January 6, 2024
25 mins read

አርበኝነት/ፋኖነት/ጀግንነት

Fano2 2 1

January 7, 2024

ጠገናው ጎሹ

መሠረታዊና አጠቃላይ በሆነ ትርጉሙ አርበኝነት (patriotism) ቅድመ ሁኔታን የማይጠይቅ (unconditional) የአገር (የወገን) ፍቅር ማለት ነው ። አገር (state) ስንል ደግሞ
) ህዝብን (ሰውን)
) ዳር ድንበሩ የታወቀና የተከበረ መልክአ ምድርን እና
) መንግሥት ብለን የምንጠራውን አካል አጣምሮ የያዘ ፅንሰ ሃሳብ ነው። በዚህ መስተጋብር ውስጥ ወሳኙን ሚና የሚጫወተው ህዝብ (ሰው) ነው። አገር ያለ ሰው አገር ሳይሆን ተፈጥሯዊ መልክአ ምድር ነው የሚሆነው።

አርበኝነት ከላይ የተጠቀሰው የአገር ምንነት፣ ማንነት፣ እንዴትነት እና ወዴትነት መስተጋብር ተጠብቆ እንዲኖር የማስቻልን አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ከትናንቱና ከዛሬው በተሻለ ሁኔታ ለትውልደ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ለሚደረግ የጋራ ተጋድሎ ቀድሞ የመገኘትንና  አስፈላጊውን መስዋእትነት የመክፈልን ግዙፍና ጥልቅ እሴትነት የተሸከመ ፅንሰ ሃሳብ ነው።

ለዚህም ነው ቀደምት ትውልዶች ሁሉ አገር ተደፈረችና ተዋረደች የሚል ጥሪ (አዋጅ) በቀረበላቸው ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሁሉ የመንግሥታቱን ወይም የገዥዎቹን የውስጥ ችግር በመስማት ሳይሆን በመኖር  እያወቁ ከእነርሱ የሚቀጥለው ትውልድ የራሱን ዘመን በሚመጥን የውስጥ ነፃነትና ፍትህ ሥር የሚኖርባት  አገር  ትኖረው  ዘንድ  በየዘመናቱ  የተነሳን  የውጭ ወራሪ ሃይል ሁሉ ፊት ለፊት እየተጋፈጡና በዋጋ የማይታመን መስዋእትነት እየከፈሉ ዛሬ ካላፈረስናትና ካላስፈረስናት በሚል ያዙንና ልቀቁን እያልንባት ያለችውን አገረ ኢትዮጵያ ያቆዩልን።

አዎ! አርበኝነት ሰፊ በሆነው ትርጓሜው በአንድ በተወሰነ ወቅትና ሁኔታ የሚወሰን የማንነትና የምንነት እሴት አይደለም። አርበኝነት የውጭ ጠላትን ከመከላከል  አልፎ የውስጥ ወይም የዜግነት ነፃነትን፣ ፍትህን ፣ ሰላምን፣ መተሳሰብን ፣ እኩልነትን ፣ ፍቅርን እና በአጠቃላይ እንደ ዜጋ ዜጋ እና እንደ ሰው ሰው ሆኖ የሚኖርባትን ዴሞክራሲያዊት አገር ከምኞት አልፎ እውን ለማድረግ የሚያስችል እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የምንነትና የማንነት እሴት ነው።

ፋኖነትም አገርና ወገን ከድተው ለጠላት ያደሩና የሚያድሩ ወገኖች መጠሪያ የሆነውን  ባንዳነት አጥብቆ የሚፀየፍ እና አገርና ወገን ተጠቁና ተዋረዱ በተባለበትና በሚባልበት ጊዜና ሁኔታ ሁሉ የራስንና የቤተሰብን ህይወት ለአስፈላጊ መስዋእትነት እስከ ማቅረብ የሚሄድ የአርበኝነት እሴት ነው። ይህ ድንቅ የአርበኝነት እሴት በዋናነት የሚታወቀው አገርን  ከውጭ ወራሪ ሃይል በመከላከልና በማስከበር መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ የአገር ውስጥ የፖለቲካ መታገያና ማታገያ  የመሆኑ ጉዳይ ጎልቶ የወጣው ከ1960ዎቹ የመደብ ትግል አብዮት ጋር ተያይዞ ነው። በዚህ ወቅት ነበር ፋኖ እና ባንዳ የሚሉ የተቃርኖ ሃይለ ቃሎች እየተለመዱ የመጡት ።  ያ ትውልድ የራሱ ድክመቶች ቢኖሩበትም ከነበረበት ዘመን ከሚመነጩ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር ሲታይ ፋኖነት  የአገር ወዳድነት ድንቅ መገለጫ ሲሆን ባንዳነት ደግሞ እጅግ አስከፊ የሆነ የአገርና የወገን ክህደት መሆኑ ይበልጥ እንዲታወቅ አድርጎታል ።

የዛሬው የፋኖነት ምንነትና እንዴትነት ደግሞ የራሱ ዘመን የሚጠይቀውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሰለባ የመሆንን እጅግ አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ ተጋድሎ የማስወገድና የሁሉም  ዜጎች ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ሰላም የሚረጋገጥበት ሥርዓትን እውን የማድረግ ሃላፊነትና ተልእኮ ነው። ለዚህም ነው እየተካሄደ ያለው የፋኖ ተጋድሎ ስኬታማ መሆን ካለበት ያለፉትን ውድቀቶች በራስ ድክመት መሸፈኛነት ሳይሆን በመማሪያነት እየተጠቀመን ዋነኛው ትኩረታችን ግን በዛሬው መሪር  ትግል የነገዋን ዴሞክራሲያዊት  አገር እውን ከማድረግ ላይ መሆን ይኖርበታል ማለት ትክክል የሚሆነው።

ጀግንነት (heroism)  ትክክለኛ ለሆነ የግል ወይም የቡድን መሠረታዊ መብት እና በተለይም አገራዊ ለሆነ የጋራ ነፃነት ፣ ፍትህና ክብር ሲባል ራስን አሳልፎ እስከመስጠት የሚሄድ እጅግ ድንቅ የሆነ  የተጋድሎ ውሎን የሚገልፅ ቃል ( ፅንሰ ሃሳብ) ነው። በየዘመኑ በሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ የመከረውንና የውርደቱን ዶፍ ያወረዱትንና እያወረዱ የቀጠሉትን ባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ጠርናፊ ገዥ ቡድኖችንና ግብረበላዎቻቸውን በጀግንነት  በመጋፈጥ የቁም ስቃይና የህይወት መስዋትነት የከፈሉና እየከፈሉ ያሉ ወገኖች መኖራቸው ከቶ አያጠያይቅም ።

ጥያቄው ይህንን የጀግንነት እሴት ያለንበትን ዘመን በሚመጥን አኳኋን የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ ቅርፅና ይዘት (ንቃተ ህሊና እና አደረጃጀት) አስይዘን ለማስኬድ ከምር የሆነና ጊዜን ግምት ውስጥ ያስገባ እልህ አስጨራሽ የጋራ ጥረት እያደርግን ነው ወይስ …? የሚል ነው።

ይህ የምንገኝበት የ21ኛው መቶ ከፍለ ዘመን የሚጠይቀውም ይህንኑ ደፋር የሆነ ራስን የመጠየቅና የመገምገም እና ወቅታዊ እርምጃዎችን የመውሰድ የፖለቲካ ባህልን ነው። ይህንን ተረድተንና ተቀብለን ኋላ ቀር ከሆነ የፖለቲካ ባህላችን የሚመነጩ የአስተሳሰብ ድህነትን (የንቃተ ህሊና ድህነትን)፣ በፍርፋሪ ተደላይነትን፣ አድርባይነትን፣ የግል ወይም የቡድን ቂመኝነትን፣ የሥልጣን ሽኩቻንና አጉል  ህልመኝነትን ፣ የጎጥ ልጅነት የፖለቲካ ጨዋታን ፣ ልክ የሌለው የኩርፊያ ፖለቲካን ፣ ወዘተ በዴሞክራሲያዊ የአርበኝነት/የፋኖነት ትግል ወደ በጎነት ለመለወጥ ካልቻልን የባለጌና የጨካኝ ገዥ ቡድኖችን የሥልጣን እድሜ በማራዘም የራሳችንንም የመከራና የውርደት ቀንበር  እናረዝመዋለን ።

የፋኖን ሁለንተናዊና እጅግ ፈታኝ ተጋድሎ ከፍተኛ በሆነ የፖለቲካ ማስተዋልና ጥበብ እንድናየው ግድ ይለናል የማለታችን ጉዳይ ዋነኛ ምክንያትም ይኸው ነው።

ከረጅሙ እና ከነጅግሮቹም ቢሆን ታላቅ ከሆነው የአገርነት ታሪካችን አንፃር ከምር ሲፈተሽ በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የባለጌና የጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞችን  ምንነት፣ ለምንነት፣ እንዴትነት እና ከየት ወደ የትነት በአግባቡና በጊዜው ተገንዝበን ለዚህ የሚመጥን የጋራ ትግል አለማድረጋችን መሪርና ገንቢ የሆነ የህሊና ፀፀት ቁጭት (ቁጣ) ሊያሳድርብን ይገባል ።

ከህልውና ትግል ተነስቶ ወደ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ ሊሸጋገር የሚችለውን የፋኖ ተጋድሎ እውን ለማድረግ ካልቻልን የሚገጥመንን የውድቀት አስከፊነት ለመግለፅ እንቸገራለን ።

የማህበረሰባቸውን ህልውና ከባለጌና እኩይ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ጨካኝ ሰይፍ የመታደግ ትግልን ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ (the ultimate goal of making democracy a reality) ጋር ያቆራኙትን የፉኖንና የሌሎች አጋር (ተባባሪ) ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴዎችን ገንቢነት ባለው ሂሳዊ አቀራረብና የተግባር ውሎ ለማገዝ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ሆነን ካልተገኘን  ከራሳችን የመከራና የውርደት ምንነትና ማንነት አልፎ የዓለም መሳለቂያነታችንና መሳቂያነታችን ይቀጥላል።

በሌላ አገላለፅ ለዘመናት ደጋግሞ የመውደቅ አዙሪት ሰለባዎች ሆነን የመጣንበት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ፍፃሜ ያገኝ ዘንድ የምንገኝበትን የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሚመጥን ደረጃ (አኳኋን) ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ የሚያስችለን ብቸኛው መንገድ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ነው።  የአትግደሉንና የአታጋድሉን ብቻ ሳይሆን ያለመገደልና ያለመገዳደል  ዋስትና የሚሆንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ወደ የሚያስችል አቅጣጫና ግብ ሊወስደን የሚችለውን የፋኖ ተጋድሎ  ገንቢ በሆነ ሂሳዊ አስተያየትና ተጨባጭ በሆነ ማንኛውም ግባት ማገዝ የግድ ከሚለን ጊዜና ሁኔታ ውስጥ የመገኘታችን መሪር እውነት ተረድተን ተገቢውን ማድረግ ካልቻልን ለዘመናት ከመጣንበት አስከፊ የውድቀት አዙሪት ለመውጣት ከቶ አይቻለንም።

ለዚህ ነው ገንቢነት ባለው ሂሳዊ ሃሳብና ውጤታማ በሆነ የደርጊት አስተዋፅኦ ማገዝ ለነገገ የሚባል መሆን የለበትም ማለት ትክክልና ትክክል የሚሆነው ። በእውን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደማህበረሰብ ወይም እንደ ህዝብ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ሰላም ፣ እድገት፣ ሞራላዊና መንፈሳዊ ልእልና ፈላጊዎች ከሆን ይህ የአንገደልምና የአንገዛም ባይነት ወርቃማ እድል ከእጃችን ወጥቶ ባለጌና ጨካኝ ገዥዎች የሚያዘጋጁልን የአዙሪት ወጥመድ ሰለባዎች እንዳንሆን በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል ። እልህ አስጨራሽ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎውን ይበልጥ አይበገሬ በሆነ አቋምና ቁመና ግቡን እንዲመታ የማድረግና የማስደረግ እልህ አስጨራሽ ሃላፊነትን  ለመሸከም ከመቸውም ጊዜ በላይ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ሆነን መገኘትን የግድ ከሚል ታሪካዊ ምእራፍ ላይ ነው የምንገኘው።

ማንም ጤናማ ህሊና ያለው ሰው ሊረዳውና ሊቀበለው ከሚችል እጅግ ግዙፍና መሪር ምክንያት (huge, intolerable, well-understood and recognized cause) የተነሳውን እጅግ ፍትሃዊ (powerfully just) የፋኖ ተጋድሎ  አሳንሶ ለማየትና ለማሳየት መሞከር ከእኩያን ገዥዎችና ከግብረ በላዎቻቸው ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት አያልፍም ።  አዎ! ተጨማሪ ውርደትንና መከራን  የሚሸከም ትክሻና የሚያስተናግድ ትእግሥት ፈፅሞ የለንም በሚል እየተካሄደ ያለው የፋኖዎች (የነፃነትና የፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን) ተጋድሎ ከእኛ አልፎ የዓለም ማህበረሰብ መነጋገሪያ የመሆኑ ጉዳይ በራሳችን ስንፍና እና አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ተመልሶ ከደበዘዘ ጥፋቱ የእኛው ያራሳችን ነውና ይህ እንዳይሆን እልህ አስጨራሽ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።

በአስደናቂ የሽምቅ ውጊያ ፣በጠንካራ ዲሲፕሊን ፣ ፅዕኑ በሆነ የሥነ ምግባርና የሞራል ልእልና እና በማይናወጥ የነገይቱን ዴሞክራሲያዊት አገር እውን የማድረግ ዓላማ የታጀበውን እጅግ ወርቃማ እድል በተገቢው ጥንቃቄና ፈፅሞ ወደ ኋላ በማይመለስ የአርበኝነት አቋምና ቁመና አማካኝነት ከማስቀጥል ውጭ ሌላ የግልም ሆነ የቡድን መብት፣ ነፃነትና ፍትህ እውን ማድረጊያ መንገድ ፈፅሞ  የለም ፤  አይኖርምም።

ፈፅሞ ልካቸውን የማያውቁ ባለጌ ፣ሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪዎችን አምርሮ በመታገል ከተቻለ ከምር በሆነ ፀፀትና ይቅርታ ወደ ሰብአዊ ህሊናቸው እንዲመለሱና ወደ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመሸጋገር ለሚያስችለው መንገድ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ፣ ካልሆነ ግን የዘመናት የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርዱበት ከኖሩትና እያወረዱበት ካለው  መከረኛ ህዝብ ትክሻ ላይ ወርደው በትክክለኛው የፍትህ ሂደት ትክክለኛ (አስተማሪነት ያለው) ብይን (ውሳኔ) እንዲያገኙ ማድረግን የግድ ከሚል ጊዜና ሁኔታ ላይ መሆናችን ግልፅና ግልፅ መሆን አለበት።

የሰላምን ጥቅም እና የጦርነትን አጥፊነት በደምሳሳው የሚሰብኩ ወገኖች እጅግ ጠንካራ  እና አሳማኝ ከሆነ ምክንያት (very strong and convincing cause) የተነሳውንና ትክክለኛ/ፍትሃዊ ( fair and just ) የሆነውን የፋኖ ተጋድሎ ፈፅሞ የመፍትሄ መንገድ እንዳልሆነ በመቁጠር በገዳይና አስገዳይ ገዥ ቡድኖች ሚዛን እኩል ለመመዘን ሲሞክሩ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኖል። የጦርነትን እና የሰላምን ለምንነትና እንዴትነት መሬት ላይ ካለው እጅግ መሪርና ግልፅ እውነታ ውጭ በደምሳሳው ማውገዝ ወይም ማወደስ ምን አይነት የፖለቲካ ሳይንስና ጥበብ እንደሆነ ለመረዳት ያስቸግራል።

ትክለኛ ጦርነት ( just war) የሚያካሂዱ ወገኖች የተነሱበትን በጎ (ትክክለኛ)  ምክንያትና ዓላማ እንዳይስቱ መምከር፣ ማስገንዘብ፣ ሂሳዊ ትቸት መለገስ ፣ እና አስፈላጊ ሲሆንም ማስጠንቀቅ አንድ ነገር ነው። ህልውናውና መሠረታዊ መብቶቹ  ጨርሶ ፀፀት በማያቁ ጨካኝ ገዥ ቡድኖች  የመጨፍለቃቸው  መሪር እውነት አስገድዶት ህልውናውን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለህልውናውና ለሌሎች መሠረታዊ መብቶቹ ዋስትና የሚሆነውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ሁለገብ ትግል ለማድረግ የተገደደን ወገን መግደልን፣ ማስገደልንና ማገዳደልን  እንደ ዋነኛ የፖለቲካ ሥልጣን መወጣጫና ማስቀጠያ በማድረግ ክፉ ልክፍት የተለከፉ ገዥዎች በሚቆጣጠሩት (በሚዘውሩት) ሥርዓት ሥር “ካልተደረደርክና “ሰላም” ካልፈጠርክ ትግልህ ፈፅሞ በጎ ለውጥ አያመጣም” የሚል የትንታኔ ድሪቶ የሚደርቱ ወገኖችን በአግባቡ መሞገት ያስፈልጋል።

አዎ እርግጥ ነው የነፃነትና የፍትህ ጠበቃ ነኝ እያለ ንፁሃንን በማንነታቸውና በምንነታቸው የሚገድልና የሚያሳድድ፣ የአገርን (የህዝብን) ንብረት የሚዘርፍ፣ ንፁሃንን እያገተ ገንዘብ የሚሰበስብ፣ ኢትዮጵያዊያንን እና ኢትዮጵያዊነትን  አጥብቆ የሚጠላ ፣ ወዘተ ሃይል ወይም ቡድን የጦርነት አውድን ወደ የሰላም አውድነት የሚለውጥ ባህሪና ችሎታ የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ይህንን አይነት እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ ከፋኖ የህልውና፣ የነፃነትና የፍትህ  ተጋድሎ ጋር በመቀላቀል ደምሳሳ ድምዳሜ ላይ መድረስና ሰውን ጨምሮ ማሳሳት ግን ከእውነተኛ የፖለቲካ ሳይንስና ጥበብ ጋር ጨርሶ ግንኙነት የለውም።

መከረኛው የአገሬ ህዝብ እና በተለይ ደግሞ በባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዘዋሪ ቡድኖች (ቁማርተኞች) እጅግ አስከፊና አስፈሪ የህልውና አደጋ የተደቀነበትን የአማራ ማህበረሰብ ተጋድሎን ሁሉም ልጆቿ (ዜጎቿ) መክረውና ዘክረው እውን ከሚያደርጓት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን ጋር አጣምሮ የያዘው የፋኖዎች ( የእውነተኛና ዘላቂ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን) ተጋድሎ ይሳካ ዘንድ ይሁንና ይሁን (አሜንና አሜን) በሚል ሳይሆን ትክክለኛነትን፣ ቅንነትንና ገንቢነትን በተላበሰ ሂሳዊ አስተሳሰብና አቀራረብ (critical approach and thinking) የበኩልን አስተዋፅኦ አለማድረግ እጅግ ከፍተኛ የፖለቲካ ስህተትና የሞራል ጎደሎነት ነውና ልብ ልንለው ይገባል።

ቀድምት ትውልዶች የውጭ ወራሪ ሃይልን አሸንፈው አገርን እንደ አገር ያስቀጠሉበትን የአርበኝነት ተጋድሎ ታሪክ ሳያስደፍሩ ለማስቀጠል ከሚደረግ የማያቋርጥ የጋራ ጥረት ጎን ለጎን የዚህን ዘመን ለማመን የሚያስቸግር ፓለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት  ቀንበር ፍፃሜ ለማስገኘት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ወደ የሚያስችል የታሪክ ምእራፍ እንዲሸጋገር ማድረግ በዚህ ትውልድ ትክሻ ላይ የወደቀ ተልእኮና ሃላፊነት ነው።

መሠረታዊ የሰብአዊና የዜግነት መብት አልባ ሆኖ በባለጌና በጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ፈጣሪና ዘዋሪ ገዥ ቡድኖች ቀንበር ሥር መማቀቅን (መከራና ውርደት መቀበልን) ለአገር ህልውና እና ልዑላዊነት እንደሚከፈል ውድ ዋጋ መቁጠር እጅግ የወረደና ትውልድ አዋራጅ አስተሳሰብ ነውና ከምር የሆነ ትግልን ይጠይቃል።

የዘመናችን የአርበኝነት/የፋኖነት/የጀግንነት ተልእኮ በዴሞክራሲያዊ የትግል አግባብ ለዜጎቿ ሁሉ ምቹ የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን በማድረግ የተሟላ ልዑላዊነትን የማረጋገጥ ታሪካዊ ሃላፊነት ነው።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop