1፤ በትግራዩ ጦርነት ከፍተኛ ሚና አላቸው በተባሉ 62 ግለሰቦች ላይ የሽብር ክስ መዝገብ መክፈቱን ዓቃቤ ሕግ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። በክሱ የአማጺው ሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔልን እና ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የክልሉ ካቢኔ አባላት ግንባር ቀደም ተከሳሾች ሆነዋል። በሕወሃት ትጥቅ ትግል ወቅት ቁልፍ ሚና የነበራቸው የኢፈርት አመራሮች፣ የግልና መንግሥት ተቋማት፣ የክልሉ ምርጫ ኮሚሽንና በምርጫው የተሳተፉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የቀድሞ የሕወሃት ከፍተኛ አመራሮች ጭምር በክሱ ተካተዋል። በመዝገቡ የተጠቀሱት ወንጀሎች ሕጋዊውን የክልሉን መንግሥት በሕገወጥ ምርጫ በመለወጥ፣ የፌደራሉን መንግሥት በኃይል ለመለወጥ መሞከር እና በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት የመፈጸም ወንጀሎች ሲሆኑ፣ ተከሳሾቹ ሐምሌ 26 እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዟል።
2፤ በትግራይ ክልል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ዛሬ በአዲስ አበባ በተመድ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት አቤቱታ ማሰማታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል። ተመድ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ወላጆች ድምጻቸውን አሰምተዋል። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በ10 አውቶብሶች ወደ ትውልድ ቦታቸው መመለስ የሚፈልጉ ተማሪዎችን ከተመድ ታዛቢዎች ጋር ወደ አፋር ክልል ቢያሻግርም፣ የአፋር ክልል ልዩ ኃይሎች አውቶብሶቹን አናሳልፍም ማለታቸውንና ቀሪዎቹን ተማሪዎች በበጀት እጥረት ሳቢያ መቀለብ እንደማይችል ከትናንት ወዲያ መግለጹ ይታወሳል።
3፤ አማጺው ሕወሃት በትግራይ ክልል የማይ ዓይኒ እና አዲ ሐሩሽ የኤርትራዊያን ስደተኛ መጠለያዎችን ለወታደራዊ አገልግሎት እየተጠቀሙባቸው እንደሆነ የስደተኞች እና ስደት ተመላሾች ኤጀንሲ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የሕወሃት ተዋጊዎች ስደተኛ ጣቢያዎቹን ከያዙ ወዲህ 6 ስደተኞች እንደተገደሉ፣ በመጠለያዎቹ ከባድ መሳሪያ እንደተተከለ፣ የኤጀንሲውና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ንብረቶች እንደተዘረፉ፣ ስደተኞች የገንዘብ መዋጮ እንደሚጠየቁ እና ከመጠለያዎቹ መውጣት እንደተከለከሉ ኤጀንሲው አመልክቷል። በስደተኞቹ ደኅንነት ላይ ከባድ አደጋ እንደተደቀነ የተመድ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነርም የገለጸ ሲሆን፣ ሕወሃት በበኩሉ በስደተኞች ላይ ደርሷል የሚባለው የመብት ጥሰት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ በቀደም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
4፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በአዲስ አበባ ከተማ በትግራይ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ነው ያለውን ጅምላ እስር ባስቸኳይ እንዲያስቆሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትዊተር ገጹ ጥሪ ጠይቋል። እስካሁን በጅምላ ታፍሰው እስር ላይ ካሉት ግለሰቦች ላይ መንግሥት በሕጉ መሠረት የወንጀል ክስ የመሠረተባቸው ስለመኖራቸው መረጃ የለኝም- ብሏል አምነስቲ። ፖሊስ መታወቂያ እያየ በብሄሩ ተወላጆች ላይ ይፈጸማል የተባለው የዘፈቀደ እስር እንዲቆም አሁኑኑ ተግባራዊ ርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አምነስቲ አክሎ አሳስቧል።
5፤ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 24 የሥራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ የክልሉ መንግሥት ማስታወቁን ዶቸቨለ ከሥፍራው ዘግቧል። ፖሊስ በሥራ ሃላፊዎቹ ላይ ምርመራ የሚያደርገው፣ ሃላፊዎቹ በክልሉ ሰላም እና ጸጥታን ለማስፈን የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም በሚል ነው። በክልሉ በሰላማዊው ሕዝብ ላይ የኃይል ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩ ሸማቂዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጧል።
6፤ አፍሪካ ኅብረት የማጓጓዣ ወጭ ለከፈሉ 27 የአፍሪካ ሀገራት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባለውን 6 ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጠብታዎችን ሊያጓጉዝ እንደሆነ መናገሩን ሲኤንኤን ዘግቧል። 18 ሀገራት እስከ ነሐሴ የማጓጓዣ ክፍያ ለመፈጸም ከዓለም ባንክና ሌሎች አበዳሪዎች ጋር ስምምነት ላይ እየደረሱ መሆኑ ተገልጧል። የክትባቱ አቅርቦት የሚጠናቀቀው በቀጣዩ ዓመት መጨረሻ ነው። የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ስትራይቭ ማሲይዋ ግን ለአፍሪካ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ክትባቱ በአፍሪካ ምድር ሲመረት ብቻ መሆኑን በመጥቀስ ለዓለማቀፍ ክትባት አምራች ኩባንያዎች ተማጽኖ አቅርበዋል።
7፤ በተመድ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆኑ የአፍሪካ እና ካሪቢያን ሀገሮች በኬንያ ናይሮቢ ስብሰባ እንደተቀመጡ ዴይሊ ኔሽን አሰነብቧል፡፡ በአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የጋራ አጀንዳ ለመንደፍ እና በምክር ቤቱ የጋራ አቋም ለማንጸባረቅ የተሰበሰቡት፣ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ቱኒዝያ፣ ግሪናዳ እና ሴንት ቪንሴንት ናቸው። የጸጥታው ምክር ቤት የሕዳሴ ግድብ ውዝግብን ለአፍሪካ ኅብረት እንዲተወው በተለይ ሦስቱ አፍሪካዊያን የምክር ቤቱ አባላት በቅርቡ የጋራ አቋም ማንጸባረቃቸው ይታወሳል።
[ዋዜማ ራዲዮ]