የሲቃ መረዋ – ተስፋዬ ሁነኛው

/

ከተስፋዬ ሁነኛው /PhD
ኢንዲያናፕነስ ፥ ኢንድያና ፥ USA
317-833-5889

ካገሬ ወደ ሩሲያ ለትምህርት ከወጣሁ 31 ሞላ። በግዝጥና ማስተርስና በፖለቲናዊ ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪ እንደያዝሁ ወደ አሜሪካ ተሰደድሁ። አስተማሪ ነኝ። እማማ ፥የምወዳት እናቴ ድንገት በስትሮክ ተመትታ፥ ከሞጣ ወደ ባህርዳር ጥበበ ግዮን ሆስፒታል በአምቡላንስ ተወስዳ ሳለ የሞጣ መስጅዶች ተጠቁ። እማማ ግን ሳትነቃና ፅልመተ ዜናውን ሳትሰማ አርብ ለት አርፋለች። እስላሞች ለኛ ፈጥኖ ደራሽና አንኝታዎቻችን ናቸው፤ በነሱ ላይ የሚደርሰን ክፉ ነገር ሳታይ ለሞሞት ፈጣሪን ትማፀን እንደነበር አብሯት ሲኖር የነበረው ታናሸ ነገረኝ። አዝኛለሁና ለሞጣ ሙስሊሞች ያለኝን ፍቅርና ባለውለታነት ለመዘከር ይሕንን ግጥም ጽፌአለሁ። አቀናብራችሁ በዩቱብ ብታቀርቡልኝ ደስ ይለኛል። እኔም እናንተን እታዘዛለሁ።

ተባረኩ !!

ለእስትንፋሴ አልፋ፣
ለሕይወቴም ተስፋ፣
በመሆን ደግፋ፤

የኖረችው ውዴ፣
እናት ዓለም…ሆዴ፣
የልቤ ጉልላት… የሰው መሆን ዘውዴ።

የሞጣዋ እናቴ፣
ማርና ወተቴ።

ወረፋ ተቀምጣ፣
ደሜን ከደሟ… ቀድታ፣
አብልታ አጠጥታ፣
ጥራ ተንከራትታ፣
አሳድጋኛለች … እናቴ በሞጣ፤
በመልካም ሙስሊሞች … ቸርነት ተፅናንታ።

የበጎነት አምላክ፣
ጌታ ሁሉን የሚያውቅ፣
ያንን ቀን እንዳታይ… ሠወራት በስትሮክ፤
ሣልስት አስቀድሞ… ከሞጣ መታወክ።

በአረፋና ፈጥር … በመውሊድ የባተ፣
በካንቦና አዳሻ … ሁሉን ያካተተ፤
ወደ መስጊዳችን … የተመመው ሆታ፣
አላሕ ወታዕላ … የምስጋና ፌስታ፣
በሸረኛው ሰይጣን … ገና ሳይመታ፣
በሌሎች ያየነው … ሳይታይ በሞጣ፣
እናቴ ‘ኢትዮጵያ ሆነች’ … ከጸጸት አምልጣ።

ለትምህርት እንደወጣሁ … ከፍቶኝ ሳልመለስ፣
እናቴ ኢትዮጵያ ሆነች … ገና መስጊድ ሳይፈርስ።

መነኩሴዋ እናቴ … እንኳንም ያላየች፣
የወገኔ አሩቶች …
በዱቤ ያሳደጉኝ ሱቆች፣
ፈራርሰው ሲወድቁ … ባዳዲስ አውሬዎች፤
ዔሎሄ፥ ዔሎሄ ላማ ሰበቅታኒን … በሳግ ያላነባች፣
የሲቃ መረዋን … እንኳንም ያልሰማች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሮ-ትርያ - አስቻለው ከበደ አበበ _ሜትሮ ቫነኩቨር ካናዳ

 

Share