የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ሕዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት መምህርት መስከረም አበራ በተከሰሰችበት የኮምፒውተር ወንጀል ጥፋተኛ ተብላ የ1 ዓመት ከ4 ወር እስር እንደተፈረደባት ጠበቃዋ ሰለሞን ገዛኸኝ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ንቃት ሚዲያ የሚል የበይነ መረብ መገናኛ ዐውታር መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ “ኮምፒውተርን ተጠቅማ በሕብረተሰብ መካከል ዐመጽ፣ ሁከት እና ግጭት ለማነሳሳት ሞክራለች” የሚል ክስ ነበር የቀረበባት።
ከሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 19 ወራት በእሥር ላይ የምትገኘው መስከረም አበራ በዚህ ክስ ጥፋተኛ የተባለችው ከሦስት ሳምንት በፊት ሲሆን የቅጣት ብይኑን ለማንበብ ከዚህ በፊት በነበሩ ቀጠሮዎች ዳኞች ሳይሟሉ በመቅረታቸው ምክንያት ሁለት ጊዜ ቀጠሮው ተራዝሟል።
ፍርደኛዋ ከዚህኛው ክስ በተጨማሪ 52 ግለሰቦች በተከሰሱበት የእነ ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ የፖለቲካ አላማን በምያዝና በመደራጀት መንግሥትን ለመጣል በሚል የሽብር ድርጊት መፈጸም ወንጀል ክስ ተመስርቶባት ጉዳዩ በሂደት ላይ ይገኛል።