ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ
የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር አመራሮች ባልታወቀ ምክንያት ከያሉበት እየታሰሩ ነው
የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሀብታሙ አያሌው፣ የማህበሩ ምክትል ሊቀመንበር ወጣት ሚካኤል አለማየሁና የማህበሩ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ብርሀኑ ተክለያሬድን በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው እየታደኑ መሆኑን ወጣት ሀብታሙ አያሌው በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገለጸ፡፡
ወጣት ሀብታሙ አያሌው እንደተናገረው ዛሬ ማምሻውን የማህበሩን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ብርሀኑ ተክለያሬድን ፖሊሶች ከጽ/ቤታቸው ውስጥ አስረውታል፡፡ ወጣት ሀብታሙ የክስ ቻርጅ ባይደርሰውም “በተገኙበት እንዲያዙ” የተባለበት ምክንያት ስላልገባው ለደህንነቱ በመስጋት እጁን ለፖሊስ ለመስጠት እየሄደ እንደሆነ ለፍኖተ ነፃነት ተናግሯል፡፡ “የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሁሉም ሰው በእጁ ካቴና ይዞ ነው የሚዞረው ተራው ይደርሰዋል” ያለው ወጣት ሀብታሙ ኢህአዴግ መወገድ አለበት የሚል አቋም በመያዝ አንድነት ፓርቲን መቀላቀሉ ና በፓርቲው ባገኘው ተቀባይነት ኢህአዴግን እንዳሰጋው እንደሚያምን ተናግሯል፡፡