July 17, 2013
13 mins read

ከኦሮሞ ፖለቲካ ወደ ጃዋር ፖለቲካ? (ከመስፍን ነጋሽ )

ወንድሜ ጃዋር (Jawar Mohamed) ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኦሮሞ ፖለቲካ እና አሁን ደግሞ ስለኦሮሞ-ኢስላም ያቀረባቸው ንግግሮች ኮርኳሪ ሆነዋል። ኮርኳሪነታቸው የሚመነጨው ግን ሐሳቦች አዲስ ስለሆኑ አይደለም፤ በአቀራረባቸውም ቢሆን ያልተለመዱ አይደሉም። “የአግራሞቱ” ወይም የንዴቱ ምንጭ ጃዋር የገነባው ወይም እየገነባው የመሰለን የፖለቲካ ማንነት እና በቅርብ ያንጸባረቃቸው አቋሞቹ እጅግ የሚቃረኑ ስለሚመስሉ ነው።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ውስብስብ ከሚያደርጉት ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የኦሮሞ ፖለቲካ ነው። ኢትዮጵያ ዜጎች ቢያንስ በመጠኑ ሐሳባቸውን በነጻነት የሚለዋወጡባት አገር ብትሆን ኖሮ ጉዳዩን ነጋ ጠባ በተነጋገርንበት፣ በተከራከርንበት ነበር። ይህ ባለመሆኑ ግን ከትልቁ የኦሮሞ ጉዳይ ይልቅ ጃዋር የተነፈሳት አንድ አረፍተ ነገር የበለጠ ቁም ነገር ያላት ሆና ተቆጠረች። መፍትሔው ጃዋርን ማውገዝ አይመስለኝም፤ ስለኦሮሞ ፖለቲካ መነጋገርና መደማመጥ ያስፈልጋል።

ጃዋር በአልጀዚራ ላይ ባቀረበው ሐሳብና በወሰደው አቋም ዙሪያ ሌላ ውይይት/ጽሑፍ የሚያስፈልገው ሆኖ ቢያንስ በክርክሩ ሐልዮታዊ መነሻዎች ላይ ግን ቢይንስ በግማሹ ከጃዋር ጋራ እስማማለሁ። መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነህ ወይስ ኦሮሞ የሚለው ጥያቄም በግለሰቦች ታሪክ፣ ከባህላቸው ጋራ ባለቸው ትስስር እና በፖለቲካዊ ርእዮታቸው የሚወሰን በመሆኑ ውይይትና ዴሞክራሲያዊ የአገር ግንባታ የሚፈታው አድርጌ እወስደዋለሁ። እኔ ያደኩበት ከባቢ ጃዋር ከኖረበት ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህ በፖለቲካዊ ማንነታችን ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ በኑሮና በእውቀት ሊለወጥ የሚችል ቢሆንም በቀላሉ የሚታይ ግን አይደለም። እኔ ባደኩበት ከባቢ ኖረው የጃዋርን ስሜት የሚጋሩ፣ እንዲሁም በተቃራኒው የሚሆኑ ሰዎች አሉ። አንዱ ከሌላው የበለጠ ትክክል አይመስለኝም።

ከብዙ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ጋራ ያለኝ ልዩነት፣ በዋናነት ያለፈውን ታሪክ በምገመግምበት መንገድ ሳይሆን መጪውን ዘመን በማልምበት ስልት ላይ የተመሰረተ ነው። ዴሞክራሲያዊት እና ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ የችግሩ መውጫ ናት እላለሁ፤ ሌላ ምርጫ የለም። የኦሮሞ ሕዝብ በመገንጠል (የራስን እድል በራስ መወሰን) የራሱን መፍትሔ ሊያገኝና ብቻውን በሰላም ደሴት ላይ ሊኖር እንደሚችል የሚያስቡ ይኖራሉ። ቁም ነገሩ መገንጠል በራሱ ከሆነ ቢሞክሩት የሚከፋ አይደለም፤ ሆኖም መገንጠል የታሪኩ መጨረሻ አይሆንም። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ባህላዊና ማኅበረሰባዊ እውነታ የኦሮሞንም ሆነ የሌሎቹን ሕዝቦች ችግሮች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል የታመቀ አቅም እንዳለው አምናለሁ። እንደ ማኅበረሰብ ይህን አቅም ለመጠቀምና የጋራ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችለን የፖለቲካ ብስለት ላይ ግን ገና አልደረስንም።

