የካቲት 21 2005
ቋጠሮ የተሰኘ ድህረ ገጽ ላይ የወጣ አንድ ቪዲዮ አየሁ። በሪያድ ሳዉዲ አረቢያ፣ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት፣ ኢትዮጵያውያንን ጠርተዉ፣ በአባይ ግድብ ዙሪያ ባነጋገሩበት ወቅት፣ የነበረዉን ሁኔታ የሚያሳይ ቪዲዮ ነዉ። «መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም»፣ «የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 27 ይከበር» የሚሉ መፈክሮች የተጻፉባቸዉ ነጭ ወረቀቶች ሲውለበለቡ ይታያሉ። ስብሰባዉ በጥሩ ሁኔታ የተካሄደ ፣ ለአባይ ግንባታም በቂ ገንዘብ የተሰበሰበ አይመስልም። [1]
የቋጠሮ ድህረ ይህንን ቪዲዮ እንደ ትልቅ አስደሳች ድል ነበር ያቀረበዉ። «ዘመቻ ጸረ-ቦንድ በድል ተጠናቀቀ» ይላል ቋጠሮ ለቪዴዮዉ የሰጠዉ አርእስት።
የፖለቲካ ልዩነቶቻችን ለአገራችን የሚጠቅመዉን እንዳናደርግ ማድረጉን ሳስብ አዘንኩ። በተለይም ደግሞ፣ በሳዉዲ አረቢያ፣ ለአባይ ግድብ ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ የተደረገው ጥረት፣ የተጠበቀዉን ዉጤት አለማስገኘቱ፣ ለኢትዮጵያ ቆመናል በሚሉ፣ እንደ ድል መቆጠሩ፣ ምን ያህል ፖለቲካችን የወረደ እንደሆነ የሚያሳይ ነዉ።
ግንቦት 3 ቀን 2003 ዓ.ም «የአባይን ግድብ መገንባት እንችላለን» በሚል ርእስ ለአንባቢያን ባቀረብኩት ጽሁፍ፣ ለአባይ ግንባታ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ዙሪያ፣ ከኢሕአዴግ ጎን መሰለፍ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደሚጠበቅ በመግለጽ ሃሳቤን አቅርቤ ነበር። «ኢሕአዴግ የሚያራምዳቸዉን ጠቃሚ ያልሆኑ ፖሊሶዎችን መቃወማችንን እየቀጠልን፣ በተለይም ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለዲሞክራሲ መስፈን የሚደረገዉን ትግል እያፋፋምን ፣ ገዢዉ ፓርቲ የሚያደርጋቸዉን የልማት እንቅስቃሴዎችንም መደገፍ የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም። ዴሞክራሲ ስለሌለ ልማት አትደግፉ ማለት ምግብ ስለሌለ ልብስ አትልበሱ ማለት ነዉ» በማለት የፖለቲካ ልዩነቶቻችን፣ ለአገራችን የሚጠቅሙ፣ በጋራ ልንሰራቸዉ የሚገቡ፣ ስራዎችን እንዳንሰራ ሊያግዱን እንደማይችሉ ሳልገልጽ አላለፍኩም።
ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት የነበሩ መንግስታት ያልሞከሩትን አገራዊ የአባይ ግድብ ግንባታ አጀንዳ ይዞ መነሳቱን አመስግኜ፣ ለግንባታዉ መሳካት ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ማሰባሰብ እንደሚገባዉም መክሬ ነበር። « የሕዝብ በአንድ ላይ መሰባሰብ አስፈላጊነቱን ኢሕአዴግ ተረድቶ፣ ዜጎች በኢሕአዴግ ላይ ካላቸዉ ቅሬታ አንጻር ከዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ፊታቸዉን እንዳያዞሩ፣ በተቻለ መጠን በሰብዓዊ መብትና በዲሞክራሲ ግንባታ አንጻር አስቸኳይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይኖርበታል። የፖለቲካ ተሃድሶ፣ ቁም ሳጥን ዉስጥ ተቆልፎበት ብዙ ወደፊት መሄድ የምንችል አይመስለኝም» [2]በማለት ፣ የእርቅ መንፈስ የሚወርድበትን ፣ መከባበር ፣ መቀባበልና አብሮ የመስራት ባህል የሚጠነክርበትን፣ የሰለጠነ ዘመናዊ ፖለቲካ የሚሰፍንበትን፣ እንዲሁም የዜጎች ሰብዓዊ መብት የሚከበርበትን ሁኔታ ኢሕአዴግ ማመቻቸት እንዳለበት አጠንክሬ ተማጽኛለሁ።
የአባይ ግድብ ግንባታ ተጀምሯል። መጀመር ማለት ግን መጨረስ ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ በወንዞቿ እንዳትጠቀም፣ ይህ ግድብ እንዳይገነባ የማይፈልጉ፣ ታሪካዊ ጠላቶች አሉን። በቅርቡ፣ ከአንድ አገር ከፍተኛ ባለስልጣን የማይጠበቅ ፣ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ጠብ-ጫሪ አስተያየት የሰጡትን፣ አንድ የሳዉዲ ጀነራልና ልኡል መጥቀሱ ይበቃል። [3]እኝህ ባለስልጣን ኢትዮጵያ የአባይን ግድብ የመገንባት መብት እንደሌላት ነዉ የተናገሩት። ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ነዉ ለኢትዮጵያ የሰጡት።
እኝህ የሳዉዲ ጀነራል የመንግስታቸውን አቋም ነዉ በይፋ የገለጹልን። ይሄም በግልጽ የሚያሳየዉ እንደ ሳዉዲ አረቢያ ያሉ፣ የአረብ አገሮች፣ በተቻለ መጠን፣ በመካከላችን ጠብና አለመግባባት እንዲፈጠርና ለአገራችን ጥቅም በጋራ እንዳንቆም በመዶለት፣ ያላቸውን የአለም አቀፍ ተጽእኖ በመጠቀም ከዉጭ ኃይላት በቂ እርዳታና ብድር እንዳናገኝ ግፊት በማድረግ፣ የአባይ ግድብ እንዳይገነባ፣ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
በመሆኑም ግድቡን በራሳችን አቅም መገንባቱ ብቸኛ አማራጭ ሆኗል። በዚህም ምክንያት ኢሕአዴግ በተደራጀ መልኩ ከፍተኛ የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ነገር ግን የአባይን ግድብ ወጪ በስፋት የመሸፈን አቅም ያለዉ ዳያስፖራው እንደሚጠበቀዉ አስተዋጾ እያደረገ እንዳልሆነ የዉጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጠቅሶ፣ ሪፖርተር ዘግቧል። «የሚኒስቴሩ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ከዳያስፖራው ለአገር ልማት ሊገኝ የሚችለውን የሀብት ፍሰትና የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥረቶች ቢደረጉም፣ እየተገኘ ያለው ግን ውስን ነው» ሲል የዘገበዉ ሪፖርተር፣ ለህዳሴው ግድብ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 3.04 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ገልጿል።
አባይን ለመገንባት ቢያንስ 4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። በዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ቢቆጠር ሁለት ሚሊዮን ይሆናል። በስድስት ወራት ሶስት ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ ማለት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በወር 25 ሳንቲም ብቻ ነው ለአባይ ያዋጣዉ እንደ ማለት ነዉ። ይሄ በጣም የሚያሳዝን፣ መሰረታዊ የሆነ መፍትሄ የሚያስፈልገዉ ጉዳይ ነዉ። እንዴት አገራዊ ለሆነ ፕሮጀክት በዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵጵያዊ በተገቢዉ ሁኔታ ሊሳተፍ አልቻለም ?
በወር ስሙኒ ከማዋጣት፣ በቀን አንድ ዶላር ብናዋጣ፣ ዳያስፖራ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ በስድስት ወራት 365 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ ይቻላል። ባለፉት ስድስት ወራት ከተሰበሰበዉ ሶስት መቶ እጥፍ ማለት ነዉ። ያለ ምንም ጥርጥር በኢትዮጵያዉያን ገንዘብ አባይን መገንባት አይደለም ሌላ ሌላም መስራት እንችላለን። እደግማለሁ በርግጥ እንችላለን። አቅሙ አለን። ችሎታዉ አለን። ችግሩ ያለዉ ፍላጎትና መተማመኑ ላይ ነዉ።
እንግዲህ ሁላችንም ፣ የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ሆንም ኢሕአዴግን እንቃወማለን የምንል፣ ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። በመካከላችን ባለዉ የከረረ ያለመቀባበል ፖለቲክ ምክንያት፣ አገራችንን እየጎዳን መሆናችንን ማስታወስ አለብን። እንዲህ ልንቀጥል አንችልም። ከሌሎች አገራት ዜጎች መማር አለብን።
ኢሕአዴግ «ልማት፣ ልማት» እያለ የሰብአዊ መብት መከበርን ወደ ጎን እያደረገ፣ የሚቃወሙትን እያሰራ፣ ሜዲያዎችን እያፈነና የፖለቲካ ነጻነትን እየገደበ፣ ብዙ ዜጎችን እየገፋ ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተለይም በዉጭ ያሉ ተቃዋሚዎች ነን የሚሉ፣ «ዴሞክራሲ የለም» በሚል፣ ልማትን በጭፍን ይቃወማሉ። ለልማት የሚደረግን እንቅስቃሴ ማክሸፍን እንደ ጀግንነት ይቆጥራሉ። ይህ አይነቱ አካሄድ መቆም አለበት።
በዚህም መንፈስ እንግዲህ ለሁሉም ወገኖች ይጠቅማል ብዬ የማስባቸዉን ምክር አዘል የመፍትሄ ሃሳቦችን በአክብሮት በትህትና እንደሚከትለው አቀርባለሁ።
ለኢሕአዴግ
- ዜጎችን ማሰር መፍትሄ አይደለም። እንደነ አቶ እስክንድር ነጋ ያሉ፣ ሰላማዊ የሆኑ፣ የታሰሩ ጋዜጠኖች፣ እንደ አቶ አንድዋለም አራጌና አቶ በቀለ ገርባ የመሳሰሉ፣ በአገሪቷ ሕግ መሰረት ተመዝግበው በሰላም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅት አመራር አባላት እንዲሁም ሌሎች በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ መፈታት አለባቸው።
- ኢሕአዴግ የምርጫ ስነ-ምግባር ኮዱን ከፈረሙ፣ ማናቸውም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመናጋገር ፍቃደኛ እንደሆነ ገልጿል። የስነ-ምግባር ኮዱን ካልፈረሙ፣ እንደ ኦብነግ ካሉ ድርጅቶች ጋር ዉይይት ጀምሮ እንደነበረም አንብበናል። በመሆኑም ለኦብነግ ያሳየዉን የመነጋገር ፍቃደኝነት፣ የስነ-ምግባር ኮዱን ላልፈረሙ፣ አገር ዉስጥ በሰላም ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንዲያሳያና ፣ ያሉ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጥሪ አቀርባለሁ።
- የተዘጉ ነጻ ጋዜጦች መታተም መጀመር አለባቸው። እንደ ብርሃነና ሰላም ያሉ የመንግስት መታሚያ ቤቶች ፣ አዲስ ዘመንን እንደሚያትሙት ሁሉ እንደ ፍኖት ለነጻነት ያሉ ጋዜጦችን ማተም ይጠበቅባቸዋል።
- ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሚደረገዉ ምርጫ 99.9 በመቶ ኢሕአዴግ አሸናፊ እንደሚሆን ከወዲሁ የታወቀ ነዉ። ይሄም፣ የምርጫ ሂደቱ ምን ያህል ጸረ-ዲሞክራሲያዊና ኋላ ቀር መሆኑን የሚያሳይ ነዉ። ኢሕአዴጎችም እራሳቸው ሊያፍሩበት ይገባል። በመሆኑም ከአሁኑ ስህተት ትምህርት ተወስዶ ፣ የፊታችን የ2007 ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ መሰረታዊ የሆኑ፣ እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለተኛ ሆነው መዋቀር ይኖርባቸዋል።
እነዚህን እርምጃዎች ኢሕአዴግ ቢወስድ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳዉም። ሕዝቡ በቀላሉ ከሚያደርጋቸው የልማት እንቅስቅሴዎች ጎን ይሰለፍለታል። ለአባይ ግድብ የሚያስፈልገዉን ገንዘብ በአጭር ጊዜ ዉስጥ መሰብሰብ ይችላል። በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የበለጠ አመኔታንና ከበሬታ ያገኛል። ኢሕአዴግ ከላይ የጠቀስኳቸው ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ መፍራት የለበትም። ድፍረቱ ሊኖረዉ ይገባል።
ሚያዚያ 9 ቀን 2003 ዓ.ም ባወጣዉ ርእስ አንቀጹ፣ ሪፖርተር ያስቀመጠዉን ግሩም አባባል ልዋስና «በመገደብ (አባይን) ልንሰራ ያሰብነዉን ታሪክ፣ ባለመገደብ (ዴሞክራሲን) ታሪክ ሰርተን አናጅበዉ»።
ኢሕአዴግንለሚቃወሙ
- ፖለቲካችን መቀየር አለበት። ኢሕአዴግ የሚያደርጋቸው አገርን የሚጠቅሙ የልማት እንቅስቃሴዎችን መደገፍ አለብን። ከላይ እንደዘረዘርኩት ኢሕአዴግ ማሻሻል ያለበት በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም የፈጸማቸው የሚያኮሩና የሚያስደስቱ ተግባራት አሉት። ይሄን እንቀበል። እንዲሁ በጭፍን አንቃወም።
- አገር ቤት ያሉ የስነ ምግባር ኮዱን ያልፈረሙ ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶ አሉ። እነዚህ ድርጅቶች ከኢሕአዴግ ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል። መቃወም ብቻ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም። ተቃዉሞ ማቅረብ የትግሉ አንድ አካል ቢሆንም፣ በሚያስማሙ ነገሮች ዙሪያ አብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ አለባቸዉ። ሕግ ሆኖ የወጣዉንና እናከብረዋለን የሚሉትን የስነ-ምግባር ኮዱ መፈረም ባይኖርባቸውም፣ ለሰላምና ለእርቅ ሲሉ ይሄን ሰነድ እንዲፈረሙ፣ ከኢሕአዴግ ጋር መነጋገር የሚቻልበት ሁኔታ እንዲያመቻቹ እመክራለሁ። ግትር አቋም መያዝ ጥቅም የለዉም። እነዚህን ድርጅቶች የምንደግፍም፣ የአመራር አባላቱ ላይ በዚህ ዙሪያ፣ ግፊት እንድናደርግ እጠይቃለሁ።
- በቋጠሮ ድህረ ገጽ ላይ እንደተዘገበው አይነት፣ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የሚደረጉ ተቋዉሞዎች መቆም አለባቸው። ይህ አይነቱን ተቃዉሞ በተዘዋዋሪ መንገድ፣ በዉጭ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጥቅም ማስጠበቅ ነዉ። የሳዉዲዉ ጀነራል፣ እነ ጄነራል ካሊድ ቢን ሱላጣንን ማስደሰት ነዉ።
- የአባይ ግድብ መገደብ አለበት። ኢትዮጵያዊ ሁሉ ገንዘብ ማዋጣት አለበት። አቅም እያለን ፣ ይሄን ግድብ መገንባት ካቃጠን፣ በአገር ጉዳይ መስማማት ካልቻልን፣ እንደ ሕዝብ ሁላችንም አብረን እንጠፋለን። ኢትዮጵያም የወላድ መካን ፣ ድሃ አገር ሆና ትቀጥላለች።
- ልማት አንድ እግራችን ነዉ። ነጻነትና የመብት መከበር ሁለተኛዉ እግራችን ነዉ። በሁለቱ እግሮቻቸን ቆመን መሄድ፣ መሮጥ እንጀምር። እግዚአብሄር ልባችንን ለፍቅሩ፣ አይምሯችንን ለጥበቡ ይክፈትልን።