የትላንቱ የፓርላማ ውሎ በብዙ አምዶች መተንተን ቢኖርበትም፤ ለዚህ መንደር ረዘም ያለ ፅሁፍ ገበያ የሌለው ቢሆንም፤ በቻልን መጠን ፍላጎቱ ላላቸው ካለፈው የቀጠለውን ሀሳብ እንዲህ ሰንደን እናዘግማለን።
በይበልጥ የሰላም ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን፦ ውስጣዊ የሰላም ጉዳዮች
ጠቅላዩ በስድስት ወሩ የመንግሥት ሪፖርት ዙሪያ ሰላምን በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ግነት በታጀቡ ቃላት መገለፁ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ ካሉ ሀቆች ጋር ከመጋጨቱም በላይ በማብራሪያቸው ወቅት የሰውነት እንቅስቃሴቸው ስለሰላም የሚያወሩ አላስመሰላቸውም ነበር።
የሆነው ሆኖ፣ ባለፉት ስድስት ወራት የገዥው ፓርቲ ውስጣዊ ቅራኔ በከፍተኛ ሁኔታ የጦዘበት፣ የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ አስኳል መሆኑ ጎልቶ የታየበት ወቅት ነበር። ኢትዮጵያም በግጭት መናጧን ቀጥላ የሀገሪቱን 85 % የቆዳ ሽፋን የሚሸፍኑትን ክልሎች የሚመሩ የክልል አስተዳደሮች በብልጽግና ውስጥ የፖለቲካ ቅራኔ አሰላለፍ ፈጥረው ታይተዋል፡፡
ሴራው በሚፈጥራቸው ፍትጊያዎች ንጹሃን ሰለባ መሆናቸውም መሬት የረገጠ ሀቅ ነበር።
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአማፂ ኃይሎች መካከል በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ በውስጥና በወሰን አዋሳኞች ዙሪያ በጦር መሳሪያ የታጀበ ግጭት ተፈጥሯባቸዋል፡፡ ከጎረቤት አገራት የሚነሱ የድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችም እንዲሁ።
ከአገሪቱ ርዕሰ መዲና 123 ኪሎ ሜትር በሚርቀው የምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች በአየር ኃይል የታጀበ የጦር ጥቃት የደረሰው በዚሁ ስድስት ወር ውስጥ ነው፡፡
በኦሮሚያ አራቱም የወለጋ ዞኖች፣ ሁለቱ የጉጂ ዞኖች፣ ቦረናና የምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ለሰሜን ሸዋ አዋሳኝ በሆኑ ከከሚሴ ልዩ ዞን የሚነሱ አማጺ ኃይሎች (አንዳንዶች OLAs Cell ቢሏቸውም ከአዋሽ አቅጣጫ የሚነሱ በአፋር ‘ዞን 3’ በኩል ሰርገው ወደልዩ ዞኑ የገቡ መንግሥታዊ ድጋፍ ያላቸው ኃይሎች ከውስጥ ካሉት ጋር ተቀናጅተው) ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን አድርሰዋል፡፡
በተለይም በጥር ወር ሁለተኛ ሳምንት በአማራ ልዩ ኃይል ጊዜያዊ ካምፕ ውስጥ በደረሰው ያልታሰበ ደራሽ ጥቃት 28 የልዩ ኃይል አባላት፣ 4 የፌዴራል ፖሊስ አባላትና 2 ሲቪሎች በድምሩ 34 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። ጥቃቱ በዚህ ሳያቆም አጣዬ ላይ በንፁሃን ላይ ጥቃት መድረሱ የጥር ወር ሐዘናችን ነበር።
በራሱ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ የኢንደስትሪ ሰራተኞችንና ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ንፁሃን ዜጎችን ኢላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችና የጅምላ እገታዎች ደርሰዋል።
በሌላ በኩል፥ በክልል መንግሥታት መዋቅር ደረጃ አፋር Vs ሶማሌ፤ ኦሮሚያ Vs ሶማሌ፤ ኦሮሚያ Vs ሲዳማ የክልል ልዩ ኃይሎቻቸውንና የአካባቢ ሚሊሻዎቻቸውን አሰልፈው መደበኛ ውጊያ እስከማድረስ ደርሰዋል፡፡
በተለይ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ግጭት ከኢትዮጵያም አልፎ ቀጣናውን ወደትርምስ ሊያስገባ የሚችልበት ዕድል እንዳለው ይታወቃል፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ ሁለቱም የኢትዮጵያ ልጆች ድንበር ተሻጋሪ ማንነቶች ያሏቸው የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ሶማሌ ሞቃዲሾ፣ ፑንት ላንድና ሶማሌ ላንድ እንዲሁም ጅቡቲ ውስጥ የቋንቋና የባህል ተዛምዶዎች አሉት፡፡ አፋር በበኩሉ ኤርትራና ጅቡቲ ካሉ አፋሮች ጋር ከድንበር ባሻገር የሚጋራቸው ማንነቶች አሉት፡፡ ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 30.3 % ያህሉን የሚሸፍነው ሶማሌ ክልል ከሦስት ሀገራት (ሶማሊያ፣ ኬንያና ጅቡቲ) ጋር፤ አፋር ከሁለት ሀገራት (ከጅቡቲና ከኤርትራ) ጋር ኢትዮጵያ በድንበር የምትዋሰንባቸው ግዛቶቿ ናቸው፡፡
የስጋት ቀለበት ውስጥ የገቡት ሁለቱ ክልሎች የኢትዮጵያ የወጭ ገቢ ንግድ ማሳለጫ የሆነው የኢትዮ-ጅቡቲ አውራ መንገድ መገኛ፤ እንዲሁም ለቀጣናው ሀገራት የብሔራዊ ደህንነት ስጋት አካል የሆነው አልሸባብ ከኢትዮጵያ ድንበር ማዶ እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡
‘አዳይቱ’፣ ‘ገዳማይቱ’ እና ‘ኡንዳፎ’ የተሰኙት የወሰን አካባቢዎች አሁንም የውጥረት ቦታዎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአካባቢው የነበረው ግጭት በአርብቶ አደሮች ደረጃ የሚታይና የግጭቱ መንስዔም ከተፈጥሮ ሃብት ሽሚያ ጋር የተገናኘ ነበር፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የታዩት ግጭቶች ግን በክልል ደረጃ ልዩ ኃይል፣ የአካባቢ ታጣቂዎችና ከመደበኛ የፀጥታ አደረጃጀቶች ውጭ ያሉ የውስጥና የውጭ የፖለቲካ ድጋፍ ያላቸው ኃይሎችም የተሳተፉበት መሆኑ የቅራኔውን የዕድገት ደረጃ ያመላክታል፡፡ ይህ ግጭት ባለፉት ስድስት ወራትም ቀጥሎ ታይቷል።
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ተመሳሳይ የግጭት ድግግሞሾች ታይተዋል።
በጃርሶ ኦሮሞ እና በገሪ ሶማሌ ጎሳ መካከል ከጥር እስከ የካቲት ቀጥሎ የታየው ግጭት በተለይም Tuuranood, Geedanood, Teero, እና Chidiile በተባሉ ቀበሌዎች የፈሰሰው ደም በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።
ይህ በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር ባሉ የክልል አስተዳደሮች የተፈጸመ መሆኑ ደግሞ ብልጽግና ውስጥ ደም እያፋሰሰ ስላለው የፖለቲካ ቅራኔ አሰላለፍ የሚያስረዳው መራር ሀቅ አለ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፥ በሶማሌ ሲቲ ዞን ምዕራባዊ ክፍል በሶማሌ-አፋር ወሰን፣ በሶማሌ-ኦሮሚያ ወሰን (ገሪ Vs ጃርሶ) ምድርን በደም ያጨቀዩ ግጭቶች፣ እንዲሁም በራሱ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ቡሌ ሆራ፣ ጉጅ የአየር ኃይል እገዛን የግድ ያሉ ግጭቶች ተፈጥረዋል።
የአዲስ አገር ማዋለጃ መሳሪያ ሆኖ በተቀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ለሁለት በመክፈል የጥቃት ዒላማ የማድረጉ ሴራን ተከትሎ በሻሸመኔ የደረሰው የክርስቲያኖች ጅምላ ፍጅትም የስድስት ወሩ ስንክሳር አካል እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም።
የሀገሪቱ ርዕሰ-መዲና አዲስ አበባ ባለፈው መንፈቅ ያለፈችበት ውጥረት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚውሉ ታዳጊ ልጆችን ሳይቀር ያስጨነቀ በመዋቅራዊ ሥርዓት አልበኝነት የተደገፈ እንደነበር ከቶውን ሊዘነጋ አይችልም። ‘ሸገር’ ይሉት የዘር ማፅዳት ፖለቲካዊ ፕሮጀትክን አልሞ የተመሰረተው ከተማ፣ የቅራኔ መከማቻ የሆነችው አዲስ አበባ ያለፈው መንፈቅ ሕማማቶቿ በርትቶ ታይቷል።
ከመሪ ድርጅቱ ውስጣዊ የጤና መታወክ አንፃር፦ የብልጽግና አባል የሆኑት ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ በፓርቲው ውስጥ ባለው የፖለቲካ ቅራኔ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካቸው ሆኖ ታይቷል፡፡ በተለይም በመበታተን ሂደት ላይ ያለው የደቡብ ክልል መዋቅር በፓርቲው ውስጥ ከሚታየው የኃይል መከፋፈል ጋር በተያያዘ መጠቀሚያ የሚሆኑ ኃይሎች እንደመታየታቸው መጠን የጎራጌ መብት ጠያቂ ልሂቃን ከሥርዓቱ ጋር ከፍ ያለ ፍች ስለመፈፀማቸው በግላጭ ታይቷል፡፡
በኦነግ ታጣቂ ኃይሎች እየተወጉ ያሉ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በበኩላቸው ለህልውናቸው ጭንቅት ውስጥ መክረማቸው አሁንም ስጋት ላይ መሆናቸው የማይታበል እውነታ ነው።
ይህን የመጭው ጊዜ ስጋት ወያኔን ወደፖለቲካ ጨዋታ ሜዳው በመሳብ በሚፈጠረው የፖለቲካ አሰላለፍ መቀየር የሚቻል እንዳልሆነ ጠቅላዩ የተረዱት አይመስልም፡፡ ለዚህም ነው የሰላም ማብራሪያው ላይ ‘ሽፍንፍን’ ‘ሽፍንፍን’ … ባሉ አቅላይ ምላሾች ለማለፍ የሞከሩት።
ለሸኔ የቀረበው የሰላም ጥሪና ምድር ላይ ያሉ ጥሬ ሀቆች
ባለፉት አምስት ዓመታት በኦሮሚያ የደረሰው ግፍና በደል ውስጥ ሞታቸው ያልተነገረላቸው ንፁሃን የኦሮሞ ልጆች አያሌ መሆናቸውን የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ያምናል። ኦሮሞ ኦሮሞ ላይ እንደዚህ ዘመን እንዳልተኮሰም እንዲሁ። በዚህ መራር እውነት ውስጥ “ባዕድ” ተብለው ሌሎች የተፈረጁ ኢትዮጵያውያን በዋናነት የአማራ ተወላጆች የበዛ የጥቃት ዒላማ ስለመሆናቸው ድርጊቱም በአንድ በኩል በረቀቀ የአፈናቃይ ተፈናቃይ ድራማ በሌላ በኩል ደግሞ በቀጥታ የጅምላ ፍጅት ንፁሃን የቅራኔ ፖለቲካ ማስፈጸሚያ ስለመደረጋቸው ከአረመኔ በስተቀር ኃይማኖት ያለው ማንም ኢትዮጵያዊ የሚመሰክረው እውነታ ነው።
ይህ ንፁሃንን ዒላማ ያደረገ የጅምላ ፍጅት መቆሚያው ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ቢሆንም ለዚህ እልቂት ታርጋ የሆነው የ OLA ኃይል ለሰላም ጥሪ ተጋበዘ መባሉ (ምንም እንኳ ፓርላማው አሸባሪ ብሎ እንደፈረጀው በሁኔታዎች ላይ ተወያይቶ ምክር ቤቱ መወሰን ሲገባው የኦሮሚያ ክልል መወሰኑ ሕግን የተፃረረ ቢሆንም ቅሉ) በበጎ የሚታይ ዜና ነበር። ችግሩ ያለው አንድም ከሸኔ በኩል የሰላም ጥሪው አልቀረበልኝም ማለቱ፤ አንድም ደግሞ የሰላም ውይይቱ ከየትኛው ሸኔ ጋር ነው የሚለው ተጠየቅ በቅጡ ያልተመለሰ መሆኑ ላይ ነው።
ፍላሚጎ ላይ የአመለካከት ተዋርሶ ያላቸውን ኃይሎች ሳንዘነጋ፣ ሸኔ አንድና ወጥነት ያለው ኃይል እንዳልሆነ ይታወቃል። በጃል መሮ፣ በጃል ሰኒ እና በጃል ፍቃዴ የሚመራ ኃይል በየቦታው አለ። ጃል መሮ ምዕራብ ኦሮሚያን ማዕከሉ አድርጎ ቀጠናውን አስፍቶ ሲይዝ፣ ጃል ሰኒ ማዕከላዊ ኦሮሚያንና የሸዋ ዞኖችን ያካልላል፣ ጃል ፍቃዴ ከጥቂት ግን የሽምቅ ውጊያ ማስተር ከሆኑ ታጣቂዎቹ ጋር ሁሮጉድሮን የሙጥኝ ብሎ ይዟል።
ይህ የሰላም ንግግር ከየትኛው ኃይል ጋር ሊጀመር እንደታሰበ አልለየለትም። ‘የጥሪ ካርዱ አልደረሰንም’ የሚለውን ሙግት በመሀል ያዙልኝ። ነገሩን ‘ብለናል’ ለማለት ካሆነ የእስካሁኑ አያያዝ ለሪፖርት አይበቃም።
ቅድሚያ ግን የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ ቁንጮ አመራሮች ከራሳቸው ጋር መታረቅ ይኖርባቸዋል። የእስካሁኑ መንገድ የነገ ተናጠላዊ ሳይሆን የቡድን ታሪካቸውን ጭምር ያበላሹ እንደሆኑ አውቆ ንፁሃንን የቅራኔ ማወራረጃ ከሚያደርግ በደም የጨቀየ የሴራ ፖለቲካ እጅን ማውጣት ይበጃል።
ከምንም በላይ ግን በሸኔ ቀውስ የሚያተርፉ ብሔርና ኃይማኖታዊ አጥር የማይገድባቸው የቀውስ ነጋዴዎች የእንጀራ ገመዳቸው ሊበጠስ የሚችለው በአካባቢው ሰላም ሲወርድ ብቻና ብቻ በመሆኑ ሰላም እንዲወርድ በጎ ምኞቴ ነው።
የአገው ሸንጎ እና የቅማንት ጉዳይ
ጠቅላዩ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በተያያዘ በሰጧቸው ማብራሪያዎች ላይ ተገቢነቱ አጠያያቂ የሆነ ማብራሪያ አንስተዋል። በማብራሪያቸው የአገው ሸንጎ እና የቅማንት ጉዳይ በሚል ሁለት ጊዜ በሥም አንስተዋል።
በእውነቱ እነዚህ ወገኖች ከOLA ም ሆነ ከወያኔ የግብር ማንነት አንፃር ጎን ለጎን ሊጠሩ የሚችሉ አይደሉም። ነገሩ አቻ ፍለጋ ካልሆነ በስተቀር።
“አገው ሸንጎ” የቤተሰብ አኩራፊ የሆኑ ወገኖች ያውም ጥቂት ወጣቶች በጦርነቱ ወቅት በወያኔ ተታለው ከቤታቸው ከመውጣታቸው ውጭ ይህ ነው የሚባል የሰላም ስጋት አልነበሩም። ለአሸባሪዎች መንገድ መጠቆም ወንጀል መሆኑን ሳንዘጋ፣ ይህም ሆኖ ባለን መረጃ መሰረት የአማራ ክልል መንግሥት ጉዳዩን በቤተሰባዊ ውይይት አርጎቦታል። የዋግ አባቶች ውለው ይግቡና ኃይማኖታዊ እሴታቸውን አስመስክረዋል፤ ወጣቶችን ከአርሶ አደር ቤተሰቦቻቸው ጋር የመቀላቀል ስራ በመሰራት ላይም ነው።
ልዩ ዞንን የቀውስ አማራጭ ዕድል አድርጎ የመጠቀም ፍላጎት ግን መቼም ሊቆም የማይችል ጉዳይ ስለመሆኑ ታውቆ ያደረ ነው። የአቻ ምስስሎሹ የዚህ ፍላጎት ቅጥያ ይመስላል- ትላንት በጠቅላዩ የታየው።
በተረፈ የቅማንት ጉዳይ ወያኔ የፈጠረው የጎንደር የአብሮነት ፈተና እንጅ ተራዛሚ የቅራኔ ምንጭ እንዳልሆ የጋራ መተማመን የተደረሰት ጉዳይ ነው። ጠቅላዩም የአብሮነት ፈተናው ቤተሰብን የረበሸ እንጅ የማያቆራርጥ እንደሆነ በቀደመ የፓርላማ ማብራሪያቸው በአደባባይ መስክረዋል። ይህ የጎንደሬዎች የአብሮነት ፈተና በጎንደሬ ማዕቀፍ እንዲፈታ ጎንደር የሰላም እና የዕድገት ማኀበር (ጎ-ሰ’ማ)ን የመሰሉ የሲቪክ ማኀበራት ከታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ወገኖች ጋር ባደረጓቸው ተከታታይ ውይይቶች፣ ከአጋር አካላት ጋር ሆነው በሰሩት ስራ ፍሬማ ውጤቶች ተገንተዋል። በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል።
የክልሉ መንግሥት ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አመራሮች ጋር በሰራው የተቀናጀ ሥራ እረቀ-ሰላም ወርዷል። ምህረቱም ገቢር ሆኗል። በርግጥ አዲስ አበባ ላይ የኮንዶሚነየም ቁልፍ የታደሉ ጥቂት ጥቅመኞች የአብሮነት ፈተናው እንዲቀጥል እንደሚሰሩ ይታወቃል፤ ነገር ግን ማኀበራዊ መሰረት እንዳይኖራቸው የሚያስችል ስራ ቀድሞ በመሰራቱ ነገሩ ‘ደሮ ብታልም ጥሬዋን’ ከመሆን አይዘልም።
በአጭሩ ከፖለቲካ ይልቅ በማህበራዊ ወጌሻ የተፈወሰን ነገር መልሶ መላልሶ ማማሰል አሁንም በአቻ ፍለጋ የመነኹለል አባዜ እንጅ ሌላ ትርጉም የለውም።
እዚህ ላይ መቀሌን በአዳማ የተካ ሥልጠና መስጠቱም ሆነ፣ በወያኔ መንገድ እግርን የመትከል አባዜ የበዛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ማስታወስ ከየዋህነት እንዳይታይብኝ። ቀየው የአጤ ቴዎድሮስ፣ ፊታውራሪ ገልሞ እና ፊታውራሪ ገብርዬ አንድ የመሆን የአንድነት መንፈስ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ በጎ ውርስ የተረፈበ ነውና!!
ለዛሬ መውጫችን
የትላንቱ የፓርላማ ውሎ የፌዴራል መንግሥቱ ከጋርዮሽ አመራር ይልቅ ወደ አንድ ፍጹማዊ ግለሰባዊ ጠቅላይ አመራር ስለመምጣቱ በአደባባይ የመጨረሻው ማረጋገጫ ሆኗል። በተለይም አምባገነን ለመሆን የቀረቡት ማስገንዘቢያዎች ውሃ ካለመቋጠራቸውም በላይ በሰውየው አንደበት በድጋሚ የተነሱ መሆናቸው ኢትዮጵያን ከዋሻው ጫፍ ብርሃን የማይታይባት አስመስሏታል።
ይህ ከውስጥ ችግሮቿ በመነጨ በአካባቢው ፖለቲካ ተደማጭነት የማጣትና ለውጭ ኃይሎች የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነት በሯን ለከፈተችው ኢትዮጰያ ከባድ ጊዜ ነው፡፡
ደጋግመን እንደምንለው ኢትዮጵያ የጋራችን መሆን ካልቻለች የማናችንም ልትሆን አትችልም!!
እናም ያለፍንበትን ስህተት ላለመድገም ብሎም የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥትን ከፍርሰት ለመታደግ፤ ችግሩን በመሠረታዊነት ለመፍታት የፖለቲካ ብልሃት፣ አካታችነት፣ ስትራቴጂያዊ ዕቅድና ጽኑ ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡
በኃይማኖት ይሁን በብሔርተኝነት ጉዳዮች ሞት የማይፈሩ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያፈራቸው ኢትዮጵያ የቅራኔና የግጭት ጉልህ ዝንባሌዎቿን ከየትም አላመጣችውም፡፡ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ የታየው የታሪክ አተረጓጎም ግጭትና ቅራኔ ላይ የሚያነጣጥር በመሆኑ ተጠፋፊ አጀንዳዎችን መሸከም የማይፈቅድ አማካይ የፖለቲካ ማዕቀፍ ማንበር ብቸኛው የኢትዮጵያ መዳኛ መስመር ነው፡፡
***
ነገር ግን… ወጥመድ ውስጥ መክተት፣ ፍርሃት መፍጠር፣ ጥርጣሬ መዝራት፣ ማዘናጋት፣ ማሳሳት፣ ማታለል፣ ማዳከም፣ ማስጨነቅ፣ ግራ ማጋባት፣ ጊዜ በመግዛት አድብቶ መምታት፣ … የትግል ስልት ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ የኢትዮጵያ ህልውና፣ የዜጎቿ ዕጣ ፈንታ ከድጡ ወደማጡ ይገባል። መቼስ 120 ሚሊየን ስደተኛ የሚሸከሙ ጎረቤቶች እንደሌሉን እኛም፣ ጠቅላዩም፣ ሰይጣኑም፣ የምናውቀው ነው!
***
ኢትዮጵያን ከአማራ ሕዝብ ልብ ውስጥ ማውጣት እንደማይቻለው ሁሉ፤ ዋጋ ሲከፍልላት ከኖረው ከሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ውስጥም ማንም ሊፍቃት አይችልም። በሌሎች የማንነት ቡድኖች (ብሄረሰቦች) ውስጥም እንዲሁ። የማወራው ስለሰፊው ሕዝብ ነው!!
ችግሩ ያለው በልሂቃን መካከል አልበርድ ያለውን ተጠፋፊ አጀንዳ አምራችነትን ከፖለቲካ ገበያው የማራቅ ፍላጎት ከመኖር አለመኖሩ ጋር የሚገናኝ ነው። ችግሩ ያለው አንዱ ሌላውን በትኜ እኔ በሰላም እኖራለሁ ከሚለው ተንሳፋፊ ምኞቱ ላይ ነው። ችግሩ መንበሩን የያዘው አካል በጥይት መጋዝኑ ውስጥ ካለው ተተኳሽ በላይ ለነፃነታቸው የሚሰው ግፉዓን እንዳሉ አምኖ ካለመቀበል ጋር የተያያዘ ነው።
‘ተረኛ ነን ባገሩ ላይ እንዘዝበት’ የሚለው የወቅቱ መሮጫ ትራክ በመጠላለፍ ውስጥ ከሪባኑ በፊት የሚያጠፋፋ እንጅ ተናጠላዊ አሸናፊ የሚረጋገጥበት አይደለም።
በበኩሌ፥ ቤተኛነትና ባይተዋርነት ሳይሰማን፤ አንዱ ቀናዒ አሳቢ ሌላው ልዩ ተጠርጣሪ መስሎ የማይቀርብባት፤ እንደግንዛቤችን ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ሆና እንድትቀጥል እሻለሁ። ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ “Those who do not remember the past are condemned to repeat it” የሚለውን የጆርጅ ሳታየንን አባባል በማስታወስ እንደማይጠቅም እናስረግጣለን።
ፈይሳ ምሽት