ሁላችንም እንደምንገነዘበው በአሁኑ ጊዜ ሕዝባችንን እርስ በርስ እያነካከስ ያለው የብሔርና የሃይማኖት ቅራኔ መሆኑ ግልጽ ነው። የብሔሮች የራስን እድል በራስ የመውሰንና፣በቋንቋ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር የጸደቀ፣ብዙዎች ሕዝቦች፣ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃ የወጡበት መርህ ነው። በአገራችንም ጀብሓ፣ ሻቢያ፣ ሕወሐት፣ ኦነግና የመሳሰሉት የተመሠረቱት፣ብሔራቸውን ነፃ ለማውጣት ነበር።
ይህም የነፃነት ትግል፣ በተለይ ከፊልስጤምና ከእስራኤል ቅራኔ የተነሳ፣ በሊቢያ፣ በግብፅ፣ በሱዳን፣ በሱማሊያና በአረብ አገሮች ይደገፍ ነበር።ስለሆነም ቅራኔው ሰፍቶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከዲስ አበባ ላማስነሳት ጥያቄ ቀረበ። በዚህም ጃንሆይ ደንግጠው ከእሥራኤል ጋር የነበራቸውን የዲፖሎማሲ ግንኙነት አቋረጡ። በአስመራ የሚገኘውንም የአሜሪካን ጦር ሰፈር ዘጉ።ሰለሆነም ንጉሱ ከውስጥም ከውጭም ደጋፍና ተባባሪ አጥተው ለወታደሮች እጃቸውን ሰጡ።
ወታደራዊ መንግሥትም ሥልጣን እንደ ያዘ፣ ጄንራል አማን አምዶምን ወደ አስመራ ልኮ፣ከሸብያና ጀብሓ ጋር ድርድር አካሄደ።ድርድሩ የብሔርና የቋንቋ እኩልነትን የሚመለከት ስለ ነበር፣ በእኛ ዘመነ መንግሥት፣ የአማርኛ ቋንቋ የግዴታ ትምህርት መሆኑ አይቀርም በማለት ድርድሩን ወድቅ አደርጎ፣ ጄኔራሉንና ስድሳዎቹን ብግፍ እሸነ። ከዚህም የተነሳ ሕዝባችን ለአስራ ሰባት አመት በጦርነት ተማገደ። ኤርትራንም የባህር በሩንም አጣ።
ይህ ነበር እንግዲህ ኢሕአዴግን ለመንግሥት ሥልጣን ያበቃው፣ አሁን ላለውም ሁኔታ መንሴ የሆነው። እኛም አሁን መጠንቀቅ የሚገባን፣ በመንግሥት ሥልጣንና በወታደራዊ ድሎች በደስታ ሰክረን፣ ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ቂም በቀል ከማትረፍ፣በድልን ለፈጣሪ አሳልፎ በመስጠት፣ ሁሉንም በልኩ በማድረግ፣ለሰላም መሸንፍ ይገባናል።
በዚህም ረገድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ በሚገኙበት ክልል፣ዞንና ወረዳ፣ በመረጡት ቋንቋ፣ ራስቸውን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ሊከበር ይገባል።የኢሕአዴግም ሆነ የሕወሐት ስህተት፣ ይህን የሕዝቦች መብት ብትክክል አለመፈጸም ነበር፣የመንግሥት ሥልጣን ያሳጣቸው። ብልፅግናም ያንኑ ስህተት ለመድገም ሕገ መንግሥቱን ሸብረክ አድርጎ፣አሐዳዊነትን በማቆለጳጰስ ላይ ይገኛል።
ስለሆነም ይህ የሕዝቦች መብት፣በፌድራል መንግሥቱ ተገቢውን አጽንኦት አግኝቶ፣ ብሔር ብሔረሰቦች በሚገኙበት፣ክልል፣ ዞንም ሆነ፣ ወረዳ፣ በቋንቋቸው ራስን በራስ በማስተዳደር፣ እምነታቸውንና ባህላቸውን በመንከባከብ፣ ቀርሳቸውን የማበልጸግ መብታቸው ሊከበር ይገባል።ይህ ከሆነ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ያከትማል፣ ጥላቻ ይወገዳል፣ሰላማችንም ይሰፍናል።
ሌላው በሕዝባችን መካከል ያለው ቅራኔ ከፌድራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ጋር የተያያዘ ነው።አገራችን በቅኝ ግዛት ባለመያዟ የገዥው መደብ የመግባቢያ ቋንቋ አማርኛ ነበር። አገራችን ደግሞ በርዋን በአለም ሥልጣኔ ላይ ዘግታ፣ በጭለማ የቆየች በመሆኗ፣ ይህ ቋንቋችን እንደተቀረው የኃይላን ቋንቋዎች፣በሳይንስና በቴክኖዎሎጂ ቃላት የዳበረ አይደለም። ለከፍተኛ ትምሕርት መስጫም አልዋለም፣ስለሆነም ከዓለም ሥልጣኔ ጋር እኩል ወደፊት ሊያራምደን አልቻለም።በዚህ ላይ ሰባ ከመቶ ለሚሆነው ሕዝባች ሁለተኛ ቋንቋ ነው።ይህም ቋንቋ የዕኩልነት መርሆን የሚያፋልስ ነው።በተለይ ደግሞ አንደበታቸውን በሌሎች ቋንቋዎች የፈቱ ልጆች፣ የአማርኛ ቋንቋ መማር የግዴታ በመሆኑ፣ ለተጨማሪ የትምህርት ጫና ዳርጎቸዋል። ይህም አድሎና ጫና ትምህርትን እንዲጠሉ፣ በፈተናም እንዲወድቁና በፌድራል የሥራ ዕድልን እንዳያገኙ በማድረጉ፣በአገራችን ያለውን የብሔር ቅራኔ ሊያባብሰው ችሏል።
ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣በቤንሻጉል፣በሱማሊያም ሆነ በገምቤላ ላለው ግጭት እውነተኛ መንስዔው፣ ይኸው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ወረራ የተጀመረ፣ የብሔርና የሃይማኖት ጭቆናና አፈና ነው።በመሆኑም ነው ትግሬ በሕወሐት፣ ኦሮሞ በኦነግ፣ አማራም በአብንና በፋኖ የተደራጁት፡፡ስለዚህም ነው ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ አማራዎች ላይ ችግሩ ተንፀባርቆ፣በሰላም አብሮት ከኖሩት ብሔሮች ጋር እየተጋጩ ከመኖሪያ ቄዬአቸው የሚፈናቀሉት፡፡
ወንድሞች ቋንቋ መግባቢያ ነው ካልን፣ የምንግባባው ስለ ምድራዊ ሕይወታችን ብቻ አይደለም።ምዕመናን የፈጣሬያችውን እውነተኛ ቃልና ፈቃድን፣ ለይተው ለማወቅ የሚችሉት በቋንቋ ነው።ስለሆነም ነው ቅዱሳት መጽሐፍት፣ ከእብራይስጥ ወደ ግሪክና እንግሊዚኛ፣ ከዚያም ወደ አረብኛና ግዕዝ፣ብሎም በአለም ቋንቋዎች ሁሉ የተተረጎሙት፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተሰጠው ዕድል ፣ለሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎችም ተሰጥቶ፣ ነፍሳት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃልና ፈቃድ እኩል ተረድተው፣ከሰይጣንና ከጣኦት አምልኮ ነፃ በመውጣት፣ የእግዚአብሔርን መንግሥቱ ለመውረስ እንድችሉ ማገዝ ይገባል።
ሌላው ሕዝባችንን በእርስ በርስ ጦርነት እየማገደ ያለው፣ የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄ ነው።የመንግሥት ሥልጣን የሚያስፈልገው ሕዝቡን በቅንነት በማገልገል በሰላም በማስተደደር ወደ ጋራ ብልፅግና ለመምራት ከሆነ፣ ሕዝቡ ራሱ መሪዎቹን መምረጥ ይኖርበታል። ሕዝብ የሚያምንባቸውን ሊመርጥ የሚችለው ደግሞ ለምርጫ ከሚቀርቡለት ዕጩዎች መካከል በመሆኑ፣የአቢዮታዊ ዴሞክራሲ የፓርቲ አመራር ተወግዶ፣ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሁሉ እኩል፣ሰላማዊ የውድድር መድርክ ሊሰፋ ይገባል። ገዥው ፓርቲ በድርጅታዊ አሠራር ራሱን የሚያስመርጥበት፣ ፓርላሜንተሪያዊ ቅርጸ መንግሥት ተወግዶ፣ በፕሬዚደንታዊ ቅርፀ መንግሥት ሊተካ ይገባል።ይህ የሥልጣን መወጣጫ ሥውር መሰላል ከተወገድ፣የቀረውን ችግር ሕዝባችን ራሱ በሂደት ይፈታዋል።
በዚህም ረገድ ከሕዝባችን መካከል ያለውን ተፃራሪ ቅራኔዎችን ካስወግድን፣ ሕዝባችን በቋንቋው ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ ባህሉን እየበለጸገ፣ቀርሶቹን እየተንከባከበ፣በሰላም እምነቱን እየተለማመደ፣በደስታ ይኖራል። በዚህም ታግዞ በሙሉ ኃይሉ ለሥራ ከተነሳ፣ ፈጥኖ በድኅነት ላይ ድልን ይቀዳጃል።በተረፈ ቅራኔን አፍኖ በልማት ላይ ብቻ ማተከር ትርፉ፣ የብብትን እያፈሰሱ መልሶ መልቀም ይሆናል።
ስለሆነም ሕዝባችን አሁን ካለበት ጦርነትና ጥላቻ ለመገላገል፣ ከሁሉ በፊት የትግራይ ሕዝብ በክልሉ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ሕወሐትም በበኩሉ የፌድራል መንግሥት ሥልጣን አክብሮ፣ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን መፈጸም ይኖርበታል።
ለዚህም ከአፍሪካ አንድነት አደራዳሪ በተጨማሪ፣ በሐወሐት የተጠቋሙ ኬኒያታ ሊታከሉ ይገባል።በባህላችንም አስታራቂ ሽማግሌ የሚመረጠው ከግራና ከቀኙ ነውና። የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ ታዛቢነትም ወሳኝ ሰለሆነ መቀበል ይገባል።መቼም ቢሆን መቼ እርቁ ሊሰምር የሚችለው በአደራዳሪዎቹ ግፊት ብቻ አይደላም።የግራና ቀኝ አጫፋሪዎች እንደበታቸውን ዘግተው፣ ሁለቱ ዋና ተደራዳሪዎችም ለሰለም ፈቅደው ሲሸንፉ ነው።
ስለሆነም ያለፈው አልፏል አሁን በወገኖቻችን ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ጦርነቱ አሁን በሚገኙበት ሥፍራ መቆም ይኖርብርታል፡፡ለጊዜው ጥላቻና ቅራኔ እስኪረግብ ድረስ በሁለቱ ጦር ግንባር መካከል የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ጓድ እንዲሰፍር መፍቀድ ይገባል። ከዚያም ሕወሐት የቡድን የጦር ትጥቅን በመፍታት ለሰላም ጓዱ ማስረከብ ይኖርበታል። ይህም በሚሆንበት ጊዜ የፌድራል መንግሥትም፣ ለትግራይ ሕዝብ የምግብና የሕክምና እርዳታ፣ የባንክ፣የቴሌፎን፣የማብራት አገልግሎት አሟልቶ ሊያቀርብ ይገባውል።ጦርንርቱ በዚህ ከረገበ የተረፈውን ችግር፣ በአገራዊ ምክክር የሚፈታ ይሆናል።ፈጣሪ አምላኩን የሚያከብር፣ወንድሙን የሚወድ ቅዱስ ሕዝብ ፣እውነትን አይፈራም፣ሰላምንም አይጣላምና፣በዚህ የሰላም ጥረት ላይ የቸሩ ፈጣሪ አምላካችን ፈቃድ እንዲታከልበት እማጸነዋለሁ!!!
ምክሬን ስሙ። ቅራኔን በሰላም ፍቱ!
ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ።