ይሁን እንጂ በእጁ ላይ ያለውን ማስላት መጭውን መገመት የተሳነው ወያኔ መራሹ ግትር መንግስት ተብየው የጥቂት ዘረኞች ቡድን ይህንም አድርጎ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ መድረሱን በማየቱ የትግል እሳቱ እጅግ የተቀጣጠለባትን የጎንደር ክ/ሀገር በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ስም ከሶስት በመቆራረጥ በልዩ ወታደራዊ ኮማንድ ሥር አስገብቶ ለመጨፍጨፍ ተዘጋጅቷል። ለዚህም ተጨማሪ ጉልበት ያገኝ ዘንድ ለዘለዓለም በማንነታቸው ይጠሩ የነበሩትን የቅማንት ማህበረሰብ “ቅማንት አይደላችሁም” ሲል ከኖረ በኋላ አሁን ደግሞ ከሆድቻው የገባ መሥሎት፤ በሰላም እና በውህደት እየኖሩ ካሉት ማህበረሰብ ጋር ለማዋጋት ሌላ የግዛት ቀጠና በስማቸው ሊመሰርት እየጎነጎነ ይገኛል።
አስገራሚው ነገር ግን፤ በወያኔ ጥርስ የሚያላምጠው በአማራው ስም የሚነግደው የብአዴን በድን ድርጅት “ቁሜልሃለሁ” ለሚለው ህዝብ እና “አስተዳድረዋለሁ” ለሚለው ክልል ሰላምና እጣ ፈንታ አንዳችም አይነት የኃላፊነት ስሜት አለማሳየቱ በአማራው ክልል ምንም አይነት ወሳኝነት የሌለው በአማራ ስም የተቀባ የወያኔ ሌላው ጥርቅም መሆኑን ስናማ ብንቆይም አሁን ግን በገሃድ ቁርጣችን ማወቃችን ነው።
ይህ በልማትና በመልካም አሥተዳደር ስም የአገሪቱን የግዛት ዞኖች እንደገና የማዋቀሩ ሂደት በጎንደር ብቻ የሚገደብ አይደለም። በቅርቡ ከጎንደር ቀጥሎ ሕዝባዊ ነውጡ እያሰጋው የመጣውን ደቡብ ኢትዮጵያን ጎጃም እና ወሎን በተመሳሳይ መልኩ እንደገና በዞን የመከፋፈል ሥራውን እያፋጠነ ይገኛል። ኢትዮጵያን በ39 አስተዳደራዊ ዞን የመበጣጠሱ እቅድ በቅርቡ የመጨረሻው የግባ ተመሬት ሙከራውን ፍፃሜ ላይ ለማድረስ ቀን ከሌት እየሰራ ይገኛል።
በአጠቃላይ ይህን ሁሉ አድርጎ ከሚመጣው ህዝባዊ ማዕበል ማምለጥ እንደማይችል የተረዳው ወያኔ በሁለት መንገድ አገራችን ጥፍቶ ለመጥፋት ስውር ደባውን ገኃድ እያደረገ ይገኛል።
1. በሌለና ባልተፈጠረ ምክንያት ባለበት ቆሞ የነበረውን የኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበር ችግር ወደ ጦርነት በማስገባት፤ በዘር የተከፋፈለውን የኢትዮጵያ ጦር ብትንትኑን አውጥቶ አገሪቱን ለባዕዳን ወራሪዎች አጋልጦ መሞት፤
2. በዘር ተደራጅተው ውስጥ ውስጡን እያደቡ ያሉ ከፋፋይ የጎሳ ድርጅቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው አገራችን ኢትዮጵያን ወደ እማይጠፋ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲዘፈቁ ማድረግና በዓለም ዙሪያ ያጣውን ተቀባይነት ለጊዜውም ቢሆን በማረጋጋት እና በሰላም ስም ትንሽ እድሜን ማግኙት የሚያስችሉትን ተንኮሎች መጎንጎን ነው።
ከዚህ በላይ የተጎነጎኑትን አጥፍቶ አጥፊ ተንኮሎች የበታች ካድሬውዎቹ ጭምር ጠንቅቀው በማዎቃቸው ምክንያት በልተው ለመጥፋት የአገሪቱን የገንዘብ አቅም በመሟጠጥ ላይ በመሆናቸው፤ በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር ሳያላምጡ እየዋጡ ካዝናዎቹን ሙሉ በሙሉ እያደረቋቸው ይገኛሉ። በዚህ ምክንያት በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ እያለቀ በመምጣቱ ህጋዊ ያልሆነ የወረቀት ገንዘብ በማሳተም በጎንደር እና በጎጃም ክ/ሀገሮች የአርሶ አደሩን መሳሪያ በግዥ ስም ለመግፈፍ ለአንድ መሳሪያ መቶ ሺ ብር በመመደብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ድብቅ ስልጡን የመሳሪያ ገዥ ቡድኖችን አሰልጥኖ በትኗል። ትጥቅህን ከትክሻህ ከወረቀት በተሰራ መቶ ሺ ብር ማስረከብ፤ ሚስትህን ከክንድህ አይንህ እያየ ለሌላ እንደመስጠት ያስቆጥራል።