ሁለተኛው የጃዋር ንግግር የኦሮሞና የእስልምናን ግንኙነት፣ ከዚህ ግንኙነት የሚፈልቀው ፖለቲካዊ አንደምታ፣ እንዲሁም ሙስሊም ኦሮሞ ሙስሊም ከሆነ ሌላ ኢትዮጵያዊና ሙስሊም ካልሆነ ኢትዮጵያዊ ጋራ የሚኖረውን ግንኙነት የሚያጣቅስ ነው። ይህ ንግግር በአቀራረቡ በሚገባ የታሰበበትና የተደራጀ አይመስልም። በይዘቱም ስሜታዊነት አብዝቶ የተጫነው ነው። ጃዋር የሰነዘራቸው ሐሳቦችና “መረጃዎች” አሁንም ቢሆን አዲስ አይደሉም፤ የኖሩ ናቸው። አቀራረባቸው ግን አስፈሪ ነው። አስፈሪነቱ ከጃዋር በማልጠብቀው መንገድ የቀረበ ነው። የአፍ ወለምታ ነው ብዬ እንዳላልፈው ደግሞ ስብራት ሆነብኝ።

ኢሉ አባቦራም ላይ ይሁን ቶራቦራ ላይ፣ በቁጥር አብላጫ መሆን ሜንጫ የመምዘዝ ነጻ ፈቃድ እንደሚያቀዳጅ እንደዋዛ ሲነገር እደነግጣለሁ። ሰብአዊ ድንጋጤ። እኔም ሆንኩ ማንም ሰው ሜንጫ መዛዡም የሜንጫ ሰለባውም እንዲሆን ስላማልፈልግ። ጃዋር ያለው ነገር የትኛውንም የኢትዮጵያ ክፍል፣ ኦሮሞውን ሙስሊም ጨምሮ እንደማይወክል እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን ጃዋር እንዲህ ያለው ሜንጫ መዘዛ ተራ ክስተት የሆነበት አካባቢ ኖሮ ቢሆን እንኳን ነገሩ ሳያስደነግጠው ቀርቶ፣ ጭራሹን በአደባባይ ለሌሎች የሚሰብከው አኩሪ ስልት ሲሆን ያስደነግጣል። ነገሩ ኦሮሚያ ውስጥ በእውነት የሚፈጸም ቢሆን እንኳን ጃዋር ድርጊቱን ማውገዝ በተገባው ነበር። በጣም ሐላፊነት የጎደለው፣ አስተውሎት የተለየው እምነትና አነጋገር ነው። ሜንጫ መዘዛ ዛሬ “በሌሎች” ላይ ስለሚፈጸም ፈቃድ ከተሰጠው ነገ ለራሱ ለሙስሊም ኦሮሞ መጥፊያ መሆኑ አይቀርም።

