ክድምጻችን ይሰማ
ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ‹‹ድምጻችን ይሰማ በሁሉም ከተማ!›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ትዕይንተ ተቃውሞ ከተጠበቀው በላይ በስኬት ተጠናቋል፡፡ የዛሬው ተቃውሞ ስኬት እንደአዲስ ተቃውሞውን የተቀላቀሉ ከተሞች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ከተሞችም በቀጣዮቹ ተቃውሞዎች ለመሳተፍ ሙሉ ፍላጎት ያሳዩበት መሆኑም ጭምር ነው፡፡
– በጅጅጋ ቢላል መስጂድ የተደረገው የመጀመሪያው የዱዓ ተቃውሞ በስኬት ተጠናቋል፡፡ ሰላት እንደጠናቀቀም የመስጂዱ ኢማም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ አላህ እንዲያስቆምልን ከፍተኛ ዱዓ ማድረግ እንዳለብን አስታውሰዋል፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በተቃውሞው ላይ ተገኝትዋል፡፡
– የበደሌ ከተማ ሙስሊሞች ከጁምዓ ሰላት በኋላ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የመስጂዱ ኢማም የመጣብንን መከራ አላህ እንዲያነሳልን ቁኑት አድርገዋል፡፡ በተቃውሞው ላይ “በቤታችን ሰላም አጣን!”፣ “ኢቲቪ ውሸታም!” እና ሌሎችም መፈክሮች አሰምተዋል፡፡ ተቃውሞው በሰላም ተጠናቆ ሁሉም ወደየቤቱ ተመልሷል፡፡
– በአፋር ክልል አሳኢታና ዱብቲ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በተገኘበት የተደረገው የመጀመሪያው ተቃውሞ በስኬት ተጠናቋል፡፡ በርካታ ሙስሊሞች እጃቸውን ከፍ አድርገው የመጣብንን መከራ አላህ እንዲያነሳልን ዱዓ አድርገዋል፡፡ ሁላችንም በዱዓ እንበርታ የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
– በጎንደር ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የተገኘብት ታላቅ ተቃውሞ ተካሂዷል፡፡ በቀጣይም ተቃውሞውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
– በአጋሮ ከተማ የዝምታ ተቃውሞው በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡ የአልአዝሐር መስጂድ ኢማም ሸህ አብድልሐሚድ አህመድ ባለፈው ሳምንት ለሰሩት ስህተት በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በዱዓ የታጀበውን የዝምታ ተቃውሞ በይፋ ተቀላቅለዋል፡፡
– በአዲስ አበባ አንዋር መስጂድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የተገኘበት ታላቅ የተቃውሞ ሥነስርዐት በሰላም ተጠናቋል፡፡
– የባህርዳር ከተማ ሙስሊሞች በሠላም በር መስጅድ በብዛት በመገኘት በዱዓ የታጀበ የዝምታ ተቃውሞ አካሄደዋል፡፡
– በወልቂጤ ከተማ ጃሚዕ መስጂድ የተደረገው ከባድ የተቃውሞ ሥነስርዐት በሰላም ተጠናቀቀ፡፡ መስጂዱን ከበው የነበሩት አድማ በታኝ ፖሊሶች በህዝቡ ሰላማዊነት አዝነው እኩይ አላማቸው ሳይሳካ ወደመጡበት እየተመለሱ ነው፡፡
– በመቀሌ በካሊድ መስጂድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማው ነዋሪና እና የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን የዱአና የተቃውሞ መርሐ ግብሩ በሰላም እና በስኬት ተጠናቋል፡፡
– አፋር ሎጊያ ሀምዛ መስጂድ
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በተገኘበት የዱአ ፕሮግራሙም በሰላም ተጠናቋል፡፡ ትግሉን አጠናክረው ለመቀጠልም ቃል ገብተዋል፡፡
– በኮምቦልቻ ኻሊድ መስጊድ የተደረገው የዱአና የተቃውሞ መርሐ ግብር በሰላም እና በስኬት ተጠናቋል፡፡
– በድሬዳዋ ሰባተኛ ሰፈር መስጊድ ደማቅ ተቃውሞ ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