February 25, 2013
30 mins read

ውዝግብ በአዲስ አበባው ሲኖዶስ ውስጥ፡ ያሳዝናል! ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ኹና አታውቅም፤ ይፋረደን!

ትናንት ዘ-ሐበሻ የዘገበችውን የሚያጠናክር ዘገባ ሐራ ተዋሕዶ ድረ ገጽ በትንታኔ ጽፎታል እንደወረደ አስተናግደነዋል።
‹‹ቤተ ክርስቲያን ስትጠራኝ እምቢ እላለኹ ወይ ! ! !›› /ብፁዕ አቡነ ማትያስ/
‹‹አጃቢ ነን!›› /ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል/
‹‹እንኳን አይደለም ፕትርክናው ጵጵስናውም ከብዶኛል፤ እኔ እጠፋለኹ›› /ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ/
‹‹እኛ መናጆ ተብለን ነው የገባነው፤ የሚመረጠው አባ ማትያስ ነው›› /ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ/
‹‹ነገ በታሪክ የሚጠየቅና የሚወገዝ ሲኖዶስና አባት መኖር የለበትም›› /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/

ከላይ በዋናው ርእስ የተመለከተው÷ ቁጭት እንጂ አቅም ያነሳቸው ንግግሮች የተሰሙት ትላንት፣ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም በፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ለመወያየት የተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውል ያለው ግልጽ ውሳኔ ላይ ሳይደርስ ከቀትር በኋላ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡

በስብሰባው ሂደት÷ ለፕትርክናው የተሠየሙትን ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ተሳትፎ በነበራቸው ብፁዓን አባቶች መካከል የነበረው የከረረ የቃላት ልውውጥ፣ ተሳትፎ ባልነበራቸው ብፁዓን አባቶች ላይ የታየው ስጋትና ድብታ፣ በኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ምትክ የኮሚቴውን ሪፖርት ያቀረበው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ለቅ/ሲኖዶሱ ጠረጴዛና ለአጀንዳው ታላቅነት የማይመጥን፣ ውክልናውና ያጸደቀለትን ማኅበር የሚያስንቅና የሚያስወቅስ ደርዝ የሌለው ንግግር፣ በዋናነትም ስብሰባው የተጠናቀቀበት ውል አልባ ኹኔታ ነው ይህን የሐዘን ንግግር ያናገረው፡፡ በዚህ ቃል ሲናገሩ ከተሰሙት አረጋውያኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥቂቱን ለመጥቀስ÷ አቡነ አትናቴዎስ፣ አቡነ ኤርሚያስ፣ አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ኤፍሬም እና ከዕጩዎች አንዱ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡

ስብሰባው ጠዋት 3፡00 ላይ በውዳሴ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ እና መልክአ ማርያም ጸሎት ከተከፈተ በኋላ ዐቃቤ መንበሩ የዕለቱን የስብሰባ አጀንዳ ሲያስተዋውቁ፣ ‹‹የአስመራጭ ኮሚቴውን ሪፖርት ሰምተን ለማጽደቅ ነው፤›› በሚል ነበር ያስጀመሩት፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ተጠርተው ገብተው በሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በኩል የዕጩዎች አመራረጥ፣ ዝርዝርና ማንነት በንባብ ከተሰማ በኋላ የነበረው የስብሰባው ድባብ ግን፣ ሰምቶ ማጽደቁ ቀርቶ የተጋጋሉ ውይይቶችንና ትችቶችን ያስተናገደ፣ ከሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው በቀር ብዙኀኑ የኮሚቴው አባላት አንዳች የውስጥ ክፍፍልን በሚያሳብቅ አኳኋን (በተለይም ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ) በእጅጉ አዝነውና ተክዘው የታዩበት፣ ኮሚቴው ከብፁዓን አባቶች ለቀረቡለት ጥያቄዎች የተረጋገጠ መልስ ሊሰጥ ያልቻለበት አሳዛኝ ኹኔታ ነበር፡፡

