የሽብርተኛ አዋጅ ደንግጎ ሽብርተኛን መፍታት ሊያመጣ የሚችለው ክስተት ምን ይሆናል?

 አክሎግ ቢራራ (ዶር)

“እንደ ሃበሻ ገበሬ (አማራ ማለቱ ነው) ጠንካራ ሰራተኛ፤ እንደሱ ሌላውን ለመጉዳት የማይፈልግ፤ መብቱንና ማንነቱን እስካልተናኮሉት ድረስ ደግሞ ማንንም አስተናጋጅ ጨዋ ሕዝብ የለም። There is no hard worker than the Abyssinian peasant, and no more harmless and hospitable person, when left alone and properly treated…”

Augustus Blandy Wylde, British Journalist in his 1923 book Modern Abyssinia,

ባለፉት አምሳ ዓመታት በአማራው ሕዝብ ላይ፤ በማንነቱ ምክንያት፤ በተደጋጋሚ የደረሰበትን እጂግ የሚዘገንን፤ ግን የምእራብ መንግሥታትና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እውቅና ያልሰጡት፤ ያላወገዙት፤ ልክ እንደ ተራ ነገር የሚያልፉት ግፍ፤ በደል፤ እልቂት፤ ውርደት ወዘተ ተካሂዷል። የአማራው እልቂት ተራ ነገር (normalized episode) መሆኑን በተደጋጋሚ የሚያሳዩ መረጃዎችን አቅርበን ሰሜ አላገኘነም። ለናሙና ያህል ለተባበሩት መንግሥት ሰብአዊ መብት ኮሚሺነር የጻፍነውን ከዚህ ሃተታ ጋር አባሪ አድርጌዋለሁ።

የዛሬ ሳምንት፤ በገና በዓል የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀን አማካሪ ጀፈሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ በበዓል ቀን ለምን እንደ ሄዱ አሳስቦኝ ነበር። የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት— የውጭ ጉዳይ ሃላፊው አንቶኒ ብሊንከን፤ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ ሙሉ ባለሥልጣን የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድና የአሜሪካ ተራድዓ ድርጅት ሃላፊ ሰማንታ ፖወር—በተደጋጋሚ መርህ ያደረጉት በትግራይ ህዝብ ላይ “ዘውጋዊ እልቂት፤ የሴቶች ድፍረት፤ በእርዳታ የሚገኝ ቁሳቁስ እንዳይደርስ መሰናክል መፍጠር”–ወዘተ የሚሉ ትግራይ ተኮር የሆኑ ትችቶች ናቸው።

ይህ ተደጋጋሚ ትችት በትግራይ ሕዝብ ላይ “የጅምላ እልቂት ወይንም ጀኖሳይድ” ተካሂዷል ወደሚል ሰብሳቢና ቀስቃሽ መፈክር ተለውጧል።

ይህ ትርክት የትግራይን ጦርነት ማን እንደ ጀመረው? ምን ወንጀል እንደ ተፈጸመ? በማን ላይ? በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ  ፈቃድና ውሳኔ ከትግራይ የወጣው በምን ምክንያቶች ነው? ይህ ውሳኔ እድል ይከፍታል? የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ውሳኔ ካደረገ ህወሓት/ትህነግም ተመሳሳይ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል ለሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎችና ትችቶች የአሜሪካ መንግሥት አንድም ጊዜ አመርቂ የሆነ መልስ አልሰጠም። በቃ (NO MORE) የሚለው ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍና እንቅስቃሴ የጀመረው የአሜሪካን ተንኮልና ሴራ በመገምገም ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ከወጣ በኋላ የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር/ትህነግ ያደረገው እርቅ፤ ሰላምና ድርድር ሳይሆን ተጻራሪውን ነው። ጦሩን፤ እልቂቱን፤ ውድመቱን ከትግራይ ውጭ አስፋፋው። “እንደ ዱቄት ብን ብሏል” የተባለው ኃይል ግዙፍ ተዋጊና መሳሪያ ይዞ ጦርነቱን በባሰ ደረጃ አስፋፋው። ቁም ነገሩ ኢላማ ያደረገው በመጀመሪያ ደረጃ የአማራውን ክልል መሆኑ ነው “ሂሳብ አናወራርዳለን” ብሎ። በትግራይ የተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያ የጋራ ኃይሎች መሆኑን ወደ ጎን ትቶ በአማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ ትውልድ ሲጠቀስ የሚኖር ሰብአዊ እልቂትና የኢኮኖሚ ውደመት አካሄደ። ሆነ ተብሎ ይሁን ሌላ በተዛማጅ እንዲጎዳ የተደረገው የአፋር ክልል ነው።

እኔ ለመጠየቅ የምፈልገው ህወሓት/ትህነግ በምን ምስጢርና መንገድ መረጃ እየተሰጠው ነው ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አፋርና ወደ አማራው ክልሎች በፍጥነት ለመሄድና ታሪክ የማይረሳው፤ ፍትህ ስኬታማ ካልሆነ በስተቀር እንደ ተራ ነገር ይቅርታ ሊደረግለት የማይችል እልቂትና ውድመት ለማካሄድ የቻለው? በምን ምክንያትና በምን መረጃ ነው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህ ሽብርተኛ ቡድን አዲስ አበባን ለመያዝ “ሳምንታት፤ ከዚያም ቀናት” ቀሩት ይል የነበረውና ይባስ ብሎ ዜጎቹን ሁሉ አስራ ስምንት ጊዜ ከኢትዮጵያ ለቃችሁ ውጡ ያለው? የህወሓትን አጥፊነትና የአሜሪካን ሴራና ተባባሪነት ለመለየት አስቸግሮኛል።

ተደራራቢ ወንጀል

ባለፉት ሰባት ወራት (June 2021 to December 30, 2021) የደረሰውን የእልቂቱና የውድመት መጠን ስገመግመው፤ ጦርነቱ ሲጀመር በሰሜን እዝ ላይ የተካሄደውን ዘውግ ተኮር እልቂት፤ ከዚያ የማይካድራን አማራ ተኮር እልቂት፤ ከዚህ ህወሓት/ትህነግ ከውጭ ኃይሎች ጋር፤ በተለይ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ያደረገውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ አስታወስኩ። ኢትዮጵያ ከህወሓት ጋር ብቻ አይደለም የምትዋጋው እያልኩ ተችቸና አስጠንቅቄ ነበር። ግን፤ “ያልጠረጠረ ተመነጠረ እንዲሉ” የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ለራሱ ስትራተጅክ ጥቅም በሚል ሰበብ “ሽብርተኞችን ፍቱና ተደራደሩ” ይላል የሚል ግምት አልነበረኝም። ምክንያቱም፤ በአሜሪካ አገርም ቢሆን ባለፈው ዓመት January 6 የተከሰተው የሽብርተኞች ሴራ ትኩረት ስለ ተሰጠው ነው። ሁለት የጸረ-ሽብርተኛ ሂደቶች አይኖሩም የሚል እምነት ስለ ነበረኝ ማለቴ ነው። ግን፤ ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ አገር፤ ድሃና ኋላ ቀር ስለሆነች መጠራጠር አስፈላጊ ነበር። የአሜሪካ መንግሥት የሌላውን መንግሥት አመራር የሚያባብልበት ግዙፍ መሳሪያ አለው (The US has a menu of tools put, pressure and force weak government leaders to cave in and do its bidding).

ተጨማሪ ያንብቡ:  እኛ ያልነው ለፉገራ... ከክንፉ አሰፋ (ጋዜጠኛ)

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ጫና ምክንያት በገና ቀን ፌልትማን ከፕሬዝደንት ባይደን የተሰጠውን የውሳኔ መልእክት ይዞ የህወሓት/ትህነግ አመጻዊያን አለቃና መሪ የነበረውን ስብሃት ነጋን ለመፍታት የተገደደበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ለአሜሪካ መንበርከክ ያስፈልግ ነበር? ሽብርተኞችን መፍታት ከጸረ- ሽብርተኛው አዋጅ ጋር አይጻረርም? ይህ ውሳኔ ለህወሓት/ትህነግ አጥፊዎች መውጫ ቀዳዳ አይከፍትም? የሕግ የበላይነትን እናስከብራለን፤ እናከብራለን የሚል መንግሥት የራሱን መርህ፤ የራሱን ፓርላማ ውሳኔ፤ የራሱን የፍትህ ሚንስትሪ (the institution itself)፤ የራሱን የጦርነት የክተት አዋጅ ወዘተ ሙሉ በሙሉ አይጻረርም? በዘላቂነት ሲገመገም፤ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት አይበክለውም? ሕዝቡስ ምን ይላል? የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥቱ አመራር ላይ ያለውን እምነት አያኮላሸውም? አሁንም የሚዋጉትና ሲዋጉ የሞቱትን ቤተሰቦች፤ በህወሓት የተደፈሩትን እህቶችና እናቶቻችን አያስቆጣም? ፍትህን ፋይዳ ቢስ አያደርግም?

“እኛም በውሳኔው ደንግጠናል” ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ ከሆነ ውሳኔው ከመሰጠቱ በፊት ለጸረ ወያኔው ጦርነት በገፍ ለወጣውና ልጁን፤ ኃብቱን ወዘተ ፈሰስ ለሚያደርገው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ወገኖቸ አሁን የመጣ ዱብዳ አለ፤ ይኼውም የአሜሪካ መንግሥት ሽብርተኞችን ካልፈታችሁ” ይህን “እናደርጋለን ብሏልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስቀድሞ እንዲያውቀውና የማይዋጥልንን ውሳኔ ብናደርግም ለኢትዮጵያ ህልውና ስንል መሆኑን እንድታውቁት እንፈልጋለን” ወዘተ ለማለት አይቻልም ነበር? ውሳኔውን ግልጽነት የሌለው፤ ሃላፊነት የማያሳይ፤ የሕግ የበላይነትን ፋይዳ ቢስ የሚያደርገው ይኼው የሂደቱ ሽባነት ነው።

እኔ እስከማውቀው ድረስ የአሜሪካ መንግሥት ለዘመናት በኢትዮጵያ ላይ በዘውግ ልዩነት ላይ ሲዶልቱ እንጅ ኢትዮጵያን በመላው ሕዝቧ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በአንድነቷ ኮርታና ተከብራ፤ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት አሮንቃ ነጻ ወጥታ ራሷን የቻለች አገር እንድትሆን የሰሩበት ወቅት ፈልጌና ተመራምሬ ለማግኘት አልቻልኩም። ለነሱ አገልጋይና ታዛዢ ለሆነው ለህወሓት መንግሥት ሰላሳ ቢሊየን ዶላር እርዳታ ሰጥተው ህወሓትን አክብረውታል። ይህ ግዙፍ እርዳታ ምን ገዛ? ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ ለአሜሪካ ጥቅም አገልጎጋይና ታማኝ የሆነ ቡድን የሚል መልስ እሰጣለሁ። በተጓዳኝ፤ በህወሓት ሽልማት የተሰጣቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉ ማጤን ያስፈልጋል።

በፕሬዝደንት ካርተር፤ በፕሬዝደንት ሮናልድ ሬገን፤ በፕሬዝደንት ቢል ክሊንቶን፤ በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እና አሁን በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የተፈጸሙትንና ወደ ፊትም ሊፈጸሙ የሚችሉትን ማጤን ያስፈልጋል። የአሜሪካ አጀንዳ ራሷን ለማገልገል ምክንያቶችን መደርደር የተለመደ ስልት ነው። ችሌ፤ ቬትናም፤ አፍጋኒስታን፤ ኢራክ፤ ሶርያ፤ ሊቢያ ወዘተ ወዘተ።

የትኛው አገር ነው በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት መጥቆ ራሱን የቻለው? ብሄራዊ ጥቅሙን ያስከበረው? በእርዳታ በኩል ስመራመረው አሜሪካ በኢትዮጵያ የሰራችው ሃዲድ፤ ግዙፍ የአስፋልት መንገድ፤ ግዙፍ ዘመናዊ እርሻ፤ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ወዘተ የትኛው ነው? ለተንኮል ግን የአሜሪካ መንግሥት ሃላፊዎች በተማሪው እንቅስቃሴ ወቅት እንኳን ተማሪው እንዲከፋፈል ያደርጉ የነበሩ መሆናቸውን አስታውሳለሁ። ምርጫም ተካሂዶ እስካሁን የሽግግር መንግሥት የሚደግፈው የአሜሪካ መንግሥት ነው።

ለአማራው እልቂትና ውድመት ማን እየተሟገተለት ነው?

ይህ እኔን ወደሚያስጨንቀኝ አስኳል ጉዳይ ይመራኛል። ህወሓት/ትህነግ ከትግራይ ወጥቶ ዋና የእልቂትና የውድመት ኢላማ ያደረገው የአማራውን ሕዝብ ነው። በወረራው ምክንያት በአማራው ክልል ብቻ የወደመው መሰረተ ልማት–የጤና ጣቢያና ሆስፒታል፤ ትምህርት ቤት፤ ድልድይ፤ የቱሪስት መናኸሪያ፤ የኪኮኖሚ ምሰሶዎች የሆኑ እንዱስትሪዎች፤ ወፍጮ ቤቶች፤ ዘመናዊ እርሻዎች ወዘተ—በድምራቸው ወደ ስድስት ($ 6) ቢሊየን ወድሟል። አሜሪካ በስድስት ዓመት ለኢትዮጵያ የምትለግሰውን ያህል መሆኑ ነው። ገንዘብ ቢኖርም፤ ባይኖርም የማይተካውን ስገመግመው ቢያንስ ሰባት ሽህ ንጹህ ዜጎች ተጨፍጭፈዋል። ከመቶ በላይ ወጣት የአማራ ሴቶችና እናቶች ተደፍረዋል። ህወሓት በአማራው ላይ “ሂሳብ አወራርዳለሁ” ያለውን ጭካኔና ግፍ ስኬታማ አድርጎታል። የወጋው የአማራውን ደረት ብቻ አይደለም። የአማራውን ስነ ልቦና አቁስሎታል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ ፌልትማንን ጨምሮ የሰማንያ ዓመት መነኩሴ እናትን የደፈረውንና ያዋረደውን ህወሓትን በሃላፊነት ትጠየቃለህ አላሉም። ይህንን ሁሉ ግፍና በደል የፈጸመው በእነሱ ረቂቅ ድጋፍ ስለሆነ እንኳን ሊያውግዙት ሊተቹትም አይፈቅዱም። እኔን በበለጠ ያስደነገጠኝና ያሳሰበኝ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ነው። የሽብርተኛ አዋጅ አውጆ እንዴት ሽብርተኞችን ይፈታል? የሽብርተኞቹ መፈታት በባሰ ደረጃ የሚጎዳው ማንን ነው?

የህወሓት/ትህነግ ዋና ኢላማ የሆነው አማራው ነው ብያለሁ። ይህ አሸባሪ ቡድን ማንን ተማምኖ? ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ የምእራብ አገሮችን፤ በተለይ የአሜሪካን መንግሥት የሚል መልስ ለመስጠት እደፍራለሁ። ህወሓት ከተመሰረተበት ጀምሮ (ወደ አምሳ ዓመት ሊጠጋ ነው) አጋሩ የአሜሪካ መንግሥት ነው። አምሳ ዓመት ታማኝ የሆነ ወዳጅን ለማውገዝ አይቻልም። የአሜሪካ መንግሥት ህወሓቶች የፈጸሙትን ወንጀል እያወቀም፤ ከአማራውና ከአፋሩ ክልል ሙሉ በሙሉ ውጡ፤ ካልወጣችሁ ግን በአመራራችሁና በደጋፊዎቻችሁ ላይ እቀባ አደርጋለሁ አላለም። ያስፈራራውና እንዲምበረከክ ጫና ያደረገው በኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች ላይ ነው። ከመንግሥት መሪዎች ጀርባ ግን ማየት የፈልግሁት በተራው ሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ተጨማሪ ግፍና በደል ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የባቢሎን ኮሙኒኬሽን የሃገራዊ ህብረታችን ጸር ነው! - ገለታው ዘለቀ

ማን የበላይ ሆነ?–የአሜሪካ መንግሥት ወይንስ ኢትዮጵያ?

የአሜሪካን መንግሥትንና ትእዛዙን የተቀበሉትን የኢትዮጵያን ባለሥልጣናት ስገመግም፤ የአማራው ግፍና በደል አያሳስበኝም ማለታቸው ይሆናል ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። “ታታሪ፤ ሌላውን የማይጎዳ፤ ካልደረሱበት በጨዋነቱና በአስተናጋጅነቱ” ወደር የሌለው የአማራ ህዝብ በተከታታይ የሚገመገመውና የሚፈረጀው በተለየ መስፈርት መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ። ለምሳሌ “ጨቋኝ፤ ቅኝ ገዢ፤ ትምክሕተኛ” ወዘተ። ይህ ተከታታይ ሁኔታ (pattern of mistreatment by demeaning Amhara) ኢ-ፍትሃዊ፤ ኢ-ዲሞክራሳዊ ነው። ለአብሮነት ዋና ማነቆ ነው። በቋንቋና በዘውግ የተዋቀረው ሕገ መንግሥት የአማራውን እጣ ፋንታ አባብሶታል። ለጥቃት አጋልጦታል። ሕገ መንግሥቱ ካልተቀየረ በስተቀር የተሻለ ሁኔት ይኖራል የሚል እምነት የለኝም።

“ምእራብ ትግራይ” ሰው ሰራሽና ፖለቲካዊ ትርክት ነው።

ይህ ብቻ አይደለም:: የአሜሪካ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የአማራው አንጡራ መሬት የሆኑትን፤ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትንና ራያን “ምእራብ ትግራይ” እያሉ ለማሳመን ሞክረዋል። አቋማቸው ከህወሓት ጋር የሳንቲም ግልባጭ ሆኗል ማለት ነው። ስለሆነም፤ ድርድር ያስፈልጋል፤ ይቅር ባይነት ወሳኝ ነው ወዘተ ሲባል፤ ማን ዋጋ ይከፍላል? በማን ጀርባ ላይ? በማን ደም ላይ? ብየ ራሴን እጠይቃለሁ። ዋናው ጉዳይ ፍትህ መኖሩ ነው። የእነዚህ መሬቶች ጥያቄ ከአማራ ማንነትና ከሰብአዊ መብቶች መከበር ጋር የተያያዘ ነው። በወልቃይት ብቻ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ቁጥር አንድ ሚሊየን ይገመታል። ከመሬቱ ስትራተጅካዊነት ባሻገር የማንነት ጥያቄ፤ የሰብአዊ መብት ጥያቄ አብሮ መታየት አለበት። የሕግ የበላይነትና ፍትህ አለ ለማለት የምችለው የእነዚህ አካባቢዎች የአማራ ሕዝብ ጥያቄ በአስቸኳይ መፍትሄ ሲያገኝ ነው።

የወልቃይት ጉዳይ የአማራ ብቻ አይደለም።

ጥያቄውን የአማራ ብቻ አድርገው የሚተቹ ግለሰቦችና ስብስቦች አሉ። እኔ ለማሳሰብ የምፍለገው ሰፋ አድርገን እንመልከተው የሚለውን ነው። ምን ማለቴ ነው? ሱዳንና ግብጽ ህወሓትን የሚደግፉበት መሰረታዊ ምክንያት የእነሱን ጥቅም ስለሚያስቀድምላቸው ነው። ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ነጥቃለች። ግብጽ፤ የሕዳሴ ግድብ እንዳይሳካ የውክልና ጦርነት ታካሂዳለች። ወልቃይት፤ ጠገዴና ጠለምት ወደ ትግራይ ቢጠቃለሉ ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ደህንነት አስጊ ሁኔታ መፍጠሩ የማይቀር ነው። ይህ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ ከመስፈርቱ ጋር አብሮ ሊታይ ይገባል።

የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ሲፈተፍቱ “የምእራብ ትግራይ” ጉዳይም መፍትሄ ያስፈልገዋል እንደሚሉ እገምታለሁ። የሚፈልጉት መፍትሄ ለአማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህልውናም አደጋን እንደሚያስከትል አስቀድሞ ማሰብ ግድ ይላል። ለምሳሌ፤ ትግራይ ከኢትዮጵያ ብትገነጠልስ?

በዚህ ከተስማማን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች ጦርነቱ “አልቋል” እና ወደ ትግራይ መግባት አያስፈልግም የሚሉትን የመጀመሪያውን ብቻ ነጥየ ስመለከተው፤ ዛሬም ቢሆን ህወሓት ጦርነቱን በየቦታው እየቀሰቀሰው ነው። በዋልድባ፤ በአላማጣ ዙሪያ ወዘተ ያለውን ሁኔታ ስመራመር እነ ስብሃት ነጋን መፍታቱ ያስገኘውና የሚያስገኘው ብሄራዊ ጥቅም ምን እንደ ሆነ ሊገባኝ አልቻለም። ህወሓት የጀመረውንና ለብዙ ወገኖቻችን እልቂትና ለኢኮኖሚ ውድመት ዋና ምክንያት የሆነውን ጦርነት በማባበል እልባት ለመስጠት የሚቻል ሆኖ አላየውም። እስከ ማውቀው ድረስ፤ ህወሓት ለእርቅ፤ ለሰላምና ለአብሮነት ፍላጎት ያለው ድርጅት አይደለም። በምኞትና የአሜሪካ መንግሥት በሚያደርገው አግባብ የሌለው ጫና አስተናግዶ ለህወሓት እውቅና መስጠት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ከፍ እንደሚል አምናለሁ። ከሽብርተኛ አካል ጋር ድርድር ማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተባባሰ እልቂት፤ ውድመትና የእርስ በእርስ ግጭት ሊወስዳት ይችላል።

ገና ያላለቀን ጦርነት አልቋል ብሎ በይኖ አማራውን ሆነ አፋሩን፤ ኦሮሞውን ሆነ ሶማሌውን ወዘተ ለባሰ ሰቆቃ እንዲጋለጥ ማድረግ በሃላፊነት የሚያስጠይቅ ሁኔታዎችን ይፈጥራል የሚል ስጋት አለኝ።

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የስልክ ጥሬ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነ ክስተትን አስከትሏል። ኢትዮጵያ ካለችበት አጣብቂኝ መጥቆ ከማውጣቱ ይልቅ ይህችን ከልጅነቴ ጀምሬ ስሟገትላት የኖርኩትን ታላቅ አገር ወደ ባሰ አቅጣጫ እየመራት ነው። ይህ ወደ ማጠቃለያየ ያመራኛል።

ምን ይደረግ?

  1. በዘላቂነት ስገመግመው፤ ኢትዮጵያ ብሄራዊ፤ እርቅ፤ ሰላምና መግባባት ያስፈልጋታል። የተቋቋመው ኮሚሽን ከማንም ፓርቲና ወገን ነጻ ከሆነና ስራውን በጥልቀት፤ በቅንነት፤ በመረጃ፤ ግብአቶችን በመሰብሰብና በማስተናገድ ከሰራ ስኬታማ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። ለይስሙላ ከሆነ ግን ባይጀመር ይሻላል።
ተጨማሪ ያንብቡ:  አብይ አህመድ በሁለት ወር ውስጥ በአስር አገራት ያደረገው ሽርሽር መለስ ዜናዊ በ27 አመት አላደረገውም (እውነቱ ቢሆን)

 

  1. የአሜሪካ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና እርጋታ እንዲኖር ፍላጎት ካለው፤ ህወሓትንና ኦነግ/ሽኔ አመጻቸውንና የእልቂት ዘመቻቸውን በአስቸኳይ አቁመው ለሰላምና ለውይይት እንዲስማሙ ጥሪ የማድረግ ግዴታ አለበት። በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ገብነቱን ማቆም አለበት።

 

  1. ህወሓት ለወደመው የአፋርና የአማራ ኢኮኖሚ፤ ለጨፈጨፋቸውና ለደፈራቸው ወገኖቻችን ካሳ የመክፍል ግዴታአለበት። ይህንን ውሳኔ በይፋ ለዓለም ማሳወቅ ያለበት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። የአፋርና የአማራ ክልል መሪዎች የማያሻማ መረጃ አዘጋጅተው (Complete inventory of human life lost, girls and women raped and social and economic infrastructure looted, vandalized, damaged and destroyed) ህወሓትና የውጭ ደጋፊዎቹ የሚከፍሉትን ካሳ ለኢትዮጵያና ለዓለም መንግሥታት ማሳወቅ አለባቸው። የአሜሪካ መንግሥት ለዚህ መልሶ ማቋቋም እቅድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ መደረግ አለበት።

 

  1. የጦርነቱን ሂደትና ትርክት በሚመለከት፤ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት ይህችን አገር ከመበታተን ለመታደግ መስዋእትየሆኑትን አካላት ሁሉ አግባብ ያለው መስፈርት አውጥቶ–ልዩ ኃይሎችን፤ ፋኖን፤ መከላከያን ወዘተ–እውቅናና ክብር መስጠት ወሳኝ ነው። ጦርነቱ የጋራ (የሁሉም ኢትዮጵያዊያን) መሆኑን ሳይሰለቹ ማስተጋባት የመሪዎችና የሚድያ ሃላፊነት ነው። በጦርነቱ ላይ የፖለቲካ ጨዋታ እንዲራመድ መፍቀድ ግን፤ ይህ ጦርነት ተካሂዶና እየተካሄደ፤ ግዙፍ ህይዎት ተከፍሎ፤ በብዙ ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሃብትና ንብረት ወድሞ፤ ከጦሩነቱ ባሻገር ሊገኝ የሚችለውን የብሄራዊ አንድነት ስሜት ማባከን ይሆናል።

 

  1. የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶችሴራቸውንና ኢትዮጵያን የማፈራረስ እቅዳቸውን አያቆሙም። ለዚህ የሚቨጀው ብሄራዊ (ኢትዮጵያዊ) አንድነት ብቻ ነው። ዘውጋዊ ልዩነቶችንና ተተኪነትን ወደ ጎን ትቶ የዜግነት መብት እንዲፋፋ፤ ጥልቀት እንዲይዝ፤ ተቋማዊ እንዲሆን፤ ብልጽግና ፍትሃዊ እንዲሆን ቀን ከሌት መስራት ነው።

 

  1. ህወሓትና የውጭ ደጋፊዎቹ የጠነሰሱት እቅድ፤ ተጠቂው አካል “የትግራይ ሕዝብ”ስለሆነ፤ በአሜሪካ መንግሥት የበላይነትና አቀነባባሪነት በትግራይ ክልል፤ “ምእራብ ትግራይን” ጨምሮ የበረራ እገዳ (NO FLY ZONE) እንዲደነገግ ነው። ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ መሆኗ አይቀርም። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ አስቦበት አማራጮችን አስቀድሞ እንዲያዘጋጅ እመክራለሁ። ከወዳጅ አገሮች ጋር መመካከር አንዱ ነው።

 

  1. በአሁኑ ሁኔታዎች በተባባሱበት ወቅት፤ ማንኛውም ግለሰብ፤ ሜድያ፤ ስብስብ በዘውግና በእምነት፤ በግልና በፖለቲካ ጥላቻ ምክንያት የጥላቻንና የቂም በቀል ትርክቶችን በመገናኛ ብዙሃን፤ በማህበረሰባዊ ሚድያና በውይይቶች እንዳያደርጉ ጥሪየን አቀርባለሁ። ትኩረቱ ከዜጎች መብት፤ ፍትህ፤ ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ እንዲሆን አደራ እላለሁ።

 

  1. በተደጋጋሚ እንዳሳሰብኩት ሁሉ በቋንቋና በዘውግየተዋቀረው ሕገ  መንግሥት በባለሞያዎች ተጠንቶ እንዲቀየር አሳስባለሁ።

 

  1. የአማራው ሕዝብ ራሱን ከባሰ እልቂትለመታደግ የሚችለው በመሬት ላይ የአላማ አንድነቱን ሲያጠናክር፤ ሲደራጅና እየተናበበ ለመስራት ሲችል ነው። መንደርተኛነት እንዲቆም አሳስባለሁ። አማራው “ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ፤ ሸየ፤ ቅማንት፤ አገውና” ሌላ መለያ እያስተጋባ ከሄደ የሚያጠናከረው አጀንዳ ለህወሓት፤ ኦነግ/ሺኔ፤ ግብጽ፤ ሱዳንና  የአሜሪካ መንግሥት የከፋፍለህ ግዛውና ብላው እቅድ ግብአት መሆኑ አይቀርም። የአማራው አንድነት ለራሱ ህልውና ብቻ አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ነው። አማራውንና ኢትዮጵያን ከጥቃት ለመታደግ ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል።

 

  1. የአማራው ልሂቃንና ምሁራን፤ ይህ ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ እንዳልጎዳ፤ እንዳልጨፈጨፈ ማስተማር አለበት። አማራው በትግራይ ሕዝብ ላይ እልቂት አለማካሄዱ ለምን ትኩረት አይሰጠውም? የትግራይ ሕዝብ በአማራው ክልልና መሬት ዋና ተጠቃሚ ሆኖ የቆየ መሆኑ ለምን ትኩረት አይሰጠውም? ጎንደር ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ሱቆቹን፤ ከባድ የመጓጓዣ መኪናዎችን በባለቤትነትን ይዘው ኃብታም የነበሩት የትግራይ ተወላጆች እንደ ነበሩ አስታውሳለሁ። በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሰቲት ሁመራ በገፍ የቀን ሰራተኛ ሆኖ ይሰራ የነበረው የትግራይ ሕዝብ እንደ ነበረም አስታውሳለሁ። ህወሓት የሚጨፈጭፈው ባለ ውለታውን ሕዝብ ነው።

 

  1. በመጨረሻ፤ ፋኖው የኢትዮጵያ ባለውለታ ነው። ፋኖ የሚገባው ትችት ሳይሆንበኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ኒሻን ሊሰጠው ይገባል። “ባለ ከዘራው” የሚባሉትስ ጀግና ለምን ተረሱ? ፋኖው ሕዝብን በራሱ ጉልበትና ወጭ የሚያገለግል የማህበረሰብ ደጀን ስለ ሆነ ወደፊትም ቢሆን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የመስጠት አቅም አለው። እውቅና ይሰጠው የሚል ጥሪ አቀርባለሁ።

 

ኢትዮጵያ ሃገራችን ተከብራ ትኑር!!

የውጭ ጣልቃ ገብነት ይውደም!!

January 14, 2022

dr aklog birara 2
Dr. Aklog Birara former Sr. Advisor at World Bank,, Commentator at Center for Inclusive Development (ABRAW) and a regular contributor to Zehabesha.com

 

 

3 Comments

  1. ዶክተር አክሎግ

    ” በህይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሬ የምለው ሰው አገኘሁ” ብለው ተመቀመጫዎ ተነስተው ለቀጣፊው አብይ የሰገዱት ቪዲዮ አለን እኮ!
    ማፈር የሚባልን ነገር ወያኔ ታለም አጠፋው እኮ! ወያኔን ለሃያ ሰባት ዓመት እንደ ባርያ ላገለገል ሰላይ ሲሰግዱ ገርሞን ነበር፡፡ አሁንም ንስሃ ገብተው ከተመለሱ አልረፈደም፡፡ ሕዝብ ግራ የሚጋባው እንደ እርስዎ ዓይነት በትምህርትም በእድሜም የገፋ ሰው ለመጣው ወጠጤ ሁሉ ካድሬ እየሆነ ስላስቸገረ ነው፡፡

  2. ምነው አገረ ኢትዮጵያ ዘመናት ያስቆጠረውን ፈተናዋን በቅጡ ተረድቶ፣ በትክክለኛና ዘላቂ መርህ ላይ ቆሞ ፣ እውን የሚሆን ዓላማና ግብ አበጅቶ ፣ ቃልና ተግባርን አዋህዶ፣ በሞራልና በመንፈስ ልእልና ታጅቦ፣ ወዘተ አንቱ እንደተሰኘ የሚዘልቅ ምሁር መናጢ ደሃ ሆነች ?
    ጥያቄው ከባድ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ መራር ነው። እንዲህ አይነቱን ጥያቄ በግልፅና በቀጥታ ከመጋፈጥ ይልቅ የሰበብ አስባብ ድሪቶ እየደረትን እና በአድርባይነት ክፉ ልማድ ዙሪያ እየተሽከረከርን ከቶ የትም አንደርስም። በእድሜም፣ በትምህርቱም፣ በህይወትና በሥራ ልምድም “አንቱ እንባላለን” እያሉ ነገር ግን የዚህ ክፉ ደዌ ልክፍተኞች የሆኑ ወገኖች በቁጥር ቀላል ያለመሆናቸው ግዙፍና መሪር እውነት ደግሞ ባያስገርምም ህሊናን በእጅጉ ይኮሰኩሳል ( ያንገጫግጫል) ። ከላይ የምናነበውን ፅሁፍ የፃፉልን ፀሃፊ ከህወሃት ጥላቻ በስተቀር እውነተኛ የሥርዓት ለውጥ ጨርሶ በሌለበት እውነታ ውስጥ ፋና ወጊ የለውጥ ምሁራን ተምሳሌት የሚምሰል ድርሰት ከሚደርሱልን (ከሚደርሱብን) ወገኖች መካከል አንዱ የመሆናቸውን እውነታ ማስተባበል የሚችል አሳማኝ ምክንያት የለም።
    እናም በግልፅና በቀጥታ ተነጋግረን ዘመናትን ካስቆጠረው እንዲህ አይነት ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልማድ እና ከሚያስከትለው የሞራል ውድቀት ራሳችንን ነፃ ካላወጣን በስተቀር የሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች (ቁማርተኞች) ሰለባዎች ሆነን የመቀጠላችን መሪር እውነታን ማስቆም አይቻለንም ። ስለሆነም አድርባይነት (ወራዳነት) አልበቃንም የሚሉ ወገኖችን ከምር በቃችሁ ማለት ግድ ነው።

  3. Dr. Aklog,

    You have completely lost your credibility since you have been Abiy Ahmad’s loyal cadre for more than three years.

    Your cry about Amara is also a crocodile tear! You failed even to run a small radio station(Asrat ) in Washington DC and you destroyed it. Sad!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share