(ዘ-ሐበሻ) ‘ኢትዮጵያ’ የተሰኘውን አዲሱን አልበሙን ለሕዝብ አቅርቦ ተወዳጅነቱን የጨመረው ቴዲ አፍሮ ለአዲሱ ዓመት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሊያደርገው የነበረው ኮንሰርት ፈቃድ እንደተከለከለ ተሰማ::
ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ዋዜማ በሚኒሊኒየም አዳራሽ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ ለነበረው ለዚሁ ኮንሰርት ቴዲ አፍሮ ፈቃድ ያስገባው ከሁለት ወር በፊት ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል ቆይቷል:: ቴዲ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ሊያደርጋቸው የነበሩ ኮንሰርቶች አስተዳደሩ በቂ ጥበቃ ኃይል የለኝም በሚል ምክንያት ሲከለክለው ቆይቷል::
የቴዲ አፍሮ ኮንሰርቶች ሲከለከሉ የሚሰጠው ምክንያት የጥበቃ ኃይል እጥረት ይሁን እንጂ ትክክለኛው ምክንያት ይህ አይደለም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር ያያዙታል::
በአዲስ አበባ ከተማ ሌሎች ድምጻውያን ካለምንም እክል ኮንሰርቶችን እንደሚሰሩ ይታወቃል::
ቴዲ አፍሮ ለአዲሱ ዓመት ኮንሰርት ባንዱን ከአሜሪካ አስገብቶ የአዲሱን አልበም ዘፈኖች ሲያጠኑ የቆዩ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች ከመጪው ሴፕቴምበር መጨረሻ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ እየተዟዟረ ሥራውን ያቀርባል ብለውናል:: አትላንታ ውስጥ የሚኖር አንድ ፕሮሞተር የቴዲ የሰሜን አሜሪካ ኮንሰርቶችን በአጠቃላይ እንደገዛቸው የዘ-ሐበሻ ምንጮች አረጋግጠዋል::