የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ ዘልቆ በድሮንና መርዛማ ቦንቦችን በታጠቁ ጀቶች፣ በመድፍ፣ በታንክ፣ በቢኤም፣ በሞርተርና በዲሽቃ ሕዝባችንን በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፍ መንግሥታዊ ሕግ፣ የፓርቲ መርሕና አሠራር የሆነባት አገር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፤ በዚህም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ ልቡናዊ ምስቅልቅል ውስጥ ከቶታል።
እንዲህ ዓይን ያወጣ የዘር ጭፍጨፋ ላይ የተሰማራውን የማፍያ ስብስብ በማጋለጥ ሰብዓዊ፣ ኅሊናዊ ግዴታን ከሚወጡ ልዩ ልዩ ተቋማት መካከል ሚዲያ አንዱ ነው። ሚዲያ የአንባገነኖችን አረመኔያዊ ግብር በአደባባይ በመግለጥ ለኅልውና፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለነጻነት የሚደረጉ ትግሎችን በመምራት በኩል ቁልፍ ሚና አለው። የጨቋኝ መንግሥታትን የእልፍኝ ውስጥ ጸረ ሕዝብ እቅዶች፣ የአስመሳይነት ጭምብሎቻቸውን፣ እንደ ሰማይ የራቁ፣ እንደ ነፋስ የረቀቁ እኩይ ጸረ ማኅበረሰብ የሆኑ ውስብስብ ጉዳዮችን በተለያየ ደርዝ ለሕዝብ አቅርቦ መፍትሄ ያመላክታል ሚዲያ። የአማራ ሕዝብ ሥርዓታዊ የመከራ ቋጥኝ ተጭኖት፣ ዘሩ እንዲጠፋ መንግሥታዊ አጥር ተሰርቶለት አስከፊ የመከራ ወቅቶችን በመግፋት ላይ እንደሚገኝ ያደረ ሐቅ ነው። ሕዝባችን በዚህ ሰዓት የሚደርስበትን ግፍና መከራ ለዓለሙ ማኅበረሰብ ሁሉ በማጋለጥ ሚዛናዊ፣ ሐቀኛ መረጃዎችን በማቅረብ ሁሉም ለነጻነቱ እንዲታገል የበሰሉ ምክረ ሃሳቦችን ከሚያቀርቡ ሚዲያዎች መካከል መረጃ ቴሌቪዥን ግንባር ቀደሙ ነው።
አማራው ሰማይ ተደፍቶበት፣ መንግሥታዊ ጠላት ተነስቶበት፣ ዓለም ሁሉ ፊቱን አዙሮበት ባለበት በዚህ ክፉ ዘመን መከራችንን ለዓለምና ለሕዝብ ሲያደርስልን የቆየው መረጃ ቴሌቪዥን፣ መንግሥት መር የዘር ጭፍጨፋው ተጠናክሮ በቀጠለበት ሰዓት በውል ባላወቅነው ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ መሆኑ እጅጉን አሳዝኖናል። ሚዲያው አሁን ከሚሰጠው አገልግሎት እጅግ በደረጀ መልኩ እንዲያድግ ገንቢ አስተያየት ከመሰጠት የተሻገረ ፍላጎትም ነበረን። ምንም እንኳን ሚዲያ የራሱ መርኅ፣ አሠራር ያለው ሕዝባዊ ውግንናን ማዕከል ያደረገ፣ በአንጻሩ ግፈኞችን፣ ጨቋኞችን፣ ቀጣፊዎችን፣ ሥርዓት አልበኞችን፣ ውስብስብ የሴራ ድሮችን በተሰነደ ማስረጃ በነጻ ፈቃዱ የሚሞግት ቢሆንም በተቀመጠለት ሳይንሳዊ መርኅ ከመመራት እስከ መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁነቶች እየመረመረ፣ እያረመ ወደፊት መቀጠል የመረጃ ቴሌቪዥን ፋታ የማይሰጥ ተግባሩ መሆን ሲገባው ሥርጭት አቋርጦ መውጣቱ “ከአማራ ሕዝብ አንገብጋቢ የኅልውና ትግል” በአቋም ከመንሸራተት አሳንሰን አንመለከተውም።
ስለሆነም መረጃ ቴሌቪዥን የሚዲያው የቦርድ አባላት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የጥይት አረር፣ እሳት የሚተፉ መርዛማ የድሮን ተተኳሿች እንደ ዶፍ እየወረዱበት ለሚገኘው የአማራም ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ብለን በጽኑ እናምናለን። ነገሮቹን ሁሉ ስታስቧቸው ሞታችንን ማን ይናገርልን?፤ ቤት አልባ የምድረ በዳ ተቅበዝባዥነታችንን ማን ይዘግብልን?፤ መኖሪያ ቤታችን ሃብት ንብረታችን በእሳት መጋዬቱን ማን ያሳይልን?፤ የመሠረተ ልማት ውድመቶችን ማን ያርዳልን? ለዚህ ሁሉ ጥያቄ ምላሻችሁ ምንድነው? ምንም የላችሁም።
ዘገባው የመረጃ ቴሌቪዥን ነው