ኮሚቴው የተረጋገጠ ወይም በቂ ያልኾነ ምላሽ ሊሰጥባቸው ያልቻለባቸውና ለተካረረ መንሥኤ የኾኑ ዋነኛ ነጥቦች፣ የመጀመሪያው÷ ዕጩ ፓትርያሪኮች የቀረበቡበት መንገድ የምርጫ ሕገ ደንቡ ተሟልቶ ያልተፈጸመበት መኾኑ ነው፤ ሁለተኛው÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይሎች ተጽዕኖ እና ለውስጥ ቡድኖች ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ እኒህን አከራካሪ ነጥቦች በየጊዜው ባወጣናቸው ዘገባዎች እያጋለጠናቸው ቆይተናል፤ እስኵ አሁን ደግሞ በስብሰባው ሂደት ከተንሸራሸሩት ሐሳቦች አንጻር በመጠኑ እንመልከታቸው፡፡

በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ከዋነኛ አነጋጋሪ ነጥቦች አንዱ÷ የምርጫው ሂደትና ጠቅላላ ኹኔታ ለውጭ ኀይል ተጽዕኖ እና ለውስጥ ኀይሎች ጥቅማዊ ፍላጎት የተጋለጠ መኾኑ ነው፡፡ የውጭ ኀይል ሲባል ሌላ ማንም ሳይኾን የመንግሥት ተጽዕኖ ማለታችን ነው፡፡

ተጽዕኖው በግልጽ ሲቀመጥ÷ አቋም ያላቸውን የአስመራጭ ኮሚቴውን አባላት በተናጠል ማስፈራራት፤ በበርካታ አህጉረ ስብከት በተለይም በሐዋሳ፣ ናዝሬት፣ አሰበ ተፈሪ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ባሕር ዳር እና ደሴ መራጮች ‹‹የመንግሥት ምርጫ ናቸው›› ለሚባሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ድምፅ እንዲሰጡ፣ ድምፃቸውን ለብፁዕ አቡነ ማትያስ ለመስጠት ፈቃደኛ ካልኾኑ በሌሎች እንዲቀየሩ፣ ፈቃደኛ ኾኑም አልኾኑ ሰንበት ት/ቤቶችን በመወከል በመራጭነት የተመዘገቡ ወጣቶች የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ከኾኑ በአስቸኳይ ከዝርዝሩ እንዲወገዱና የማኅበሩ አባላት ባልኾኑ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንዲተኩ፤ ከፍተኛ የካህናትና ምእመናን ጥቆማ ያገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ራሳቸውን ማሸማቀቅና ‹‹ዐርፈው እንዲቀመጡ›› በዛቻ ማስፈራራት፣ በምትኩ እነርሱ በሚመሯቸው ሀ/ስብከት መንግሥት ለወደዳቸው ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኀይልና ሽብር በመንዛት የሚካሄደው የድጋፍ ቅስቀሳ እንዲጧጧፍ መርዳት በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

በምሳሌነት የቀረቡት እኒህ የመንግሥት ተጽዕኖ መልኮች በትላንቱ ስብሰባ ጥቂት በማይባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ተረጋግጧል – ‹‹ሥራ አስኪያጆቻችን የደኅንነት ወከባና እንግልት ተፈጽሞባቸዋል›› በሚል፡፡ ከዚህ በመነሣት በትላንቱ ስብሰባ ለአስመራጭ ኮሚቴው ከቀረበሉት ጥያቄዎች አንዱ ‹‹መንግሥት ጣልቃ ገብቷል ወይስ አልገባም?›› የሚል መኾኑ ተገቢ ነው፡፡ ግና ምን ያደርጋል፤ ከአስመራጭ ኮሚቴው አባላት አንዳቸውም ለጥያቄው ምላሽ ሊሰጡ አልደፈሩም፡፡ [ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በምርጫው ወቅታዊ ኹኔታ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ በተጠራው የማኅበረ ቅዱሳን የአመራርና የአስፈጻሚ አባላት ጉባኤ ላይ ሪፖርት ያቀረበው የአስመራጭ ኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ግን፣ የመንግሥትን ተጽዕኖ የሚቀርቡ ዜናዎች ፍጹም ሐሰት መኾናቸውን፣ በምትኩ ‹‹እኛ ሄድን እንጂ መንግሥት አልጠራንም›› በሚል በርካታ ዘገባዎችን አስተባብሎ ነበር፡፡]

ከዕለቱ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ብርቱ ተናጋሪዎች አንዱ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ግን፣ ‹‹መንግሥት ፓትርያሪክ አይመርጥልንም›› ሲሉ በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው በአብዛኞቹ አህጉረ ስብከት የብፁዕ አቡነ ማትያስን አስቀድሞ መመረጥ የሚያሳዩ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚጥሱ ያልተገቡ ተግባራት በመታየት ላይ መኾናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ከዚህ በማያያዝ ሕጉ እንደኾን አንድያውን የተጣሰ በመኾኑ ከዚህ በኋላ የሽፋን ምርጫ ሳያስፈልግ አቡነ ማትያስን ለመሾም የፈለገው አካል በቀጥታ በደብዳቤ እንዲሾማቸው እንጂ ሂደቱ የምልአተ ጉባኤው ውሳኔ እንደማያስፈልገው፣ እንደማይገባውም አስታውቀዋል፤ አቋማቸውንም ሲያስረግጡ በውሳኔው ላይ ፊርማቸውን አስቀምጠው በምርጫው እንደማይሳተፉ ገልጠዋል፡፡

በዚሁ መንፈስ ከተናገሩትና ከብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘኢየሩሳሌም ጋራ ቀጥተኛ ምልልስ ካደረጉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ሢመተ ፕትርክናው ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ ካልኾነ በቀጣይ የሚኖረውን ኹኔታ የሚያመለክት ነው፡፡ ብፁዕነታቸው ለንግግራቸው መነሻ ያደረጉት በቂ ምላሽ ካልተሰጠባቸው የምልአተ ጉባኤው ጥያቄዎች አንዱ በኾነው የብፁዕ አቡነ ማትያስ ዜግነት ጉዳይ ላይ ለሰጡት ምክር ብፁዕ አቡነ ማትያስ የሰጡት ምላሽ ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሰጠ የተባለው ደብዳቤ (ብፁዕ አቡነ ማትያስ በሐምሌ 2004 ዓ.ም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተቀበሉት ተነግሯል) አሜሪካዊ ዜግነትዎን ለመመለስዎ ማረጋገጫ አይኾንም፡፡

ብፁዕ አቡነ ማትያስ፡- ከዚህ በላይ ምንድን ነው የምትፈልጉት?

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ደብዳቤ ማረጋገጫ ሊኾን አይችልም፡፡ ደርግን አልፈልግም ብለው ዜግነትዎን ቀየሩ፡፡ አሁን ደግሞ አሜሪካዊ ዜግነቴን መልሻለኹ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚሉ ከኾነ ማረጋገጫው ፓስፖርቱ ነው፤ ፓስፖርቱን ያምጡ?

ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- የውጭ ጉዳዩ ደብዳቤ ዜግነቱ እንደተመለሰ ይገልጻል፤ ሊመልስ አይችልም፤ ጉዳዩ ሊፈጸም የሚችለው በአሜሪካው እንጂ በዚህ አይደለም፤ ስለዚህ የውጭ ጉዳይ ደብዳቤ ማስረጃ ሊኾን አይችልም፤ ሰርቲፊኬቱን ያምጡ፡፡

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፡- እንዴት ሊሰጥ አይችልም፤ ከዚህ በላይ ምን ይምጣ? ሌላ ተልእኮ አላችኹ?

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- እኔ ያን እስካላየሁ አልመርጥዎትም፣ ብፁዕ አባታችን፤ ይህን ይወቁት፡፡

ብፁዕ አቡነ ማትያስ፡- ቤተ ክርስቲያን ስትጠራኝ እምቢ እላለኹ ወይ?

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ገና ዕጩ ነዎት፤ እርሱም ቢኾን በአበው ሥርዐት ሹመት ሲሰጥ አልኾንም፤ አይገባኝም ነው የሚባለው፡፡ ለኅሊናችንና ለቤተ ክርስቲያናችን መኖር መቻል አለብን፡፡ አለበለዚያ ቀድሞ በደርግ ጳጳሳቱና ካህናቱ እየተጠሩ አቡነ መርቆሬዎስን ምረጡ ብሎ እንዳደረገው የእርስዎም ሹመት እንደዚያ ነው የሚኾነው፡፡ ፓትርያሪክ በመንግሥት ተሾመ ተብሎ በሕዝቡ ዘንድ ጥላቻ መታየቱ በአራተኛው ፓትርያሪክም ያየነው ነው፡፡ ይህ ተቀባይነት የለውም፤ መደገምም የለበትም፤ ነገ የሚወገዝ፣ ነገ በታሪክ የሚጠየቅ አባትና ሲኖዶስ መኖር የለበትም፡፡ በሕገ መንግሥቱ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ ተደንግጓል፤ ስለዚህ ገብቶ ከኾነ እጁን እንዲያነሣ እንጠይቃለን፡፡

በአስመራጭ ኮሚቴው ምላሽ የተነፈገው የመንግሥት ተጽዕኖ ጉዳይ እንግዲህ ይህን ያህል አነጋግሯል፤ ‹‹የቀረበባቸውን ተቃውሞ በዝምታ አልፈውታል›› በሚል በአንዱ ጦማሪ ያልተጣራ ዘገባ የተሠራላቸው አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስም ይህን ያህል ተከራክረዋል፤ ‹ጥሪው›ም የተሰማቸው ከዕጩነት ባሻገር ጮኾና ጎልቶ እንደኾነ አረጋግጠውልናል፡፡ ከዕጩነት ባሻገር የተሰማው ጥሪ አቡነ ማትያስ ቀጣዩ ፓትርያሪክ እንደሚኾኑ ነው፡፡

ብፁዕነታቸውን ለማስመረጥ የተደረገው ሽርጉድ ግን በአስመራጭ ኮሚቴው የዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱትን ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ደስ አላሰኛቸውም፡፡ የኮሚቴው ሪፖርት በንባብ ተሰምቶ እንደተጠናቀቀ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ÷ ‹‹በአበው ገዳማዊ ሥርዐት በዕጩነት መመረጥ አይገባኝም፤ እንኳን አይደለም ፕትርክናው ጵጵስናውም ከብዶኛል፤ ይህን ነገር ከሰማኹ ጀምሮ ብርክ ይዞኛል፤ እኔን ተዉኝ፤ እኔ እጠፋለኹ፤›› ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በበኩላቸው÷ ‹‹እኛ መናጆ ተብለን ነው የገባነው፤ የሚመረጠው አባ ማትያስ ነው፤ ይህ መንፈስ ቅዱስ የተለየው፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ያልጠበቀ ምርጫ ነው፤ ያኔ በዕጣ ይኹን ብዬ ተከራክሬ ነበር፤ የኾነ አካል አባ ማትያስን አምጥቶ ያስቀምጣል፤ እኔ መናጆ አይደለኹም፤ መናጆ አልኾንም፤›› በሚል አጽንዖት ተናግረዋል፡፡ ብፁ ዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለየት በሚለው የአነጋገር ዘዬአቸው ‹‹ያው አጃቢ ነን፤ እናየዋለን›› በሚል ምፀታዊ መንፈስ መልሰዋል፡፡

አምስቱ ዕጩዎች የተመረጡት ብቃትን ዋና መነሻ በማድረግ አይደለም፡፡ ምርጫው የተመሠረተው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የፓትርያሪክ ምርጫ አከፋፈል በትውልድ አካባቢ በተለዩ ዞኖች/ትግራይ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ እና ኦሮሚያ(?) መኾኑ ተገልጧል፡፡ ከትግራይ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ ከጎንደር ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ከወሎ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ከሸዋ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እና ከኦሮሚያ(?) ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ መኾኑ ነው፡፡ የዕጩዎች ምርጫው ለቤተ ክርስቲያን ተገቢ ከኾነው መንፈሳዊ ብቃት ይልቅ የጎሳ/ትውልዳዊ ማንነትን የተከተለ፣ የጊዜው ፖሊቲካዊ አስተሳሰብና ስሜት የተጫነው መኾኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህም ኾኖ የኮሚቴው አሠራር ዕጩዎቹ ያላቸውን ስብጥር ያህል ሁሉንም በሁሉም አካባቢ በእኩልነት የሚያስተዋውቅ አልነበረም፤ የግል መረጃዎቻቸውን፣ ታሪካቸውንና ለዕጩነት ያበቃቸውን የሥራ ፍሬዎቻቸውን ከመመዘኛው አንጻር እኩል አጽንዖት ሰጥቶ በተሟላ ይዘት የቀረበበት አልነበረም፡፡

የጉባኤው የክርክር ማእከል የነበሩትን ብፁዕ አቡነ ማትያስ የግል መረጃና ታሪክ ሲታይ ዕድሜያቸው (ከ75 በላይ መኾን አለመኾኑ) በግልጽ ተረጋግጦ አልቀረበም፤ እንደ አንዳንድ ምንጮች ጥቆማ የነበራቸው የግል ማኅደርም እንዲጠፋ ተደርጓል፤ ዜግነታቸውን ስለመመለሳቸው ቤቱን ያሳመነ ምላሽ አልተሰጠም፡፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ‹‹ሁለት ማትያሶች አሉ፤ ኮሚቴው በማትያስ ላይ ማትያስ የተሾመበትን ታሪክ ለምን አልገለጸም?›› የሚል በሦስተኛው ፓትርያሪክ ዘመን ተላልፎባቸው የነበረውን ውግዘት የሚያስታውስ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የብፁዕ አቡነ ማትያስ ቀራቢው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በተቃውሟቸው የብፁዕነታቸውን የዕርግናና የጤንነት ይዞታ የተመለከተ ጉዳይ አንሥተዋል፡፡ ብዙዎቹ ነጥቦች ከፓትርያሪክ ምርጫው ሕገ ደንብ አንጻር በተለያየ ጊዜ ስለዳሠሣናቸው እንለፋቸውና ‹‹ሁለት ማትያሶች አሉ›› ለሚለውና የብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥያቄ በስብሰባው ላይ ሳይናገሩ ዋሉ ተብሎ የተዘገበላቸው ብፁዕ አቡነ ማትያስ÷ ‹‹እርሱም የኾነብኝ ደርግን ስለተቃወምኹ ነበር፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፤ ይልቅዬስ ጥያቄውን በዝምታ ያለፈው ኮሚቴው ነበር እንጂ እርሳቸውማ እንዴታ!

ትኩረት ሳቢ የኾኑ ሌሎች ሁለት ጥያቄዎች፡-

‹‹በአምስቱ ዕጩዎች ተስማምታችኹ የተፈራረማችኹበት ቃለ ጉባኤ አለ ወይ?››
‹‹ብፁዕ አቡነ ማትያስን የጠቆሙ ካህናትና ምእመናን አሉ ወይ? ካሉስ ብዛታቸው ምን ያህል ነው?››
ኮሚቴው በዕጩዎቹ ማንነት ላይ በአንድ ድምፅ፣ ያለልዩነት የተፈራረመበት ቃለ ጉባኤ ስለመኖሩ ከኮሚቴው የተሰጠ ምላሽ ስለመኖሩ አልተዘገበም፡፡ ለነገሩ እንዴት ሊኖር ይችላል? በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ላይ ዋና ጸሐፊው ሊቀ ማእምራን ፈንታሁን ሙጩ አልታዩም፤ በሕመም ምክንያት ነው ቢባልም የሁሉ ገባሪ ኾኖ ከሚታየው የሕዝብ ግንኙነቱ ሓላፊ ጋራ እንዳልተስማሙ ተሰምቷል፤ ከታዋቂ ምእመናን የተወከሉት በተለይም ቀኝ አዝማች ኀይሉ እንዲያውም ራሳቸውን ስለማግለላቸውና በልዩነታቸው ምክንያት በሰበብ አስባቡ እንደሚጠፉ ነው የሚታወቀው፡፡ ኾኖም የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ቀደም ሲል በጠቀስነው የተወከለበት ማኅበር የአመራሮችና አስፈጻሚዎች የጋራ ስብሰባ ላይ÷ ‹‹ልዩነት አይደለም በድምፅ ብልጫ እንኳ የወሰነው ውሳኔ የለም፤ ሁሉንም በስምምነት ነው የወሰነው፤›› በማለት ተናግሯል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማትያስን የጠቆሙ ካህናትና ምእመናን በቁጥር ቢያንሱም ቢበዙም ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፤ ለብፁዕነታቸው የተሰጠውን ጥቆማ ጨምሮ ኮሚቴው ስለጥቆማው ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ስለመኖሩም አልተሰማም፤ ከዚህ ጋራ በተያያዘ የካህኑና ምእመኑ ጥቆማ ተገቢውን ዋጋ እንዳላገኘ ተነግሮታል፡፡

በትላንቱ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በአስመራጭ ኮሚቴው ለቀረበው የዕጩዎች ዝርዝር ግልጽ ድጋፋቸውን በመስጠት ቅ/ሲኖዶሱ እንዲያጸደቀው ጠንካራ ድጋፍ ሲሰጡ የዋሉት÷ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ናቸው፡፡ ከእኒህ ብፁዓን አባቶች መካከል በአንድ ወቅት ‹‹የደርጉ ጳጳሳት›› ተብለው ሲታሙ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ለብፁዕ አቡነ ማትያስ ስሜት የተቀላቀለበት ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ ተስተውለዋል፤ መብታቸው ነው፤ ወዳጅነታቸው፣ አባታዊ ውሳኔያቸው ሊከበር ይገባል፡፡ ቁም ነገሩ፣ ሥልጡንነቱ በአንጻሩ ሌላውን አባት በመደገፍ ተቃራኒ አቋም የያዙ አባቶችን መብትና ውሳኔ ማክበር ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤልያስም የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ሲኰንኑ የነበሩትን ብፁዕ አቡነ አብርሃምን÷ ‹‹መንግሥት፣ መንግሥት አትበል፤ ራስኽን ቻል፤›› ብለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የተናገሩት ተግሣጽ÷ በደረቁ እውነት ነው፤ ተግሣጹ ግን ተግሣጽ ከመኾኑ በቀር ራሳችንን እንዳንችል ካደረጉን ምክንያቶች አንዱ የኾነውን የመንግሥት ተጽዕኖ እንዴት መግራት እንደምንችል /ሕገ መንግሥቱ ወይም ለብዙዎች እንደሚመስላቸው ጨርሶም ነጻ መኾን ስለማይቻል/ አያሳይም፡፡

ኮሚቴው ምላሽ ከሰጠባቸው ይልቅ ያልሰጠባቸው ጥያቄዎች በዝተው ዝምታው፣ አንገት መድፋቱ፣ መተከዙ፣ መቆዘሙ (በተለይ በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እና በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ላይ ጠንክሮ ታይቷል፤ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የተቃውሞ/ልዩነት ቃል ቢናገሩ ምላሳቸው እንደሚቆረጥ የሚገልጽ ጽኑ የማስፈራሪያ ቃል ከአንድ ጎምቱ ባለሥልጣን እንደደረሳቸው ተዘግቧል፤) ጠንቶ በታየ ጊዜ የኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ቢጨንቃቸው ሁሉንም ሥራ ለቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ አሳልፎ የመስጠት ንግግር ተናግረዋል፡- ‹‹የኮሚቴው አካሄድ ሕጉን ሥርዐቱን ካልጠበቀ የማስተካከል የማረም የመጨረሻ ሓላፊነቱ የምርጫው ባለቤት የኾነው ቅ/ሲኖዶሱ ነው፤ አስፈላጊውን ውሳኔ መስጠት ይችላል፤ እኛ ያልነው ይኾናል፤ ሌላ ነገር አንነጋገር፡፡››

የምልአተ ጉባኤው መጨረሻ ግን÷ በአንድ በኩል፣ አስመራጭ ኮሚቴው ያቀረበው ሥራ/ሪፖርት ምንም ዐይነት ውሳኔ መስጠት እንደማያስችል በመግለጽ የውሳኔውም የምርጫውም አካል እንደማይኾኑ ግልጽ ያደረጉ ብፁዓን አባቶች የታዩበት ነው፡፡ እኒህ አባቶች አስመራጭ ኮሚቴው የሕግና የታሪክ ተጠያቂ እንደሚኾንም አስጠንቅቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ነገሩ ከተበላሸ ቆይቷል፤ ከተበላሸ ስለቆየ እናጽድቀው›› የሚሉ አባቶች የታዩበት ነው፡፡ እኒህ አባቶች ውሳኔው አጽድቀው እንደወጡ ተናግረዋል፡፡ በሐተታችን መግቢያ እንዳመለከትነው ደግሞ÷ ‹‹ያሳዝናል! ያሳዝናል! ያሳዝናል! ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ኹና አታውቅም፤ ይፋረደን፤ ይፋረደን!!›› የሚል ቁጭት ያሰሙ ሽማግሎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ፡፡

የኾነው ኾኖ ቃለ ጉባኤ በውል ያልተያዘበት፣ የተጨበጠ ውሳኔም ያልተላለፈበት የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ነበር፡፡ ቃለ ጉባኤው ገና ተጽፎ በነገው ዕለት ለፊርማ የሚቀርበው በአስመራጭ ኮሚቴው አባላት መኾኑ ተመልክቷል፡፡

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop