February 15, 2024
21 mins read

የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እና የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት (ክፍል -፩-)

In the early 1970s, a growing student movement sought to overthrow the Ethiopian Emperor Haile Selassie and usher in democratic rule. The emperor was instead replaced by a military dictatorship. (Submitted by Tamara Mariam Dawit)
እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን ለማውረድ እና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ለማምጣት የተማሪዎች እንቅስቃሴ እያደገ መጣ። በምትኩ ንጉሠ ነገሥቱ በወታደራዊ አምባገነንነት ተተኩ። ( ታምራት ማርያም ዳዊት አቅርቧል)

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

(ይህ ጽሑፍ ማስታወሻነቱ፤ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት የማይዳሰሱ ቅርሶች /Intangible Heritage/ ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ የኢትዮጵያና አፍሪካ ታሪክ ተመራማሪ፣ ተቆርቋሪ ለነበረው ለወዳጄ፤ ለነፍሰ ኄር አቶ ኃ/መለኮት አግዘው እና በቅርቡ በሞት ለተለየን፤ ‹ለታሪክ አዋቂውና ለታሪክ ነጋሪው› ለነፍሰ ኄር፣ ገነነ መኩሪያ/ሊብሮ ይሁንልኝ)፡፡

Walelign Mekonnen (left) and his brother Getachew Mekonnen 1967
ዋለልኝ መኮንን (በግራ) እና ወንድሙ ጌታቸው መኮንን

 

‹‹… ይኸው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት፣
የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት…!!››

ee9a9cef423e7d3c0dbe0a8c34969cda
Birhanmeskel reda,walelegne, Getachew maru and Martha Mebratu- all mrtyers.

(አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ አዛውንቱ ዶክተር ኃይሉ አርዓያ- በዛን ጊዜው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ/የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት በ1950ዎቹ ስለኢትዮጵያ ከቋጠሩት ስንኝ/እንጉርጉሮ የተወሰደ፤)

በዘንድሮው፣ በያዝነው ወርኻ የካቲት የ1966ቱ የኢትዮጵያ፣ ሕዝባዊ አብዮት ከፈነዳ 50ኛ ዓመቱን ይደፍናል፡፡ ይህን ተከትሎም አንዳንድ ሰዎች፤ ‹‹ይህ ሕዝባዊ የኾነ የኢትዮጵያ አብዮት ተገቢው ታሪካዊ ስፍራና ክብር ተሰጥቶት በቅጡ ሊዘከር፣ ሊታሰብ ይገባዋል እኮ…?!፤›› የሚል እንድምታ ያለው አሳብ እዚህም እዚያም ሲነሳ ታዝቤያለሁ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ፣ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር)፤ የዚህ የ66ቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት በቅጡ ለማሰብና ለመዘከር እምብዛም እንቅስቃሴ ባለማስተዋሉ ነገርዬው አብከንክኖት ይመስላል፤ በአማርኛው ቢቢሲ ድረ-ገጽ ላይ፤ ‹‹የኢትዮጵያ አብዮት 50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓልን የመዘከር ፋይዳ›› በሚል አርእስት ቁጭት አዘል ሰፋ ያለ ጽሑፉን አስነብቦናል፡፡

343f23011d9e6dbef5ac75a72b7cde3b

የአብዮቱ ጉዞ ፍጻሜ ምንም ይሁን ምንም ይህ አብዮት በአገራችን ትልቅ የኾነ የታሪክ ምዕራፍን የከፈተ፣ ከፍተኛ የኾነ ሕዝባዊ መሠረት የነበረው፣ የብዙ እልፍ ወገኖቻችንን እንባ፣ ላብና ደም ያስገበረ አገር አቀፍና ስር ነቀል የለውጥ እንቅስቃሴ መሠረት፤ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የታሪክ አካል ስለኾነ በቅጡ ሊዘከር፤ ሊታወስ ይገባዋል፤ የሚል የመከራከሪያ አሳቦችን በጥቂቱም ቢሆን ሲዘዋወር እያስተዋልን ነው፡፡

Students protest in Addis Ababa, Ethiopia, September 17, 1974, against the military committee that seized political power last week. Photograph: AP
ባለፈው ሳምንት የፖለቲካ ስልጣን የተቆጣጠረውን ወታደራዊ ኮሚቴ በመቃወም በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ መስከረም 17 ቀን 1974 ተማሪዎች ተቃውሞ አሰሙ። ፎቶ፡ ኤፒ

