ታሪክ እንደሚያስረዳውና እንደምናውቀው ፋኖ አገር ስትወረር፣ የሕዝብ ኑሮና ሰላም ሲናጋ እንደ አንበሳ አግስቶ ጠላትን የሚመክትና የሚያንበረክክ እምቅ ኃይል ነው፡፡ ለሺህ ዘመናት ፋኖ ኢትዮጵያን የወረረውን ኃይል ሁሉ ደቁሶ የአገሪቱን ዳር ድንበርና ክብር ሲያስጠብቅ የኖረ የአገር መከታ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በታሪካዊ የሩቅና የቅርብ ጠላቶች ታዝዞና ታግዞ አገር ለማፈራረስ የመጣውን ባንዳ በመጋፈጥ ላይ የሚገኝም ነው፡፡
እንደ አለመታደል ግን ፋኖ ተደራጅቶ እንዳይጠነክር የባንዳዎቹ የድሮ አሽከሮች ተጽዕኖ እያሳደሩበት ነው፡፡ እንዲያውም ላንዳንዶቹ የባንዳዎች የድሮ አሽከሮች ፋኖ ጠንክሮ ተሊጥ ተሸካሚዎች ነፃ ተሚያወጣቸው ተመልሰው የሊጥ ተሸካሚ ሌባዎች ሎሌ መሆን የሚመርጡ እየመሰለ ነው፡፡ ፋኖ በሎሌነት የተጎለቱበትን የሰላሳ ዓመት ወንበር የሚነጥቃቸው እየመስላቸው ነው፡፡
ጊዜ የሰጣቸው ባለስልጣናት የፋኖን እውነተኛ ታሪክ ረስተዋል ፡፡ ፋኖ ወራሪና ባንዳን በክርኑ አንበርክኮ ወደ ሥራው እንደሚመለስ የአምስቱ ዘመን ታሪክን ማወቅ ተስኗቸዋል፡፡ የገበሬው ፋኖ ወደ ግብርናው፣ የነጋዴው ፋኖ ወደ ንግዱ፣ የተማሪው ፋኖ ወደ ትምህርቱ፣ የአስተማሪው ፋኖ ወደ ጠመኔው ወዘተርፈ እንደሚመለስ አላምን ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ባለስልጣናት የድሮ ጌቶቻቸው ጉረሯቸውን ሊያንቋቸው ሲደርሱ ፋኖ ድረስ፤ ፋታ ሲሰጧቸው ደሞ ፋኖ ፍረስ ሲሉ ይታያል፡፡
ባለስልጣኖች ሆይ! ተመልሳቸሁ ሕዝብ የሊጥ ሌባ ለሚላቸው ባንዳዎች አሽከር ተምትሆኑ ፋኖ እንዲጠነክር እድል ብትሰጡ ይሻላችኋል፡፡ ፋኖ የአገርን ዳር ድንበር ይጠብቃል፣ የሕዝቡን ደህንነት ያስከብራል፣ እናንተንም ነፃ አውጥቶ ስልጣናችሁን እንደገና በባንዳዎች ተመነጠቅና ቀና ብሎ የማያይ ልሙጥ ሎሌ ተመሆን ያድናችኋል፡፡
ተሰደህ የምትኖር ኢትዮጵያዊ እባክህ ስማ! ዘራፊዎች እንደገና ሊያፈርሱት ተሚችሉት ጎጆ በፊት ፋኖን ገንባ!
አብዛኛህ በየዋህነት አንዳድህ ደሞ በዘልዛላነት ዘራፊዎች እስከመጨረሻው የተባረሩ መስሎህ የተጎዱ ወገኖችን መኖሪያ፣ ት/ ቤት፣ የሕክምናና የሌሎችም አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎችን ለመገንባት ገንዘብህን በመመስለጥ ላይ ትገኛለህ፡፡ አንተ የዋሁ በውጪ የምትኖር ኢትዮጵያዊ የሕዝብን ደህንነትና ንብረት የሚያስጠብቅ የጠነከረ መንግስት ያለ መስሎሀል፡፡ በማፈግፈግ “ስልት” የአገዛዙ ጦር ከመቀሌ ደብረ ብርሃን በአጭር ጊዜ መስክ ላይ ከተለጋ ኳስ በበለጠ ፍጥነት እንደ ደረሰ “አጪሩ ሚሞሪህ” ረስቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግም ፋኖ አብሮ ሲሰለፍ ሌባዎች የተሸከሙትን ቡሃቃ ጥለው አስፋልት ላይ ከተለጋ ኳስ በበለጠ ፍጥነት በስብት ተቃራኒ አቅጣጫ (against gravity) ወደ መጡበት እንደተመለሱ ማገናዘብ ተስኖኻል፡፡
ዶላር መዛዡ ኢትዮጵያዊ ሆይ! ራያና ቆቦ ሲያዙ የወልዲያን ሆስፒታል ወልዲያ ሲያዝ ደግሞ የደሴን ሆስፒታል አገልግሎት ፋኖን ተመገንባትህ በፊት ገንብተህ ነበር፡፡ ዳሩ ግን የሕዝብ ደህንነትና ንብረት ያስከብራል የተባለው ኃይል ፊቱን ሳይሆን ጀርባውን ለባሩድ ሰጥቶ አዳኝ እንደ ታያት ሚዳቋ ሲፈተለክ የሊጥ ሌባ የምትላቸው ዘራፊ ባንዳዎች ሞጭልፈው አገራቸው መውሰዳቸውን እረስተሃል? መልሰህ የገነባሃው አጣዬ መዘረፉንና መውደሙን ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ዘንግተሃል?
