች ችግሮቿን ለግዜውም ቢሆን ለመፍታት መሞከሯ አይቀሬ ነው።

እነዚህን ተግዳሮቶች እንደ መነሻ በመያዝ በአባይ ጉዳይ ላይ ከኢትዮዽያ ጎን መሰለፍ የሚያስከትለው መዘዝና ተግዳሮቶቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ በመሆኑ በመንሸራተት የግብፅን እና የአሜሪካንን አቋም የመደገፍ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ ይዳዳት ይሆናል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ሱዳን ያለባትን የውጪ ግፊትና ጫና በመገንዘብ እስከተቻለ ድረስ በአባይ ግድብ ላይ ያላትን የድጋፍ አቋም አጠናክራ እንድትቀጥል ማበረታታት ያስፈልጋል።

የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ብሎም በአደራዳሪነት የመግባት ፍላጎት ለምን?

የዓለም የገንዘብ ተቋማት ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የአሜሪካን ጉዳይ አስፈፃሚ እና የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያዎች ናቸው። በመሆኑም ሁለት ስም ይዘው ቢገቡም ያው የአሜሪካ መንግስት በሚል ጥቅል ስም ማየቱ ተገቢና ለእውነታው የቀረበ ይሆናል፡፡ የአሜሪካ መንግስት በታዛቢነት የመግባት ፍላጎት በመሰረቱ የቆየውን የግብፆች ጥያቄ ለመመለስ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። በቀደሙት የሶስትዮሽ ድርድሮች  ግብፆች ሶስተኛ አደራዳሪ አካል ይግባበት የሚል አቋም በመያዝ በኢትዮዽያ በኩል ደግሞ የለም ሶስተኛ ወገን የሚባል አናስገባም ስትል ሱዳኖች ደግሞ የኢትዮዽያን አቋም በመደገፍ ሲከራከሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ ግብፆች ይዘውት የነበረውን አቋም ማስፈፀም እንዲያስችላቸው ከአሜሪካን እና ከዓለም ባንክ ጋር በሰሩት  ሻጥር ታዛቢ በሚል ሰበብ እንዲገቡ እና ይህን ክፍተት ተጠቅመው ወደ አደራዳሪነት ሚና እንከመጫወት ብሎም ጫና የመፍጠርና  ማስገደድ የሚያስችል እርምጃም ሊወስዱ እንደሚችሉ  ሆን ተብሎ እየተሠራበት ይገኛል፡፡

አሜሪካኖች ከብሔራዊ ጥቅማቸው እንጂ ከእውነትና ፍትህ መቸውንም ቢሆን ቆመው አያውቁም። በተለይ ደግሞ ከኢትዮዽያ ጎን የቆሙበት ታሪካዊ አጋጣሚ ታይቶም አያውቅም። ይህ እየታወቀ በኢትዮጵያ መንግስት ለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በተለይም የአሜሪካ መንግስት እንደገለልተኛ ወገን ታዛቢ ሆኖ እንዲገባ መስማማቱ ከፍተኛ ስህተት ነው። አሜሪካኖች ከግብፆች ጋር የሚወግኑበት መሰረታዊ ጉዳይም የመካከለኛው ምስራቅ እና የአረቦችን የኋይል ሚዛን ከመጠበቅ አንፃር እንደ ሥልታዊ አጋር በመቁጠር ፖለቲካዊና የበጀት ድጋፍ፣ ዘመናዊ ወታደራዊ ትጥቆችን በማስታጠቅና እንዲሁም ለግብፅ ብሄራዊ ጥቅም መሰረታዊ የሆኑ እንደ አባይ ወንዝ ጉዳዮች ላይም መጠነ ሰፊ የዲፕሎማሲ እርዳታን በመስጠት ነው። በመሆኑም የአሜሪካ መንግስታት ለረጅም ዘመን ለግብፅ ያላቸውን የውጪ ፖሊሲ ለመተመለከተ መልሶ እንደ ገለልተኛ ዳኛ መጋበዝ የዋህነት ነው።

ምን ይሻላል? የኢትዮዽያ መሪዎችና ተደራዳሪዎች አሁንም ዜው አልመሸባችሁም

ተጨማሪ ያንብቡ:  የማይቀጡት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል - ይሄይስ አእምሮ