ከ10 ዓመታት በፊት የ1966ቱ አብዮት 40ኛ ዓመትን አስመልከቶ ይህ ሕዝባዊ አብዮት በተለያዩ ዝግጅቶች መዘከር ወይም መከበር እንደሚገባው ይሟገቱ የነበሩ ሰዎችንና ጸሐፊዎችን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲሁም በማኅበረሰብ ድረ-ገጾች ይህንኑ የኢትዮጵያ አብዮት ለመዘከር አንዳንድ ሰዎች አዲስ ድረ-ገጽን ያስተዋወቁም ነበሩ፡፡

እነኚህን ሰዎችና ሐሳባቸውን የደገፉ ሌሎችም ይህን ገጽ በመቀላቀል፣ በማስተዋወቅና እንዲሁም የ1966ቱ አብዮት በተመለከተ በእጃቸው የሚገኙትን ማንኛቸውንም ዓይነት የጽሑፍ፣ የምስል፣ የኦዲዮና የቪዲዮ መረጃዎችን በመለጠፍና በመለዋወጥ ፈቃደኛ መሆናቸውን ከመግለጽም ባሻገር፤ ስለዚሁ ሕዝባዊ አብዮት ያለንን እውቀትና መረጃ ከፍ ለማድረግ በማሰብ ይህን ገጽ መክፈታቸውን በስፋት አስነብበውን ነበር፡፡

እንደ ታሪክ ተማሪነቴም እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ፤ ይህ ትውልድ የትናንትናው ትውልድ ለውድ አገሩና ለወገኑ ስለነበረው ተቆርቋሪነት፣ ሕልምና ርእዩ፣ ብሩሕ ተስፋው፣ ስለከፈለው መሥዋዕትነት፣ ስለ መንፈስ ጽናቱና ብርቱ ተጋድሎው፣ ስለ ጀብደኝነቱና ቆራጥነቱ፣ ስለ አንድነቱና ልዩነቱ፣ ስለልማቱና ጥፋቱ፣ ስለሕይወት ፍልስፍናው፣ ርዕዮተ ዓለሙና እምነቱ፣ ስለ ተጓዘበት ረጅምና ውስብስብ የታሪክ ጉዞው.. ወዘተ. በሚገባ ለማወቅ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ብዙዎችን ያስማማል ብዬ አምናለሁ፡፡

እናም ያገባናል፣ የታሪኩ አካል ነን የሚሉ ሁሉ አብዮቱንና የትናንትናውን ትውልድ በተመለከተ የዛሬው ትውልድ በሚገባ የሚያውቅበትና በሰከነና በረጋ መንፈስ፣ በቅንነት፣ በጨዋነት የሚወያይበት የተለያዩ መድረኮች ደግመው፤ ደጋግመው ቢያዘጋጁ በግሌ መልካምና የሚገባም ነው እላለኹ፡፡ የምክክር ኮሚሽኑም በሀገራችን ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የ66ቱ ሕዝባዊ አብዮት ካለው ትልቅ ስፍራ አንፃር ይህን የ66ቱን አብዮትና ተያያዥ ጉዳዮችን በትልቁ ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 

የ‹‹ያ ትውልድ›› የታሪክ ማስታወሻዎች

red EPRP

ባለፉት ሠላሳና ዐርባ ዓመታት ውስጥ፤ የዛን ትውልድ ትግልና አብዮታዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ የዛ ትውልድ አባላት ለመጻፍ ሞክረዋል፡፡ የኢሕአፓው ክፍሉ ታደሰ፤ ‹‹ያ ትውልድ›› ቅጾች፤ የአንዳርጋቸው አሰግድ፤ ‹‹የመኢሶን ታሪክ በአጭር የተቀጨው ረጅሙ ጉዞ››፣ የሕይወት ተፈራ፤ ‹‹ታወር ኢን ዘ ሰካይ››፤ የአምባሳደር ታደለች፤ ‹‹ዳኛው ማነው››፤ የባቢሌ ቶላ፤ ‹‹ቱ ኪል ዘ ጄኔሬሽን/የትውልድ እልቂት››፤ በሚል ርእስ ያስነበቡን መጻሕፍት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እንዲሁም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ የዛ ትውልድ አባላት ምሁራንም በዩኒቨርስቲዎች፣ በበርካታ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና የውይይት መድረኮች ላይ፤ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴንና ያን ተከትሎም ስለተከሰተው የ66ቱ ሕዝባዊ አብዮት በርካታ የጥናት ወረቀቶችን አቅርበዋል፡፡

እንደእነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ተሻለ ጥበቡ (ዶ/ር)፣ ገብሩ ታረቀኝ (ዶ/ር)፣ ኢንጀነር ኃይሉ ሻውልን የመሳሰሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች የተማሪውን እንቅስቃሴና ይህንንም ተከትሎ ስለተከሰተው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ያለንን መረጃና ዕውቀት ሊያሰፋ የሚችል የራሳቸውን የኾነ ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ አስተዋፅዖ አድርገዋል ማለት ይቻል ይመስለኛል፡፡

