እንደ መግቢያ፤
“የኢትዮጵያ ሀገሬ ታጠቂ በገመድ፤
የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፤
ያም ልጅሽ ያም ልጅሽ፤
ያም ዘመድ ያም ዘመድ፤
ለማን ታድያለሽ … ለማንስ ይፈረድ?!
(የባህል ሙዚቃ ንግሥቷ ማሪቱ ለገሠ/እንደው ዘራፌዋ)
የኢትዮጵያና የኢትዮጵያን የታሪክና የሥልጣኔ እምብርት፤ የክርስትና እና የኢስላም ሃይማኖቶች (የርዕሰ አድባራት አክሱም ጽዮን እና የአልነጃሺ) መሠረት/መነሻ ምድር ኢትዮጵያ/አክሱም/ትግራይ፤
ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ጫፍ ተጠራርተው ብሔርና ጎሳ፤ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይለያቸው በአጥንታቸው ብዕርነት በደማቸው ቀለምነት የነጻነትን ክቡር መንፈስ ከፍ ባደረጉበት፤ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ሰንደቅ በተውለበለበባት፤ የኢትዮጵያዊነት የቃልኪዳን ውሉ በተቋጠረባት በዐድዋ/በትግራይ ምድር፤
በወንድማማች ጦርነት በአንድ ጀምበር ለወሬ ነጋሪ አንዱ እንኳን ሳይተርፉላት አምስቱም ልጆቿ/ሁሉም ማለቃቸውን ሰምታ ራስዋን ስላጠፋች፤ ኀዘን አቅሏን ስላሳታት የትግራይ/የኢትዮጵያ ምስኪን እናት ምን ምላሽ፤ ምንስ የማጽናኛ ቃል አለን…?!
በአማራ፣ በአፋር፣ በቤሻንጉል ጉሙዝ፣ በወለጋ… በሁሉም ኢትዮጵያ ምድር በጦርነት ነዲድ እየተለበለቡ በገፍና በግፍ ስላለቁትና እያለቁ ስላሉት የኢትዮጵያ ልጆች ምን እያልን፤ ምን እያሰብን ይሆን…?!
በቤተ መቅደሱ ደጃፍ ስለታረዱት ካህናት፣ ደማቸውን ውሻ ስለላሰው፣ በድናቸውን ለአውሬና ለአሞራ ሲሳይ ስለዳረግናቸው ወገኖቻችን፤ ስለተደፈሩ መነኮሳት፤ የሴትነታቸው ክብር በአደባባይ ስለተዋረደባቸው፣ ስለተጎሳቆለባቸው ምስኪን እናቶቻችና እህቶቻችን ምን ቃል፤ ምንስ አንደበት ይኖረን ይሆን…?!
የጦርነት ነጋሪት ስንጎስም፣ በወንድማማች ሕዝብ፤ በኢትዮጵያውያን መካከል የጥላቻን፤ የመለያየትን ዘር ስንዘራ የነበርን ነፍሰ-ገዳዮች/ቃኤላውያን ሆይ አሁን ገና የደም ግብራችን አልረካ ይሆን…?!
የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በኢትዮጵያ [በትግራይ] ተሰማ…!!
እነዚህ ኃይለ-ቃላት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ጥቅሶች ሲሆኑ፤ በተለያዩ ጊዜያት የእግዚአብሔር ነቢያት ስለ እስራኤል፣ ስለ ኢየሩሳሌም/ስለጽዮን ውርደት፣ መከራና ሰቆቃ የተናገሯቸው ናቸው። ጥቅሶቹ የእናት ምድራችንን የኢትዮጵያን ኀዘን፤ የኢትዮጵያውያን እናቶችን ሰቆቃ/ታላቅ ስብራት የሚገልጽ መስሎ ስለተሰማኝ ነው- ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በመተካት አካፍላችሁ ዘንድ የወደድኹት።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ [በትግራይ] ተሰማ፤ ራሔል [ኢትዮጵያ] ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን ፈጽሞ እንቢ አለች።”
(ትንቢተ ኤርምያስ ፴፩፤፲፭)።
“ድምፅ በኢትዮጵያ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ የትግራይ እናት ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትንም አልወደደችም።”
ኢትዮጵያ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የእናቶች ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአልና፤
የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ ደናግላን ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ።
ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች [የአክሱም መንገዶች] አለቀሱ፤ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ፤ እርስዋም በታላቅ ምሬት ውስጥ አለች።
በኢትዮጵያ ሴቶችን፥ በከተሞቿም ደናግልን አጐሰቈሉ፤ አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ በመቅደሱ የካህናት፣ በአደባባይም የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም።
ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ። ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ።
አቤቱ፥ ተጨንቅናል፥ አንጀታችም ታውኮብናልና፤ ተመልከት፤ ልባችን በውስጣችን ተገላበጠብን፤ በሜዳ ሰይፍ ልጆቻችንን አጠፋ በቤታችንም ሞት አለ።
ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። ስለ ወገናችን ሴት ልጆች ቅጥቃጤ ዓይናችን የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይናችን ሳያቋርጥ ዝም ሳይሉ እንባን ያፈሳሉ።
የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል፤ ዓይናችን በእንባ ደከመች፥ አንጀታችንም ታወከ፤ ስለ ኢትዮጵያ ወገኖቼ ቅጥቃጤ ጉበታችን በምድር ላይ ተዘረገፈ።
ኢትዮጵያ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው?
ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል።
እንደ መውጫ፤
አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ፣ አዛውንቱ ዶክተር ኃይሉ አርዓያ- በዛን ጊዜው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ/የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት በ1950 ዎቹ ስለኢትዮጵያ የቋጠሩት ስንኝ ለአሁኗ ኢትዮጵያም የሚስማማት ይመስለኛል። እንሆ ከዶ/ር ኃይሉ አርዓያ እንጉርጉሮ/ስንኞች፤
“… ይኸው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት፣
የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት…!!
(ሰቆቃው ኤርምያስ ምዕ. ፭)
———-
፲፯፤ አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ። ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ።
፲፰፤ ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል።
፲፱፤ አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።
፳፤ ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ?
፳፩፤ አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።
፳፪፤ ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቈጥተኸናል።
ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ሰላም ለምድራችን