        በመሰረቱ የአባይን ግድብና የውሃውን አጠቃቀም በተመለከተ የሚደረገው ድርድር በሶስቱ ሃገራት እስር በርስ የመተማመን ብሎም የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅና ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ እስከተቻለ ድርስ አሁንም ቢሆን ድርድሩ መስመር እንዳይስትና የዘላለም የውዝግብና ሸፍጥ ምክንያት እንዳይሆን ለማድረግ የሚቻል ይመስለናል። ይህ ይሆን ዘንድ ግን የሚከተሉት ጉዳዮችን በጥሞና መመርመሩ ተገቢ ነው።

  1. በእኛ እምነት የኢትዮጵያ መንግስትም ይሁን በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ በራሱ ፍቃድ የአባይን ወንዝ ግድብም ሆነ የውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ብሔራዊ ምክክርና ስምምነት ሳይደረስበት መፈራረም አይኖርበትም። ባለቤት ነህ ተብሎ የአባይ ግድብ ግንባታው የተሳተፈው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በውሳኔው ላይ ይምከርበት፣ድምፁን ይስጥበት፣ ብሎም ውሳኔውን ይውሰድበት፡፡  ስለዚህ ተደራዳሪው ቡድን የህዝባችን ፍቃድ ስለሚያስፈልገን ጠብቁን ማለት ይገባዋል፡፡ ይህን ስንል የገንዘብ ክልከላውና ጫናዎች እንደ ቅድመ ሁኔታ መቅረባቸው እንደማይቀር አስበን ህዝባችንንም ማነቃነቅ ቀጣዩ ተግባር ሊሆን ይገባዋል እንላለን፡፡
  2. በሐገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙ ኢትዮዽያውያን ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ ዳያስፖራውና ይመለከተኛል የሚል ኢትዮጵያዊ በማስተባበርና በማሰባሰብ ሊደርስ ከሚችለው የውጪ ጫና ለመታደግ የራሱን ሚና እንዲጫወት ማስቻል ተገቢ ነው።
  3. በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርቶ የሚመጣ ግንኙነት ሲሆን ብቻ ተቀብሎ ማስተናገድ የመሪዎቻችን ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
  4. የህዳሴ ግድባችን መላው የኢትዮዽያ ህዝብ በድህነት እየኖረ ከሚያገኛት የእለት ጉርሱ ቀንሶ በማዋጣት የትላንቱን ሳይሆን የነገን ብሩህ ተስፋ በማየት እየገነባው ያለውን ግድብ በሰበብ አስባብ ለማስቆምም ይሁን ለማዘግየት እንዲሁም ኋይሉን እንዲቀንስ ለማድረግ የሚደረግን እንቅስቃሴ ማንኛውም የግድቡ ባለቤት የሆንክ አካል ሁሉ በንቃት መከታተል፣አላስፈላጊ ውሳኔዎችን በፅናት መቃወም፣ እስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ ማናቸውንም የትግል አካሄዶች በመከተል ታላቁ የህዳሴ ግድባችን በታሰበው ግብ እንዲደርስ ዘርፈ ብዙ ጥረት እንዲያደርግ ይገባል።
  5. ሃገራት የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን በሙሉ አቅማቸው ደግሞም ድንበር ተሻጋሪ ሃብታቸውን በጋራ የመጠቀም መብትና ሃላፊነት አለባቸው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ህዝባቸው በድህነትና በምግብ ዋስትና ችግር የሚንገላታባቸው ሃገራት ህዝባቸውን የመታደግ ተቀዳሚ ሃላፊነትም አለባቸው። ለምሳሌ በደቡባዊ ክፍለ አህጉራችን እንኳን ብንመለከት ሌሶቶ ለደቡብ አፍሪካ የውህ ሀብቷን ስታቀርብ በአሁኑ ጊዜ እንኳ በየዓመቱ ከ$50 ሚሊዮን በላይ ታስከፍላለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ የተፈጥሮ ሃብቷ የሆነውን የአባይን ውሃ ሁሉንም ተጠቃሚ ሃገራት በሚጠቅም መልኩና አብሮ የማደግ መርህን በመከተል ተገቢ ሲሆን ለዚህም የሚስማማ ስምምነት ላይ መድረስ ይገባታል። የሌሎች ሃገራትን ብሄራዊ ጥቅምን ሳይነካ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም የምታስጠብቅበትን ስምምነት ለመተግበር በርትቶ መስራት ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት ባለስልጣናትም ሆነ የባለሙያ ድጋፍ ሰጭ ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት ነው።
  6. በዕርግጥም የአባይ ግድብ የውሃ አሞላል ጉዳይ ግብፅንም ሆነ ሱዳንን ያሳስባቸዋል። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላትና በሙሉ አቅሙ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያመነጭ ለማስቻል የዝናብ ወራትን ጠብቃ የምታከናውነው በመሆኑ አዝጋሚ ስራ ነው። አሁን በግብፅ መንግስት በኩል የሚቀርበው ጥያቄ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ተጨማሪ ወጪ ከማስከፈልም አልፎ ከኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ ልታገኝ የሚገባትን ገቢ ያሳጣታል። በመሆኑም የውሃ አሞላልን በተመለከተ የተቀመጠውን ትንበያ በመመርኮዝ የሙሌት መጓተት የሚፈጥረውን ተጨማሪ ወጪና የሚታጣ ገቢ በማስላት ፍትሃዊ የሆነ ካሳ እንዲከፈላት ግብፅንም ሆነ ሱዳንን መጠየቅ ይኖርባታል። ይህንን ማድረጓ ፍትሃዊም ተገቢም ሲሆን ለስምምነትም ተጨማሪ ግብዓት ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ነው ብለን እናምናለን።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝም ሆነ ሁሉንም የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀምና ለልጆቿ ጥቅም የማዋል ሙሉ መብት ያላት መሆኑን የዓለም ህዝብ እንዲያውቀውና በዚህ መብቷ በፍፁም የማትደራደር መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ይገነዘበው ዘንድ በግልፅ ቋንቋ መንገር የሁላችንም ሃላፊነት ነው። በተለይም ሃገራችንን ወክለው በሁለትዮሽም ሆነ በዓለም አቀፍ ድርድሮች ላይ የሚወክሏት የመንግስት ባለስልጣናትም ይህንን እውነት ሳያመነቱና ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጡ የማስረዳት ከባድ ሃላፊነት አለባቸው። ይህንን መዘንጋትም ሆነ ብሔራዊ መብታችንን ለድርድር ማቅረብ በታሪክም ሆነ በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ተገንዝበው አቋማቸው የህዝብና የሃገር አደራን በአገናዘበ መልክ ይሆን ዘንድ በአፅንዖት እንጠይቃለን።

ኢትዮዽይ ለዘላለም ትኑር

እግዚሃብሄር አገራችንን ይባርክልን

ጉዳዮ በጣም ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን

አቶ ኪዳነ ዓለማየሁ
ፕ/ሮ አቡ ግርማ
ፕ/ሮ ሰይድ ሀሰን
ዶ/ር ጌታቸው ተመስገን
ዶ/ር አጀቡሽ አርጋው
ወ/ሮ ዳግማዊት ዓይንዓለም
ወ/ሮ ሳሊ መሀመድ
አቶ ብሩክ ታደሰ
ፕ/ሮ ማሞ ሙጪ

1 Comment

  1. አሜሪካ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የላትም የተባለው እውነት ነው፡፡ ለማንኛውም በኅብረት መቆማችን ጊዜው አሁን ነው!!! መከፋፈላችን እንደ ውሻ ርስበርስ መነካከሳችን፣ መጨቃጨቃችን ለጠላት በር እየከፈትን መሆኑን ነገሮች ካለፉ ዋጋ ካስከፈሉን በኃላ ብንገነዘበው አይጠቅምምና አብረን እንቁም፡፡ ግብፅ ታሪካዊ ጠላታችን ናት፡፡ የተዳከመች የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት ብሔራዊ ራዕይዋ ነው፡፡ ለዚህም በአገራችን ፖለቲካ እና እሰጥ እገባ ዋና ጠንሳሽ እና ተዋናይ መሆኗ ግልጥ ጉዳይ ነው፡፡
    አብዛኛው ፖለቲካዊ አካሄዳችን እና አጀንዳችን የሕዝባችንን ታሪክ ፣ ጥቅም፣ እና አብሮ የመኖር ባህል ያላገናዘበ መሆኑ ፖለቲካዊ መስመራችን አገር በቀል ሳይሆን ከውጭ የገባ (Imported politics) በመሆኑ እንዲሁ እንዳክራለን እንጂ ከችግራችን አያወጣንም፡፡ ስለዚህ የአገራችንን ሕዝብ ትስስር፣ ባህልና አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸርና ለማጥፋት የሚሯሯጡ ፖለቲከኞችን በቃችሁ አትበጁንም በማለት እንደ ሕዝብ ለብሔራዊ ጥቅማችን ቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት ብቸኛው አማራጫችን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share