April 29, 2013
23 mins read

የመለስ መታሰቢያ ተቋም (Foundation) የደቀነብን አደጋዎች! – ክፍል 1 – ከግርማ ሞገስ

ግርማ ሞገስ (girma.moges@yahoo.com)

ይኽ ጽሑፍ አራት ክፍሎች ይኖሩታል። የመጀመሪያው ክፍል ከአሚሪካ ቀድሞ ፕሬዘዳንቶች መታሰቢያ ተቋሞች ልምዶች ለመውሰድ ጥናት ያደርጋል። ሁለተኛው ክፍል የአቶ መለስ ቅርስ (Legacy) ኮሚቴ፣ ህውሃት እና እንድሪያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር) ስለ አቶ መለስ አገር ወዳድነት፣ ፓን-አፍሪካዊነት፣ ሰላም ወዳድነት እና ሰላም አምጭነት፣ የፍትህ፣ የጥሩ አስተዳደር እና የዲሞክራሲ አባትነት፣ የልማት ጀግናነት የሚያሰራጩትን ፕሮፖጋንዳ ነጥብ በነጥብ በማንሳት መልስ ይሰጣል። ሶስተኛው ክፍል ስለ አቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም አስፈላጊነት የታወጀው መንግስታዊ አዋጅ ዲሞክራሲያ አለመሆን፣ ስለ ስመ-ጥሩዎቹ የአነስታይን፣ የኖቤል እና ጆን ኦፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ተቋሞች አጫጨር ማስታወሻዎች እና የሚለግሱን ትምህርቶች፣ በወይዘሮ አዜብ ፕሬዘዳንትነት ስለሚመራው የአቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም አስፈሪ ግቦች፣ ስለ አቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም አስተዳዳሪ ቦርድ አባላት አይነት እና አስደንጋጭነት፣ ጥቂት ምክሮች ለወይዘሮ አዜብ፣ የአቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም ገንዘብ ምንጭ ህገ-ወጥነት እና ታክስ ከፋዮች ወደፊት ወይዘሮ አዜብን ህግ ፊት ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የተነትናል። አራተኛው ክፍል “ምን ይበጃል?” የሚለው ሲሆን ቀደም ብለው የተነበቡትን ሶስት ክፍሎች መሰረት በማድረግ ጸሐፊው ይበጃሉ የሚላቸውን ተግባሮች ለውይይት ያቀርባል። [መልካም ንባብ!]

ክፍል አንድ (ከአራት ክፍሎች)፥ የአሜሪካ ቀድሞ ፕሬዘዳንቶች መታሰቢያ ተቋሞች

የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዘዳንት የአቶ ቡሽ (ትንሹ) ቤተ-መጽሐፍት እና ቤተ-መዘክር ያካተተ የመታሰቢያ ተቋሙ ምረቃ ስነስርዓት በዳላስ ከተማ (ቴክሳስ) ተፈጸመ። ዕለቱ ሐሙስ ሚያዚያ 17 ቀን 2005 (25 April, 2013) ዓመተ ምህረት። ሲ.ኤን.ኤን. (CNN) የምረቃውን ፕሮግራም ማሳየት ሲጀምር እንደአጋጣሚ ቴሌቪዥን አጠገብ ነበርኩ። በፕሮግራሙ ላይ አራቱ የቀድሞ ፕሬዘዳንቶች፣ ካርተር፣ ቡሽ (ትልቁ)፣ ክሊንተን፣ ቡሽ (ትንሹ) እና ፕሬዘዳንት ኦባማ በመታሰቢያ ተቋሙ ምረቃ ስነስርዓት ላይ ነበሩ። በእንደዚኽ አይነት ፕሮግራም አምስት ፕሬዘዳንቶችን በአንድ ጊዜ ማግኘት ሁልጊዜ የሚሆን ባለመሆኑ እና ስለ አቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም በመጻፍ ላይ ስለነበርኩ ፕሮግራሙን አፍ ተልብ ሆኜ ተከታተልኩ። እንደሚታወቀው ከእነዚህ አምስት ፕሬዘዳንቶች ውስጥ ቡሽ (ትልቁ እና ትንሹ) ረፓብሊካን ሲሆኑ የቀሩት ሶስቱ ዲሞክራቶች ናቸው። ስለዚህ በመካከላቸው የፖሊሲ ልዩነቶች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በምረቃው ስነስርዓት ላይ ባደረጉዋቸው ንግግሮች ውስጥ በግልጽ ጎልቶ ይታይ የነበረው ልዩነታቸው ሳይሆን ተመሳሳይነታቸው ነበር። ሁሉም አሜሪካዊ መሆናቸው። በፖለቲካም። በተጨማሪ ከንግግሮቻቸው ውስጥ የሚከተሉትን ታዘብኩ፥ (1) አምስቱም ፕሬዘዳንቶች ስለዲሞክራሲ ሲያወሩ ዲሞክራሲ በሚለው ቃል ላይ ‘አብዮታዊ’ የሚል አጭበርባሪ ቅራቅንቦ አይለጥፉም ነበር። ለእነሱ ዲሞክራሲ አንድ እና አንድ አይነት ብቻ ነው። (2) መጠኑ ቢለያይም እያንዳንዳቸው የፖለቲካ እምነታቸውን በአገራቸው እና በህዝባቸው ላይ ተፈጻሚ በማድረግ የአገራቸውን ታሪክ አቅጣጫ ቀይረዋል። ይኽን ያደረጉት ግን ህዝቡ በነፃ ምርጫ ይሁንታውን ከሰጣቸው በኋላ ነው። የመንግስት ስልጣን የህዝብ መሆኑን በሚያረጋግጥ ነፃ ምርጫ ማለት ነው። አምባገነኖቹ መንግስቱ ኃይለማሪያም በመፈንቅለ መንግስት እና መለስ ዜናዊ ደግሞ በእርስ በርስ ጦርነት በኢትዮጵያ ስልጣን እንደያዙ እና የኢትዮጵያን ታሪክ አቅጣጫ አደበላልቀውት እንደሄዱ አስታወሱኝ። (3) የአሜሪካን መንግስትን ወክሎ በፕሮግራሙ ላይ የተገኘው ኦባማ ስለ ቡሽ (ትንሹ) መታሰቢያ ተቋም በፕሮግራሙ ላይ ከሚሰማው በስተቀር ቀደም ብሎ የሚያውቀው አንድም ነገር እንደሌለ ታዘብኩኝ። የቡሽ (ትንሹ) መታሰቢያ ተቋም ምስረታ በእሱ፣ በሚስቱ፣ ቤተሰቦቹ እና በደጋፊዎች እንደተጀመረ፣ ህንጻው የተገነባበትን መሬት እንዴት እንዳገኘ? ህንጻውን ለመገንባት 350 ሺ ያህል ደጋፊ ግብር ከፋይ አሜሪካውያን በፈቃዳቸው ከኪሳቸው እንደረዱት፣ መታሰቢያ ተቋሙን የሚመሩት እሱ እና ባለቤቱ ከመንግስት ነፃ ከሆነ ሙያተኛ ድርጅት ጋር ተቀናብረው እንደሆነ፣ ተቋሙ ትርፍ ከመስራት ነፃ እንደሆነ እና ሌሎች ጉዳዮችን በሙሉ ሲያብራራ ለእኔ አዲስ ዜና የነበረውን ያህል ለቀሩት የቀድሞ ፕረዘዳንቶች እና መንግስትን ወክሎ በፕሮግራሙ ላይ ለተገኘው ለወቅቱ ፕሬዘዳንት ኦባማም አዲስ ዜና ነበር። ስለዚህ የአሜሪካ መንግስት ከፕሬዘዳንቶች መታሰቢያ ተቋም ምስረታ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በግልጽ አየሁኝ።

ፕረዘዳንቱ በአገሩ እና በለም አቀፍ ደረጃ ለህዝብ ታላላቅ ስራዎች ያከናወነ እና ከአገሩ አልፎ በአለም አቀፍ ያሉ ታሪክ ጸሐፊዎች ሰፋፊ ምዕራፎች ቢጽፉለትም መታሰቢያ ተቋም የራሱ የፕሬዘዳንቱ፣ የቤተሰቡ፣ የራሱ ፓርቲ፣ የደጋፊዎች የግል ጉዳይ ሲሆን መታሰቢያ ተቋሙን መገንቢያ ገንዘብ ምንጭም መንግስት ሳይሆን ደጋፊዎቹ ከግል ኪሳቸው በለገሱት ገንዘብ ነበር። ይኽን ነጥብ በአሜሪካ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ዛሬም ታዋቂ እና ተወዳጅ የሆነውን የፕሬዘዳንት ሩዝቬልትን አጭር ማስታወሻ እንድንመለከት ያስገድደናል።
ፕሬዘዳንት ፍራንክሊን ዲ. ሩዝቬልት (1933-1945) የአሜሪካ ፕረዜዳንት ሲሆን አሜሪካ ትልቅ ችግር ውስጥ ገብታ ስራ ጠፋ። ህዝብ የሚበላው ጠፍቶ የሩዝቬልት መንግስት ህዝቡን ማብላት ጀመረ። ረሃብ እና ጤና ማጣት እጅግ በበረታባቸው በርካታ የአሜሪካ ከተሞች መንግስት የምግብ ማብሰያ ካምፖች መስርቶ ህዝቡን በየቀኑ መመገብ ጀመረ። ሩዝቬልት በአንድ እጁ ህዝቡን ከሞት የማትረፍ ትግል እያደረገ በዚያኑ ጊዜ ብዙ ፕሮጀክቶች ወጥኖ ፕሮክቶቹ ሲጀመሩ የህዝብ መመገቡ ስራ እዚያው ፕሮጀክቶቹ ባሉበት አካባቢ እንዲቀጥል አደረገ። ከወጠናቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ አንደኛው ብዙ ያልተገሩ ጅረቶችን የሚገሩ የኤሊክትሪክ ማመንጫ ግድቦች መገንባት፣ የኤሊክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ ይኽን የኤሊክትሪክ ኃይል በመጠቀም ለህይወት የማይመቹ ግዛቶች መብራት እንዲያገኙ፣ የአየር ጸባያቸው እንዲቀየር፣ የእርሻ ስራ እንዲጀመርባቸው እና ህዝብ እንዲሰፍርባቸው ማድረግ ነበር። ይኽ ፕሮጀክት ብዙ ስራ ፈጠረ። በዚኽ ረገድ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ተሳኩ። የዛሬዋ ዋሽንግተን ክፍለ አገር (ሲያትል) የታላቁ ኩሌ ግድብ (Grand Coulee Dam) ውጤት ነች። በረሃማው የካሊፎርኒያ ግዛት ልማት የሁቨር ግድብ (Hoover Dam) ውጤት ነው። የቴናሲ (Tennessee) ክፍለ አገር ልማት የኖሪስ ግድብ (Norris Dam) ውጤት ነው። እነዚህ ሶስቱ ታላላቅ ያልተገሩ ጅረቶችን ገርተው ለሰው ልጅ ትልቅ ጥቅም የሰጡ ግድቦች ሲሆኑ በሌሎች ግዛቶችም የተለያዩ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል። ሁለተኛው ፕሮጀክት ደግሞ ክፍለ አገሮችን የሚያገናኙ ትላልቅ ጎዳናዎች መገንባት ሲሆን ይኽ ፕሮጀክትም ለህዝቡ ብዙ ስራ ከፈተ። ሶስተኛው ሩዝቬልት የፈጸመው ታሪካዊ ተግባር ደግሞ በአገሩ ልማት እና ግንባታን በመምራት ላይ ሳለ በአለም አቀፍ መድረክ አሜርካን በሁለተኛው አለም ጦርነት መምራት ነበር። ጦርነት ውስጥ የገባው ወዶ ሳይሆን ተገዶ ነበር። አሚሪካን በማልማት ላይ ሳለ ሁለተኛው አለም ጦርነት ተቀሰቀሰ። ጀርመን አውሮፓን መውረር ስትጀምር ጃፓን በአካባቢዋ ያሉትን አገሮች ከወረረች በኋል አሜሪካን በአየር ደበደበች። የጃፓንን ቦንብ ድብደባ ተከትሎ ሩዝቬልት “ምንም ነገር አንፈራም። የምንፈርው ነገር ቢኖር እራሱን ፍርሃትን ብቻ ነው” የሚል ምላሽ በአደባባይ ሰጠ። እስከዛሬ ድረስ ዝነኛ ጥቅስ ነች። የሆነው ሆኖ ሩዝቬልት ፓርላማውን አስፈቅዶ አሜሪካን ይዞ ሁለተኛውን አለም ጦርነት ተቀላቀለ። ትረካዬን ላሳጥር። ሩዝቬልት በአገሩ ውስጥ የመራውን ልማት እና አገር ግንባታ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ የመራውን ሁለተኛ አለም ጦርነት በድል ፈጸመ። በሙያዬ የኤሊክትሪክ ኃይል እንጂነር በመሆኔ የማወቅ ጉጉት ገፋፍቶኝ ዝነኞዎቹን የሩዝቬልት የኤሊክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች እና ከግድቦቹ የሚገኘው የኤሊክትሪክ ኃይል የሚሰጠውን ጥቅም ለማየት በአሜሪካ ተጓጉዣለሁ። የኖሪስ ግድብ በቴናሲ (Tennessee) እና የሁቨር ግድብን በካሊፎርኒያ በረኃ ላይ የፈጠሩትን ልማቶች ተዟዙሬ በአይኔ አይቻለሁ። የታላቁ ኩሌ ግድብ ለዋሽንግተን ክፍለ አገር የሰጠውን ልማት ለማየት እድሉን አላገኘሁም። ግድቡን እና የኤሊክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያውን ግን በቪዲዮ አይቻለሁ። ወደፊት በአካል የማየት እቅድ አለኝ።
ይኽ ፕሬዘዳንት በአሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ እና ለመጨረሻ ጊዜ (እስከዚኽ ድረስ) የአሜሪካ ህዝብ እራሱ ህገ-መንግስቱን ጥሶ ለሶስተኛ ዘመን (ለ12 አመቶች) አሜሪካን በፕሬዘዳንትነት እንዲመራ ያደረገው ተወዳጅ ፕሬዘዳንት ነው። ፕሬዘዳንት ፍራንክሊን ዲ. ሩዝቬልት (1933-1945) ቢሮው ውስጥ ስራ ላይ ሳለ ሞተ። ለምግብ ሊጠሩት ቢሮው ሲገቡ በወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ያገኙት እሬሳውን ነበር። ለዚህ የአገሩን ህዝብ ፍቅር እና አክብሮት ላገኘው የቀድሞ ፕሬዘዳንትም ቢሆን መታሰቢያ ተቋም በመንግስት አዋጅ አልተገነባለትም። አቶ መለስ ከሩዝቬልት ተርታ የሚቀመጥ ሰው አይደለም።
‘በአብዮታዊ ዲሞክራሲ’ አገሮች ካልሆነ በስተቀር በዲሞክራሲ አገሮች መንግስት የመሪዎች መታሰቢያ ህንጻ እወጃ እና ግንባታ ውስጥ አይገባም ማለት ነው። መንግስት የአጠቃላይ አሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ አስተዳዳሪ እንጂ መታሰቢያ ተቋም የሚሰራለት ፕሬዘዳንት ደጋፊዎች ብቻ አስተዳዳሪ ስላልሆነ ከመታሰቢያ ተቋም መንግስት እራሱን ነፃ ማድረግ አለበት ማለት ነው። ስለዚኽ መንግስት ማለት የፖለቲካ ፓርቲ ማለት እንዳልሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ማለትም መንግስት ማለት እንዳልሆነ እንዲሁም በመንግስት እና በፖለቲካ ፓርቲ መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት መኖሩን ማወቅ በአምስቱም ፕረዘዳንቶች ዘንድ የሰረጸ ልማድ መሆኑን በግልጽ ታዘብኩኝ። የነበረኝ እምነት ተጠናከረ። የአቶ መለስን መታሰቢያ ተቋም አስመልክቶ በጀመርኩት ጽሑፍ ውስጥ ስከተላቸው የነበሩት መርሆዎች ትክክል መሆናቸውን ቢያንስ እነዚህ አምስት ፕሬዘዳንቶች አረጋገጡልኝ ማለት ነው።
የሆነው ሆኖ የመጨረሻ ተናጋሪ የነበረው ቡሽ (ትንሹ) በንግግሩ መገባደጃ ግድም ሰለ አሜሪካ እና ኢራቅ ጦርነት በንግግሩ ጠቀሰ እና የጦርነት ፕሬዘዳንት መሆን ግን ምኞቱ እንዳልነበር ተናገረ። ለጥቆ “ህዝባችንን እና አገራችንን የተለያዩ እንቅፋቶች ቢገጥሙዋቸውም የአገራችን ብሩህ ቀኖች ገና ከፊታችን ስለመሆናቸው ያለኝ እምነት የማይናጋ ነው” በማለት ላይ ሳለ ድምጹ ተቀየረ። የአገር ወዳድነት ስሜቱ መጥቶበት ይሁን ወይንም በስልጣን ላይ ሳለ የጦር ጊዜ ፕሬዘዳንት በመሆን በአሚሪካ እና በኢራቅ ታሪክ ላይ ያስከተለው የታሪክ አቅጣጫ ለውጥ አስዝኖት ግልጽ አይደለም። ድምጹን እና አይኖቹን መፈታተን የጀመረው ስሜቱ ሳያሸንፈው ንግግሩን ቋጭቶ አይኖቹን በእጆቹ ጠረገ። የንግግር ወለሉን ለቆ ወደመቀመጫው አመራ። ባለቤቱ ሎራ ጎን ሊቀመጥ። በአጠገቡ የነበሩት አራት ፕሬዘዳንቶች ከነቤተሰባቸው እና በመታሰቢያ ተቋሙ ምርቃት ላይ እንዲገኝ የተጋበዘው ህዝብ በሙሉ ጸጥ አለ። ቡሽ (ትንሹ) ፊቱ ላይ ፈገግታ ለማስቀመጥ እየታገለ በአንድ እጁ አይኖቹን መጥረጉን ቀጠለ።