አንተ የዋሁ አገርህን የምትሞድ ኢትዮጵያዊ የሚታመን ጠባቂ ያለ መስሎህ ለእነዚህ ሌባዎች የኋላ ደጀን እንደነበርክና በቁሳቁስ እንደረዳኻቸው ዘንግተህ ቁጪ ብለሃል? ዘራፊዎች በላከው ገንዘብ እየታከሙና እየተመገቡ ማፈግፈግ የማይሰለቸውን “ጦር” እያባራሩ የወሎንና የሸዋን ከተሞች እንደ ባቢሎን ግንብና እንደ ሰለሞን ቤተመንግስት እንዳጠፉ ተገንዝበሃል?
ማፈግፈግ ባህሉ ያልሆነውን ፋኖ ብትገነባና ብታጠነክር ኖሮ ያወጣኻው ገንዘብ ለወንበዴዎች ጉልበት መሆኑ ቀርቶ ይኸኔ ከአብራኩ የወጣኻውን ሕዝባ ያገለገል እንደነበር ማሰላለስል ችለሃል?
ዛሬም ፋኖን በማጠንከር ፋንታ የፈረሰ መንደርና ከተማ ልትገነባ በየአዳራሹ በስሜት እየጨፈርክ ገንዘብህን ስታወጣ ይታያል፡፡ ፋኖ በባለጊዚዎች ተፈረሰ ወይም ታልጠነከረ ብር እየመሰለጥክ የገነባሀው መንደር ወይም ከተማ መልሶ በወንበዴዎች ላለመዘረፉ ምን ዋስትና ተሰጥቶኻል? ዛሬም ማፈግፈግ ተፈጥሮው ወይም ባህሉ በሆነው በእነ እንቶኔ በሚመራው ጦር ታምናልሀ ወይስ በዝርፊያ የተጠመቀ ወንበዴ ንስሃ ገብቶ ዘረፋውን እንደገና ተመጀመር ይቆጠባል ብለህ “በአጪር ሚሞሪ” ታስባለህ?
ቦንድ ቦንድደህ ለትግሬ ነፃ አውጪ መርክብ የገዛህ፤ ፈንድ ፈንድደህም ሁለተኛውን ይህ አድግ ያደላደልክ ጥገቱ “ዲያስፖራ” ሆይ:-
መለኮት የሚያስተውል ልብና የሚያሰላስል አይምሮ ይስጥህ! ወንበዴ ደጋግሞ በሚወረው አገር ዘበኛ ወይም አጥር ሳትገነባ ነገ ተመልሶ የሚፈርስና የሚዘረፍ ጎጆ መስራት ይቅርብህ፡፡ የምትሰራው ጎጆ ተእነ ቡሃቃው እንደገና ሳይወድም ወይም ሳይዘረፍ አገልግሎት እንዲሰጥ ከፈለክ መጀመርያ ጠንካራ አጥር ወይም ብርቱ ዘበኛ ይኑርህ፡፡ ያ ጠንካራ አጥር ወይም ብርቱ ዘበኛ ፋኖ ነውና ተጎጆው በፊት ፋኖን ገንባ፡፡ እባክህ ንቃ! ብርህን እየመሰለጥክ ዘላለም ሌባንና የወገንህን ከተማ የሚያጋይ ወንበዴ በተዘዋዋሪ አትርዳ! ለብዙ ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያ አጥር፣ መከታና ዋልታ ፋኖ ነውና ፋኖን እርዳ! ፋኖን ገንባ! አመሰግናለሁ፡፡
በላይነህ አባተ ([email protected])
ጥር ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.