በተጨማሪም፤ ‹‹ከፈረሱ አፍ›› እንዲሉ፤ የደርጉ ዋና ሊቀመንበርና የኢሕዲሪ ፕሬዚደንት የነበሩት ጓድ፣ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም፤ ‹‹ትግላችን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ››፤ ቅጽ. 1 እና 2 መጻሕፍት፤ የደርግ አባልና በወቅቱ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር የነበሩት ሻምበል፣ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፤ ‹‹እኛና አብዮቱ››፤ የጓድ/የአቶ ፋሲካ ሲደልል፤ ‹‹የሻምላው ትውልድ›› በሚል ርእስ ለንባብ ያበቋቸው መጻሓፍትም- ታላቅ ሕዝባዊ መሠረት ስለነበረው ስለ 1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ለዛሬውና ለመጪው ትውልድ ሰፊና ጥልቅ የሆነ መረጃን የሚሰጡን ናቸው፡፡

የእርስ በርስ መወቃቀሱና መፈራረጁ ማብቂያው መቼ ይሆን…?!

ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ፤

ለሀገር ብልጽግና ለወገን መከታ፡፡››

(በዘመኑ ይዘመሩ ከነበሩ አብዮታዊ/ሕዝባዊ መዝሙሮች አንዱ)

በእርግጥ በአብዛኛው ስለትናንትናው አብዮተኛ ትውልድ ሲነሳ በአንዳንዶች ዘንድ ጎልቶ የሚሰማው አፍራሽነቱ፣ የጥላቻና የእርግማን ድምፅ ነው፡፡

በአንጻሩም ደግሞ፤ የትናንትናው ትውልድ አባላቶችም፤

‹‹… ይህ ወኔ ቢስ ትውልድ›› በምን ሂሳብ ነው ያን ተራራ፣ ቁልቁለትና ዳገት ሳይበግረው፣ የመከራ ውርጅብኝና ናዳ ወኔውን ሳያላላው፣ ረሃቡና ጥሙ፣ ስደትና መንገላታቱ ሳይፈታው፣ የአምባ ገነኖች ጭካኔና ‹የቀይ ሽብር ይፋፋምብን!› ዘግናኝ እልቂትና የጠራራ ፀሐይ ነፃ ርምጃ ቅንጣት ሳያስፈራው፣ ከሞት ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጠ፣ እንባውን፣ ላቡንና ደሙን ለአገሩና ለወገኑ የከፈለን፣ ያን ለነፍሱ እንኳን ያልሳሳውን ‹ተራራን ያንቀጠቀጠ› ጀግና ትውልድ በጎሪጥ ለማየት፣ ለመተቸትና ለመውቀስ ምን የሞራል ብቃት አለው፤ እንደምንስ ይህን ለማለት ይደፍራል?!›› የሚል ድምፅ አብዝቶ ይሰማል፡፡

‹የጥላቻና የመጠፋፋት ፖለቲካ› በእጅጉ የሰለቸውና ያማረረው የዛሬው የእኔ ትውልድም፤

‹‹እናንተና ትውልዳችሁ ምን አተረፋችሁልን? ከእልቂትና ከመከራ በስተቀር፣ ምድሪቱን የደም ምድር/አኬልዳማ፣ የእልቂትና የራብ ምድር የሚል ቅፅል እንድትጎናጸፍ ከማድረግ ባሻገር… ዛሬ እንኳን በሽምግልናችሁ ዘመን ‹ለይቅርታና ለዕርቅ› ልባችሁ ገና እንዳልተከፈተ ነው በአደባባይ እሳያችሁን ያለው፡፡ ዛሬም ከነጋሪታችሁ የሚሰማው ‹የበቀል፣ የጥላቻ፣ የፅንፈኝነትና የመለያያት ድምፅ› እንጂ ‹የሰላምና ዕርቅ ድምፅ› አይደለም…፤›› ሲል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዛሬም እጃቸው ረጅም የሆኑትን የዛን ትውልድ አባላቶች በብርቱ ይወቅሳል፤ ይኮንናል፡፡

ለዚህ እጅግ በመረረ ስሜት፣ ምሬትና ቁጭት ትውልዱ ለሚሰነዝረው ትችትና ወቀሳም የትናንትናው ትውልድ አባላቶች ምላሻቸው በአብዛኛው ‹‹ታሪክን የማያውቅ፣ ውለታ ቢስ፣ ምስጋና የለሽ ትውልድ›› በሚል ቁጣና ኃይለ ቃል የተቀላቀለበት እንደሆነ ነው በተደጋጋሚ የተስተዋለው፡፡

ዛሬም የትናንትናው አንጋፋ ትውልድ የዛሬውን ትውልድ ‹‹የመከነ ዘር፣ የጨነገፍ፣ ከንቱና የባከነ ትውልድ›› የሚል አንድምታ ካለው ምሬትና ቁጭት የተላቀቁ አይመስሉም፡፡ እናም በነጋ ጠባ በትውልዱ ላይ ያላቸው ምሬታቸውና ብሶታቸው ነው ጎልቶና አይሎ የሚሰማው፡፡

በአንፃሩ ቁጭትና እልህ በሚያንገበግባቸው በሌሎች በትናንትናው ትውልድ አባሎች ዘንድ ደግሞ፤

‹‹ለፍሬ ይሆናል ያልነው የደከምንበት ዘራችን ዋግ፣ ኩብኩባና ተምች መታው፤ ተስፋ ያደረግነው ቡቃያችን በአረምና በአርማሞ ተውጦ፣ በእሾህ ታንቆ ከንቱ ሆነ… መና ቀረብን…›› የሚሉና በዘሩት ዘር መምከን፣ በትውልዱ መጨንገፍ/መክሸፍ ነጋ ጠባ የኀዘን፣ ቁጭትና የእሮሮ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ይደመጣሉ፡፡

በአንፃሩም ደግሞ የዛሬው ትውልድ ለአባቶቹ ወቀሳም ሆነ ምሬትና ቁጭት የራሱን መልስ እንካችሁ ከማለት ወደኋላ አላለም፡፡ ዘርታችሁ ያበቀላችሁን እናንተው ናችሁ፤ መቼም ‹‹ያልዘሩት አይበቅልምና›› ዘራችሁ መልካም በሆነ እኛም መልካም በሆንን ነበር፡፡ ‹‹ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮኻል›› አሉ በሚል አገሪኛ ብሒል ለአባቶቹ ወቀሳና ምሬት ዋጋ ቢስነትንና ከንቱነት ላይ በመሳለቅ ዛሬም ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልስ ከመስጠት አልደከመም፣ አልቦዘነምም፡፡

የበእውቀቱ ስዩም፣ ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› የምትለው ግጥሙ የተሰደሩ ስንኞች  በትናንትናውና በዛሬው ትውልድ መካከል ያለውን ይኸውን ሙግት የምታጎላ ሳትሆን አትቀርም፡፡

‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›

‹‹አያቶች!

በባዶ መስክ ተመራምረው

ጥበባቸውን

ዕድሜያቸውን

ገብረው

የጎጆ ንድፍ ሲያበጁ

አረጁ

ዘመናቸውን ፈጁ

አባቶች!

መላ ዘመናቸውን

ጎጆ በመቀለስ አሳለፉ

ሳይኖሩት አለፉ

ልጆች!

ጎጆውን ለመውረስ ሳይከጅሉ

እንዲህ አሉ

ያ’ባቶቻችን ጎጆ

ይኹን ባዶ ይኹን ኦና

በ’ኛ ቁመት

በ’ኛ መጠን

አልተቀለሰምና፡፡››

ይሄ የትናንትናውን ትውልድ ተጋድሎና ሕዝባዊ መሠረት ነበረውን የ1966ቱን አብዮት ክስተት 50ኛ ዓመቱን አስመልክቶ ‹ከታሪካችን ማስታወሻ› በመጠኑ ለመፈተሽ የሚሞክረው ይህ ጽሑፍ ዋንኛ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ከትናንትና ታሪካችን እርስ በርስ እንድንማማርና የዛሬው ትውልድ ከትናንትናው ትውልድ ከዛሬው ትውልድ ጋር መማር የሚችልበት መድረክ ሊመቻች ቢችል በሚል ቅን ምኞት ነው፡፡ ‹‹ታሪክ የትውልድ መገናኛ ድልድይ ነው፤›› እንዲሉ የታሪክ ሊቃውንቱ፡፡

በቀጣይ ጽሑፌ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴንና የ1966ቱን ኢትዮጵያን ሕዝባዊ አብዮት በተከታታይ በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

(ጸሐፊው ተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ፤ በደቡብና በምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆኑ፤ በአሁን ሰዓት ደግሞ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ/ሪሰርቸር፤ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ባለሙያ ናቸው፤ እንዲሁም Universal Peace Federation/UPF የሰላም አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፤ የሪፖርተር ጋዜጣ የረዥም ጊዜ ጸሐፊና ደንበኛ ናቸው)፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop

Don't Miss

1967-74: Ethiopia's Student Movement

የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ዋዜማ – ፫ በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

(ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. ከ 1950-1975 ‹‹…