ክሊንተን ቀደም ብሎ በተራው ንግግር እያደረገ ሳለ ለፈገግታ ከማገልገልም ባሻገር አንድ ለጥናታችን ጠቃሚ የሆነ ቁምነገር እንደ ቀልድ አድርጎ ተናግሮ ነበር። እሱም፥ “ከስልጣን በኋላ የቀድሞ ፕረዘዳንቶች ፈተና መታሰቢያ ተቋሞች በመገንባት ታሪካቸውን እንደገና ለመጻፍ መታገል ነው እያልኩ ለኦባማ ሁልጊዜ እነግረዋለሁ” የሚል ነበር። ከፊል ያህሉ ተሰብሳቢ ስቆለታል። እርግጥ ነው አንዳንድ የቀድሞ ፕሬዘዳንቶች ወይንም ጠቅላይ ሚንስትሮች ከሞቱ በኋላ መጪ ትውልድ ጥሩ ሰው አድርጎ እንዲያስባቸው መመኘታቸው አይቀርም። ያን ማለቱ ነው። ያ እንዳይሆን ከዚህ በኋላ የቡሽ (ትንሹ) መታሰቢያ ተቋም የአሜሪካ ህዝብ ንብረት በመሆኑ ማንኛውም ጉብኚ ዜጋ የፈለገውን የመመርመር ህጋዊ መብት ይኖረዋል። በመሆኑም ቀጥሎ መሆን ያለበት በመታሰቢያ ተቋሙ ቤተ-መጽሐፍት እና ቤተ-መዘክር ውስጥ ለህዝብ ይፋ የተደረጉ እና ያልተደረጉ ሰነዶችን ታሪክ ጸሐፊዎች እና ተመራማሪዎች በጥልቀት እና በስፋት መመርመር ነው። ከምርምራቸው እና ከጥናታቸው በኋላ እነዚህ ሰዎች በዜና አውታሮች አማካኝነት ወይንም መጽሐፍት በመጻፍ ከህዝባቸው ጋር ውይይት ሊከፍቱ ይችላሉ። ይከፍታሉም። ታሪክም ዳኝነቷን ትሰጣለች።
እርግጥ የአቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም ውጥን ኢላማ ያደረገው የአቶ መለስን ታሪክ አሻሽሎ ለመጻፍ ይሁን ወይንም በስኮላርሽፕ ስም ድጋፍ በመስጠት ብዛት ያላቸው ‘አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ካድሬዎች አምርቶ አቶ መለስ በህይወት ሳለ በመገንጠል፣ በባህር በር፣ በነጻ ምርጫ፣ በዲሞክራሲ፣ በሰባዊ መብቶች እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሲያራምዳቸው የነበሩትን አምባገነናዊ ፖሊሲዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ይሁን ግልጽ አይደለም። አዜብን ጨምሮ የመለስ ደቀመዝሙሮች የመታሰቢያ ተቋሙ ዋንኛ ግብ የአቶ መለስን ራዕይ ከትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ እና ማስረጽ ነው ማለታቸው በሰፊው ተዘግቧል።
ያም ሆነ ይኽ በብእዴኑ በአቶ አዲሱ ለገሰ እና በህውሃቱ በአቶ ካሳ ተ/ብርሃን የሚመራው የአቶ መለስ ቅርስ (Legacy) ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና የአቶ መለስ አማካሪ የነበረው እንድሪያስ እሸቴ (ፕሮፈሰር) በአገር ውስጥ በጉባኤዎች እና በዜና ማሰራጫዎች (ኢቲቪ እና ሬዲዮኖች) የአቶ መለስ በሳል አመራር ለኢትዮጵያ እና ለአለም ህዝብ ያበረከታቸውን ውለታዎች በማተት ህዝብ ማጭበርበር ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ክፍል አንድ ይኼን ፕሮፖጋንዳቸውን ነጥብ በነጥብ መርምሮ አጭበርባሪነቱን ለአንባቢ ያቀርባል።
[ክፍል ሁለት ይቀጥላል]

 

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop