June 10, 2024
4 mins read

ከተሰወሩ 3 ወራት ተቆጥሯል!! (እየሩሳሌም ዓለሙ -አሻም)

448095691 857731069735329 4606614059049850902 n
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፌዴሬሽንና የክልል ምክር ቤት ተመራጩ ሀብታሙ በላይነህ ከተሰወሩ ከ3 ወራት በላይ እንዳስቆጠሩ እህታቸው ለአሻም ተናገሩ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በመወከል የአማራ ክልልና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባሉ ሀብታሙ በላይነህ በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ለስብሰባ በሚል ከመኖሪያ ቤታቸዉ ወደ አራት ኪሎ ባቀኑበት ወደቤታቸው ሳይመለሱ ቢሰወሩም ዛሬም ያሉበትን ማወቅ እንዳልተቻለ እህታቸው ደብሪቱ በላይነህ ለአሻም ነግረዋታል፡፡
የምክር ቤት አባሉ በ2013 ዓ.ም በተካሄደዉ 6ተኛው ዙር ምርጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)ን በመወከል በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ከቋሪት ምርጫ ክልል አሸንፈዉ የክልሉና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባል በመሆን እስከተሰወሩበት ቀን ድረስ በስራ ላይ ነበሩ፡፡
እህታቸዉ ደብሪቱ በላይነህ ለአሻም እንደነገሯት ከሆነ ባለፉት ሶስት ወራት ከሚኖሩበት ወረዳ እስከ አዲስ አበባና ፌደራል ፖሊስ መፈለጋቸውን፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ጭምር አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ነው የሚባል ፍንጭ ሳይገኝ 3 ወራት አልፈዋል ይላሉ፡፡
‹‹ ሀብታሙ በላይነህ አንድ ግለሰብ አይደለም፤ በስሩ መርጦ ለምክር ቤት የወከለዉ ህዝብ አለ ›› የሚሉት ደብሪቱ ይገኝበታል ሲሉ የገመቷቸው ተቋማት ሁሉ ደጅ መጥናታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና እንደራሴው የት እንደገቡ ማወቅ አልተቻለም፡፡ መንግስት ያሉበትን በማሳወቅ እንዲተባበረን ሲሉ ተማጽነዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖለሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንዳር ማርቆስ ታደሠ መረጃው እንደሌላቸው ጠቅሰው ማንኛውም የቤተሰብ አባል ‹‹ ሰው ተሰውሮብኛል በሚል ጥቆማ ከመጣ ክትትል እንደሚያደርጉ ›› በመጥቀስ በውል ሀብታሙ በላይነህ የት እንደሚገኙ መረጃው እንደሌላቸው ለአሻም ነግረዋታል፡፡ ወደ ፊት በክትትል ከደረሱበት ለቤተሰብም ሆነ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ግን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄይላን አብዲ በበኩላቸው ይህን የሚመለከተው የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም፡፡
በተመሳሳይ ይሄዉ ጉዳይ የተነሳለት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣዉ መግለጫዉ አስገድዶ መሰወርና አስሮ ማቆየት በሚል ንዑስ ርእስ ስር ተጠናቅሮ በሪፖርቱ ይፋ ማድረጉን የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ሚዛኔ አባተ(ዶ/ር) ለአሻም በማስታወስ ነግረዋታል፡፡
በእለቱ ባወጡት ሪፖርትም በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸሙ እገታዎችና ስወራዎችን እንደሚጠቃልል በመግለጽ፤ እነዚህ ችግሮች እልባት እስከሚያገገኙም ክትትላቸዉ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop