አሳማ አንሁን! የሆንም ከአሳማነት ባህሪ እንላቀቅ!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የገና ጾም መፍቻ በግ እንድገዛ ቤተሰብ ጠይቆኝ ዛሬ ታህሳስ 28 ቀን ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም ጠዋት ወደ በግ መሸጫና ማረጃ ቤት ተጓዝኩ፡፡ በጉዞዌ ሰዓትም ለአምስት ሺህ ዘመናት ታሪክ ሰርተው ያለፉትንና የአሁኖችንም ፋኖዎች የሚያሞካሹትን በአንጣሩም  ባንዳዎቹን የሚወቅሱትን እንደ አዋዜ በቅኔ የታሹ ዜማዎችን መኮምኮም ጀመርኩ፡፡ ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላም ተሉካንዳው ቦታ ደረስኩ፡፡ የገደል ግማሽ የሚመስለው የሉካዳው ባለቤት ጉረኖ ውስጥ ተሰበሰባቸው በጎች እንድመርጥ እድሉን ሰጠኝ፡፡ እኔም ራቅ ብዬ እንደ ፍታውራሪ ጫኔ ኮራ ብዬ ቆሜ በመጀመርያ ሁሉንም በጎች በዓይኖቼ ቃኘሁና ቀልቤ ያረፈባቸውን ሶስት በጎች ለመፈተሽ ወሰንኩ፡፡ ከሶስቱ አንድ ለመምረጥ እንደ ዘመዶቼ የቀኝ ክንዴን በበጎቹ የፊት እግሮች መካከል እያስገባሁና ብድግ እያደረኩ እየመዘንኩ፣ ጀርባቸውንና ደንደሳቸውንም በጣቶቼና በመዳፊ ጫን ጥስቅ እያደረኩ የያዙትን የሥጋ መጠን ለካሁ፡፡ የዚህ አገር በጎች እዚህ ግባ የሚባል ላት ስለሌላቸውና ላታቸውን በመዳፌ ወደ ላይ ቼብ ቼብ እያደረኩ ባለመመዘኔ የጎደለ ነገር ተሰማኝና ትንሽ ቅር ተሰኘሁ፡፡ ከጥቂት ማሰላሰል በኋላ አንዷን መረጥኩና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ብለህ ይህችን ባርከህ አዘጋጅልኝ ስል አራጁን ጠየቁ፡፡

አራጁ የመረጥኳትን በግ መርጦ ሲጎትታት ሁሉም በጎች ዘመደ ብዙ ሰው ሲሞት የሚለቀሰውን ያህል “ብኣ! ብኣ!” … እያሉ ተብላሉ፡፡ በጎች ከእነሱ ተነጥላ በሄደችዋ በግ ሐዘን ሲብላሉ ተበጎች ጋር ታጉረው የነበሩት ጥቂት አሳማዎች ግን የሚበላ ፍለጋ ተአራጁ እግር ስር ለስር አፈሩን ማፍለሱን ቀጠሉ፡፡ ከአስራ አምስት ደቂቃዎች በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ አራጁ በጓን ባርኮና ቆዳዋን ግሽልጥ አድርጎ ሰጋውን መቆራረጥ ጀመረ፡፡ እኔም የማልፈልገውን የሥጋ ክፍል ከፈለክ ራሱ እንዲወስደው አለዚም እንዲጥለው ጠየኩ፡፡ እርሱም “ብዙ እሚፈልገው ፍጥረት እዚህ አካባቢ አለ!” አለና ቀለደ፡፡ ሞራውን ጣለው ስለው ወደ አንዱ ውሻው ወረወረው፡፡ ሳንባውን ጣለው ስለው ወደ ሌላኛው ውሻው ጣለው፡፡ አንጀቱን ጣለው ስለው እግሩ ስር ይልከሰከስ ወደ ነበረው አሳማ ጣለው፡፡ አሳማው የበጓን አንጀት እየጎተተ እንደ ጣሊያን ፓስታ ጠቅልሎ ዋጠው፡፡ የጨጓራውን ፈርስ አውጥቶ ሲዘረግፈው አሁንም አሳማው መጣና ሱፋሌ “ሊፕ ስቲክ” በመሰለው ከንፈሩ ጠራርጎ ቃመው፡፡ በበጎችና በአሳማው መካከል ያየሁት ልዩነት ገረመኝና በሐሳብ ዓለም ውስጥ ሰመጥቁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግዱን ለመጣል ቅርንጫፉን መመልመል - ይገረም አለሙ

“አሳማ የእንሰሳት ፈርስም ይበላል ማለት ነው” ብዬ አራጁን ስጠይቀው “የእርሱ ተራ እስከሚደርስ የምሰጠውን ሁሉ ይብላ!” አለና ፈገግ አለ፡፡ እኔም “ይህ አሳማ አብራው ተጉረኖ የነበረችውን በግ አንጀትና ፈርስ የሚበላው ምን አልባት በጓን እንደ ባዕድ ቆጥሯት ወይስ የአሳማ አንጀትና ፈርስም ቢሆን ይበላው ይሆን?” እያልኩ ማውጣት ማውረድ ጀመርኩ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሐሳብ ውስጥ ሳለሁ አንድ አሳማ መግዛት የሚፈልግ ወጠምሻ ኩልኩልት እንዳነቀው ተላይ ተላይ እየተነፈሰ መጣ፡፡ “ይህ ወጠምሻ ይኸንን የእኔን በግ አንጀትና ፈርስ የበላውን አሳማ መርጦ ሊያሳርደው ነው!” ብዬ ስጠብቅ እሱን ዘለለና ሌላኛውን አሳማ መረጠና እርድልኝ አለው፡፡ ወጠምሻው የመረጠው አሳማ ታርዶ የታረደው አሳማ ልፋጭ ለዚያ የበጓን አንጀትና ፈርስ ለበላው አሳማ ሲጣልለት አሁንም ሙጥጥ አርጎ የአሳማውን ሥጋ ዋጠው፡፡

እኔ የገዛሁት ሥጋ ተቆራርጦና ተጠቅሎ ተሰጦኝ ልጭን ስዘጋጅ ሌላ አሳማ ገዥ ሰው ከተፍ አለ፡፡ እኔም የዚህን አግበስባሽ አሳማ መጨረሻ ሳላይ አልሄድም በሚል መንፈስ ለመጫንና ቦታውን ለቆ ለመሄድ ተመጣደፍ ተቆጠብኩ፡፡ ቄራውን ሳለቅ ይህ ሁለተኛው አሳማ ገዥም ያንን ሲያግበሰብስ የቆዬ አሳማ ለእርድ መረጠውና አረፈው፡፡ የራሱን ዘር የአሳማ ልፋጭ ሳይቀር ዳረጎት ሲያጎርሰው  የነበረው አራጅ እዚያው ላይ አጋደመና በቃኝ ሳይል ሲያግበሰብስ የቆየውን አሳማ አረደው፡፡ የአሳማን ጨምሮ ሌሎችን እንሰሳት ሥጋ ሲውጥ የነበረው አሳማ የመጨረሻ እጣ ፈንታ እየገረመኝ የገዛሁትን ሥጋ ጫንኩና እንደ በፊቱ የፋኖን ዜማ ሳይሆን የአሳማን ተፈጥሮና የባንዳ ሰዎችን ተመሳሳይነትና ልዩነት እያወጣሁ እያወረድኩ ወደ ሰፈሬ አቀናሁ፡፡

ባንዳ ሰው እንደ አሳማ በጌታው የሚቀለብ ተንከሲስ ፍጡር ነው፡፡ ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ሁሉን አግበስብሶ በልቶም በቃኝን የማያውቅ አጋርቲ ነው፡፡ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ሁሉ አራጁ ወይም ጌታው ልፋጭ ሲወረውርለት የወደደው የሚመስለው ከንቱ ፍጡር ነው፡፡   ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ሁሉ ተሰጡት እንኳን የባእድን የራሱን ወገንና ወዳጅ እንደ አንጀት እየጎተተና እንደ ፈርስ እየቃመ  ቅርጥፍ አድርጎ የሚበላ ነው፡፡ ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ሁሉ በጌታው የሚታረድበትን ወይም ከጥቅም ውጪ የሚሆንበትን ሰዓት የማያውቅ ፍጡር ነው፡፡ ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ሁሉ ሲው እስቲል የወገኑን ሥጋ ቅርጥፍ አርጎ የሚበላ ከንቱ ነው፡፡ ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ሁሉ ሆዱ አደንቁሮት በራሱ ላይ ቢላዋ ሲፋጭ እንኳ የማይሰማ አስገራሚ ፍጡር ነው፡፡ ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ፍጥረታት ከአጠቀቡ እየተጎተቱ ሲታረዱ ደመ ነፍሱ የማይቀሰቅሰውና ድምጥ የማያሰማ እርኩስ ፍጡር ነው፡፡ ባንዳ ሰው እንደ አሳማ ሁሉ ያለፈውም ሆነ የወደፊት ታሪኩ ግድ እማይለው ህይወቱ እስክታልፍ ስለሆዱ ብቻ እያሰበ የሚኖር ህሊና ቢስ ፍጡር ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   ከአድዋ ድል ብቻ ሳይሆን ከክፉ ቀን ድልም እንማር!!  - ከ ይሁኔ አየለ

እንዲያውም በትክክለኛ ሚዛን ሲመዘኑ ባንዳ ሰው ከአሳማም የባሰና የወረደ ፍጡር ነው፡፡ አሳማ የአሳማነት ባህሪው ከአፈጣጠሩና ከተፈጥሮው  ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባንዳ ሰው ግን የአሳማነት ባህሪን የሚላበሰው እግዚአብሔር “ሰውን በአምሳላችን እንፍጠር” ያለውን ትእዛዝ እንደ ቅይድ ቦጭቆ፣ በራስ ቅሉ የተሸከመውን አይምሮና ህሊና እንደ ቆዳ ገሽልጦና የደመነፍስ ባህሪውንም እንደ ሎተሪ ቲኬት ሙልጪ አርጎ ፍቆ ነው፡፡ ባንዳ ከመካከሉ ሕዝብ ወይም ሰው ለእርድ፣ ለእስራትና ለስደት ሲጎተት የበግ ያህል እንኳ ሰብሰብ ብሎ“ብኣ! ብኣ!” የማይል እንዲያውም ታራጁና ታሳሪው እጅ ምግብ የሚቀበል ልክስክስ ፍጡር ነው ነው፡፡

ስለዚህ ሰዎች ሆይ ተፈጥሮ ህሊና ተነሳው አሳማም አንሰን ህሊናችንን እንደ ሞራ ገሽልጠን አንጣል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ተበጎች የምንጋራውን የደመነፍስ ባህሪያችንን አንፋቅ፡፡ ወገኖቻችን በአራጆች፣ በአሳሪዎችና በአሰዳጅ ጭራቆች እየተለዩ ሲታረዱ፣ ሲታሰሩና ሲሰደዱ እንደዚያ እንዳየሁት አሳማ ያላየን ያልሰማን ምስለን አፋችንን ተምግብ መትከሉን ትተን የበጎችን ያህል እንኳ “ብኣ!..” እያልን ድምጥ እናሰማ፡፡ ተአራጆች፣ ተአሳሪዎችና ታሰዳጆች እንደ ልፋጭ በሚጣልልን ጥቅማጥቅም ተደልለን ተጭራቆች ጋር የወገኖቻችን ሥጋና ደም አንብላ፡፡ የሕዝብ አራጅ ጭራቆችን ጌቶቻችን አርገን ሕዝብ እያረዱ፣ በርሃብና በበሽታ እየገደሉ የተቃጠለ አንጀትና የአረረ ልብ ሲጥሉልን እንደ አሳማ እየጎተትን የምንበላ እርጉሞች አንሁን፡፡ ሆዳችን አይናችንን አውሮን፣ ጆሯችንን አደንቁሮንና ህሊናችንንም ሸፍኖን ወገናችን በተለያዬ የመከራ ካራ ሲገዘገዝ ያላዬ ያልሰማ መስለን እንደዚያ አሳማ በልቶ መሞትን አንምረጥ፡፡ ከአሳመነት ጅል አመል ወጥተን በወገኖቻችን ላይ የሚሳለውን ቢላዋ አበክረን የምናውቅ ሰዎች እንሁን፡፡

ሰዎች ሆይ! መለኮት በአምሳሉ ፈጥሮን ሳለ በራሳችን ምርጫ አሳማ ሆነን አራጅ ወገንን አርዶ ሥጋቸውን በጥቅማጥቅም መልክ ሲጥልልን ጥሽቅም አርገን የምንውጥ አንሁን፤ የሆንም በአስቸኳይ ከአሳማዊነት ባህሪ እንላቀቅ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰማያዊ ፓርቲ ያላቻ ጋብቻ (ከይድነቃቸው ከበደ)

 

ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share