March 29, 2023
5 mins read

ጀግኖችን አለማክበር ሌሎች ጀግኖች እንዳይወጡ እንቅፋት ነውና አፈናው ይቁም! – እናት ፓርቲ

General Tefera Mamo 1 1

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በየትኛውም መመዘኛ ሰብዓዊ መብቶች ለድርድር የማይቀርቡ ተፈጥሯዊ መብቶች መሆናቸው በዓለም አቀፍ ሕግጋት የተደነገገ ሲሆን በሀገራችን ሕገ መንግሥት ውስጥም ተካቶ ይገኛል፡፡ ይኹን እንጂ በሀገራችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለይ ላለፋት ሃምሳ ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፋ ኹኔታ እየተፈጸመ የሚገኝ ሲሆን ከዚሁ እኩይ ልማድ መላቀቅ ባለመቻሏ በህመም የሚሰቃዩ ዜጎችን ሕክምና እስከመከልከል የደረሰ ዜጎቿን በጭካኔ አለንጋ የምትገርፍ ሀገር ሆናለች።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ሀገር የሕልውና አደጋ ውስጥ በገባችበት ወቅት መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው በሙያቸው ለማገልገል የሕይወት ዋጋ ሊያስከፍል የሚችለውን ተልእኮ ተቀብለው ዋጋ ከከፈሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በከፍተኛ ሕመም እየተሰቃዩ መሆኑን ከቤተሰባቸው ጭምር መረጃ አግኝተናል፡፡ ሕክምና ካላገኙ ሕይወታቸው ጭምር አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል መገንዘብም ችለናል። ጀኔራሉ ሕመማቸው በጦርነቱ ወቅት በጥይት በመመታታቸው ከደረሰ ተደጋጋሚ ጉዳትና ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት በውል ሊታከሙት ካለመቻላቸው ጋር የተያያዘ መሆኑንና በሀኪሞች ቦርድ ምክርና ምሥክር መሠረት የግዴታ የውጭ ሕክምና ማድረግ እንዳለባቸው ቢረዱም መታከም እንዳይችሉ በመንግሥት መከልከላቸውን ገልጸዋል።

እኒህና መሰል ለሀገር መጽናት በሕይወታቸው ተወራርደው ዋጋ የከፈሉ የሀገር ባለውለታ ጀግኖችን በሚገባቸው ልክ ክብር መስጠት ባይቻል እንኳን በደረሰባቸው ጉዳት ከሚያሰቃያቸው ሕመም ለማገገም በራሳቸው ወጪ ሕክምና እንዳያገኙ መከልከል ሀገር ተቆርቋሪ እንድታጣ የሚያደርግ፣ “ነግ በኔ” የሚያስብል፣ ጀግኖች በከፈሉት ዋጋ እንዲኮሩ ሳይሆን እንዲያፍሩበትና “ምን ባጠፋ ነው?” እያሉ እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ ስሑት አካሄድ ነውና በጊዜ ሊታረም ይገባል።

በሌላ በኩል ለሀገር ሊከፈል የሚገባ የመጨረሻ የሆነውን የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ የሀገር ባለውለታዎችና ቤተሰቦቻቸው የሚገባቸውን ያህል ክብር ባይቸራቸው ቢያንስ ግን ዋጋ በከፈሉላት ሀገር በሕይወት የመኖርን ያህል መንግሥት ሊያከብረውና ሊያስከብረው የሚገባ ሰብዓዊ መብት ሊነፈጉ አይገባም። ጀግኖቻችንን በገፋን ቁጥር ኢትዮጵያችን ጀግኖቿን እያጣች መጭውም ትውልድ አርዓያ ሰቡን እያጣ ጠላትን ከወራሪ የሚመክት ተቆርቋሪ ትውልድ ማፍራት እንዴት ይቻላል?!

ስለሆነም መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ ተቆጥቦ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ ሕክምና እንዲያገኙ እንዲፈቅድ ፓርቲያችን በአጽንዖት ይጠይቃል። በሌላ በኩል እኒህን መሠል ዋጋ የከፈሉ ጀግኖችና ቤተሰቦቻቸው ከያሉበት እየተፈለጉ የሚዲያ ትኩረት እንዲሰጣቸው፣ መንግሥት በቂ የሆነ መዋቅራዊ እገዛ እንዲያደርግላቸው እና ሕዝብም ጀግኖቹን በብርታታቸው ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግራቸውና በድካማቸው ጊዜም አለኋችሁ እንዲላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

እናት ፓርቲ

መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop