February 25, 2013
16 mins read

የሚሳናቸው የለም

በቸሩ ላቀው

ሿሚ፣ ሻሪ፣ ሀገር መከፋፈልና መገነጣጠል የነርሱ ተግባር ሆኗል። መለስን ሾሙብን፣ ሀገርን ገንጥለው ኢሳያስ ኣፈወርቂን ኤርትራን ይዘህ ራስህን ቻል ኣሉት። ከመለስ ሹመት ጋር ኢትዮጵያን በጎሣ ከፋፍለው እያወደሟትና እያደቀቋት ነው።
በቅርቡ ደግሞ ትኩረት ተሰጥቶት በኢትዮጵያን ሪቪው ድረ ገጽ ላይ ምኒልክ ሳልሳዊ በተባለ ግለሰብ (http://www.ethiopianreview.com/forum/viewtopic.php?f=2&t=47866) እንደተጻፈው ከሆነ ኢትዮጵያን መበታተኑ ኣልበቃ ብሎኣቸው ለወደፊቱም ከኣፍሪካ ካርታ ላይ የቀድሞውን ስሟንና ቅርጿን ይዛ እንዳትታይ ተሰርዛ ለብዙ ሺህ ዓመታት የምናውቃት ኢትዮጵያ ሰሟ የማይታወቅ የጥንት ታሪክ መዛግብት ቤት ግብቶ ወያኔም እንደሚፎክርብን ኣዲስቱን ኢትዮጵያን ልናይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የወያኔ የመገንጠልና የትግራይ ትግሪኝ መንግሥት መመስረት ሕልም ቅዠት ሆኖ ሊቀር ነው።
ኣዲስ ኣበባ ቀድሞ የጀርመን ትምህርት ቤት በኣፀደ ሐፃንነት ትምህርት ቤት ይጠቀምበት የነበረውና መንግሥት ከወረሰ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደረው ኣምስት ኪሎ የሚገኘው ኣፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ልጆቼን ኣስገብቼ ስለነበር ለመውሰድ ስሔድ የመውጫ ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ኃላፊ ከነበረችው ኤርትራዊት ጋር እንጨዋወት ነበር። ከተጨዋወትናቸውም መካከል ሁለት ነገሮችን ይዤላታለሁ።
ኣንደኛው ሰዎች ይታሰራሉ፣ ይሰቃያሉ፣ ይገደላሉ፣ የት እንደደረሱም የማይታወቁ ሞልተዋል ብዬ ሳጫውታት ምንም ነገር ሰምታ እንደማታውቅ ስትመልስልኝ ጤነኛ ሰው ነች ወይ ብዬ ተገረምኩ። የሰው ልጆች ማኅበራዊ እንስሳት እስከሆኑ ድረስ ከሰዎች ጋር ይገናኛሉ፣ ሐሳብ ለሐሳብ ይለዋወጣሉ፣ የተለያዩ ዓይነት ያላቸውን ጭውውቶች ይጨዋወጣሉ። ጎረቤታሞች ብዙ ሐሳብ ይለዋወጣሉ። ከዚያም በተጨማሪ ሬድዮ በማዳመጥ፣ ቴሌቪዥን በማየትና በስልክም ከጓደኖች ጋር ሲነጋገሩ የተለያዩ ዜናዎችን ያገኛሉ። ይህች በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ያለች የኣፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ኃላፊ ከዚህ ሁሉ ተለይታ ምንም ኣለመስማቷ ምን ብትሆን ነው ብዬ ምክንያቱን ጠየቅኋት። ሃይማኖቷ ስለማይፈቅድላት ምንም እንደማታዳምጥና እንደማትሰማ ነገረችኝ። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች የኋሊት ጉዞ ላይ መሆናቸው ገረመኝ፣ ኣሳዘነኝ። ኣታድርጉ የተባሉትን ካደረጉ “እንደሚቀሰፉ” ይፈራሉ። ራስን ማታለል ነው። ራስን ኣለማወቅ ነው። ይህች የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ መሃይም ኣዲስ ኣበባ ከተማ ተቀምጣ እንኳን በከተማው ውስጥ ቀርቶ በመንደሯ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የማታውቅ ከሆነች ብቻዋን ቤት ዘግታ የምትኖር ግዞተኛ ነች ማለት ይቻላል።
በጨዋታችን መካከል በሁለተኛነት የያዝኩላት ቁም ነገር በፀሎት ቤታቸው የተነገራትን የነገረችኝ ግን ወደ ዋናው ርዕሴ የሚወስድ ነው። ኢትዮጵያ የኣፍሪካ መናኸሪያ ስለምትሆን ኣዲስ ኣበባ የኣፍሪካ ዋና ከተማ ትሆናለች። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ደግሞ ባሕር ዳር ይሆናል ያለችው እነርሱ ካዘዙ ሊሆን ይችላል ብዬ ተቀብያታለሁ። የኣፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ኣገዛዝ ነፃ ከወጡ በኋላ ለነፃነታቸው ታግለው የነበሩና ነፃነታቸውን እንዲጎናጸፉ ኣድርገው የነበሩ መሪዎች ሀገር ወዳዶች ስለነበሩና ለኃያላን መንግሥታት ኣንበረከክም ብለው ስለነበር በመፈንቅለ መንግሥት ተገድለዋል። ኣሁን ያሉት ግን በነርሱ የተሾሙና የተቀመጡ ግዑዛን ስለሆኑ ትዕዛዙ ሲሰጣቸው ከመፈጸም ወደኋላ ስለማይሉ ሴትዮዋ ያለችው ሊሆን ይችል ይሆናል። ይኸንኑ መረጃ ከነርሱ በነርሱ ኣማካይነት ያገኘች ስለሆነ ቀደም ተብሎ የተጠናና የታሰበበት መሆኑ ነው።
በቅርቡ ከላይ በተገለጸው ድረ ገጽ ላይ የተናፈሰው ዜና ከዚህ ጋር ቅርበት ያለው ቢሆንም የኣፍሪካን ካርታ ቅርፅ የሚለውጥ ይሆናል። ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጣ ቀጥሎ በተመለከተው መሠረት ይገለጻል።
ሱዳን እጅ ኣልሰጥም ብላ ባቋሟ ስለፀናች ሀገሪቷን ለኣራት ከፍለው ምዕራብ ሱዳን፣ ምሥራቅ ሱዳን፣ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ብለው በመሰየም ሌላ ሀገር ፈጥረዋል። በዚህኛው ክፍፍል ደግሞ ከምዕራቡ በኩል ቆርሰው ዳርፉር ከቻድ ጋር ማዋኸድ ሲሆን ምሥራቁን ወስደው ከኢትዮጵያ ጋር ቀላቅለው ፖርት ሱዳንን በመንጠቅ ወደብ ኣልባ ትንሽ ሀገር እንድትሆንና እንድትሞት ተቀይሷል።
በኣዲሱ የሰሜን ምሥራቅ ኣፍሪካ ወይም የኣፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ካርታ ኣሠራር ከሱዳን ቀጥሎ ግብፅን፣ ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲንና ሶማሊያን የሚመለከት የሚከተለው የኣከፋፈል ቅያስ ተዘጋጅቷል።
ግብፅን በተመለከተ ለጊዜው ዕቅዱ ያለቀለት ደቡባዊው የክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮቹ ተገንጠለው “ከኣዲስቷ ኢትዮጵያ” ጋር ሊቀላቀሉ ሲችሉ የሲናይ ክልሉም እንደሚገነጠል ነው። ይኸ የሚያሳየው ግብፅ ለሦስት ቦታ መሰንጠቋን ነው።
ምሥራቅ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ትቀላቀላለች። ኤርትራና ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ይቀላቀላሉ። ድሬ ዳዋ፣ ሰሜን፣ ደቡብና የኦጋዴን ሶማሌዎች ተቀላቅለው ታላቋን ሶማሊያን ይፈጥራሉ። ባሌ፣ ቦረና፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ የኦሮሚያ ግዛት ይመሠርታሉ።
ከብዙ ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውን ዐማርኛን ለማጥፋትና የእንግሊዝኛን ቋንቋ የኢትዮጵያ ሀገር ቋንቋ ለማድረግ ሲዘመትበት እንደቆዩ ቀደምት ኣባቶቻችን ምን ያህል ሲታገሉ እንደነበሩ ይታወቃል። ኣሁን ግን ገና ዐዋጁ ሳይታወጅ በኢትዮጵያ በሁሉም ክፍለ ሀገራት ከትናንሽ መንደሮች እስከ ዋናዋ ከተማ ኣዲስ ኣበባ ድረስ በየጉራንጉሩ ነጋዴዎች የሱቆቻቸውን ስም ኣስጽፈው የሚለጥፉት በእንግሊዝኛ ነው። ፊደል ያልቆጠረው ሁሉ የሚያስጽፈው በባዕዱ ቋንቋ ነው። ባሁኑ ኣዲሱ ዕቅድም የሥራ ቋንቋ እንግሊኛ እንደሚሆን ተወስኗል።
በኣዲሱ ኣከላለል ኢትዮጵያ ሰባት ክፍለ ሀገራት ወይም ክልሎች ወይም ምን እንደሚሉ ኣልተገለጸም ትከፋፈላለች።
ኣንደኛው ዐማራ ሲሆን በዚህ ምድብ ሥር ከምሥራቅ ሱዳን እንዲቀላቀሉ የታዘዙት:-
1ኛ ከሰላ 4ኛ ብሉ ናይል
2ኛ ገዳሪፍ 5ኛ ሬድ ሲ ከፖርት ሱዳን ወደብ ጋርና
3ኛ ስናር 6ኛ ከግብፅ የክርስቲያን እምነት ተከታይ ክፍል።
ሁለተኛው ትግራይ
ሦስተኛው ኣፋር:- ጂቡቲና ኤርትራን ኣጠቃሎ
ኣራተኛው ኣዲስ ኣበባ። የሚያጠቃልላቸውም፡-
1ኛ ኢሉባቦር 5ኛ ሰሜን ሸዋ
2ኛ ምዕራብ ወለጋ 6ኛ ምዕራብ ሸዋ
3ኛ ምሥራቅ ወለጋ 7ኛ ምሥራቅ ሸዋ
4ኛ ጂማ 8ኛ ኣርሲ
ኣምስተኛው ደቡብ ሕዝቦች። የሚያጠቃልላቸውም፡-
1ኛ ደቡብ ኦሞ 8ኛ ደራሼ 15ኛ ሐዲያ
2ኛ ቤንች ማጂ 9ኛ ኮንሶ 16ኛ ኣንጋጫ (ኣንጋቻ)
3ኛ ሸካ 10ኛ ቡርጂ 17ኛ ኣላባ
4ኛ ከፋ 11ኛ ኣማሮ 18ኛ ሲልጤ
5ኛ ዳውሮ 12ኛ ጌዴኦ 19ኛ ጉራጌ
6ኛ ባስኬቶ 13ኛ ሲዳማ 20ኛ የም።
7ኛ ጋሞ ጎፋ 14ኛ ወላይታ
ስድስተኛው ጋምቤላ
ሰባተኛው ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ
የኣፍሪካ ሀገሮች ለብዙ ዓመታት ታግለው ቅኝ ገዢዎቻቸውን ኣባረው ነፃነታቸውን ሲጎናጸፉ የነፃነት ጥም ተጠምተው የነበሩና ለሰው ልጅ ነፃነት ሲያስቡና ሲጨነቁ የነበሩ ሀገሮች ሕዝቦች ሁሉ ተደስተውና ፈንድቀው ነበር። በኃይል ተገፍተው ከያገሮቹ የተባረሩት ቅኝ ገዢ ሀገሮች ሲለቁ ግን ጊዜያቸውን እየጠበቁ የሚፈነዱ ፈንጂዎችን ቀብረው ነበር የሔዱት። በመሆኑም ከብዝበዛ፣ ከኣስከፊ ኣድሎኣዊ ኣስተዳደር፣ ከበታችነት ኑሮ፣ ከበይ ተመልካችነት ነፃ ወጣን ብለው ተደስተው የነበሩ ሀገሮች ለካ ነፃነታቸው የይስሙላ መሆኑን ኣላወቁም ነበር።
የተቀበሩት ፈንጂዎች ቀስ በቀስ መፈንዳት ጀመሩ። በሀገር ውስጥ ኣንዱ ጎሣ ከሌላው ጎሣ ጋር እንዲጣላ፣ ኣንዱ ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት ጋር እንዲጣላ፣ ሀገሮች ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በድንበር እንዲጋጩና እንዲጣሉ ተደርገው የነበሩ የተንኮል ዘዴዎች መከሰት ጀመሩ። በነዚህም የተንኮል ሴራዎች መገዳደልና በጦርነት መፈላለግ እስካሁንም ኣላባሩም። በኣንድ በኩል እርቅ ወርደ ሲባል በሌላ በኩል ደግሞ የተዳፈነው እሳት መቀጣጠልና መንደድ ይጀምራል።
ኢትዮጵያ እንደ ኣጋጣሚም ከመሆኑም በተጨማሪ ሕዝቡም ለተገዢነት ኣመቺ ሆኖ ስለኣልተገኘና ስለኣልተመቻቸላቸው በቅኝ ግዛት ገዢነት ለመያዝ ሞክረው ኣልተሳካላቸውም ነበር። ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ ተሸንፋና ተዋርዳ በመመለሷ ውርደቱ የኢጣሊያ ብቻ ሳይሆን የመላው ኣውሮፓ ሀገሮች ነው ብለው ኣፍረውበት ስለነበር በተለያዩ ዘዴዎች ለመግባትና ለማንበርከክ ሲያደቡና ሲጥሩ ቆይተው የሥልጣን ያለህ እያለ በመቅበዝበዝ ላይ የነበረውን የሀገርና የሕዝብ ስሜት የሌለውን ወያኔን ስለኣገኙ በርሱ ኣማካይነት በጅ ኣዙር ቅኝ ገዢነት ኢትዮጵያን ለመያዝና ለመቆጣጠር በቅተዋል። ይኸም ኣልበቃ ብሏቸው የኣፍሪካን ካርታ እነርሱ በሚፈልጉትና ለብዝበዛ በሚያመቻቸው መንገድ ለመቀየስ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ናቸው። ይህ ከላይ ያየናቸው የኣፍሪካ ቀንድ ሀገሮችን መከፋፈልና ኣዲስ ካርታ መሥራት የዚሁ ዓላማቸው ዘዴና ኣካል ነው።
ከላይ እንደተገለጸው የኣፍሪካ ሀገሮች ነፃነታቸውን ተጎናጽፈዋል ተባለ እንጂ እያደር ሲታይ ግን የይስሙላ ነፃነት ሆኖ ታይቷል። ሀገሮች ነፃ ናቸው ከተባለ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውና በፖለቲካው ነፃ ሆነው ራሳቸው በሚፈልጉት መንገድ መጓዝ ሲችሉ እንጂ በኋላቸው ሆነው ሌሎች የሚያዙዋቸው ከሆኑ ነፃነታቸው የስም ብቻ ይሆናል። ኣሁንም እኛ ራሳችን ለራሳችንና ለሕዝባችን የሚበጀውን ማድረግ ሲገባን በነርሱ ፍላጎት የምንቀሳቀስ ከሆነ ኢትዮጵያም የነበራትን ነፃነት የተገፈፈችና በነርሱ ኣንቀሳቃሽነት የምትታዘዝ መሆኗ የሚያሳዝንና የሚያስገርም ነው። በትግራይ ሕዝብ ነፃ ኣውጪ ግንባር የውርደት ካባ ተከናንበናል። ተዋርደናል። ነፃነታችንን ተነጥቀን ለእጅ ኣዙር ቅኝ ኣገዛዝ ተዳርገናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ነፃነቱን ለመጎናጸፍ ለሚያደርገው ሁለገብ ትግል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ ይወጣ። ዳር ቆሞ ተመልካችነት ይቁም። ለእውነተኛው ትግል ሁላችንም እንነሳ!
ቸሩ ነኝ በቸር እንገናኝ።

abatemsas@gmail.com.

Go toTop