ሌላው እጅግ በጣም አስደንጋጩ ነገር የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ብሶት” ያቀረበበትና የለካበት መንገድ ነው። ስለሙስሊሞች መገፋት በመርህና ላይ ተመስርተው የተናገሩና የታገሉ ክርስቲያኖች በሚሊዮን በሚቆጠሩባት ኢትዮጵያ በማንኛውም መንገድ የሙስሊሞች ትግል ከክርስቲያኖች ጋራ የሚደረግ አስመስሎ ማቅረብ ስሕተት ነው። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተፈጸመባቸውን ታሪካዊ በደል ማቅረብ፣ በደሉ እንዳይደገም፣ ሙስሊሞች ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው እኩል ተከብረው የሚኖሩባት አገር እንድትፈጠር መቀስቀስ የተገባ ነው። አሁን የሚፈጸመውንም በደል ማቅረብ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎችንም መደገፍ ያባት ነው። በዚህ ሁሉ ከጃዋርና ከሌሎቹም ሙስሊም ወገኖቼ ጋራ እቆማለሁ። ይህን ሲያስረዱ የሚያቀርቡትን ምሳሌ መምረጥ ግን የተናጋሪ ሸክም መሆኑን ጃዋር ዘንግቶታል፤ ወይም የታናገረው የሚያምነውን ነው። እውነት የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ቁልፍ ጥያቄና ህልም አክሱም ላይ መስጊድ መገንባት ነው? ለሌሎች ታሪክና ባህል ክብር ካለን፣ ዜጎች በተቻለ መጠን ተከባብረውና ተቻችለው እንዲኖሩ ማድረግ ቀዳሚ ፍላጎታችንስ ከሆነ በዚህ ጥያቄ ወደ ግጭት መግባት ይኖርብናል? የጃዋር ኢትዮጵያ ብትፈጠርና የፖለቲካ ስልጣን ሁሉ እርሱ በሚላቸው አይነት ሙስሊሞች ቢያዝ፣ አንዱ አጃንዳቸው አክሱም ላይ መስጊድ መስራት ነው ማለት ነው? አክሱም ላይ መስጊድ ቢገነባ ለአንድ በአካባቢው ለማይኖር ኢትዮጵያዊ ሙስሊም የሚሰጠው የድል ስሜት ከምን የሚመነጭ ነው? መካ ላይ ቤተ ክርስቲያን ወይም ምኩራብ፣ ቫቲካን ውስጥ መስጊድ ወዘተ እንዲሰራ መታገልና ማለም እውነት ሊታገሉለት የሚገባ ምድራዊ ዓላማ ነው? (ሰማያዊ ዓላማ ከሆነ ሌላ ጥያቄ ነው።) በድጋሚ እጅግ ሐላፊነት የጎደለው የተሳሳተ አስተሳሰብና አነጋገር ነው።

የጃዋርን ንግግሮች ስሰማ በተደጋጋሚ የሚታወሰኝ በቀለ ገርባ ነበር፤ በግልጽ ምክንያት። (ስለበቀለ የፍርድ ቤት ንግግር የጻፍኩትን ማስታወስ።)

ለማጠቃለል፣ ውይይቱ ስለጃዋር ከመሆን አላመለጠም። (ፖለቲካዊ) ማንነት የእቅድና የአጋጣሚዎች ድምር ውጤት ነው። ጃዋርም ማንነቱን በዚሁ መንገድ እየቀረጸ ይታያል። ጥያቄው ጃዋር አንዳንዶቻችን ያሰብነው አይነት፣ በዴሞክራሲያዊ መርሆች የምሩን የሚያምን፣ ስለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ነፃነት ሲታገልና ተረዱኝ ሲል በተራው ለሌሎች ማንነትና ፍላጎት ክብር የሚሰጥ፣ በመስጠትና በመቀበል የፖለቲካ መርህ የሚገዛ፣ ከቅርብ ነጠላ ድሎች ይልቅ ለረጅም ጊዜ ሰላምና ነጻነት የበለጠ ክብደት የሚሰጥ፣ ወይም ይህን ሁሉ የሚሞክርና የሚመኝ ይሆናል ወይስ ተቃራኒውን የሚል ነው። ጃዋርን በፊትም አሁንም ከእነዚህ አንዱንም አይደለም የሚሉ ወዳጆች አሉኝ። በፊት የነበረውም ሆነ አሁን ያለው ጃዋር ምንም ይሁን፣ የወደፊቱን ተክለ ቁመናውን መወሰን ለእርሱ ብቻ የተከለለ መብቱ ነው። እርግጥ ጃዋር እዚህ እኔ ከተመኘሁት የተለየ ሰው እንዲሆን የሚመኙና የሚጋብዙት ሌሎች ወገኖቼም እንዳሉ አውቃለሁ። ምርጫው የባለቤቱ ነው። ምርጫው የትኛውም ቢሆን ግን ስለሜንጫ መዘዛው ይቅርታ ቢጠይቅ ጃዋር ይከበርበታል እንጂ ይዋረድበታል ብዬ አላምንም። ጥያቄው መሆን አለመሆን ነው፤ አንዱን ወይም ሌላውን።

ከዚህ ቀደም እንደሆነው ሁሉ ከነልዩነቶቻችን ከጃዋር ጋራ ውይይታችንና ግንኙነታችን ይቀጥላል።

Latest from Blog

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop