በአሜሪካ ህንዶች መፈናቀልና የዘር ጭፍጨፋ፣ በአፍሪካ ባሮች ጉልበት የዛሬ ~250 አመት በተመሠረተ፣ የአለምን ጥሬ ሀብትና የሰለጠነ የሰው ሃይል በማግበስበስ በጠነከረ እና የአለምን ስልጣኔዎች ሁሉ እያፈረሰ ባለ አሜሪካ በተባለ አገር፣ ሰባዊ መብትና እርዳታ በሚል ሽፋን ልንታወክ አይገባም። የምዕራባዊያን የአፍሪካን መንግስታት፣ በመፈንቅለ መንግስት፣ በግድያ፣ በርስ በርስ ጦርነት፣ በሕዝብ አመጽ የማስወገድ ዘዴ እንደሚከተሉ ይታወቃል። ምዕራባውያን መሪዎቻችንን ሲመርጡልን ከርመዋል። አሁንም እሱን ለማስቀጠል፣ በርስ በርስ ጦርነት እያፋጁን ነው። የአሜሪካና የቻይና ውድድር በእኛ በደካሞቹ የፈጠረው ችግር በጣም ግዙፍ ነው። የቻይናን ወደ አፍሪካ የመግቢያ በር የመዝጊያ መንገድ ደግሞ ኢትዮጵያን መበጥበጥ ሆኗል። የትናንትናው የቀኝ ግዛት፣ የአሁኑ ኒዮሊብራሊዝም እንቅፋት፣ ኢትዮጵያ ያላት ስቴራቴጂክ አቀማመጥ፣ ያላትና ይኖራታል ተብሎ በሚታሰበው የማዕድንና የነዳጅ ሃብት፣ የአፍሪካ የእድገት አረዕያ እንዳንሆንና የጥሬ እቃ ማግኛና የሸቀጥ ማራገፊያቸው እንዳይነጥፍ ጠንክረው እየሰሩ ነው።
የውጪና የአደጉ አገራት ተጽዕኖ እንዴት ይገለፃል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያለበት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የሚገለጥበት መንገዶች ሃይማኖት ልስበካችሁ፣ የትምህርት ካሪክለም ልቅረጽላችሁ፣ እርዳታ እንስጣችሁ፣ የሆሊውድ ፊልምና ሙዚቃ፣ ትልቆቹ ሚዲያዎች እነሱን ከፍ ሌላውን ዝቅ የማድረግ ስነልቦናዊ ተጽዕኖ፣ በቀኝ እንያዝና እናሰልጥናችሁ፣ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ማግለል፣ የእነሱና እናንተ የከፋፍለህ ግዛ፣ የአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ጅርጅት የፖሊሲ ተጽዕኖ፣ አገሮች ወደ ጦርነት እንዲገቡ ገንዘብ ለመረጡት ቡድን መርዳት ወዘተ ይሆናሉ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ደግሞ ጥቅማቸውን ለማስከበር በኛው ሃይል፣ በነሱ እውቀትና ብዙ ትርፍ በሚያመጣ ትንሽ ወጪ ነው። አሁንም። የአሜሪካ መንግስት African Growth and Opportunity Act (AGOA) የንግድ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያን አስወጥቻለሁ ብሏል። ይህን የማድረግ መብት ያላቸውን ያህል፣ ነጻነታችንን በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሰበብ አሳልፈን የማንሰጥ መሆናችንን ሊያውቁ ይገባል። ማደግ የምንችለው አሜሪካ፣ እንግሊዝ ወይም የአውሮፓ ህብረት የፖለቲካ መንገዱን ስላሳዩን፣ የአለም ባንክ ወይም አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ ስለሰጡንና የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን ስላስቀየሩን፣ በተረኝነት ከስልጣን ማማ ላይ ስለወጣን፣ ዜጎቻንን ስላሳደድን፣ የተገነቡ ከተሞችን ስላወደምን አይደለም። ማደግ የምንችለው ለሁላችንም የሚሆነ ስርዓት መገንባት ስንችል ብቻ ነው።
የምዕራባዊያንን የቀኝ ግዛት መስፋፋት ለማገዝ ተግባር ላይ ከዋሉ ዘዴዎች መካከል፣ የስነ ልሳንና የዘር አመጣጥ ታሪክን ማጥናት ይገኝባቸዋል። ይህንም መረጃ ሕዝብን ለመነጣጠልና አንድነቱን ለማድከም፣ ብሎም የቀኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ተጠቅመውበታል። ለዚህም ነው፣ የሰውን ልጅ የካም፣ የሴምና የያፌት በሚል የእምነት መሠረት ያለው ክፍፍል በማድረግ ካምን የተረገመው ጥቁር፣ ሴሙን ከያፌት እኩል ያልሆነው ነጭ?፣ ያፌትን ባለ ትልቅ አዕምሮ አሳቢ አድርገው የሳሉት። አገራችንን በተመለከተ እዚህ ላይም አላቆሙም። ቋንቋችንን ሴሜቲክ፣ ኩሺቲክ፣ ኦሞቲክና ናይሎቲክ ብለው ከፍለው የጊዜ ልዩነት ቢኖረውም ሁላችንን በስደት የመጣን ስደተኞች አድርገውናል። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ የእኛው ታሪክ ጸሐፊዎች ይህንን መንገድ መከተላቸው ነው። ይህንን የሐሰት የቀኝ ገዢዎች ክፍፍል የኛው ፖለቲከኞች ሲጠቀሙበት ማየትም ያሳፍራል። እውነቱ ግን ከአጎራባቾቻችን የተዳቀልን የዚህችው ምድር ውጤት የሆንን፣ ቋንቋችንም እንደሰፈርንበት እርቀትና ቅርበት ያለው፣ በታሪክ ሂደት ሲቀያየር የኖረ ነው። የጀነቲክስ ምርምሮችም የሚያሳዩት በእኛ ጎሳዎች መካከል የጎላ ልዩነት አለመኖሩንና ጎረቤት ከሆኑት ቅርብና እሩቅ ምስራቅ ዝምድና እንዳለን ብቻ ነው።
ምዕራባዊያን፣ ባለራዕዩ መሪያችን አፄ ቴዎድሮስ እራሱን እንዲያጠፋ አድርገዋል፣ በሂወት ስምምነት ምክንያት ከመሃዲ ድርቡሾች ጋር እንድንጣላና አፄ ዮሃንስ ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርገዋል፤ የአባይን ውሃ እንዳንጠቀም የሚያግድና ለቀኝ ግዛታቸው ግብጽና ሱዳን ብቻ የሚጠቅም ውል ፈርመዋል፤ በስትሬሳው የሆር–ላቫል–ሞሶሎኒ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያን በጣልያን አስወርረዋል፤ በንጉሣዊ ስልጣን እጃቸውን በማስገባት ለእያሱ ስልጣን መልቀቅና ሞት ምክንያት ሆነዋል፤ መንግስቱን ያለ አማራጭ በማሰቀረት ተገፍቶ የሶሻሊስት ጎራ እንዲገባና አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት እንድትታመስ አድርገዋል፤ አገራችንን በዚያድባሬ የታላቋ ሶማሊያ ትርክት እንድንወረር አድርገዋል፤ አገራችንን ያለ ወደብ አስቀርተዋል፤ አማጺው ትህነግ መንግስታዊ ስልጣን እንዲይዝ፣ አገራችን በዘር እንድትከፋፈል፣ የአገር ሃብት እንዲባክንና አሁን ደግሞ በዚሁ ቡድን አነሳሽነት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አስገብተውናል። ትግራይ ክልል ግጭት ሲጀመር፣ የምእራባውያን ጋዜጠኞች ያስነበቡን መጣጥፍ፣ ሱዳን ኢትዮጵያን መውረር እንዳለባት የሚያትት ነበር። እሱንም የሱዳን የወታደራዊ መንግስት እውን አድርጎታል። የትህነግን መመታት ተከትሎ ምዕራባውያን ያደረጉት ደግሞ የኢትዮጵያን መንግስት በጦር ለመወንጀል፣ በቲዊተርና በየቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸው የስም ማጥፋት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ደግሞ በትግራይ ጉዳይ በየጊዜው መሰብሰብ ነው።
ከጣልያን ወረራ ጀምሮ እስከነፃነት ማግኘትና ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የተደረጉትን የዲፕሎማሲ ትግሎች መልክ አሁን እየደረሰብን ካለው ጫና ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነበር። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን እስከ በጣልያን መወረር ድረስ፣
ዘዴያቸው ሕዝቡ በባርነት እየማቀቀ ነው የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ፣ በየአገራቱ የሚኖሩና በባርነት ወደየአህጉሩ የተወሰዱ ጥቁሮች የመምረጥም ሆነ ሌላው ነፃነት አልነበራቸውም። በተለይም የኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ ጋር መወሃድ እውን እየሆነ ሲመጣ፣ በዘውዳዊ መንግስት እየተዳደረ ከአለ አገር ጋር ሌላውን በፌዴሬሽን ማዋሃድ የሚያመጣው ችግር ሳይታያቸው ቀርቶ ሳይሆን ችግሩን ለራሳችው ጥቅም መፈለጋቸውን ያሳያል። የግብጽን ሁሉ ድጋፍ ያገኘ መሆኑም የዚሁ ግልጽ ማሳያ ነው። የታላቋ ትግራይ፣ የታላቋ ሶማሊያ፣ የአባይ ሸለቆ ህብረት የሚሉ ሃሳቦች ፍጥረት ምክንያትም ይኸው አፍሪካን እንዳታድግ አስሮ የመያዝ መንገድ ነው። ይህም የ30 አመት ጦርነትን፣ የሃብትና የሰዎች እልቂትም አስከተለ። ከሰላሳ አመት በኋላም ውጤቱ ለኤርትራም፣ ለኢትዮጵያም ኪሳራ እንጂ ትርፍ አላመጣም።
አሁንም ይኸውን ዘዴ በትግራይ እየተገበሩት ነው። የትግራይ ጉዳይን በየቀኑ ሳያነሱ አያልፉም። ምክንያቱም፣ በእነሱ ለ30 አመታት የነገሱትና ታዛዦቻቸው መሬት ግባታቸው እየተረጋገጠ ስለሆነ ነው። ችግሩ ይህ የሚሉት ሁሉ በእነሱ በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በየመን ወዘተ የተፈጸመ መሆኑ ነው። እነዚሁ ሃብታም አገሮች አማጺ ቡድን የሆነውን ትህነግ ከጫካ አምጥተው አራት ኪሎ የሚኒሊክ ቤተ መንግስት ሲያስገቡትም የተገበረው ይኸውን የሃብታም አገሮች ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት የሚያዳክም መንገድ መከተል ነው። ለዚህም የአገርን አንድነት የሚያደክም ህገ መንግስት፣ ከፌዴሬሽን ይልቅ ወደ ኮንፌዴሬሽን የሚያደላ የክልላዊ መንግስት በማቋቋም፣ የራሳቸውን የክልል ጦር በማቋቋም፣ እስከ ጊዜው ልገዛ፣ ከዚያ እገነጠላለሁ አይነት መንገድ እንዲከተሉ አድርጓል። ይህ ካልገዛሁ እገነጠላለሁም፣ የምዕራባዊያን ስራ እንደሆነ እያየን ነው። ተበድያለሁ ልገንጠል ሳይሆን፣ ካልገዛሁ፣ ካልዘረፍኩ ልገንጠል ነውና።
የአፄ ቴዎድሮስና አፄ ኃይለስላሴ የዘመናዊነት ፕሮጀክት የወደቀበትም ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያን ዘመናዊነት ከማይፈልግጉት አገሮች እገዛ ጋር የተጣበቀ ስለነበር ነው። ይህም ማነኛውንም የእድገት ውጥናችንን ከተቻለ በራሳችን፣ ካልተቻለ ወዳጅ መፈለጉ ላይ ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል። ለዚህም የህዳሴ ግድባች ወደ መጠናቀቁ መቅረብ ትልቅ ማሳያ ነው። ለወደፊቱም ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው። እድገት፣ የአገር ደህንነት፣ የሕብረት ውጤት መሆኑንም ማሳያ ነው። የጣልያን ወረራ ወቅት፣ የተማሩና በአለአቅም ዜጎች ተጨፍጭፈዋል። አሁን ተምረናል የምንባለውም፣ ከእኛነታችን በሚያወጣና መሠረት የለሽ በማድረግ፣ የጣልያኑን የመግደል አላማ የሚያሳካ፣ እያሉ አለመኖርን የሚያስከትል፣ የምዕራባውያን የትምህርት ስርዓት ውጤቶች አድርገውናል። ይህም ለአገራችን ጥሩ ማበርከት እንዳንችል፣ ለስደት ወደ ውጭ የምናይ አድርጎናል።
ምዕራባውያን ችግሩ እንዲሰፋ እንጂ እንዲፈታ የሚፈልጉ ከመሰለን ተሳስተናል። ምዕራባዊያን ማንንም ደገፉ ማንንም፣ የሚደግፉት ለማንም አስበው ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም አስልተው መሆኑን አንርሳ። የሚደግፉትም፣ የሚቃወሙትም አብሮ ሲደክም ማየት የደስታ ምንጫቸው ነው። የሚፈልጉት፣ የደከመና የአገሩን ሃብት የማይጠቀም፣ ሃብቱን ለእነሱ ሰጥቶ፣ ለነሱ የሸቀጥ ማራገፊያና ከነሱ የሚለምን ምስኪን ተመጥዋች ሕዝብ ማየት ነው። ማዕቀብ ፈርቶ፣ ሞትን ፈርቶ መሠራት ካለበት መሸሸትም ለነገ የባሰ ችግር ውስጥ ለመግባት መንገድ መጀመር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ለምዕራባውያን፣ ኢትዮጵያን በእርዳታ ስም ለማወክ የሚሄዱበትን መንገድ እንዲያቆሙ፣ የእርዳታ ድርጅት መሪዎችና ሰራተኞችም+ ሰላዮችና የችግር ምንጮች መሆናቸውን ማስገንዘብ፣ እርዳታ በኢትዮጵያ መንግስትና ሌሎች አካላት በትብብር እንጂ በተናጠል የሚደረግ አለመሆኑን፣ አገር ከፍታችሁ ስጡንና እናፍርሳችሁ የማይሰራ መሆኑን፣ ያለዚያ እርዳታቸውን ይዘው ከእኛ እንዲርቁ በግልጽ ቋንቋ ሊነገራቸው ይገባል። እርዳታ፣ ጥገኝነትን እንጂ ምን ፈየደልን? በእርዳታስ ያደገው አገር የትኛው ነው? ማዕቀብስ ቢሆን በራሳችን መቆም እንድንችል ያስተምረን ይሆናል እንጂ ምን ያህል ሊጎዳን?
ምዕራባዊያን የሚፈልጉት አገራዊ አመለካከት ያለውን ማነኛውንም ማህበረሰብ ማድከምና ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። እኛ ግን ይህን የምንወጣበትን መንገድ ማሰብና መስራት ሲገባን በተረኝነት ተጠፍረን ታስረን እየተቸገርን ነው። ይህ ደግሞ ሁላችንን እንድንሸነፍ የሚያደርግ፣ ለአገር አንድነትም እንቅፋት የሚሆን ነው። የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በተመለከተ፣ ማየት ያለብን ወደ ምዕራብ ወይም ወደ ምስራቅ አይደለም። ማየት ያለብን ወደ እራሳችን ነው። ወደ እራስ ማየት እራስን ችሎ ለመቆም፣ ከሁሉም ጋር የሚበጅን ለመምረጥ፣ ጠላትን ለመቀነስ ይጠቅማልና። ከአንዱ ወደ ሌላው ማየት አለቃን የመቀያየር የባርነት አባዜ ነው። መሆን ያለበት፣ እኛ እነሱን የምንፈልጋቸውን ያህል፣ እነሱም እኛን እንዲፈልጉን የሚያስችል ስትራቴጂ መዘርጋትና መተግበር ነው። የጦርነቱ አላማ ችግር ፈጣሪውን በጊዜ በማስወገድ፣ ሞትን መቀነስ ነው። የተሻለው በጊዜ ሂደት ከያንዳንዱ ክልል የሰለጠነ ሚሊሻንና ልዩ ሃይልን፣ ከአዲስና ነባር ወታደሩ ጋር በመጨመርና መልሶ በማደራጀት፣ በየስርቻውና በየቤቱ የተሰገሰገን ህወሓትና ኦነግ ማጽዳት ብቻ ነው። ይህ ጣልቃ ገብነት የሚቆመው፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን በማነኛውም መንገድ ከችጋራችን መውጣት፣ ለዚህም የሚያስፈልገውን እውቀት መገብየት ስንችል ነው። ያለዚያ የምዕራቡ አለም ባርነታችን ይቀጥላል።